Tag Archives: Professor Mesfin Woldemariam

ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ ይባል ነበር ዱሮ ወግ ነው ምርጫ ማሸነፍ ሆነ ዘንድሮ! አስተሳሰብና ጉልበት (ሕገ አራዊት)

31 Jan

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

በረከትን በደንብ የሚያውቀው ያሬድ ጥበቡ ሙልጭ አድርጎ ነግሮታል፤ ያሬድ ከዚህ በፊትም ስለበረከት ጽፎ ነበር፤ አሁን ከጻፈው ጋር ሳስተያየው አንድ ግጥም ትዝ ይለኛል፤ አንዲት የቸገራት ሴትዮ ያንጎራጎረችው ይመስለኛል፡-

ወደድኩህ ወደድከኝ፤ ጠላሁህ፤ ጠላኸኝ፤
እንደሚጣራ ጠጅ እየጣልክ አታንሣኝ!

ያሬድ ስለበረከት በሚጽፈው ሁሉ እያነሣ የመጣልና እየጣለ የማንሣት ዝንባሌን ያሳያል፤ እስከዛሬ በናፍቆት የሚጠብቀውን ወዳጁን ሸፍጥንና የአእምሮ ሕመምን ሲያለብሰው ማንኛቸው መቼ እንደተለወጡ ለመረዳት ያስቸግራል፤ ለማናቸውም የዲክንስን መጽሐፍ ያሬድ እንደሚለው በረከት ከመጀመሪያው ገጽ በላይ አነበበም አላነበበ እንግሊዝኛው ትርጉም መሆኑን የተረዳሁት ከያሬድ ነው፤ ለምን ወደ እንግሊዝኛ እንደተሄደም አልገባኝም፡፡

በዚህ ዓመት ታላላቅ የአገር መሪዎች የሚያስተምሩን ነገር ባይኖራቸውም ‹‹የታሪክ››መጽሐፍት የሚሉትን አሳትመዋል፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና አቶ በረከት ስምዖን፤ ሁለቱ ሰዎች በብዙ ነገር የሚመሳሰሉ ቢመስሉም እውነትን በመናቅና በመጥላት አንድ ናቸው፤ ዛሬ እኔ ላነሣ የፈለግሁት ግን በአስተሳሰብ ግድፈት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

በ1997 የፖለቲካ ክርክር ላይ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ሠላሳ በመቶ የሚሆነው ስለሰብዓዊ መብቶች የሚናገር ስለሆነ ይህ ቀረው የሚባል አይደለም፤ ችግሩ በተግባር የምናየው ሕገ አራዊት መሆኑ ነው ብዬ የተናገርሁትን ጉልበተኛው በረከት ወዲያው ቀለብ አድርጎ ‹‹ሕገ መንግሥቱን ሕገ አራዊት ነው አለ፤›› ብሎ ወነጀለኝ፤ ለጉልበተኛው ሕገ ኀልዮትም ሆነ ሕገ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ አይደሉም፤ ዛሬ ረዳቱ የሆነውም ጠበቃው የገዛ ጆሮውን ከድቶ በጉልበተኛው የተነገረውን እያስፋፋ በፍርድ ቤቱ አስተጋባ፤ ዳኞቹም ጠበቃውን ሰምተው ፈረዱ፤ ዛሬ እነሱ አንገታቸውን አጎንብሰው ይሄዳሉ፡፡

ዛሬም ያው አስተሳሰብ (አስተሳሰብ ካልነው) እንደተለመደው ቃላትን እየዘለዘለ ለውንጀላ ያቀርባል፤ አንዱዓለም አራጌ ‹‹የአምባ ገነን አገዛዝ ባለበት የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው፤›› አለ ይባላል፤ ጉልበተኛው እንደለመደው መጀመሪያ የተባለውን ቀንጭቦ ኪሱ ከተተና (!)አንዱ ዓለም ‹‹የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው›› አለ ብሎ ለውንጀላ ያመቻቸዋል፤ የአንዱ ዓለም መታሰር እሱ ራሱ ያለውን ያረጋግጣል? ወይስ አለ የተባለውን ያረጋግጣል? ወይስ ሁለቱንም ያረጋግጣል? በመሠረቱ አንዱ ዓለም ያለው ሙሉ ቃልና ጎዶሎው ልዩነት የላቸውም፤ የጉልበት አገዛዝ ባለበት የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው፤ የሚለውና ያለመነሻ የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው፤ የሚለው በአንድ ነገር ይመሳሰላሉ፤ ጀግናን የጥቃት ኢላማ በማድረግ ይስማማሉ፤ ከዚያም አልፎ ጀግንነትን መጠቃት አድርገው የሚያቀርቡት ይመሳሰላሉ፤ የተዛባ አስተሳሰብ!

ቀጥዬ የምጠቅሰው ምሳሌ ከላይ ከተጠቀሱት የባሰ የአስተሳሰብ ግድፈትን የሚያመለክት ነው፤ አቶ መለስ ‹‹የተሃድሶ እንቅስቃሴያችንን በከፍተኛ ፍጥነት ከሚወርድና በየደቂቃው ፍጥነት እየጨመረ ከሚጓዝ ናዳ አምልጦ ወደ ጠንካራ ከለላ ለመግባት ከሚሮጥ ሰው ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡›› ሲል ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ውስጥ ተናግሮአል፤ በ1997 ምርጫ አቶ መለስ ብዙ አጃቢዎቹ (አቶ በረከትን ጨምሮ) ስለዌደቁበት የናዳውን ኃይል በትክክል ገምቶ የተናገረ ይመስለኛል፤ መለስ የተናገረው ወደበረከት ስምዖን ጆሮ ሲደርስ ግን ሌላ ሆኖ ነበር፤- ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ! መለስ ወደፊት ሂድ! ሲል በረከት ስምዖን ቀኝ-ኋላ ዙር! ይላል፤ ወደፊት አልሮጥም የማለት መብት አለው፤ ጥያቄው ይህ አይደለም፤ የአስተሳሰብ ግድፈቱ ወደፊት ሂድ ማለትና ቀኝ-ኋላ ዙር ማለትን አንድ ማድርጉ ላይ ነው፤ በወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን የመጣ የአፈፃፀም ጉድለት የሚባለው ነገር ምንጩ እንዲህ ያለ የግንዛቤ መዛባት መሆኑ ነው፡፡

ለምራቂ አንድ ሌላ ግድፈት ላቅርብ፤ የመጽሐፉ ዋና ርዕስ ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› ነው፤ ምን ማለት ነው? ወግ የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም አለው፤ አንዱ ትርጉም ወሬ ነው፤ ሁለተኛው ትርጉም ሥርዓት ማለት ነው፤ ከሃምሳ ዓመታት በፊት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ በራስ ቢትወደድ እንዳልካቸው የተደረሰ ጨዋታ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ታይቶ ነበር፤ አቶ አሐዱ ሳቡሬ ሲተቹ ድራማ ብለውት ነበር፤ እኔ ግን ጨዋታ ነው ብዬ ‹‹አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም›› ለዚያ ለሞተ ጨዋታ ተስማሚ ስም ነው በማለት ጽፌ ነበር፤ እንዲሁም የሁለት ምርጫዎች ወግ በሁለቱም የወግ ትርጉሞች ተስማሚ ስም የተሰጠው ተረት ነው፤ እውነቱ ጸሐፊው በዚያ ምርጫ መውደቁ ነው፤ እውነቱ ጸሐፊው እንደገና በልዩ ዝግጅት ተመረጠ መባሉ ነው፤ ታሪክን፣ ያውም የቅርብ ታሪክን ወደተረት ለመለወጥ ለጉልበተኛም ቢሆን አስቸጋሪ ነው፤ ተዋንያኑ ሁሉ ገና በሕይወት አሉ፤ ጸሐፊው ልማድ ሆኖበት አላነበባቸውም እንጂ አንዳንዶቹም ስለምርጫው ከወግ ባለፈ ጽፈዋል፡፡

ስለ2002 ምርጫ በቅርቡ እንኳን በአሐዝ የተደገፈ ጥናት ወጥቷል፤ አንደኛ ከአጠቃላይ የየክልሉ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ የመረጡትን ስናይ ምርጫው ወግ ብቻ እንደነበረ ገሀድ ይሆናል፤ ለምሳሌ ከየክልሉ የመረጡት በኦሮሚያ 31 ከመቶ፣ በአማራ 33 ከመቶ፣ በደቡብ 27 ከመቶ፣ በትግራይ 39 ከመቶ፣ በአዲስ አበባ 19 ከመቶ፣በአፋር 66 በመቶ፣ ከዚያ ደግሞ በድሬደዋ 57 ከመቶ ሲሆኑ በሐረርና በኦጋዴን ደግሞ ለወግም የማይመች በመሆኑ አልተገለጸም፤ ናዳው የምርጫውን ወግ እንኳን እንደደፈጠጠ በተለይ የአፋርና የድሬዳዋ የመራጮች አሐዝ ምስክር
ነው፤ እድሜያቸው የማይፈቅድላቸው ሁሉ ካልመረጡ በቀር፤ ወይም በእነዚህ ክልሎች አብዛኛው ሕዝብ በልዩ ተአምር እድሜው ከ18 ዓመት በላይ ካልሆነ በቀር ከላይ የተገለጸውን ያህል መራጭ ሊያገኙ አይችሉም፤ እንዲሁም በመረጡት ወንዶችና ሴቶች መሀከል በየክልሉ የሚታየው ድርሻ ወንድና ሴቱ እኩል እንዲሆን ተደርጎ የተደለደለ መሆኑ ይታያል፤ ይህንን ሁሉ የዘነጋ ከታሪክ ይልቅ ወደተረት ያዘነበለ ጨዋታ ነው፤ ተረቱ የሚጣፍጠው ከተገኘ!

ሁለተኛ አቶ ኡስማን አሊ የሚባል ሰው 368,211 ድምጽ፣ አቶ ሽመልስ ከማል ብርሃን የሚባል ደግሞ 19,647 ድምጽ ለወጉ አግኝተው ተመርጠዋል፤ ከተመራጮቹ 64 በመቶ ያህሉ ያገኙት ድምጽ ከ50,000 በታች ነው፤ መለስ ዜናዊ ያገኘው 40,302 ነው፤ በትግራይ ወይዘሮ አልማዝ የሚባሉ 87,185 ድምጽ ማግኘታቸው ቱባ ቱባ ባለስልጣኖቹ ካገኙት ጋር ሲወዳደር ሰማይ ያደርሳቸዋል ስለ2002 ምርጫ በአገቱኒ ውስጥ ዝርዝር መረጃ ቀርቦአል፡፡

መጽሐፍ ያውም የታሪክ መጽሐፍ ለመጻፍ ለእውነት ክብር መስጠትና ለእውነት ተገዢ መሆን ያስፈልጋል፤ አለዚያ ጉልበትና የአቶ አላሙዲንን ገንዘብ ማጥፋት ነው፡፡

Feteh

ወይ! ጋሽ ደቤ !!!!!

12 Dec

For Amharic PDF file click here:  gash debe

አኬልዳማን ባየሁ ማግስት ስለ ጋሽ ደቤ መናገር የፈለኩኝ ቢሆንም አለማለቴን ግን አሁን ነው የወደድኩት፤ ምክንያቱም እኔም ፤ጋሽ ደቤም ስሜት ውስጥ ሆነን(እንዳመጣልን) የምንለው፤ነገር፤ ለህዳሲውም ግድብ ይሁን …………ለኢንዱስትሪው(እርሻ) መርህ ስትራቴጂያችን ጠቃሚ ስለማይሁን፤

አኬልዳማን ለተመለከተ ማንኛውም ኢትዮጲያዊ የተደበላለቀ ስሜት መፈጠሩ ተገቢም ተፈጥሮአዊም ይመስለኛል፤፤ አንድም፤ የተለመደው የአቶ በረከት ስራ ሳይሆን እንደማይቀር ገምቶ ችላ ብሎ ማለፍ ፤ተስፋዬ ገ/አብ እንደሚለን ከሆነማ ፤የቅንድቡ ያማረ፤ ለአቶ መለስ የተዜመውን የሰለሞን ተካልኝ ዘፈን እንኳ ገጣሚና ደራሲ፤ አቶ በረከት ስምኦን እንደሚሆኑ ሳይንሳዊ መላምቱን አሰቀምጣል፤፤ በ21 ክ/ዘመን በአለማችን ለቅንድባቸው ማማር የተዘፈነላች መሪም ብሎዋቸዋል፤፤

ሁለተኛው ደግሞ የፕሮፌሰር መስፍንን የማሪያም መንገድ ተከትዬ ነው ተብሎ ፤ ወይንም እውነቱን ተናግሮ የመሹበት ማደር የተባለውን ተረት ወስዶ…….. ያለ፤ የሌለውን ተናግሮ ከእስር መውጣት፤ ሌላኛው ቴክኒክ ነው፤፤ ለእኔ ሁለቱም ለህዳሲያዊዋ ኢትዬጲያ (በደርግ አባባል ደግሞ ፤ ለአዲሲቷ ኢትዮጲያ) የኪሳራ ድራማዎች ናቸው፤፤

ለፌስ ቡክ ዘወትር ተጠቃሚዎች የጋሽ ደቤን ተጠርጥሮ እስር መግባትም ይሁን መውጣት በፍጥነት ያበሰረን እውቁ የ ሲፒጄ ተሸላሚ፤ የአውራምባው ስደተኛ ዳዊት ከበደ መሆኑን አስታውሳለሁ፤፤ አብዛኛዎቻችን የቀድሞ ስርአት ናፋቂዎችና የቅንጅት ርዝራዦች፤ ተብለን የምንታወቀው፤ የፌስ ቡክ ፕሮፋይል ፎቶዎቻችንን በቅፅበት በጋሽ ደቤ ይለቀቅ (Free Debebe) በሚሉ መልእክቶች ማስዋባችንን አስታውሳለሁ፤፤ አብዛኛዎቻችንም ጋሽ ደቤ ያለውን ስብእና ለማጉላትም ይሁን በየዋህነት ፤ ሻፍት ኢን አፍሪካ በተባለው ታዋቂ ፊልም ላይ ያበረከተውን ድርሻ፤ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ስለተከማቹት የመፃኅፍት ብዛት፤ በቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት ኃይለ ስላሴ በዓለ ውርደት (ሲወርዱ) መገኘቱን ፤ በቀድሞ ቅንጅት አመፅ ማረሚያ ቤት ጋሽ ደቤ እየታረመ በነበረበት ወቅት የፃፈውን መፅሀፉን ለማውጣት የተጠቀመበትን ታክቲክና ቴክኒክ እያደነቅን …………………….ብቻ የጋሽ ደቤ ገድል የቀረን ያለ እስከማይመስል ድረስ ስንፖተልክ መቆየታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሆኖ አልፏል፤፤

ፕሮፊሰር መስፍንም እንደእኛው ከተሸወዱት አንዱ እንደነበሩ በሚያሳብቅ መልኩ ፤እኔ ደበበን አውቀዋለሁ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ ይገባል የሚል እምነት የለኝም፤ ብለው ነበረ፤፤ ፕሮፌሰርም፤ እኛም (የፌስቡክ አብዬተኞች) ተሳስተናል፤ ስህተታችን የተለያየ ቢሆንም፤፤ ፕሮፌሰር፤ ደበበን አለማወቃቸው ሲሆን ፤ እኛ ደግሞ ጋሽ ደቤ እንደዛ ቡና እየጠጣ ፤ ያለ፤ የሊለውን ተናግሮ፤ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎችን ስልትና ሰንሰለት እንደዛ ባለ መልኩ ያጋልጣል ብለን አለማመናችን ይመስለኛል፤፤

በጥንቷ ግሪክ ባሪያዎች ከፍተኛ የምርመራ እንግልት እንደሚደርስባቸው ታሪክ ፅፏል፤ በመሆኑም ባሪያዎቹ የሚሰጡት የምርመራ ቃል(ውጤት) ተአማኒነት አለው ከሚባሉት በላይ አሳማኝ እንደሆነ ይነገርለታል፤፤ ጋሽ ደቤ ይህ አይነት እንግልት ይድረስበት፤ ወይንም የ እንደ ቀድሞ ናዚ መርማሪዎች እንደሚያደርጉት ድራግ(መድሃኒት) ይስጡት………፤ እኔ በበኩሌ የማልጠብቀው የምርመራ ውጤት ሰምቻለሁ፤፤ ናትናኤል (አንደኛው የሽብር ተጠርጣሪ) ለፍርድ ቤት እንዳሳበቀው፤ በውሃ ውሰጥ በመንከር፤ የሚደረግ የምርመራ አካሄድ ጭምር እንደነበረበት በአደባባይ መስክሯል፤፤

አሜሪካን በአፍጋኒስታንና በጓንታናሞ ቤይ ተመሳሳይ እንግልቶችን እንድታቆም ከፍተኛ ትግል ያካሄዱት፤ ከባራክ ኦባማ ጋር ባደረጉት ፉክክር በአግባቡ ያወቅናቸው ጆን ማኬይን መሆናቸውን አሜሪካኖች በኩራት የሚናገሩት ነው ፤፤ ጆን ማኬይን በቪየትናም ጦርነት ወቅት ተማርከው በቪየትናም መንግስት ከፍተኛ እንግልት የደረሰባቸው ናቸው፤፤ እሳቸውም ለእንግልት ስቃይ ፤ማስተካከያ ያስፈልገዋል በማለታቸው ፤የእንግልት ማስተካከያ (Torture Amendment) ወይንም Mc cain Amendment የማኬይን ማስተካከያ፤ የሚባል ህግ በአሜሪካ ኮንግረስ በ2005 ዓ.ም. እአአ አፅድቀዋል፤፤ የኛዎቹ አብዛኛዎቹ፤ የአሁኑ ባለስልጣናት፤ በደርግ ዘመን በእነሱ ወይ በዘመዶቻቸው ላይ እንግልት መቅመሳማቸውን በተደጋጋሚ ለሃያ አመታት የሰማነው ይመስለኛል፤፤ ግን ማናቸውም ለእንደዚህ አይነት እንግልት አላስፈላጊነት ጥብቅና ሲቆሙ በበኩሌ ሰምቼም አይቼም አላውቅም፤፤

ከዚህ ቀደም ጋሽ ደቤ፤ ፕሬስ ኮንፈረንስ እየተሰጠ እና ጋዜጠኞች የአፍ ወለምታ በጉጉት በሚጠብቁበት ሰዓትና ቦታ ላይ ዶ/ር ያዕቆብ የተናገረውን አይመለከተኝም በማለት የተናገረው ለወራት ማወዛገቡ የሚታወስ ነው፤፤ ድሮስ አንተ እኮ አርቲስት ነህ፤፤ አንተም ጠበቃ የሚሉ ሰጣ ገባዎችን በአደባባይ ሰምተናል፤፤ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ ቢቸግራቸው ነው መሰለኝ ፤ ይህን ሁሉ የሚሰሩት ጋዘጠኞች ናቸው ብለው እርፍ፤፤ አሁን ደግሞ ቃል በቃል ባይሆንም ፤ ጋሽ ደቤ አኬልዳማ ላይ ሲናገር የተደመጠው እንደሚከተለው ነበር፤ መራራ ማለት ለእኔ እንደፓርላማ አጫዋች ነው የማየው ………፤ ነጋሶ ደግሞ ምን አገባው ስለ ሲውዲን ጋዜጠኞች የሚከራከረው፤ ምን አገባውውውውውውው?????????????.. ለምርመራ አስፈላጊ ያልመሰሉኝን እና በጋሽ ደቤ የቀረበውን ዝግጅት በተለይ ደግሞ በዶ/ር መራራ እና በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ላይ የተካሄደውን ዘለፋ ባየሁ ጊዜ፤ የኛ አገር ምርመራ፤ እላፊ የሚያስኬድ አይነት አያያዝ ሳይኖረው እንደማይቀር ገመትኩ፤፤ ለደረሰባቸው ዘለፋ ከ ዶ/ር መራራ የመጣው የመልስ ምት ፤ እኔ ከደበበ ጋር የእግዜርም ሰላምታ እንኳን የለኝም፤ የሚልና ቀለል ያለ መሆኑ ከአንድ ዶክተር የሚጠበቅ እንድል አድርጎኛል፤፤

ሌላው ደግሞ ቀጣሪና ሰራተኛ አልገናኝ ብሎ እንደሆነ እንጂ፤ እነ ዶ/ር ብርሃኑስ ምን ሆነው ነው፤፤ ደበበ እሸቱን ዩጋንዳ ወስዶ ቃል አቀባይ የማድረግ ስራ ያሰቡት፤ ወይምን ያልገባኝ ሌላ ነገር እንዳለ እንጃ???? አላውቅም፤፤ እኔ መቼም ለነ ዶ/ር ብርሃኑ አይጠፋቸውም ብዬ የምገምተው ነገር፤ ጋሽ ደቤ በደንብ የገለጸው ይመስለኛል፤፤ ቤተሰቡን በጥሩ ሁኔታ እየመራ ያለንና ፤ሚስቴ ፤ልጄ፤አባቴ፤ እናቴ ከሚል ሰው ጋር መቀጠል ግንቦት 7፤ሁለገብ ለሚለውን ስራ ያመቸዋል ብዬ አላሳብም፤፤ የአሁኑ አይነት የድራማና የስብዕና ኪሳራ ያስከትላልና፤፤ የነውጠኛው ሂዝቦላ መሪ፤ ሃሰን ናስራላህ፤ አራት ልጆች ነበሩት፤ ከነዚህ ውስጥ ትልቁ ልጁ የሞተው በ 2006 ዓ.ም. እ.አ.አ እስራኤሎች ላይ በተነኮሰው ትርምስ ነው፤፤ ግንቦት ሰባትም ፤ በሁለገብ እስትራቴጂው ፤ ብርጭቆም ቢሆን አይሰበርም ብሎ ያስባል ብዬ አልገምትም፤፤

ክብር! ለእምነታቸው በአደባባይ እንደጧፍ ለሚነዱ እብዶች!!!!!!

Jonas Jontambek

ሽብር ማለት የየካቲት 12 ሽብር

5 Dec

For Amharic PDF file visit here: Terrorism

መስፍን ወ/ማርያም /ፕሮፌሰር/

የኢትዮጵያ ህዝብ ለልጆቹ ስም ሲያወጣ ሽብሩ፣ አሸብር፣ ወንድይራድ፣ ያየህይራድ ይላል፤ ሽብርን ፈልጎ አይደለም፤ ሽብርን ራሱን አስፈራርቶ ለማስቀረት ነው፤ ጥቃትን ለመከላከል የፈጠረው ዘዴ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሽብር ጠላት መሆኑን አንድ ማስረጃ ላቅርብ፤ ስለችጋር ሳጠና በችጋር ጊዜ ሽብር፣ ዝርፊያና ቅሚያ፣ ረብሻ የማይታይባት ኢትዮጵያ ብቻ ነች፤ በችጋር ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብርና ዝርፊያ ያየ ሰው ቢነግረኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ አሁን ወደ የካቲት 12 ሽብር ልግባ፤ ሽብር እንደማናውቅ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡

ኢያን ካምቤል የሚባል ብሪታንያዊ በየካቲት 12/1929 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣልያን እንደራሴ፣ ግራዚያኒን ለመግደል ስለተደረገው ሙከራ አንድ መጽሐፍ አሳትሞአል፤ በመጀመሪያ አንድ ነገር መናገር አለብኝ፤ መንግስት ቢኖር፣ ወይም ለታሪክ ክብር የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን ምሑራን ቢኖሩ እስከዛሬ ድረስ ጉዳይ ብለን ሳናጠናው የተውነውን ትልቅ ጉዳይ ኢያን ካምቤል ስለጻፈልን በጣም የሚመሰገን ነው፤ እኛን ግን በጣም የሚያሳፍረን ነው፤ እኔማ ብዙዎቹ ሰዎች በቅርቤ የነበሩ ዘመዶችና ወዳጆች ስለነበሩ ይበልጥ ያሳፍረኛል፡፡
ስለ የካቲት 12 ሽብር፣ ስለ አብርሃ ደቦጭና ስለ ሞገስ አስገዶም ላይ ላዩን እሰኪበቃን ሰምተናል፤ ዋናውንና ዝርዝሩን ጉዳይ ግን ሳናውቀው ቆይተን ነበር፤ ሁለቱ የኤርትራ ወጣቶች በኢጣልያ የቅኝ አገዛዝ መስሪያ ቤት ውስጥ ታማኝ አገልጋዮች ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፤ በአንድ በኩል ውስጣቸው የተቀበረ የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ በሌላ በኩል ከኤርትራ ተከትሎአቸው የመጣው የፋሺስት ኢጣልያኖች ንቀትና ማዋረድ አንገፍግፎአቸው ክፉ ጥላቻ በውስጣቸው አሳደረባቸውና በፋሺስት እንደራሴው ላይ ጉዳት ለማድረስ ወስነው ተነሱ፤ ተዘጋጁ፡፡
ለየካቲት 12 የኢጣልያ አገዛዝ የኢትዮጵያ ህዝብ የማስገበሪያ ልዩ ዝግጅት አድርጎ በቤተ መንግስት (በኋላ የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርስቲ) በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ግቢውን ሞልተውት ነበር፤ ለፋሺስት ኢጣልያ እንዲገብሩ የተጠሩት ታላላቅ የኢትዮጵያ መሳፍንትና መኳንንት፣ የተማሩ ወጣቶች፣ የተማሩ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ የኢጣሊያን ታላቅነትና ቸርነት እንዲቀምሱ የተጠሩ በሺህ የሚቆጠሩ ደሀዎች፣ አካለ ስንኩላን፣ ዓይነ ስውሮች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ሁለት ሁለት ጠገራ ብር ምጽዋት ለመቀበል ተኮልኩለው ነበር፤ እንግዲህ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በሀጂ በዳሶ በኩል ከድሬዳዋ የመጣላቸውን ቦምባቸውን ታጥቀው በሰገነቱ ላይ ነበሩ፤ የመጀመሪያውን ቦምብ ሲጥሉና መሬት ሲጨልም ግራዚያኒ ሲሸሽ ሌላ ቦምብ ወረወሩና ከኋላው ክፉኛ አቆሰሉት፤ ቁስሉን ሁለት ወር ተኩል ያህል በራስ ደስታ ሆስፒታል (ያኔ የኢጣልያኖች ሆስፒታል ነበረ) ተኝቶ ቢታከምም እስከ ህይወቱ መጨረሻ ከውስጥም ከውጭም ህመምተኛ ነበር፤ ከግራዚያኒ ጋር ብዙ የፋሺስት ሹሞች ቆስለዋል፤ ከኢትዮጵያውያን መሀከልም ራስ ኃይለ ስላሴ ጉግሳና ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስም ቆስለዋል፡፡
ከቦምቡ በፊት ግራዚያኒ ባደረገው ዲስኩር የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያን ለማዳን እግዚአብሔር የላከው እንደሆነና የአማራን የአረመኔና የግፍ አገዛዝ እስከዘላለም ለማስወገድና አማራዎች ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡
ሁለት ሰዎች ቦምብ ስለወረወሩና ምንአልባትም ከአሥር የማይበልጡ ሌሎች ሰዎች ስለተባበሩአቸው ምንም አይነት ምርመራ ሳያስፈልግ፣ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይሰበሰብ በመጀመሪያ እዚያው ግቢ ውስጥ ለማዳመቅና ለመገበር የተሰበሰቡት መሳፍንትና መኳንንት፣ ለምጽዋት የተጠሩ ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ድሆች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ አካለ-ስንኩላን ተጨፈጨፉ፤ ቀጥሎም የተማሩ የተማሩ ሰላማዊ ወጣቶች፣ የጦር መኮንኖችና ነቃ ያሉ ካህናት፣ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በሙሉ እየተለቀሙ ተጨፈጨፉ፤ ሽብር ይህ ነው፤ ኢትዮጵያውያንን በቤት ውስጥ እያስገቡ ከውጭ ቆልፈው ቤንዚን እያርከፈከፉ አቃጠሉአቸው፤ ሽብር ይህ ነው፤ ጠመንጃ የሌለው ፋሺስት በአካፋ፣ በዶማ፣ በመጥረቢያ በተገኙበት ኢትዮጵያውያንን እየቆራረጠ የደረቀውን የበጋ መሬት የኢትዮጵያውያንን ደም አጠጣው፤ ሽብር ይህ ነበር፡፡ የፋሺስቱ ሰራዊት ደብረ ሊባኖስን ከነመነኮሳቱ አቃጠለው፤ ይህ ሽብር ነበረ፤ አዲስ አበባ ሬሳ በሬሳ ላይ የተከመረባት፣ የደም ጎርፍ የሚወርድባት፣ ዓየሩ በተቃጠለ የሰው ሥጋና በሬሳ ሽታ ተበክሎ መተንፈስ አስቸጋሪ የነበረባት ከተማ ነበረች፤ ሽብር ይህ ነው፤ ኡኡታው፣ ለቅሶው፣ ዱብ ዱብ እያለ ከደም ጋር የሚደባለቀው እንባ.. ይህ ነው ሽብር.. ወደ ሰማይ የሚከንፈው ጩኸት አምላክን ሲያስከፋና ሲያሳዝን፣ይህ ነው ሽብር..
ግራዚያኒ ትንሽ ሲያገግም ከአማራ መኳንንት ጋር ለመገላገል ከዚህ የተሻለ ዕድል አይኖርምና ሁሉንም ጨርሱ፤ ብሎ አዘዘ፤ ሽብር ይህ ነው..
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በፋሺስት ተይዘው ሊሰቀሉ ሲሉ አብርሃ ደቦጭ ..የወንድሜን ስቅላት አላይም፤ እኔን መጀመሪያ ስቀሉኝ.. ስላለ እንደፈለገው ሊሰቅሉት ሲዘጋጁ ..ለአገሬ በአደረግሁት ነገር ሁሉ እኮራለሁ፤ አሁንም በደስታ ለአገሬ እሞታለሁ…. ብሎ ሲናገር የፋሺስቱ አዛዥ በንዴት ተበሳጭቶ አብርሃንም ሞገስንም በሽጉጥ ገደላቸውና ሬሳቸውን ሰቀለ፤ እብደት የሽብር መጨረሻ..
ፋሺስቱን አዛዥ ምን አሳበደው? ያቺን ጠምዝዞና ጨምቆ፣ ዳምጦና ፈልቅቆ ከውስጣቸው አስወጥቻለሁ ብሎ የገመተው ኢትዮጵያዊነት ፊት ለፊት ገጠመው.. ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ፋሺስቱ አዛዥንም ሞትንም እያዩ በአንድ ላይ ተጋፈጡአቸው፤ ኢትዮጵያዊነት የተሸፈነበትን የፋሺስት መንጦልያ ቀዳዶ ወጣ.. ፋሺስቱንም ሞትንም ናቀ.. ለሞት የተዘጋጀ ሰው ሲንቅ፣ ለመግደል ለተዘጋጀው ሰው የመንፈስ ሞት ነው..
በዚያው እለት ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጋፍጦ የአበደው የፋሺስት አዛዥ ቀኛዝማች ወርቁ በሚባሉ አርበኛ ጦር ተመትቶ አብርሃ ደቦጭንና ሞገስ አስገዶምን ተከትሎ ሄዶአል፤ የሽብር መጨረሻው ይህ ነው..
ፈሪሃ እግዚአብሔር አለውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽብር ይፈጸምበታል እንጂ ሽብር አይፈጽምም፡፡

የአስተሳሰብን ህግ ካልጠበቅን ለመግባባት ያቅተናል – Professor Mesfin Woldemariam

11 Oct

For Amharic pdf file click here: Professor Mesfin

ለብዙ ዓመታት የማውቀው ወዳጄ ገብሩ ታረቀኝ በፍትህ ጋዜጣ ላይ፣ የማላውቀው አቶ ዓሥራት በአድማስ ጋዜጣ ላይ በትግሬነታቸው ተቆርቁረውና እኔን ባዕድ አድርገው የጻፉትን አንብቤ ሁላችንንም የሚያውቁ ሌሎች ሰዎች አስተያየት እንዲሰጡበት በማለት መልስ ከመስጠት ተቆጥቤ ቆየሁ፤ ሆኖም እስካሁን ከአንድ ሰው በቀር የደረሰልኝ የለም፤ ስለዚህ እኔው ልጋፈጠው፡፡
ገብሩ ወዳጄ ነው የምለው ሰው ስለሆነ የጋለ ስሜቱን ይዞ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ከእኔ ጋር ጉዳዩን አንስቶ አለመወያየቱ ከሚችለው በላይ የሆነ ግፊት ቢያጋጥመው መስሎ ታየኝ፤ እንዲያውም ሌላ ሰው እሱ ያለውን ሲናገር ቢሰማ ለእኔ ቆሞ ይከራከራል ብዬ የምገምተው ሰው ነበር፤ አንድ ሳይካያትሪስት (የአእምሮ ሐኪም) ሲናገር እንደሰማሁት የጎሳ አስተሳሰብ የጎሳን ድንበር ጥሶ ወዳጅነት የሚባል ነገር አያውቅም ያለውን አስታወሰኝ፤ ይህ እንደማይሆን ተስፋ አለኝ፡፡
በምን ላይ እንደጻፍሁት ሳልናገር ለሁለቱም የትግራይ ተቆርቋሪዎች የሚከተሉትን አጫጭር ነጥቦች ላመልክታቸው፡-
1. ወያኔ ..ከሚኒልክ በፊት ኢትዮጵያ አገር አልነበረችም ሲል የአፄ ዮሐንስንና የራስ አሉላን ትግሬነትና ኢትዮጵያዊነት በመካድ.. ጀመረ፤
2… የጎንደርን በሬ፣ የጎጃምን በሬ፣ የሸዋንም በሬ፣
ባንድ አርጎ ጠመደው የትግሬው ገበሬ..
(የትግራይን የኢትዮጵያዊነት መሰረት ለማስረዳት የጠቀስሁት)
3. ..የትግሬ ዘር (ኤርትራውያንን ጨምሮ) የኢትዮጵያ መሰረት ነው፤ የትግሬ ዘር የኢትዮጵያን ታሪክ ተሸካሚ ነው፤ እንኳን በኢትዮጵያዊነታቸው ያሉትን ትግሬዎች የተገነጠሉትንም ለማጥፋት ማሰብ በምድርም በሰማይም ይቅርታ የማያስገኝ ወንጀል ነው፡፡ ከኤርትራውያን ጋር የተደረገውንም የወንድማማቾች ጦርነት አጥብቄ የተቃወምሁት በዚህ ምክንያት ነበር፤ በሰሜን ያሉትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከመቅጽበት ወደባዕድነት ለውጠን አሁን ደግሞ የተረፍነውን አጥፊና ጠፊ አድርጎ መፈረጁ ለማንም የሚበጅ አይሆንም፡፡..
ብዙ ሌሎችንም መጥቀስ እችላለሁ፤ ልብ ላለው ይበቃል፡፡
በደርግ ዘመን በዩኒቨርስቲ ውስጥ ስናወራ ስለ የአእምሮ ወዝ-አደር ስናገር አንዱ ካድሬ የአእምሮ ወዘ-አደር የሚባል ነገር የለም ብሎ ተቆጣ፤ አብረውን የነበሩት ሁሉ በስምንት ተኩል እኔ ቢሮ እንዲመጡ ጋበዝሁና መጽሐፉን ይዤ መጣሁና ለካድሬው አሳየሁት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌኒን ተናዶ በደርዘን የሚቆጠሩ ካድሬዎችን በአንድ ትጉህና ታታሪ ባለሙያ የሚለውጠኝ ባገኘሁ ብሏል ስል ያው የማይማር ካድሬ ተቆጣና ..አይወጣውም…. አለ፤ መቶ ብር ከኪሴ አወጣሁና አንድ ጊዜ በነፃ አስተምሬሃለሁ፤ አሁን ግን መክፈል አለብህ፤ የሌኒንን ጽሑፍ ካላመጣሁልህ መቶ ብር ታገኛለህ፤ ካመጣሁ ግን መቶ ብር ትከፍላለህ ብለው አሻፈረኝ ብሎ በስሀተቱ ጸና፤ አቶ ዓሥራት ብዙውን ጽሑፎቾን አንብቤአለሁ ሲል እውነት እንዳልሆነ ስለማውቅ ውርርድ ላቀርብለት ፈልጌ ነበር፤ ስለአማራ የተናገረው እኔ የጻፍሁትን እንዳላነበበ ጥሩ ማስረጃ ነው፤ ሳያውቁ በእርግጠኛነት አዋቂ መስለው ለሚቀርቡ ቀላሉ መንገድ በአደባባይ ውርርድ ነው፤ ገብሩ ታረቀ እንኳን በአሜሪካ የፈረንጅ ልጆች ሲያስተምር ስለኖረ በአገር ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ ማንበቡ አጠራጣሪ ነው፡፡
ለነገብሩና ለነዓሥራት ትልቁ ፍሬ ነገርና ቁም-ነገር ትግሬነታቸውን ለብቻቸው የያዙት መስሎአቸው ነው፤ በትግሬነታቸው ውስጥ አነሱንና እኔን የሚያያይዙ ብዙ ከባድ ሰንሰለቶች መኖራቸውን አያውቁም፤ ለነሱ ትግሬ ከትግሬነት ሌላ ፋይዳ ወይም ትርጉም የለውም፤ እንደዚህ ያለ ክርክር መነሳቱ ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል እንደላላ የሚያመለክት ነው፡፡
..ማወቅ ወደ እርግጠኛነት የሚያመራው በመጠራጠርና በመጠየቅ ነው፤ አለማወቅ ግን ምንጊዜም ወደጠን ካራ የጨለማ እርግጠኛነት የሚመራ ነው፤ አለማወቅ ከኃይል ጋር ሲጋባ የአምላክን ቦታ ይይዝና እስመ አልቦ ዘይሰአኖ ይሆናል፡፡..
ሁለቱም ሰዎች፣ ፕሮፌሰር ገብሩም አቶ ዓሥራትም ባሳዩዋቸው ሁለት የእውቀት ጉድለቶች ልጀምር፤ ይህንን ማድረጉ አያስደስተኝም፤ ነገር ግን አለማወቅን ወደ እውቀት እየለወጡ ሰዎችን ማሳሳቱ፣ ከዚያም አልፎ በትግራይ ማህበረሰብ ላይ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የጥላቻ መርዝን ለመንዛት የሚደረገውን ሙከራ አገርን የሚጎዳ ነውና ሊታለፍ አይገባም፤ ፕ/ር ገብሩም አቶ ዓሥራትም በሂሳብ ትምህርታቸው ስለ Set theory ትንሽ ቢያውቁ ..የኤርትራና የትግራይ ዜጎች..ያልሁት ደማቸውን አያፈላውም ነበር.. ትግራይ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ውስጥ ይገኛሉ፤ የኔ ስህተት የአንባቢዎችን ደረጃ ከፍ አድርጌ መመደቤ ነው፡፡
ሌላው የእውቀት ልዩነት ሰው የመሆን ግንዛቤያችን ነው፤ ለእኔ ሰው በቁና የሚሰፈር፣ ወይም በከረጢት የሚታሰር አይደለም፤ እያንዳንዱ ሰው በነጠላ ለራሱ ስራ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤ እንኳን በ2004ዓ.ም ጥንትም ቢሆን ጽድቅም ሆነ ኩነኔ የግል ነው፤ በጎሳ ወይም በጅምላ አይመጣም፤ የሰው ልጅ እንደ አይጥና እንደድመት አይደለም፤ እንኳን አብሮ የኖረና የተዛመደ፣ አንዱ ለሌላው የመጨረሻ መስዋዕትነት የከፈለ ቀርቶ እንግዳም ቢሆን አንዱ ለሌላው መሰረታዊ ጠላትነት የለውም፤ ፕ/ር ገብሩና አቶ ዓሥራት እንጀራቸውን ለማብሰል ለትግሬዎች ዘብ የቆሙ መስለው ባልገባቸው ነገር ሁሉ ደማቸውን ያገነፈሉት እኔን ባዕድ በማድረግ ለመጠቀም ነው፤ ለእነሱ አዝናለሁ፤ የትግራይ ህዝብ እኔን በነሱ ዓይን እንደማያየኝ አምናለሁ፡፡
ፕ/ር ገብሩ ..እኔም እንደአስገዶም ገ/ስላሴ የወዲያ ማዶ ልጅ ነኝ.. ይላል፤ ወዲያ ማዶ ስል ትግራይ ማለቴን ማን ነገረው? ስብሐት ነጋን ወዲህ ማዶ ሳደርገው በገብሩ ግንዛቤ ትግሬ አይደለም ማለቴ ነው መሰለኝ.. ገብሩን ወዴት ከፍ ከፍ እለዋለሁ.. ገብሩ የወዲያም የወዲህም ልጅ አይደለም፤ የባህር ማዶ ልጅ ነው..
ሁለተኛ ስለኤርትራውያን የተናገረው መልካም ስሜቱን ከመግለጽ በቀር መጽሐፉን ቢያነብበው ኤርትራውያን በስሜት ሳይሆን በተግባር እሱ ..እስረኞች.. ያላቸው ሰዎች የገለጹትን እውነት ያስተባብለዋል፤ በተጨማሪም ለታሪክ ባለሙያው መንገር ካልሆነብኝ የሠርጸ ድንግልን ዜና መዋዕል ቢያነበው ከወራሪ መከላከል እንደሚችሉ ሊገነዘብ ይችላል፡፡
ሶስተኛ፣ ..የሞራል ሉዓላዊነት.. በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ አልገባኝም፤ አላግባብ ተሰካክቶ የተደነቀረ ነገር ነው፡፡
አራተኛ፣ ለኢጣልያ ገብረው የጠላት ወታደር በመሆን ወገናቸውን የወጉት ኤርትራውያን እጅና እግር መቆረጡ በአሁኑ ጊዜ ላለነው የሚዘገንን ነው፤ ነገር ግን ፕ/ር ገብሩ በዓድዋ ጦርነት በምኒሊክ አገዛዝ የተደረገውን ሲናገር በቅርቡ በማይጨው የደጃዝማች ኃ/ስላሴ ጉግሳን ሆነ በሌላ የተፈፀመን ቅጣት አለማንሳቱ፤ በአገራችንም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን አልሰማም ይሆን? የአጼ ዮሐንስንስ አልሰማም ይሆን? ወይስ እኔ እንዳነሳለት ፈልጎ ይሆን? አንዳንድ ነገሮችን እየነቀሱ በማውጣት ታሪክ እንደማይጻፍ ለፕ/ር ገብሩ መንገር አያስፈልግም፤ የምኒልክን ሀጢአት ለማበራከት ከሆነ ከሸዋ ሳይወጣ በጧፍ ያነደዱትን ሊጨምርበት ይችላል፡፡
አሁን ከባድ ወደሚመስሉኝ ነጥቦች ልምጣ፤ ለእኔ እንደሚገባኝ ታሪክ ሁነትን በመግለጽ ይጀምራል፤ በትክክል ለተመዘገበው ሁነት ፍቺ መስጠት፣ ወይም ጥሩና መጥፎነቱን በመግለጽ ፍርድ መስጠት በኋላ የሚመጣ ነው፤ በሌላ አነጋገር ፍርድ ሁነትን ተከትሎ ይመጣል እንጂ የሁነቱ ፍቺ ወይም በሁነቱ ላይ የሚሰጠው ፍርድ አይቀድምም፤ ይህ ከሆነ ፈረንጆች እንደሚሉት ፈረሱን በጋሪው ለመጎተት እንደመሞከር ይሆናል፤ አጉል ድካም ነው፤ አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ለሁለት ጊዜ ገብሩ ለማድረግ የሚፈልገው ይህንን ነው፤ ምን እንደተናገርሁ ለአንባቢው ሳይነግር፣ በራሱ ግምት የተናገርሁ ለመሰለው ነገር ፍቺና ፍርዱን መስጠት ይጀምራል፤ ይህ የእውቀትና የእውነት ፈላጊ ምሁር የአጻጻፍ ስርዓት አይደለም፤ በዚህ ጉዳይ አቶ ዓሥራት እኔ ያልሁትን በትክክል ጠቅሶ ወደራሱ አስተያየት ይሻገራል፤ ይህ ተገቢ ነው፡፡
ገብሩ ግን ..ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በትግራይ ዜግነት መተካትዎ ምን ቢያስቡ ነው?.. ይለኛል፤ መጀመሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ ምን እንደተናገርሁ አይገልጽም፤ የተገነጠለውን ኤርትራን ይገድፍና ዘልሎ ትግራይን ለማስገንጠል የፈለግሁ ለማስመሰል ..ምን ቢያስቡ ነው?.. ይለኛል.. ኤርትራን የጨመረ እንደሆነ ተንኮሉ ይበላሻል.. ለኢትዮጵያውያን ነግሮ ሊያስወነጅለኝ ፈልጎ ነው? ወይስ ለአስገንጣዮቹ ነግሮ ሊያስሸልመኝ.. ለተገንጣዮቹና ለአስገንጣዮቹ በስሜት ማንኛችን እንቀርባለን?
ከላይ እንደጠቀስሁት በሂሳብ ወይም በፍልስፍና ንባብ ቢደገፍ እዚህ ስህተት ላይ አይወድቅም ነበር፤ ..ምን አስበህ ነው?.. የሚለው ለመወንጀልና ለማስወንጀል የተቃጣ ለማንም ግልጽ የሆነ ንጹህ ተንኮል ነው፤ ከኢትዮጵያ ዜግነት የተለየ የትግራይ ዜግነት መኖሩን ሊነግረኝ ያሰበ ይመስላል፤ እንዲህ ያለ መያዣና መጨበጫ የሌለው ነገር እኔ አልተናገርሁም፤ በ1998 ጓደኞቼና እኔ ከተከሰስንበት አንዱ የትግሬን ዘር ለማጥፋት መሞከር የሚል ለጆሮም የሚቀፍ ነገር ነበር፤ በ1998 ፍርድ ቤት በቀረብንበት ጊዜ የዛሬው የገብሩ ጽሑፍ ቢገኝ ትልቅ ማስረጃ ሆኖ ይቀርብ ነበር፤ እግዚአብሔር ሲያወጣን ገብሩ በዚያን ጊዜ ከእኛ ጣጣ ተከልሎ በአሜሪካው ነበር፤ ዛሬም 1998 እየሸተተ ነውና ገብሩ ስራ አያጣም፡፡
አንድ የታሪክ ባለሙያ ፕ/ር ትናንት በጋዜጣ የተጻፈውን በትክክል መድገም ሲሳነው ከአስር፣ ከሃምሳ፣ ከመቶ ወይም ከዚያ በላይ የቆዩ ጉዳዮችን እንዴት አስታውሶ እውነቱን ሊናገር ነው? እኔ የጻፍሁትን እሱ በመሰለው ተርጉሞ ከአገርና ከዘመድ ጋር የሚያጣላ ከባድ ነገር ሲለጥፍብኝ በጣም ያሳዝናል፤ መቼም ኢትዮጵያ ሆነና ነው እንጂ በሌላ አገር ቢሆን የጋዜጣው አዘጋጅ ያልተባለ ነገር ተቀብሎ አያሳትመውም ነበር፤ ከዚያም በላይ ገብሩና እኔ ስለምንተዋወቅ እሱ የጻፈውን ሌላ ሰው ቢጽፈው ገብሩ ይቃወማል ብዬ ሙሉ እምነት ነበረኝ፤ እንዲህ ዓይነት ጭራሽ ትርጉም የሌለው ነገር እኔ አልወጣኝም፤ ከኢትዮጵያ የተለየ የትግራይ ዜግነት የሚባል ነገር መኖሩንም አላውቅም፤ ዜግነት ምን እንደሆነና ከጎሳዊነት የተለየ መሆኑን አውቃለሁ፤ ዜግነትን በጎሰኛነት የሚተኩት እነማን እንደሆኑ ገብሩ አላወቀም ማለት ነው፤ ወይም አምስት መቶ ዶላር ኪራይ የሚከፈልበት ጊዜያዊ ዜግነት ከሌለው በቀር ወደ ቀበሌ መታወቂያ ለማውጣት ሲሄድ ያስረዱታል፤ እኔ ግን ዜግነትንና ጎሰኛነትን አላነካካቸውም፤ ዜግነቴንም እንዲያው በዋዛ አላየውም፡፡
* ..የኤርትራና የትግራይ ዜጎች.. ያልኋቸው ኢትዮጵያውያን ካልሆኑና የዜግነት ግዴታ ከሌለባቸው ኃላፊነቱን ከየት አምጥቼ ጫንሁባቸው?
* ገብሩስ የኢትዮጵያ ዜግነታቸውን ተገፈፉ ብሎ ወደቁጣና ወደመከፋት ያመራው ዜግነታቸውን ከዜግነታቸው ግዴታ እንዴት ለይቶ ነው?
የዜግነት መብትና ግዴታ በእያንዳንዱ ግለሰብ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው፤ ዘርን ወይም ጎሳን ከዜግነት ጋር ማገናኘት ግልጽ ስህተት ነው፤ በ1969 ሶማልያ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ አንድ የትግራይ ዜጋ በራሱ ፈቃድና ወጪ አዲስ አበባ መጥቶ ለመዝመት መወሰኑን በቴሌቪዥን አይተናል፤ የኢትዮጵያ ዜጋ ስላላልሁት በተግባር የገለጠውን የዜግነት ግዴታ ይፍቀዋል የሚል የጎሳ ህመም የያዘው ብቻ ነው፡፡
እጅግ የሚያስደንቀውና ከገብሩ በጭራሽ የማልጠብቀው የቼኮዝላቫኪያውን ጸሐፊ የሀበሻ ጀብዱ የሚለውን መጽሐፍ ገና ሳያነብበው መጥላቱ ነው፤ እኔ ሰውዬውን ጎበዝ በማለቴም የተበሳጨ ይመስላል፡፡
..የትግሬ ሽፍቶች.. በሚለውም ጥቅስ ተበሳጭቷል፤ የእሱ መበሳጨት አንሶ ሌሎችን ለመቆስቆስ ..በዚህ አባባልዎ ብዙዎች ዜጎችን ሳያስከፉ እንዳልቀሩ ሳልጠቅስ ለማለፍ አልፈልግም.. ይላል፤ ብዙ ሰዎችን የሚያስከፋው አባባሌ ምን እንደሆነ የታሪክ ፕ/ሩ አልተናገረም፤ የእኔን ጽሑፍ ያላነበበ ሰው አንድ መጥፎ ነገር የተናገርሁ ይመስለዋል፤ እኔ ያልሁት ስላልተጠቀሰ አንባቢው የራሱን ፍርድ ለመስጠት እንዳይችልና የገብሩን ፍርድ ብቻ ተቀብሎ መስመር እንዲይዝ ይጋብዘዋል፤ ከገብሩ እኔ የምጠብቀው አንደኛ ምንም ያህል ቢያስከፋ እውነትን ለመቀበል ዝግጁ መሆንን ነበር፤ ሁለተኛ ፀሐፊው የጠቀሳቸውን የትግሬ ሽፍቶች ለትግራይ ህዝብ በሙሉ ማልበስ አጉል ጎሰኛ አስተሳሰብ ነው፤ ትዕግስትና ፍላጐት አድሮበት መጽሐፉን ቢያነብበው የራስ ስዩምም ጦር ከራስ ካሣ ጦር ጋር ተሰልፎ ሲዋጋ እንደነበረ መረዳት ይችል ነበር፤ በህገ ኀልዮት (ሎጂክ) ለጥቂቶች የተነገረውን ለጠቅላላው ማልበስ ልዩ ስም ያለው የአስተሳሰብ ጉድለት ነው፤ ነገር ግን ፕ/ር ገብሩ በዚህ በህገ ኀልዮት ስሀተቱ እኔን ለማቄል ..በሽፍቶች አሳበው መላውን ትግሬ ለመፈረጅ ነው የሚል እሳቤ የለኝም ይላል፤.. እንኳን ይቺንና የዝንብ ጠንጋራ እናውቃለን ሲባል አልሰማም መሰለኝ..
በፍትህ ጋዜጣ ከአቶ ስብሓት ነጋ ጋር የተጀመረው ክርክር በአንድ ጉዳይ ላይ ነበር፤ ከዚያ ክርክሩ እየወረደ የጎሳ ሽታ ይዞ መጣ፤ የኔ የመጨረሻ ጥረት ይህንን የጎሳ ሽታ ለማስወጣት ነበር፤ ሐጎስ እርገጤ ሌባ ነው ሲል በላቸው የሚናደድ ከሆነ፣ እርገጤ ሐጎስ ሌባ ነው ሲል ጥዑም የሚናደድ ከሆነ እንደሰዎች ለመነጋገር የምንችልበት ጊዜ አልደረሰም ማለት ነው፤ በግላችንም ሆነ በህዝብነታችን የሚያዳክመን አጉል መሸፋፈንና ድብብቆሽ ነው፤ እውነቱን ለማወቅና እውነቱን ለመናገር ድፍረቱን ከአገኘን ሳንጎዳዳ እንደልብ ለመነጋገር እንችላለን፤ ለጋዜጦቹም ሆነ ለአንባቢዎች አንድ ለመግባቢያ የሚረዳን ሀሳብ ላቅርብ፤ INTERNET ውስጥ ገብተን LOGICAL FALLACY ብለን ብንጠይቀው በምንነጋገርበትም ጊዜ ሆነ በምንጽፍበት ጊዜ ሊረዳን የሚችል ትምህርት የምናገኝ ይመስለኛል፤ በገለባ እየለወጥን የምናውቀውንም የማናውቀውንም እያደባለቅን ብንነታረክ ዋጋ የለውም፤ ከዚያም በላይ እያንዳንዳችን ተምረናል፤ አውቀናል፤ ብለን በውስጣችን ያለውን መርዝ ከምንነዛው በውስጣችን ይዘነው እኛኑ እንዳደረገ ያድርገን፡፡

Feteh.

ቀዳሚ ቃል:- መስፍን ወልደማርያም /ፕሮፌሰር/

2 Sep

The PDF format for “Introduction to Dekekee Estifano’s Pain” by Professor Mesfin Woldemariam

በፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተተረጎመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ሰቆቃ ያስደነግጣል፤ ያሳዝናል፤ ያስቆጣል፤ የማናውቀውን ራሳችንን እርቃናችንን ያሳየናል፡፡ ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላም ፍንክች አለማለታችን ውስጣችንን እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ ይህንን መጽሐፍ ሳነብብ ምዕራባውያን (በእንግሊዝኛ) “ቶርቸር” (የግዕዝ ፀሐፊዎች “ኩነኔ”) የሚሉትን ሰውን የማሰቃየትን ዘዴ እኛ የፈጠርነው መሰለኝ፡፡ ቻይናውያን በዚህ ክፉ ዘዴ እንደሚታሙ አውቃለሁ፤ እኛም ሆንን ቻይናውያን የታሪካችንን ርዝመትና ያለንበትን የደኽነት አዘቅት ለመገንዘብ ይህ የክፋት ዘዴአችን ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ይመስለኛል፡፡ ከሰዎች በፊት በስልጣኔ በራፍ ላይ ደርሰን ከኋላችን የመጡት በአዳራሹ ሲገቡ እኛ አሁንም ውጭ ቆመን መቅረታችንና በልመና የምንኖር መሆናችን የገዥዎቻችን የአፈና ተግባር የማይቀር ውጤት ሆኖ ነው፡፡ በህገ አራዊት እየተመራን የሰውነት ሀብታችንን፣ አእምሮአችንና መንፈሳችንን ታፍነን ኑሮአችንን የምናሻሽልበትን ዘዴ ለመፍጠር አልቻልንም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ወኔ የነበራቸውና ሃሳባቸውንና እምነታቸውን ማንንም ሳይፈሩ በአደባባይ ለማውጣት የቻሉ ሰዎች መገኘታቸው ከአፈናው ባሻገር ጭራሹን ባዶ አለመሆናችንን ያሳየናል፡፡ ትልቁ ነገር የነዚህን የደቂቀ እስጢፋኖስን ሃሳብና እምነት መቀበል ወይም አለመቀበል አይደለም፤ ትልቁ ቁምነገር አባ እስጢፋኖስ በማንም አፋአዊ ኃይል ተመርተው ወይም ተገድደው ሳይሆን በራሳቸው የውስጥ የአእምሮ ብርሃን ተጉዘው ከ..ሲወርድ ሲዋረድ.. አስተሳሰብ ተላቅቀው ወደ አንድ መደምደሚያ ላይ መድርሳቸው ነው፡፡ ለማንም ማህበረሰብ ለትምህርትና ለእውቀት፣ ለእድገትና ለመሻሻል፣ ለልማትና ለብልጽግና አዲስ ፈርን እየቀደዱ አዳዲስ ደረጃ ላይ የሚደርሱት እንደዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ሰዎች እንደተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ እያሉ ድርግም በማለታቸው አገሪቱ ከነሱ ልታገኝ የምትችለውን ዘለቄታ ያለው ጥቅም አጣች፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት “ሲወርድ ሲዋረድ” በሚል በማያስብና በማያሳስብ የቁልቁለት አስተሳሰብ ለብዙ ምእት ዓመታት ተጓዙ፤ ውጤቱ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የቤተክህነት ትምህርት አእምሮን የመሳል ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው አያጠራጥርም፡፡ የተሳለና የሰለጠነ አእምሮ በጥልቀት ያስባል፤ ትክክለኛ የአስተሳሰብ ስልት በመከተልም አዲስ ሐሳቦችን ያፈልቃል፤ አዲስ ሐሳቦች አዲሱን ትውልድ ወደ አዲስ የእድገት ደረጃ ላይ ያወጡታል፤ አዲስ ሐሳቦች ከቆዩ ሐሳቦች ጋር እየተጋጩ በህገ ኃልዮት ያሸነፈው ይቀጥላል፤ የተሸነፈው ይሞትና ወደታሪክ ማህደር ይገባል፡፡ ወይም አዲሱና አሮጌው ተፋጭተው ከሁለቱም ውህደት ሌላ አዲስ ሀሳብ ይወጣል፡፡ የምዕራቡ ህብረተሰብ የተጓዘበት እውቀትን የማስፋት መንገድ ይህ ነው፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስ ሰቆቃ በግልፅ የምናየው ግን በእኛ ማህበረሰብ አዲስ ሀሳብ ጠላት ሆኖ መታየቱን ነው፤ ህገ ኀልዮት በህገ አራዊት መደቆሱን ነው፡፡ ሀሳብን በሀሳብ መቋቋም የማይችሉ የስልጣን ጉጉት የአእምሮ ስንኩላን ያደርጋቸው የሚቀናቸውና የሚቀልላቸው የሚጠሉት ሐሳብ ማህደር የሆነውን ሰው ማጥፋቱ ነው፡፡ የኖረውን ያለውን በግድ ተቀበሉ እየተባለ አዲስ ነገርን ማሰብና መግለጽ አደገኛ ተግባር እየሆነ ይሄዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ማሰብን ማስቀረት የማይቻል ቢሆንም ሐሳብን በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ማውጣቱ ለኢትዮጵያውያን እስከዛሬ አስቸጋሪ ነው፤ ስውርና የተለባበሰ አነጋገር እስከዛሬም ባህላችን ሆኖ የቆየ ይመስለኛል፡፡
ስለደቂቀ እስጢፋኖስ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክና ባህል በአዲስ መንፈስ እንደገና እንድንመረምር የሚጋብዘን ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን የአይሁድ አገር ለማድረግ፣ የእስላም አገር ለማድረግ የጠፋው የሰው ህይወት፣ የፈሰሰው የሰው ደም፣ የወደመው ንብረት ለህገ አራዊት እንደተገበረ መስዋዕት ልንወስደው የምንችል ይመስለኛል፡፡ የሚያሳዝነው ለህገ አራዊት መገበሩ ገና ዛሬም አለማብቃቱ ነው፡፡ ይህ ነው እያንዳንዳችን ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን፤ ምንድን ነው በእኛ ውስጥ ወይም በባህላችን ውስጥ ሐሳብን እንደጦር የሚፈሩ ሰዎች አናታችን ላይ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው? በተራው ኢትዮጵያዊም ዘንድ ቢሆን ይኸው ሐሳብን የመፍራት አዝማሚያ እንዴት ባህል ሆነ? ጭቆናን የኢትዮጵያውያን ባህርይ ያደረገው ምንድን ነው? ከምንም ህዝብ የተለየ የጭቆና ዝንባሌ የለንም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን እውነት ለመካድ መሞከሩ አይረዳንም፤ መድኃኒት የሚሆነን መቀበሉና መመርመሩ ነው፡፡
ጌታቸው በመግቢያው ላይ ደቂቀ እስጢፋኖስ ከማርቲን ሉተር ሰላሳ ዓመታት ቀድመው ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያመጡ ሰዎች ነበሩ ይላል፡፡ ይህ ትልቅ ነጥብ ነው፤ ማርቲን ሉተር በአውሮፓውያን አእምሮ ላይ ያመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ በሃይማት ላይ ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በዓለማዊው ጉዳይ ላይ የነበረው ተፅእኖ ማክስ ቬበር በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መሀከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማሳየት በዘገበው አንድ የቀልድ አባባል ይገለጣል፤.. ..ወይ በደንብ ብላ፤ ወይ በደንብ ተኛ፡፡.. Max Weber (tr. Talcott parsons), The protestant Ethic and the spirit of capitalism, ለዚህ የቬበር መጽሐፍ ቀዳሚ ቃሉን የጻፈው የእንግሊዙ የኢኮኖሚክስ ታሪክ ሊቅ ታውኒ ፕሮቴስታንትነት በአመጣው ለውጥ “ስራ የኑሮ ዘዴ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዓላማም አገኘ” ይላል፡፡ ይላል በዚሁ በማክስ ቬበር መፀሀፍ ገፅ ሶስት ላይ አእምሮ ከአፈና ሲወጣና ነፃነትን ሲያገኝ ከሰው ልጅ ውስጥ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይወጣል፤ ወሰኑ የማይታወቅ የመፍጠር ችሎታ በተጨባጭ ተግባር ይገለጣል፡፡ በዓለም ውስጥ ዛሬ በበለፀጉትና በሚደኸዩት አገሮች መሀከል ያለው ትልቁና ዋናው ልዩነት የአእምሮ ነፃነት ነው፡፡ ለምሳሌ በሚደኸዩት አገሮች ውስጥ ባለው ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት ይበልጥ የሚጠቀሙበት የበለፀጉት አገሮች ናቸው፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስም ላይ ቢሆን የአእምሮ ነፃነት ከሃይማኖት አጥር ውጭ ያለውን ዓለም የማሻሻል ችሎታን እያሳየ ነበር፤ አባ ዕዝራ ስለተግባረ እድ ተጠይቀው ሊያደርጉ የሚችሉትን ሁሉ ሲዘረዝሩ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ በውስጣቸው መኖሩን ያልተገነዘበው የንጉሱ መልእክተኛ መልስ “ይህን ሁሉ አደርጋለሁ የምትለው እግዚአብሔር ነህ እንዴ?” የሚል ነበር፡፡
አንድ ተጨማሪ ነጥብ መነሳት ያለበት ይመስለኛል፤ ከእለት ተእለት የኑሮ ትግል በቀር ማሰብን እንደሙያ የያዙ ሰዎች ከሃይማኖት ውጭ በኢትዮጵያ ነበሩ ለማለት ያስቸግራል፤ እነዚያውም በሃይማኖት አጥር ውስጥ ሆነው የማሰብ ችሎታቸውን ያሳዩ ሰዎች …እንደ አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው፣ ከዚያም በኋላ እንደፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ያሉት..ለስደትና ለስቃይ መዳረጋቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብ የተከለከለ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ትምህርቱ በተራቀቀበት በሃይማኖቱ አጥር ውስጥ ማሰብ ከተከለከለ ትምህርት በሌለበት ከሃይማኖቱ አጥር ውጭ ማሰብ ጨንገፎአል ማለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በሃያኛው ምእት አመት የዘውዱ ስርዓት ከፈጠረውና ከብዙ ዓመታት ትግል በኋላ የኢትዮጵያ መካነ ኀልዮት ከሆነው ደርግ ቢያዳክመውም ካልገደለው ዩኒቨርስቲ ወያኔ አርባ መምህራንን ማስወጣቱና ብዙዎቹን ለስደት መዳረጉ የሚያመለክተው አለመለወጣችንን ብቻ አይደለም፤ ከሃያኛው ምእት አመት ወደኋላ ተመልሰን አሁን በኢትዮጵያ ማሰብ የተከለከለ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም እኩይ የወያኔ ማን አለብኝነት ዩኒቨርስቲውን ቢያንስ ሰላሳ ዓመታት ወደ ኋላ እንደመለሱት ማሰብ ስለሚሳናቸው ሊገባቸው አይችልም፤ የአገሪቱን ዓይን እንደማጥፋት የሚቆጠር ነው፡፡
ጌታቸው ስለደቂቀ እስጢፋኖስ “አበባቸውን አረገፉት፣ የእንቅስቃሴያቸውን ነበልባል ውሐ ቸልሰውበት ሳይቀጣጠል ቀረ” ሲል የደቂቀ እስጢፋኖስን ሐሳብና እምነት መዳፈን በሚገባ ይገልጠዋል፡፡ ውጤቱ ግን በደቂቀ እስጢፋኖስ የተወሰነ አልነበረም፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የአእምሮ ነፃነት ተዳፍኖ እንዲቀርና ኢትዮጵያ በልጆቿ የአእምሮ ኃይል እንዳትጠቀምበት ሆኗል፡፡ ይህም ደኽነታችንንና ኋላቀርነታችንን ፍንትው አድርጎ የሚያስረዳን ይመስለኛል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ባንቱስታን መሰል የጎሳ ክፍፍል በሚታመስበትና በጥላቻና በመፈራራት መንፈሳዊ ውሳኔ ተሙዋጥጦ ባለበት ጊዜ የደቂቀ እስጢፋኖስ ታሪክ ልዩ መልእክት አለው፤ አገዛዙ ምንም ያህል በህገ አራዊት ላይ የተመሰረተ ክፉ ጭካኔ ቢያሳይም የሰው ልጅ መንፈስ የማይበገርና እምቢ ባይ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ቁም ነገሩ ደቂቀ አስጢፋኖስ መሸነፋቸው አይደለም፤ ቁምነገሩ እየተሰቃዩ መታገላቸው ላይ ነው፤ ለህገ አራዊት አንንበረከክም ማለታቸው ነው፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ነገር አንድም የደቂቀ እስጢፋኖስ አባል ሲሞት ሞተ አለመባሉ ነው፤ “ሰማዕትነቱን” ወይም “ገድሉን ፈጸመ” ይላሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጥልቅ መልእክት ያለው ሆኖ ይሰማኛል፡፡ የሰው ልጅ ህይወት እንደእንሰሳ ህይወት አይደለም፤ ዓላማ አለው፤ መልእክት አለው፡፡ ቁም ነገሩ ዓላማውን ወይም መልእክቱን መፈጸም ነው እንጂ መኖር ብቻ አይደለም፤ ሐሳብንና እምነትን እንደያዙ በነፃነት ማለፍ ሐሳብንና እምነትን አስረግጦ ከመኖር የተሻለ ነው ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ ለዛሬው ትውልድ ይህ ኃይለኛ መልእክት ነው፡፡
የዛሬው ትውልድ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ባለውለታ ነው፤ እነዚህ ለአዋቂው ለውጪው ዓለም ክፍት ሆነው፤ ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተቆልፈውበት የነበሩ ጽሑፎች ናቸው፡፡ እስከዛሬ አንድም ንጉስ ወይም ፕሬዚዳንት እነዚህን ታሪካዊ ሰነዶች አላስተረጎመና አላሳተመም፡፡ ጌታቸው በራሱ ጥረት ብቻ እነዚህን ጽሑፎች በአማርኛ እየተረጎመ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ ስላበቃቸውና ስለራሳችን እንድንማር በሩን ስለከፈተልን ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ በበኩሌ የምጨምረው በዚህ ሳያበቃ እግዚአብሔር እድሜውንና ብርታቱን ሰጥቶት ሌሎቹንም እንዲያበረክትልን ነው፡፡

ፍትህ

ንግግራችን ትርፋማ እንዲሆን ከአሉባልታ እንውጣ

14 Aug

መስፍን ወልደማርያም /ፕሮፌሰር/

ሰሞኑን አልጀዚራ ላይ ካፌው ወይም የቡና ቤቱ በሚል ርዕስ አንዲት የኬንያ ጋዜጠኛ ከዚያው ከናይሮቢ የምታስተላልፈውን ፕሮግራም ስመለከት ምን ያህልና በስንቱ ነገር ወደኋላ መቅረታችን አሳዘነኝ፤ በአንጻሩ በረከት ስምዖንና ሽመልስ ከማል በእኛ አገር እንዲህ ያለነገር ባለመኖሩ እንዴት እንደሚደሰቱና እንደሚኮሩ አሰብሁ፡፡ አሁን እንኳን የፈለግሁት አቶ ስብሓት የአልጀዚራን ቡና ቤት እንዲጎበኘው ለመጋበዝ እንጂ ስለአፍ ጠባቂዎች ለመናገር አልነበረም፡፡
አቶ ስብሓት ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች እየሰራ ነው፤ በቀላሉ ልጀምር፤ በጽሁፉ ከባድ የሆነ የአስተሳሰብ ስህተት ይታያል፤ አንድ ምሳሌ፡-
…የውጫሌ ውል ለምን አስፈለገ… ጣልያን ኤርትራን ለምን ያዘ… የወቅቱን ጥያቄዎች አንስተን ትክክለኛ መልስ እንዲያገኙ ለታሪክ ባለሙያዎች ብንተወው ምናልባት መልሱ ኤርትራም በጣልያን አትያዝም ነበር፡፡ የአድዋ ጦርነትም አይኖርም ነበር ሊሆን ይችላል (……)
ይህ አባባል እምብዛም ትርጉም የለውም፡፡ ወተት ቢኖር በእንጀራ አምገህ ትበላ ነበር እንዳለችው ሴትዮ ነው.. ቢሆን ኖሮ በማለት ክርክሩን ለመለወጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በኤርትራና በትግራይ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራና የትግራይ ዜጐች ተግተው ኢጣልያንን ቢወጉ ኖሮ ከሐረር፣ ከሀድያና፣ ከሲዳሞ፣ ከሸዋ… ወደ ሰሜን መዝመት አያስፈልጋቸውም ነበር፤ ይህ ቢሆን ዛሬ ሌሎች ያልሞቱትን ሞት በመሞታቸው አይወቀሱም ነበር፤ ከኋላዬ ሁለት ተጨማሪ ዓይኖች ቢኖሩኝ፣ ቁመቴ አስር ሜትር ቢሆን፣ …እያሉ መከራከር የትም አያደርስም፡፡ ለልብ-ወለድ ስራ እንጂ ለታሪክ አይበጅም፤ የተዛባ አስተሳሰብ የሆነውንና ያልሆነውን፣ ያለፈውንና የሚመጣውን፣ እውነትና ሐሰትን ለይቶ በግልጽ እንዳያዩ አእምሮን ይጋርዳል፡፡ ስለዚህም አእምሮ ክፍት፤ ህሊና የፀዳ ሲሆን ለመግባባት ያመቻል፡፡
ስብሓት …..ታሪካችን ይጠና፣ ይመርመር፣ ይጻፍ፣ ህዝቦች ይወቁት….. የሚለው ትክክል ነው፡፡ ስለዚህም ነው ከማጥናትና ከመመርመር በፊት የሆነውን እንዳልሆነ፣ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ መናገር ወደ ስህተት የሚያመራው፤ የራሱን መመሪያ ቢከተል ከስህተት ይድን ነበር..
ሁለተኛው የሁነት ስህተት ነው፣ ይህም የሆነውን እንዳልሆነ፣ ያልሆነውን እንደሆነ እያደረጉ መናገር ነው፡፡ በአገር ጉዳይ በምንነጋገርበት ጊዜ ምንም ያህል የስልጣን ሰይፍ ብንታጠቅም በአገር ጉዳይ ሁላችንም እኩል ነን፡፡ ስለዚህም ለእውነት ምስክር የሚሆኑ ሰዎች አይጠፉምና እውነቱን በሻሽ መሸፈን እውነቱን ላይሸሽገው ተናጋሪውን ከባድ ትዝብት ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ስብሓት ስለአፄ ኃይለ ስላሴና ስለደርግ፣ እንዲሁም ታች ወርዶ ስለሽፈራውና ስለእኔ የሚናገረው እንኳን መመርመርና ማጣራት ቆም ብሎ ማሰብ የሌለበት አፍ ላይ የወጣውን መወርወር ነው፤ በማንአለብኝነት ጭልጥ ብሎ ወደስህተት መግባት፤ ለምሳሌ፤… በደርግ ዘመን የኤርትራ ..መሬትዋና ባህርዋ እንጂ ህዝቡ አያስፈልገንም የሚል በግልጽ ተዘመረ፤ የተግባር መመሪያም እሱ ሆነ፤.. ስብሓት ነጋ ይህንን የደርግ መመሪያ የሚለውን የሰማው በህልሙ ይመስለኛል፤ እውነት ከሆነ እኔን ትልቅ ነገር አምልጦኛል፡፡
እንዲሁም ቀደም ሲል በወጣው ጽሑፉ ላይ ሽፈራውና መስፍን ..ማህበረ ቅዱሳንን በጥናት ጉዳዮች ይደግፋሉ.. የሚለው የጤፍ ቅንጣት ያህል እውነት የለውም፡፡ እኔ ስለማህበሩ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ በመሬት ላይ የማውቀው ቅዱስም የለም፤ ከየት አንስቶ እንደለጠፈብኝ አላውቅም፡፡ መጥፎና ግልፅ ተንኮል ነው፡፡ የጎሳው ውንጀላ አነሰኝና አሁን ደግሞ የሃይማኖት ውንጀላ የሚጋብዝ ተንኮል ይመስላል፡፡ እኔ ይህንን መጨበጫ የሌለው አሉባልታ ከየት አገኘኸው ብዬ አጥብቀ አልጠይቅም፤ አቶ ተመስገን ለአቶ ስብሓት ጥያቄዎች በማስረጃ እንደመለሰው ስብሓት ሊመልስ አይችልም፡፡
ስብሓት ነጋ ስለወያኔ ድርጅት የሚናገረው እኛ ሃያ ዓመታት ሙሉ ከተከታተልነውና ከአወቅነው በፍፁም የተለየ ነው፡፡ ምናልባት እሱ ከፍ ብሎ ማማው ላይ ተቀምጦ የሚታየውና እኛ ታች ሆነን የሚታየን አይመሳሰልም ይሆናል፤ የምንሰማው ግን ጆሮአችንን ካልደፈንነው በቀር ሊለያይ አይችልም፤ ከወዲያ ማዶ እግዚአብሔር አቶ አስገደ ገብረ ስላሴ የሚባል ሰው አስነስቶ ያልተበረዘውን ደረቁን እውነት እንዲመሰክር እያደረገልን ነው፡፡ ስብሓት ነጋ ጥላሸት እንዳይቀባቸው እንጂ አንገፍግፎአቸው ከተሰደዱትም ምስክሮችን መጥራት ይቻላል፡፡ አቶ ስብሓት እናንተን ማየቱና እናንተን መስማቱ አቃተኝ ከአለ አቶ አስገደን ቢያዳምጥ እውነቱ ይገለጥለታል፡፡ ነገር ግን እውነቱ ቢገለጥለትም የማይቀበለው ከሆነ ለአክሱም ጽዮን እንሳልለታለን፡፡
አቶ ስብሓት ነጋ ህወሓት የሚማር ድርጅት ነው ሲል ህወሓት እንኳን መማርና የተማረ ሰው አጠገቡ እንደማያስደርስ ሃያ ዓመታት ሙሉ ያወቅነውን ሊያስክደን ነው? መማር የሚለው በተላላኪና በዶላር የሚገኘውን ዲግሪ ይሆን? ስብሓት ነጋ እየደጋገመ ስለታሪክ ይናገራል፤ የዛሬ መቶ ዓመትና ሁለት መቶ ዓመት የሆነውን ከማውራት የዛሬውን ምስክርነት ማስተካከሉ አይበልጥም ወይ? የህሊና ፍርድም ለመስጠት ከደረቁ እውነት መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የአድዋን ጦርነት እናንሳ አፄ ምኒልክ ከደቡብ፣ ከምዕራብና ከምስራቅ ጦራቸውን ሰብስበው ለጦርነት ሲዘጋጁ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባቸው? መንገዱ ምን ያህል ጊዜ ወሰደባቸው? የምኒልክ ጦር ከኢጣልያ ጦር ጋር ሲወዳደር ምን ያህል የሰለጠነ ነበር? የምኒልክ መሳሪያ ከኢጣልያ ጋር ሲወዳደር እንዴት ነበር? ስብሓት ሊመልሰው የሚገባ ሌላም በጣም በጣም ዋና ጥያቄ አለ፤ …አፄ ምኒልክ ጦራቸውን ሰብስበው በእግርና በበቅሎ ከደቡብ ተነስተው ትግራይ እስቲደርሱ ኤርትራና ትግራይ ምን አድርገው ጠበቁዋቸው? የኢጣልያ ጦር ትግራይን ሰንጥቆ አምባ አላጌ እስቲደርስ ማን ሊያቆመምው ሞከረ? የኢጣሊያ ጦር መቀሌ ገብቶ ሲመሽግ ማን ተከላከለው? ስብሓት እስከዛሬ ሳይገለጥለት ቀርቶ ከሆነ የኢጣልያንን ጦር ከአምባ አላጌ ያስወጣው የምኒልክ ጦር ነው፡፡ ከመቀሌም ምሽግ ያስወጣው የጣይቱ ዘዴና የምኒልክ ጦር ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ተሸፋፍኖ የቆየውን እናፍረጥርጠው ከተባለ ለማን አሳፋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡
ስለአድዋው ጦርነት ምስክርነት የሚሰጠን ገለልተኛ ታዛቢ እስክናገኝ ስለማይጨው ጦርነት የነበረ የዓይን ምክስር አንድ በቅርቡ ያነበብሁት መጽሐፍ ትዝ አለኝ፤ አንድ የቼኮዝላቫኪያ ጎበዝ የጻፈውን የሃበሻ ጀብዱ የሚል መጽሐፍ ተጫነ ጆብሬ መኮንን የተባለ ሰው የተረጎመውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳትሞታል፤ አቶ ስብሓት ብቻ ሳይሆን ማንበብ የሚችል ሁሉ ሊያነብበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፤ እኔ ፈረንጅ ስለኢትዮጵያ የፃፈውን ማንበብ ከተውሁ ብዙ ዓመታት ሆኖኛል፡፡ ይህንን ግን በአንድ ቀን ተኩል ጨረስሁት፤ የኢትዮጵያን ዘማቾች ከኋላ እያጠቁ ስለነበሩት ..የትግራይ ሽፍቶች.. ማን ይናገር? የነበረ፤ ነውና እንዲህ ይላል፡-
….የትግራይ ሽፍቶች) ለምን ወንድሞቻቸውን ይገድላሉ?… ከመሀል አገር ስድስትና ሰባት ወር ሙሉ ፍዳውን እያየ ሲጓዝ ከርሞ እዚህ የደረሰው ወንድማቸው፣ የነዚህን ምስኪኖች ህይወትና ንብረት ከጠላት ለመከላከል የገዛ ህይወቱን አልጋ ላይ ጥሎ፣ ቤት ንብረቱን በትኖ መከራውን ባየ ለምን ይገድሉታል?..
እነዚህ ሽፍቶች ወንድሙን የገደሉበት አብቹ የሚባል የአስራ ስድስት ዓመት የሰላሌ ዘማች በጣም ተናዶ የራሱን የግል ቡድን አቋቁሞ ያሳድዳቸው ነበር፡፡
ከዚያም በላይ እህል ውሃ ለዘማቹ እንዳይሸጡ ኢጣልያኖች በመከልከላቸው ዘማቾቹ ችግር ነበረባቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ለመናገር አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህንን እውነት ለመሸፈን በመሞከር የመሀል አገሩን ሰው መወንጀል ትክክል አይደለም፤ እውነት ተደብቆ አይቀርም፡፡
እንነጋገር ማለት አንድም ሆነ ሁለት የጋራ ችግር አለን ማለት ነው፡፡ እንነጋገር ማለት የጋረ አገር፣ የጋራ ወገን፣ የጋራ ሀብት፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ራዕይ አለን ብለን ማመን ነው፡፡ እንነጋገር ማለት እውነትን በማስረጃ አስደግፎ ነው፤ እንነጋገር ማለት እንግባባ ማለት ነው፤ እንግባባ ማለት ባንስማማም እንፋቀር፣ አንሸዋወድ፣ አናስሸብር ማለት አይደለም፡፡
በመጨረሻ ግራ ያጋባኝ ነገር አለ፤ አቶ ስብሓት ደጋግሞ ለኤርትራ መከታ መስጠት አለብን ሲል ከዝምድና ስሜት የመነጨ ነው ወይስ…፤ እንዲያውም ኤርትራን ..ከውጭ ወራሪ ለመከላከል እንኳን ገንዘብ ህይወትም መቆጠብ የለብንም.. ይለናል አቶ ስብሓት፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ይህንን ቢሰማ የሚቆጣ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አይቆጣም..
የእኔ አድናቆት ችግር እንዳያስከትል እንጂ ኢትዮጵያ እንደ አቶ አስገደ ገብረስላሴ ያለ ሰው እንዳታጣ የእግዚአብሔር በጎ መንፈስ አይለያት፡፡

The PDF file, hereunder:

https://jontambek.files.wordpress.com/2011/08/doc23.pdf

“የስልጣኔው መንገድ ሳይጣሉ መነጋገር ነው” – ፕ/ርመስፍን ወ/ማርያም

29 Jul

ግንቦት 2002 በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ቲያትር ከተደረገው ስብሰባ በኋላ በጋዜጣ ያየሁት የመጀመሪያው ጽሑፍ፣ ከዚያም ቀጥለው የወጡት ጽሑፎች የሚያወሱት ስለስብሰባው ርእስ ሳይሆን ስለአቶ ስብሐት ነው (ጋዜጣው እንዳለው አቦይ እንዳልለው ካልካደ እኔ በእድሜ ደህና አድርጌ እበልጠዋለሁ..፡፡ ስብሓት ርእስ መሆኑ አግባብ ያለው ቢሆንም የስብሰባውን ርዕስ ፍፁም እንዲሸፍነው መሆኑ ድንገተኛ ጎርፍ እየመጣ ከተኛንበት እያንቀረቀበ ሲወስደን የምናወራው ስለጎርፍ ሳይሆን አትግፉኝ፤ አትንካኝ እየተባባልን የመነታረክ አይነት ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ሆኖ ለውይይት ከቀረበው ጉዳይ ጋር ሲተያይ ስብሓት ነጋ ንጉስም ቢሆን ኢምንት ነው፡፡ ከስብሰባው በኋላ ዋናው ጉዳይ ቀርቶ እሱ የጋዜጦች ርዕስ መሆኑ ያለንበትን የድንብርብር ዘመን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህንን ለመግቢያ ያህል ካልሁ በሚቀጥለው አጭር መተላለፊያ ወደጋዜጣ ርዕስ ልግባ፡፡
አሁንም ዋናው ጉዳይ ጨርሶ እንዳይረሳ ፍሬ ነገሩን ባጭሩ ለማስታወስ በአስራ አምስተኛው ምዕተ-ዓመት አባ እስጢፋኖስ የሚባሉ መነኩሴ ከእግዚአብሔር በቀር ለማንም ለምንም መስገድ ተገቢ አይደለም የሚል እምነት ይዘው ተነሱና ብዙ አባሎችን አፈሩ፤ ይህ የሆነው በአውሮፓም ገና ሉተር የሚባለው የፕሮቴስታንት መሪ ከመነሳቱ ከሰላሳ ዓመት ግድም ቀድሞ ነው፡፡ ከተለመደው የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ልማድ በመውጣቱ ደቂቀ እስጢፋኖስ በሚባሉት የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች ላይ የደረሰባቸውን መከራና ስቃይ የሚገልጸውን ገድላቸውን ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአሜሪካ አሳትሞት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አማካይነት አሳትሞታል፡፡ የስብሰባው ዋና ርዕስ በዚህ መጽሐፍ የተገለፀው የደቂቀ እስጢፋኖስ አበሳና መከራ፣ ሞት ነበር፡፡ በእለቱ ከተናገርሁት ውስጥ የሚከተለውን ብያለሁ፡፡
..እነዚያ ሟቾችና ገዳዮች ለኛ ዛሬ ለምንኖረው ምን የሚያዛልቀን ትምህርት አስተምረውናል? የአቅመ-ቢሶቹ የደቂቀ እስጢፋኖስ ስቃይና ሞት ያስተማረን ነገር አለ? የጉልበተኞች ማሰር፣ ማሰር ሲሰለቻቸው ምላስና አፍንጫ መቁረጥ፣ ምላስና አፍንጫ መቁረጥ ሲሰለቻቸው እግርና እጅ መቁረጥ፣ እግርና እጅ መቁረጥ ሲሰለቻቸው መግረፍ፣ መግረፍ ሲሰለቻቸው መገደል አስተምሮናል? ይህ ትምህርት የዛሬ ስድስት መቶ ዓመት ግድም ከነበረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የተሻልን ሰዎች ፣ የተሻልን ኢትዮጵያውያን አድርጎናል? ከታሪካችን ብንማር ነው በአስራ ስድስተኛው ምዕተ ዓመት ደግሞ በክርስቲያንና በእስላም መሀከል አስራ አምስት ዓመታት ያህል የፈጀ መተላለቅ የተደረገው? በአስራ ሰባተኛው ምዕተ-ዓመትስ በካቶሊኮችና በኦርቶዶክሶች መሀከል የተፈፀመውስ ግፍና ስቃይ? ለዛሬውስ የኑሮ ስርዓታችን ምርኩዝ የሚሆነን ከታሪካችን የተማርነው ነገር አለ?
ምንም ዓይነት አስተያየት ሳልሰጥበት ከታሪካችን መማራችንን ወይም አለመማራችንን የሚያሳይ አንድ እውነት ላሳያችሁ፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በታተመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድል ትርጉም ውስጥ በገጽ 18 ላይ ተርጓሚ ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ የሚከተለውን ይላል፡፡
የረጅም ዘመን ወዳጄ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም ረቂቁን አንብቦ እንደሱ..ህግ ይዳኘን.. ከማለት በምንም ምክንያት ወደ ኋላ ላላሉ ኢትዮጵያውያን ታሪክ መግቢያውን የሚያዳብር ..ቀዳሚ ቃል.. ስለጻፈልኝ አመሰግናለሁ፡፡
ሆኖም መጽሐፉን ብታገላብጡት መስፍን ወልደ ማርያም ጻፈው የተባለውን ..ቀዳሚ ቃል.. አታገኙትም፡፡ ይህ የሚያሳዝን ስህተት የመጽሐፍ ተርጓሚ የዶ/ር ጌታቸው ኃይሌና የአዲስ አበባው አሳታሚ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው እኔ የጻፍኩትን ..ቀዳሚ ቃል.. ከአዲስ አበባው እትም እንዲወጣና ሺፈራው በቀለ በጻፈው እንዲተካ ሲያደርግ ከላይ የተጠቀሰውን ረስቶታል፡፡ ጌታቸውም ..የረጅም ዘመን.. ወዳጁን እንዳያሳዝን ..መስፍንን አስፈቅዱት.. ብሎ ከኃላፊነት ለመውጣት ሞከረ፡፡ መስፍን የጻፈው የወጣበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ጌታቸው ኃይሌም ሆነ ሺፈራው በቀለ የጻፉት በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እንደተለመደው የተሸበበ የታሪክ አጻጻፍ ነው፡፡ ዛሬ ከአለንበት ሁኔታ ጋር ለማያያዝ አይፈለግም፡፡ ያለፈውን ከዛሬው ጋር ካያያዙትና ዝምድና ካገኙበት የደቂቀ እስጢፋኖስን ያህል ባይሆንም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይህንን ጉዳይ የማነሳው መስፍን የጻፈው በመውጣቱ ቆጭቶት ነው የሚል ከአለ ክፉኛ ይሳሳታል…፡፡..

ስለመጽሐፉ ይህን ካልሁ በኋላ ወደ ጋዜጣው ውይይት እገባለሁ፡፡

በመጀመሪያ በጣም የተደሰትሁባቸውን ጉዳዮች ልዘርዝር፤ አንደኛ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ቲያትር ከብዙ ዘመናት በኋላ ለውይይት ተከፍቶ (ለእኔ ማለቴ ነው) ማየቴ በጣም ደስ ሲለኝ የስብሰባው መጨናገፍ ቢላዋ ሰጥቶ ስጋ መንፈግ ዓይነት መሆኑ ቅር ያሰኛል፡፡ ሁለተኛ ከዚህ በፊት የጻፉት ሁሉ ደህና አድርገው እንደገለጹት የስብሓት ነጋ በስብሰባው ላይ መገኘት የፓርቲውን ሳይሆን የግሉን የዴሞክራሲ ዝንባሌ የሚያሳይ በመሆኑና በተሳትፎውም ባሳየው መንፈሳዊ ወኔ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በአንጻሩ በቅርቡ በአጋጣሚ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን ሳይ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ጠቅላላ ሚኒስትሩን ጨምሮ በየተራ እኛ (ኢትዮጵያውያን) ከማን እናንሳለን የሚል ዓይነት ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ውይይት ነው ብለው ማቅረባቸው እንደሆነም አላውቅም፡፡ አንዱ ተናጋሪ በአየርላንድና በዴንማርክ የዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመት ግድም ረሀብ ነበረ ሲል የሰማሁ መሰለኝ.. ይህ ሰው ስንት ሚልዮን ኢትዮጵያውያንን አሳስቷል? ማንም አላረመውም.. በኢትዮጵያ ያለው ትልቁ ችግር መሰላል ላይ ወጥቶ ቁልቁል ዲስኩር የሚግተው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ለንግግር፣ ለውይይት ቢያንስ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የሚያቀረሸውን ዲስኩር መጋት ለምንም አይበጅም፡፡ ሸለብ ቢያደርገውም ያልኩበት ምክንያት በጻፈው ውስጥ ..ቤተ ክህነትን የሚጎዳ አመለካከትና አካሄድ.. እንዳለ አስመስሎ የራሱን ምኞት መናገሩ በዕለቱ የተናገርሁትን አለመስማቱን ስለሚያረጋግጥ ነው፤ ..ጳጳሶቹ አይረቡም.. ያለው እሱ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ በሌላ በኩል ስመለከተው በቤተ ክህነትና በቤተ ክርስቲያን መሀከል ያለውን ልዩነት የተገነዘበ አልመሰለኝም፡፡ አሸልቦት ነበር ያልሁት የሚከተለውን ስናገር አልሰማኝም ለማለት ነው፡፡
..ዛሬ በተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተከፋፍለው ስንትና ስንት ሺህ ሰዎች ተቀጥረው የሚያሰሩት አብዛኛው ስራ ያለምንም ክፍያ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትሰራው ነበር፡፡ ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ትምህርት በተለያየ ዘርፍ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ዛሬ ዩኒቨርስቲ እስከሚባለው ድረስ የትምህርት ገበታ ዘርግታ በነፃ ታስተምር ነበር፡፡ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ጋር የማትደፈር የደካሞች መጠጊያና የሙጥኝ የሚባልባት አድባር ነበረች፤ ነበረች ነው ማለት የምንችለው፡፡
ሶስተኛ በአቶ ደሳለኝ የተጻፈው (ከአቦይ ስብሃት ምላሽ በስተጀርባ) ግሩም በሆነ የጨዋ አጻጻፍ ዋና ዋና ሀሳቦቹን በመግለጹ በአብዛኛው የምስማማበት ነውና አልደግመውም፡፡
ስብሓት በጽሁፉ ላይ የደረደራቸው ጥያቄዎች መረጃ ለመፈለግና ለማስፈራራት ይመስላል፡፡ በአደባባይ ከተራ ህዝብ ጋር ተገናኝቶ በነፃና በእኩልነት ደረጃ መነጋገር ልማድ የሌለው ሰው ከእሱ ሀሳብ ጋር የማይለጠፉትን ሁሉ እንደስድብ ወይም እንደ ድፍረት ቢቆጥራቸው አያስደንቅም፡፡ ከላይ ሆኖ መናገርን ሲረሳና በእኩልነት መነጋገርን ሲለምድ የሌሎችን ሀሳብና አስተሳሰብ ባይቀበልም የሚያከብርበት ጊዜ ይመጣል፡፡ አንዳንድ ጓደኞቹ ለምደዋል፤ እሱም ይህ የሚያቅተው ሰው አይደለም፡፡ ለእኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ዋናውና ትልቁ ችግር መነጋገር አለመኖሩ ነው፤ እንግሊዝኛው ይበልጥ ለሚገባቸው ሰዎች..ሽሮቁቄሸበስ) ወይም ዲያሎግ የለም፤ሁሉም ልናገር አዳምጡኝ እዚህም ላይ ስብሓት በመናገርና በመነጋገር መሀከል ያለውን ልዩነት የተገነዘበ አይመስለኝም፤ ..ሰው እየጻፈ፣ እየተናገረ፣ እየተደራጀ ነው፤.. ይለናል፡፡ ተመስገን የሚለው አልተነጋገርንም ነው፡፡ ስብሓት የሚለው ትናገራላችሁ ነው፤ ተመስገን የሚለው አላዳመጣችሁንም ነው፤ እንዲህ ያለው አለመግባባት የሚመጣው ካለመነጋገር ነው፡፡
ትክክለኛ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት የማን ነው?

ለአቶ ስብሓት ነጋ አንድ ቁም-ነገር ላስታውሰው፤ ወደደም ጠላም እሱ የህዝብ ሰው ነው፡፡ ማለትም የአደባባይ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ስለሱ የሚባለው ነቀፌታ ሁሉ ሊያስከፋው አይገባም፡፡ በተለይም በዚህ ሁሉም ነገር ምስጢር በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ሃሜት ይትረፈረፋል፡፡ ለዚህ ኃላፊነታቸው ለህዝብ መሆን ያለባቸው ዜና ማሰራጫዎች ናቸው፤ ዱሮ ሰዎች ሲሾሙም ሆነ ሲሻሩ በአደባባይ እየተነገረ ነበረ፡፡ ዛሬ በምስጢርና በግል የሆነ ይመስላል፡፡ ታዲያ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሰዎች በመረጃ እጥረትና በወሬ ቢደናበሩ ምን ያስደንቃል? ስብሓት አልሰማ እንደሆነ እንጂ አንዳንዶቻችን በወሬ ፍዳችንን አይተናል፡፡ በእኩይ ክስ እሱና እኔ ጠላቶች ተደርገን እድሜ ልክም ተፈርዶብን በምህረት ወጥተናል፡፡ አሁንም አንዳንድ ሰዎች ፍዳቸውን እያዩ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ቅዱስ ተብለው ታቦት ተቀርፆላቸው እንደነበረም (በካህናት) ይገለጻል፤.. ይህንን ጭፍን የሐሰት ወሬ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነው፡፡በአንዳንድ ቤተክርስቲያኖች ስዕላቸው በመግቢያው ላይ በመደረጉ እንኳን ከባድ ተቃውሞ ነበር፡፡ ወያኔ ..ስር የሰደደ ዴሞክራሲያዊ አንድነት.. አረጋገጠ ማለት ሌላው የሚናገረውን ካለመስማት የሚመጣ ቀረርቶ ነው፡፡ አጨብጫቢዎች መስሚያ ጆሮ፣ ማመዛዘኛ አእምሮ እንዳላቸው አድርገን ስንገምት ወደዚህ መደምደሚያ እንደርሳለን፡፡ የሰሙትን በጥያቄ ለማጣራት ያልደረሱ፣ እምነታቸውን በሰሙት የሚከልሱ፣ ለስደት ሲበቁ እውነትን ይተነፍሱ..
በመጨረሻ ስብሓት የችግሮቻችን ሁሉ መነሻ የሆነውን አውራ ችግር ለማናቸውም ዓይነት ሳይንሳዊና ፍሬያማ ውይይት አስፈላጊ የሆነውን መመሪያ እንደሚከተለው ገልፆታል፡፡ …..የፖለቲካ ልዩነት ካለው አካል ጋር መወያየት ጠቀሜታ አለው፤ እኔ በዚህ ዓይነት ሂደት በጽኑ አምናለሁ፡፡.. እስከዛሬ ሳይገለጽለት በመቅረቱ ባዝንም ለወደፊቱ ያበርታህ፤ ያበርታን፡፡