Archive | Melkamsew Corner RSS feed for this section

እኛም የአረብ አብዮት ያስፈልገናል!

25 Oct

For PDF file please click here

ጋዳፊ ሲሞት በውነት ቅር አለኝ፤ እጅግ በጣም ቅር አለኝ፡፡ በርግጥ እሱ ስልጣን የተባለ ሰይጣን የተጠናዎተው ከንቱ ሰው ነው፡፡ ሰይጣን የሰፈረበት ሰው ይታዘንለታል እንጂ አይታዘንበትም፡፡ ጋዳፊን ለመተቸት አትቸኩሉ ጎበዝ፡፡ አዕምሯችን ውስጥ ስንት ጋዳፊዎች አሉ መሰላችሁ!? ወዳጅ መስለው የተቀመጡ እምቢተኛ አስተሳሰቦች፡፡ ሆኖም ጋዳፊ ከአረባዊነቱ ይልቅ አፍሪካዊነቱን ስለሚያስቀድም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ መቼም አፍሪካን መውደድ ማለት ለእኔ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ አፍሪካ የተናቀ አለም ነው፡፡ አፍሪካ በገዛ ልጆቹ ሳይቀር የተጠላ አለም ነው፡፡ ኦባማ እንኳ እኛ ወልደነው ፀጉሩን ግራጫ ያደረገው የእዬሩሳሌም ጉዳይ ነው፡፡ በውነቱ አፍሪካ በደል የተፈፀመበት አለም ነው፡፡ አፍሪካ የምንዱባን አለም ነው፡፡ አፍሪካ እናውቅልሃለን የሚሉት የበዙበት በራሱ ለራሱ ፈራጅ ያልሆነ አለም ነው፡፡ ይህ ያስቆጨኛል፡፡ ….አፍሪካዊ ነኝና አፍሪካን ከመውደድ የተሻለ ምርጫ የለኝም ደግሞ፡፡ ጥቁር ሆኜ በነጭ አለም ውስጥ ባለመወለዴ ጌታዬን ሁሌም አመሰግነዋለሁ፤ ነፃነትን የመሰለ ፀጋ በተጎናፀፈች ታላቅ አፍሪካዊት አገር በመወለዴም እጅግ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በኢትዮጵያ የነፃነት ምልክትነት ውስጥ የአፍሪካ ተስፋ ከርቀት በባይናኩላር እንደሚያዩት ተራራ እጅግ ቀርቦና ገዝፎ ይታዬኛል፡፡ ጥቁር ከቀዩም ሆነ ከነጩ ቢበልጥ እንጂ አያንስም የሚለውን እምነት ኢትዮጵያ ስላሳዬችን ልንወዳት ይገባል እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ልብ ናት፡፡ ….ልብ መሆን ግን በጉሮ ወሸባ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሆኖ ማሳየትና ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ስል ነገር ፈልጌ ነው፡፡

…እና ጋዳፊ አውቆም ይሁን ሳያውቅ አፍሪካን ይወድ ስለነበር እኔም እሱን እወደው ነበር፡፡ አሟሟቱ በጣም ደስ አይልም፡፡ ግን ጋዳፊ አብዮት የሚያስፈልገው ሰው አይደለም ብዬ አልከራከርም፤ ምክንያቱም የእያንዳንዱ አፍሪካዊ አዕምሮ አብዮት ያስፈልገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንግዲህ ጋዳፊን እወደዋለሁ፤ ምኑ ይደንቃል ሂትለርን የሚወዱ ሰዎች አሉ አይደል እንዴ? ስለሞሶሎኒ የሚዘምሩስ ስንትና ስንት ናቸው? እውነት ለመናገር የጋዳፊ አምባገነንነት የሂትለርና ሞሶሎኒን ክፉ ስራ የማስረሳት አቅም የለውም፡፡ ከሂትለርና ሞሶሎኒ አንፃር ጋዳፊ ቅዱስ ነው፡፡ …..ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤማ የቅዱሶች ቅዱስ፡፡

የረሳሁት ነገር፤ ከጋዳፊ በፊት ሮበርት ሙጋቤን እዎደዋለሁ፡፡ ምነው መውደድ አበዛህ እንዳትሉኝ፤ ከጥላቻ ያተረፍኩት ጨጓራ በሽታ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ጥላቻን በፍቅር ሚሳኤል ድምጥማጡን ላጠፋው ቆርጫለሁ፡፡ ሙጋቤን ስለወደድኩት ይሄኔ ብዙ ሰዎች እየረገሙኝ ይሆናል፡፡ አልፈርደባቸውም ከኢቴቪ ቀጥሎ የሚሰሙት ቢቢሲና ሲኤንኤን ስለሆነ ነው፡፡ ያለምክንያት የአረብ አብዮት አይነት ያስፈልገናል አላልኩም፡፡ አዕምሯችን ውስጥ ሂትለርን የሚያክል ነጭ ጋኔን ተጎልቷል፡፡ ታዲያ ሰው ወዶ የራሱን እያጣጣለ የሌላውን ያገዝፋል ወይ?

እስቲ የምታውቁትን ሃቅ ላውራላችሁ፡፡ እንግሊዝ የተሰኙ ወራሪዎች ብሪታኒያ ከተባለ አገራቸው ተነስተው ዜምባቡዌ ደረሱ፡፡ ከዚያም የጥቁር መሬት ቀምተው ለነጭ ዘመዶቻቸው ሰጡ፡፡ ከዚህ በላይ በደል የለም፡፡ ቆይቶ እንግሊዞቹ የሰው አገር ለመልቀቅ ተገደዱ፤ ስንት ደም ከፈሰሰ በኋላ፡፡ ጥቁር ነጻነቱን አገኘ ተባለ፡፡ ነፃነቱ ግን ጎዶሎ ነበር፡፡ አሁንም አብዛኛው የዜምባቡዌ መሬት በነጭ የተያዘ ነው፡፡ (ከጥቁር ዜምባቡዌያውያን ሰፊ የእርሻ መሬት ያለው መንግስቱ ሃይለማሪያም ብቻ ነው አሉ፡፡ አይገርማችሁም?) ሙጋቤ መሬቱን ለድሃ ጥቁር ዚምባቡዌያውያን ያድል ጀመር፡፡ ምክንያቱም ምርጫ የለውም፤ የነፃነት ጎዶሎ የለውምና፡፡ ደግሞኮ ሙጋቤ በኤማሌ ቲዬሪ መሰረት መሬቱን ለነጭም ለጥቁርም ዜጎች አከፋፈል እንጂ እንግሊዞች እንዳደረጉት የአንዱን ቀምቶ ላንዱ አልሰጠም፡፡ ..ብቻ በዚህ የተነሳ ሙጋቤ የደረሰበትን እናውቃለን፡፡ እኔ እዬማልኩ መመስከር እችላለሁ፤ አብዛኛው አፍሪካዊም ሆነ ኢትዮጵያዊ ሙጋቤን የሚያውቀው በራሱ መንገድ ሳይሆን በእንግሊዞች መንገድ ነው፡፡ እኔን እጅግ የሚያሳዝነኝ ግን የኛ ነገር ነው፤ የአፍሪካ ምልክቶች ነን ብለን አካኪ ዘራፍ የምንለው እኛ፤….ከቢቢሲና ሲኤን ኤን ከእንግሊዝኛ የተረጎምነውን አዕምሮችን ውስጥ ለተጎለተው ጋኔን አቀብለን እንደ ሙጋቤ አይነቶቹን ጥቁር አንበሶች ዲያብሎስ አስመስለናቸው እርፍ፡፡ ሙጋቤ ለነጭ ልብለጥ ባይ አስተሳሰብ እምቢተኛ ቅድመ አያቶቻችን ያስታውሰኛል፡፡ እኛ የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ሳንሆን ሙጋቤ የአድዋ ገድል ዋና ተዋንያን የነበሩት አንበሶች የልጅ ልጅ ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ የተቆጣ አንባቢ እንዳለ ይታዬኛል፡፡ ቁጣ ለግስላም አልሆነ፡፡ ከቁጣ እኔስ ምን አተረፍኩ፤ ጨጓራ ነው እንጂ፡፡ ከመቆጣት ለምን ብሎ መጠየቅ መሰልጠንን ያመለክታል፡፡ ፈረንጂ ጋኔን ያለው ለእኛም ጋኔን አይደለም ወይ፤ ፈረንጂ ቅዱስ ያለው ለእኛስ ቅዱስ አይደለም ወይ፤ ወጣቶቻችን እግራቸው እዚህ ልባቸው እዚያ አይደለም ወይ፤ ስንቱ ነው የራሱ ያልሆነውን የሚናፍቀው፤ ቅኝ ግዛት ይሏችኋል እሱ ነው፡፡ እና ዋሸው? ተወደደም ተጠላ ቅኝ ግዛት ላይ እንገኛለን፤ እናም የአረብ አብዮት እጅግ ያስፈልገናል፡፡ አንድ ኢትየጵያን ጠንቅቆ የሚያውቅ ቦትስዋናዊ ኢትዮጵያ በአዕምሮ እንጂ በአካል ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ሲል አላግጦብኛል፡፡ የማልክደው ሃቅ ነውና በሳቅ አሳብቤ ሃፍረቴን ከመሸፈን ውጭ ምን አማራጭ ነበረኝ፡፡ ኢትዮጵያዊ በመሆን ከማፈር የባሰ ሞት የለምና የሞትኩ ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ደረትን ነፍቶ ኢትዮጳያዊ ነኝ የሚባልላት አገር አሁን አሁን አንገትን ደፍቶ እንትና እያሉ የሚጠሯት እሆነች ነው፡፡ ይህን ለመቀልበስ አብዮት ያስፈልገናል፡፡ አብዮቱ ቀናነትን፤ አብዮቱ የአገር ፍቅርን፤ አብዮቱ የስራ ፍቅርን ያመጣልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እናም አምባገነን አስተሳሰቦቻችን መወገድ አለባቸው፡፡ የአዕምሯችን ሂትለሮችና ጋዳፊዎች ካልተወገዱ ግን ስንዝር ወደፊት መራመድ አይቻልም፡፡ ሰውን ከሰው የለዬው መሰረታዊ ነገር አስተሳሰቡ ብቻ ነው፡፡ አለቀ!

ጀረሚ ሙስዌማ የተባለ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወላጅ የሆነ ወዳጄ አለ ደግሞ፡፡ አቤት ሞቡቶ ሲሴሴኮን ሲወደው፡፡ ሉሙምባን ቢያስገድልም ኮንጎን ግን አገር አድርጓታል ባይ ነው፡፡ እኔ ጀረሚን ከማወቄ በፊት ሞቡቱ ጭራቅ ነበር የሚመስለኝ፤ አትፍረዱብኝ እንግሊዝኛን እንጂ ሊንጓላ ወይም ስዋሂሊ አልሰማ፤ የሆሊውድ ፊልም እኮመኩም እንደው እንጂ የአፍሪካን ታሪክ የት አውቄ፤ ታስታውሱ እንደሆነ አፍሪካ በገዛ ልጆቹም የተጠላ አለም ነው ብያችሁ ተማምነናል፤ ከላይ፡፡ …ስርዓተ ትምህርቱ ሳይቀር ከአፍሪካ ታሪክ ይልቅ ለአውሮፓው ታሪክ ሰፊ ሜዳ ይሰጣል፡፡ የራቀው የሚናፍቀን ግን ለምንድን ነው?

..…ለማንኛውም ጀረሚ የነገረኝን የዚያችን የቤልጄም ባለውለታ እጅግ ባለፀጋ የሆነች ኮንጎን አስደማሚ ቅንጭብ ታሪክ ልንገራችሁ፡፡

የሉሙምባ ኮንጎ የሞቡቱ ዛዬር የካቢላ ኮንጎ ከቤልጄም ነፃ የወጣችው በ1960 እ.ኤ.አ. ነው፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ የተባለ ጥቁር ሙሴ ጥቁሮችን ከነጭ ፈርኦኖች ነፃ አወጣቸው፡፡ ሉሙምባ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነ፡፡ ነጮቹን አምርሮ ይጠላ ነበር፡፡ ምክንያቱም አራዳዎቹ ፈረንጆች ከኮንጎ የወጡት በአካል ብቻ ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ ዛሬ ሳይቀር ኮንጎ የቤልጄም ቅኝ ተገዥ ናት ማለት ይቻላል፤ በአሁኑ ሰዓት የትኛውም አይነት አለማቀፋዊ ፖለቲካዊም ሆነ ኤኮኖሚያዊ የኮንጎ ጉዳይ ውሳኔ ለማግኘት በቤልጄም በኩል ማለፍ አለበት፡፡ ኬንሻሳ ላይ አንድ ህንፃ ለማቆም የቤልጄም መንግስት ይሁንታ ያስፈልጋል፡፡ አይገርማችሁም? እኔን ግን አናቴ እስኪዞር ያናድደኝ ነበር፤ በአዲሱ አመት ንዴት አቁሜያለሁ እንጂ!)

ሉሙምባ ስልጣን ከያዘ በኋላ ‹‹የነፃነት ጎዶሎ የለውምና በኮንጎ ጉዳይ አሜሪካም ሆነች ቤልጄም መግባት የለባቸውም!›› የሚል ጠንካራ አቋም ያዘ፡፡ በጊዜው የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አይዘናዎር ለሉሙምባ አቋም ለቤልጄም ያስተላለፉት መልዕክት አንድና አንድ ነበር፤ ‹‹Lumumba Must Be killed!>>

የሉሙምባን አሟሟት ሳስብ ሰው መሆኔን እጠላለሁ፤ እንኳንም ኮንጎ አልተወለድኩ እላለሁ፡፡ በሉሙምባ ደግ ዘመን ቤልጀም ይማር የነበረ አንድ አፈቀላጤ ወይም ጋዜጠኛ ነበረ፡፡ ሞቡቶ ሲሴሴኮ ይባላል፡፡ ጭንቅላቱ ውስጥ ነጭ ጋኔን የታሰረለት ሞቡቶ ከቤልጄም ወደ ኮንጎ መጣ፤ አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ ሉምምባ ወደደው፡፡ እና የጦር ሃይሉ ዋና አዛዥ አድርጎ ሾመው፡፡ ሰው ከአጥፊው ጋር ይውል የለ፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ ልክ ዛሬ ሙጋቤ ያደርገው እንደነበረው ፀረ – ነጭ አቋሙን ቀጥሏል፡፡ በሞቡቶ አዕምሮ ውስጥ የተቀመጠው ነጭ ጋኔንም ስራውን እየሰራ ነው፡፡ አንድ ቀን ሉሙምባ አገር ሰላም ብሎ ቤተመንግስቱ ተቀምጧል፡፡ የገዛ ወታደሮቹ እቢሮው ገቡ፡፡ አንጠልጥለውት ወጡ፡፡ በሲሴሴኮ ቁጥጥር ስር የዋለው የኮንጎ ጦር የክፉ ቀን መሪውን መልሶ ለጠላት ቤልጄም አሳልፎ ሰጠ፡፡ ሞቡቶ አዕምሮ ውስጥ የተጎለተው ሰይጣን ጮቤ ረገጠ፡፡ እየቀፈፈኝ ሉሙምባ እንዴት እንደሞተ ልንገራችሁ፡፡ …ህዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ ቶርች አደረጉት (ገረፉት የሚለው ስልማይገልፀው ነው)፤ ከሞተ በኋላ ቆዳው ተገፈፈ፤ እጁን፣ እግሩን እያንዳንዱ አካሉን ቆራረጡት፡፡ ይብሉት አይብሉት አላውቅም፡፡ ብራስልስ አደባባይ የሉሙምባ ሬሳ በተጎተተበት ስፍራ ሆኜ ነጮቹ የአህያ ስጋ ሲበሉ አይቻለው፤ አረቦች መጋዣነታቸውን ለመርሳት አህያን ከጥቁር ነጭን ከውሻ ጋር ያነፃፅራሉ እያሉ ያሟቸዋል ቱርኮቹ አረቦቹን፡፡ እኔም ድሮ ብስጩ በነበርኩበት ጊዜ እንደነሱው አስብ ነበር፡፡ አሁን ተበሳጨሁ ልበል፡፡ ውሻ እንደ አህያ ስጋ የሚጣፈጠው ነገር አለመኖሩን ልጅ ሆኜ አህያችን የሞተ ዕለት ውሻችን የተደሰተውን ደስታ በማዬት አረጋግጫለሁ፤……በአንድ ወቅት ሮበርት ሙጋቤ የምዕራባውያንን ስነ ምግባር ለመተቸት ‹‹ከአሳማ ጋር ለወሲብ የሚዳራ ፍጡር ከእኔ ጋር እኩል ሊያወራ የሞራል ብቃት የለውም!›› ብሎ ነበር፡፡ እመቤቴን! እኔ ይሄን አላዬሁም!!

ብቻ ሞቡቶ ሉሙምባን አስገድሎ ስልጣን ያዘ የሚለው ነው የወሬው ጭብጥ፡፡ ሞቡቱ በተፈጥሮው አምባገነን ስለነበረና በሉሙምባ ላይ የደረሰው አይደርስበት ዘንድ የኮንጎን ጦር በራሱ ቁጥጥር ስር አዋለው፡፡ የዛዬር ፕሬዚዳንት እንዲሁም የጦር ሃይሉ ጠቅላይ አዛዥ፡፡ ቁጭ መንጌ!!

የሚገርመው ሞቡቱ ስልጣን ሲጠግብና ሲሰለቸው በር ዘግቶ ያለቅስ ነበር አሉ፤ የሉሙምባ ደም በየቀኑ እየጮኸ ረፍት ነሳው፡፡ ለዚህ ያበቁትን አሜሪካና ቤልጄምን ረገመ፤ ጠላ፡፡ በዚህ ምክንያት በኮንጎ አልማዝ የተመሰረተችው፤ ቀነኒሳ ከሰሜን ጫፍ ደቡብ ጫፍ ቢሮጥባት በደቂቃ የሚጨርሳት ትንሽዬዋና የተፈጥሮ ሃብት ድሃዋ ቤልጄም እጅ ያጥራት ጀመር፤ እንደተለመደው አቤቱታዋን ለእቴጌ አሜሪካ አቀረበች፡፡ አሁንም የጊዜው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሬገን ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ Mobutto must Be Vanished!

አምባገነኑን ሞቡቶን እንደ ዴሞክራቱ ሉሙምባ በቀላሉ መያዝና መግድል ቀላል አልነበረም፡፡ ሁሌም የኢትዮጵያን ሜዲያ በቀላሉ በዝረራ የሚጥለው የቢቢሲና ሲኤንኤን ፕሮፖጋንዳ ሞቡቱንና ዛዬርን ሊበግር አልቻለም፡፡ ግን ደግሞ የሉሙምባ ደም አለ፤ ዘወትር ይጮሃል፡፡ ሎራ ካቢላ የተባለ ሺፍታ ከወደ ደቡብ ምስራቅ ኮንጎ ተነሳ፡፡ ቤልጄም የሰራችውን ቤልጅግ ታጥቆ ወደ ዛዬር ገሰገሰ፡፡ ዛዬር ውጥንቅጧ ወጣ፡፡ እንደለመደችው በጦርነት ትታመስ ገባች፡፡ ኮንጓውያን በአገራቸው መቀለድ ይወዳሉ፤ በተለይ በጦርነት ታሪካቸው እንዳላገጡ ነው፡፡ ጀረሚን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኘውና ስለኮንጎ ስጠይቀው እንዲህ ማለቱ ትዝ ይለኛል፤ Congo: the country of everything even fighting!!

ጭንቅላቱ ውስጥ የሰፈረው ነጭ ጋኔን ወደ ኬንሻሳ አምዘገዘገው፤ ካቢላን፡፡ በአፍሪካ እጅግ ሃይለኛ የተባለ የጦር ሃይል የነበረው ሞቡቱም የሚበገር አልሆነም፡፡ ነገሩ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲሆን በመሃል ማንዴላ ገቡ፡፡ ሞቡቱንና ካቢላን ጆሃንስበርግ ጠሩ፡፡ ማንዴላ በሞቡቱ ፈረዱበት፤ አገር ከሚያልቅ አንተ ልቀቅ፡፡ ሞቡቱ ማንዴላ ፊት አለቀሰ፡፡ ወደ ካቢላም ዞሮ ‹‹ከዚህ በኋላ እኔ ለበሽታዬ ማርከሻዬን አግኝቻለሁ፤ ከዚህ ወዲያም የሉሙምባ ደም በሌሊት እጮኸ እረፍት አይነሳኝም፤ የማዝነው ላንተ ነው፤ የእነሱ (ነጮቹ) አሽከር ለሆንከው፤ለአንተ …አትጠራጠር በአንተም ላይ የሚጮህ ደም ይኖራል!››

ሞቡቱ እንዳለውም የኮንጎ ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡ በኮንጓውያን እጅግ ተወዳጅ እንደሆነ የሚነገርለት ሎራ ካቢላ ለፈረንጆቹ አልታዘዝም ማለት ሲጀምር በተቀነባበረ ሴራ በገዛ ጠባቂዎች ተገደለ፡፡ የታሪኩ አካሄድ አንድ አይነትና ተመሳሳይ መሆኑ ያስገርማል፡፡ የዚህኛውን ታሪክ እጅግ አሳዛኝና የበለጠ አስደማሚ የሚያደርገው ደግሞ በሎራ ካቢላ ግድያ የገዛ ልጁ ጆሴፍ ካቢላ (የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት) አለበት መባሉ ነው፡፡ …..እና እኛ አፍሪካውያን አብዮት አያስፈለግንም ወይ?

ጀረማያህ ወዳጄ ይህን ታሪክ ከነገረኝ በኋላ ‹‹ፈረንጆቹ አሁን የረሱን መስለዋል፤ ምክንያቱም የኮንጎን አልማዝና ወርቅ በጆሴፍ ካቢላ በኩል እንደ ልብ እየዛቁ ነው፤ ለመሆኑ አፍሪካ ከእንዲህ አይነቱ አዙሪት የምትወጣው መቼ ይመስልሃል?›› አለኝ፡፡ ከአብዮቱ በኋላ ስል መልሸለታለሁ፡፡ እኔ አብዮት ያስፈልገዋል የምለው የራሳችን አስተሳሰብ እንደሆነ ጀረሚ ይግባው አይግባው አላውቅም፡፡

***

በውነቱ እያንዳንዱ አፍሪካዊ ከየትኛውም አብዮት በፊት በራሱ አስተሳሰብ ላይ አብዮት ማካሄድ ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የሰው ልጆች በሌላው አካባቢ ከሚኖሩ የሰው ልጆች እንደ ህዝብ የሚለያቸው መሰረታዊ ነገር የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው፡፡ አፍሪካን ለበደል የዳረጋት የአስተሳሰብ ኋላ ቀርነት እንጂ የኤኮኖሚ ኋላ ቀርነት አይደለም፡፡ በኤኮኖሚ ማደግ የሚቻለው ጤነኛ አስተሳሰብ ይዞ ህዝብን ለልማት ማደራጀት ሲቻል ነው፡፡ ከካልሲው እና ከጫማው የቱ ይቀድማል?

የኛ ነገር እንዲህ ነው፡፡ አንዱ የሰራውን አንዱ ያፈርሳል፡፡ አንዱ ያፀዳውን አንዱ ያቆሽሻል፡፡ ሳልረሳው ልንገራችሁማ፡፡ እኔ እስካሁን አጥር ስር ሲሸኑ የማውቀው ወንዶችን ነበር፡፡ በቀደም ወደ ቤቴ ስገባ የማውቃቸው የሰፈራችን ትልቅ እናት እዛው የፈረደበት መከረኛ አጥራችን ስር ተቀምጠው ያንፎለፉለታል፡፡ ውሃ ያድርገው ብዬ እቤቴ ገባው፡፡

የኛ ነገርኮ ለሰሚው ግራ ነው፡፡ ነጮቹ ጫካ ሆነው እንደ ዝንጆሮ አጋምና ቀጋ ይለቅሙ በነበረበት ዘመን የስልጣኔን ጣራ እንዳልነካን ዛሬ ተመልሰን የነሱ መቀለጃ!! ….እባካችሁ መናደድ ያልሰለቻችሁ ተናደዱ!

እንግሊዝና ፈረንሳይ በሊቢያ መልሶ ግንባታ ጉዳይ ፀብ ጀምረዋል ሲባል ሰምቼ አልገረመኝም፡፡ የኔቶ ጦር አውሮፕላኖች ኢላማቸውን እየሳቱ በወገን ወረዳ ህንፃዎች ላይ መዓት የሚያወርዱት ወደው አይደለም፤ ሊቢያን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ እንደገና መስራት በምዕራባውያን የአምስት አመት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የሰፈረና በ2012 መፈፀም የሚጀምር ነው፡፡ ፈረንጆቹ የተሰራውን አፍርሰው የዛጉ ማሽኖቻቸውን ወደ ስራ መመለስ አለባቸው፡፡ በራሴና በኢትዮጵያ ስም ለቃል ኪዳኑ ጦር አንድ መልዕክት ላስተላልፍ ነው፡፡ እንዲህ የሚል፡፡ ‹‹እባክህ ኔቶ የምትችል ከሆነ በአስተሳሰባችን ላይ ዝመት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ጋዳፊ ከተባለ አምባገነን የባሰ አምባገነን በአምሯችን ውስጥ ተቀምጦ ማሰቢያችን በመዝጋት የአገር ፍቅር፤ የስራ ፍቅር እንዲሁም ግብረገብ የተባሉ መሰረታዊ ባህሪያቶቻችን አሳጥቶናልና ደምስስልን!›› ከማለቴ በፊት እያንዳንዳችን በአዕምሮአችን አሰራር ላይ አብዮት ማድረግ አለብን፡፡

ለምሳሌ ዛሬ ዛሬ (ለነገሩ ድሮም ነበር) ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ነገሮችን መሆን አይቻልም፤ ነፃ (neutral) የፖለቲካ አቋም መያዝና ሴት መሆን፡፡ እግዜር ለሰው ልጅ የሰጠውን ነፃ ፈቃድ ሰው ሆዬ ይገባበታል፡፡ ለምሳሌ የአንዱን ጓደኛዬን የፖለቲካ አቋም ለመመርመር ቀሪዎቹ ጓደኞቼ ዋርካው ምስለኔ ጉባኤ ተቀምጠዋል፡፡ ‹ለዚህ ጉዳይ የምታጠፉትን ጊዜ ስራ ብትሰሩበት ከበርቴ ትሆኑ ነበርኮ› ብላቸው ጭራሽ አንተም ላይ እንዳንቀመጥ ብለውኝ እርፍ፡፡ ደግሞ ቆንጆ በመሆኗ እግዜርን የምታማርር ሴት ልጅም ገጥማኛለች፡፡ በቃ ቆንጆ በመሆኗ ነፃነቷን ተቀማች፡፡ በርሷ ጉዳይ ጓደኞቿም፤ ቤተሰቧም ማህበረሰቡም የሚመለከተው ሆኖ አረፈው፡፡ ባለፈች ባገደመች ቁጥር ለከፋ ነው፡፡(ሰውን ሲለክፍ የምናውቀው ውሻ ነበር!)፡፡ እንትናን ካላገባሽ ነው፡፡ እከሌ ይሻልሻል ነው፡፡ ትምህርት ቤት ሂጂ የሚላት የለምኮ፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የሚለው አንቀፅ 39 ምናለ ለሴቶቻችንም ቢሰራ፡፡ ለሌሎች ምንም ጥሩ ነገር ማድረግ ባንችል በገዛ ጉዳዩ ጣልቃ አለመግባት እንዴት ያቅተናል?

በውነቱ አንድ ሰው ነፃነቱን ከተቀማ ሰው መሆኑ አብቅቶለታል በቃ፡፡ ለዚህ እኮ ነው እግዜር ራሱ ነጻነት ለሰው ልጅ እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ፍጹም የሆነ እሱ እንኳ የማይነካው ነፃ ፈቃድ የሰጠን፡፡ እግዜር በማይገባበት ጉዳይ ሰው ከገባ የጤና አይደለም ማለት ነውና አብዮት ያስፈልገዋል፡፡

ኢትዮጵያችንም ሆነች አፍሪካችን ብዙ አብዮቶች ያስፈልጋቸዋል፡፡ የመጀመሪያው አብዮት ግን በራስ ላይ የሚደረግ አብዮት ነው፡፡ የኢትየጵያ ህዝብ በታሪኩ ብዙ አብዮቶችን አከናውኗል፡፡ ሁሉም ግን የተሳኩ አይደሉም፡፡ ምክንያቱ ጫማውን ከተጫማን በኋላ ነበር ካልሲውን ለማድረግ ስንታገል የነበረው፡፡ አንድ ሳይሉ ሁለት ማለት አይቻልም፡፡ የተፈጥሮን ህግ ለመለወጥ መሞከር ግድግዳን በቴስታ ብሎ እንደማድማት ይቆጠራል፡፡ ግድግዳን በቴስታ ብሎ መድማት እንጂ ማድማት የለም፡፡

ሰው በራሱ ላይ አብዮት ማዎጅ ቢከብደውም ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ስንል፤ ከመጭው ትውልድ ወቀሳ ለመዳን ስንል፤ ኖረን ማለፋችን ካልቀረ ለቀሪው ትውልድ የሚጠቅም ስራ ሰርተን ለማለፍ ስንል በራሳችን አስተሳሰብ ላይ አብዮት እናውጅ እላለሁ፡፡ ሰው በራሱ ላይ የአስተሳሰብ መፈንቅለ መንግስት ያድርግ፤ መሪዎቻችን ህዝቡ ከመነሳቱ በፊት እነሱው በራሳቸው ላይ ይነሱና ይችን አገር ባቆረቆዛት አስተሳሰባቸው ላይ መፈንቅለ መንግስት ያድርጉ፤ ህዝቡም ማህበረሰባዊ ችግሮቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንጦርጦስ ይወርውር፡፡ እንደዚያ የሚሆን ከሆነ ገነትን የመሰሉ አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ዓለማት እኔ ይታዩኛል!!

ደጉን ጊዜ ይመልስልን!
መልካምሰው አባተ

Advertisements

የኢሳያስ ኮማንዶዎች

15 Jul

አሁን ያለሁት ሽመልባ ነው፡፡ ሽመልባ በትግራይና ኤርትራ ድንበር የሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ነው፤ ከሳዋ ያመለጡ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖሩበታል፡፡ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ጸጥና ረጋ ያለው ቡኒ አካባቢ በአዲስ አበባ ጩኸት ቀልቡን አጥቶ ለሰነበተው እኔ አሪፍ ለውጥ ነው፡፡ በዚያ ላይ ሃፍቶምና ደረሰ የተሰኙ እንክትክት ያሉ ያራዳ አስመራ ልጆችን ተዋውቄያለሁ፡፡ ..በተለይ ደረሰ አስደናቂ ልጅ ነው፡፡ 20 ዓመት የሞላው አይመስለኝም፡፡ አስመሪና ከተማ አባ ሻውል ሰፈር ነው ያደገው፡፡ አባ ሻውል እነ ጸሓይቱ ባራኪ ሁሉ የዘፈኑለት የአስመራ መንደር ሲሆን፤…ባለውቀውም በአይነ ህሊናዬ ከአዲስ አበባው መርካቶ ጋር እንዲሁ ስዬዋለሁ፡፡ እንዴት ሳልከው? አባ ሻውል’ኮ ከመርካቶ ጋር በፍጹም አይመሳሰልም ከነውቤ በረሃ ጋር እንጂ የሚል ሰው ካለ፤…በቃ ይለፈኝ፤ እኔ ድሮም ስዕል አልችልም፡፡ ትሪያንግል ሳልኩ ብዬ ሲክስአንግል የምስል ቀሽም ሰው ነኝ፤…

ከደረሰ ጋር ላስተዋውቃችሁ፡፡ እንደነገርኳችሁ ደረሰ አስመራ ተወልዶ ነው ያደገው፡፡ …..ሽመልባ ለእርሱ ብቻ የተመቸች ትመስላለች፡፡ አማርኛው ደግሞ ጎንደርን፤ ትግራይንና ኤርትራን የሚዋስን ነው፤ contemporary geez በሉት፡፡

ተጫዋችና የሁሉም ዘመድ ነው – ደረሰ፡፡ የኔም ዘመድ ሆነና በቃ አሪፍ ጓደኞች ሆንን፡፡ ….እና የማያወራኝ ነገር አልነበረም፡፡ ለነገሩ እኔስ ምን ያልጠየኩት ነገር አለ?…..

‹‹ምንድንነት ይሰማሃል?›› አልኩት መጀመሪያ

‹‹ሰውነት›› ሲል መለሰልኝ..

‹‹አይ ኢትዮጵያዊነት ነው ወይስ ኤርትራዊነት ማለቴ ነበር›› ስል ጥያቄዬን አስተካከልኩ…

‹‹ሶማሊያዊነት›› አለ ደረሰ

በጣም አሳቀኝ፡፡

‹‹እሽ ከመለስ እና ከኢሳያስ ማን ይሻልሃል?››

‹‹አልበሽር!›› አለና ሳቀ በተራው፡፡ ቀጥሎም ‹‹ስሚ የመለስ ሰላይ ነሽ እንዴ?….ጥያቄሽ አላማረኝም!›› አለኝ፡፡

‹‹እኔ ደግሞ ስምሽ አላማረኝም!›› አልኩት

‹እንዴት?› አለ ደረሰ…

‹‹አስመራ ተወልደሽ አስመሮም አሊያም ዘረ-ሰንበት አይነት መባል ሲገባሽ የምን ደረሰ ነው?›› ስለው ከልቡ ስቆ ስሙን አስቀይሮት እንጅ የዝጊ ቤተሰብ መሆኑን ነገረኝ፡፡

‹‹…ደግሞ የዝጊ ቤተሰብ ማለት ምንድን ነው?…›› ብዬ መጠዬቄ እንደማይቀር ግልፅ ነበር፡፡

ደረሰም የጠየኩትን መመለሱ አልቀረም፤….እነሆ የደረሰ የዝጊ ቤተሰብ ትንታኔ፡፡…

‹በኤርትራ ቤተሰባዊ ዳይናስቲ አንድ የዝጊ ቤተሰብ የሆነ ልጅ ስሙ እንደየዕድገት ደረጃው ይለዋወጣል…በዚህም መሰረት ሊረገዝ ከታሰበበት ጊዜ ጅምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ስሙ እንደሚከተለው ይሆናል፤…

እናትና አባቱ ሲገናኙ…..ተክለ – ዝጊ ይባላል

ሲረገዝ…..ዘረ – ዝጊ

ሲወለድ…..ወልደ – ዝጊ

ሲጎረምስ…..ጊላ – ዝጊ

ከኮማንዶነት አምልጦ ሽመልባ ሲገባ….ወዲ – ዝጊ

ውጭ አገር ለመሄድ ፕሮሰስ ሲጀምር…….ተስፋ – ዝጊ

አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሲገባ…..ሃብተ – ዝጊ

ትዳር ሲመሰርት… ፍቅረ – ዝጊ

ልጆች ሲዎልድ…ፍሬ – ዝጊ

ሲሞት….ናይ – ዝጊ

ደረሰ ሳቄን በቁሜ ካስጨረሰኝ በኋላ ስለ ኢሳያስ ኮማንዶዎች ደግሞ ነገረኝ፡፡…

በኢሳያስና በታማኝ ጠባቂዎቹ (ኮማንዶዎቹ) መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የውሻ አይነት ነው፡፡….የኮማንዶዎቹ አፈጣጠርና ማንነት ደግሞ እጅግ ያስደንቃል፡፡ አባታቸውም፣ እናታቸውም፣ እግዜራቸውም ኢሳያስ አፈወርቂ ነው፡፡

ደረሰ ይሄን እዬነገረኝ ተመሳሳዩ ታሪክ ማለትም የእስራኤል ኮማንዶዎች ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ሞሳድ የሚያሳድጋቸውና ካደጉ በኋላ የመላዕክና ዲያብሎስ ባህሪ የሚጎናፀፉ ሰላዮች አሉት፡፡ እስራኤላውያን እናቶች አይናቸውን በአይናቸው ለማዬት ሆስፒታል ይገባሉ፡፡ አምጠው ከወለዱ በኋላ ሞሳድ ልጆቻቸውን ሰርቆ ህፃናቱን በሌላ ዓይነት የወላጅነት ፍቅር ያሳድጋቸዋል፡፡ ….ከዚያም የጎሽ ልጅ ለእናቷ ስትል ተወጋች ይሆናል ተረቱ ተገልብጦ፡፡ …ይህ የሞሳድ ጥንካሬ አንድ ምስጢር ነው፡፡

የኢሳያስ ኮማንዶዎች ውልደትና ዕድገት ከሞሳድ ‹ልጆች› የሚለዬው ኤርትራውያን እናቶች ልጆቻቸውን የሚወልዱት ሆስፒታል ሳይሆን ሳዋ መሆኑና ንጉስ ኢሳያስ ልጆቹን የሚያገኘው በስርቆት ሳይሆን በስምምነት በመሆኑ ነው፡፡ ….መጀመሪያ ወላድ ኤርትራውያን እናቶች ከየአካባቢው ይሰበሰባሉ፡፡ ቀጥሎም ኤርትራዊ ብሄርተኝነትን ይሰበካሉ፣…ናቅፋም ይሰጣቸዋል፡፡…ከዚያም እነ ማሙሽ ይወለዱና በኢሳያስ ቁንጥጫ ታንፀው አድገው ታማኝ ውሾች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ …ድምፃዊ አብርሃም አፈወርቂ ቀይ ባህር ሲዋኝ ቁልቁል የጎተተው ጋኔን የኢሳያስ ኮማንዶ ነው ይባላል፡፡ (ሰማይ፤ ሰማይ፤ ሰማይ፤ሰማይ፤ ሰማይ፤….ይል ነበር አብርሽ!)

የደረሰን ጨዋታ እንባው አቆመው፤ አብርሃምን እጅግ እንደሚወደው ተረዳሁለት፤ እኔም አብሬው አለቀስኩ፡፡ ያስለቀሰኝ የአብርሃም ያለዕድሜው መሄድ አይደለም፡፡ ….አብርሃምማ

‹‹….አንቺ ያስመራ ፀዓዳ፤

ጎጃምን ተሻግረሽ

ጎንደርንም ዞረሽ

በወለጋ አቋርጠሽ

ነይ አዲስ አባባ፤

ጠዋት በማለዳ፤……››

ሲል የተዘጋውን የአስመራ – አዲስ አባባ መንገድ በፀዓዳ ድምፁ ከፍቶታል፡፡ እና አብርሃም አፈወርቂ ይዘፈንለታል እንጂ አይለቀስለትም፡፡ እርሱ ከዘርያ ደረስና በዓሉ ግርማ ጎራ ነው ምድቡ፡፡ የኔና ደረሰ ለቅሶ የሚለየውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ደረሰ መክሊታቸውን ለወገን ፍቅር ለሰውት ሰማዕታት ያለቅሳል፤ እኔ ደግሞ መክሊታቸውን የዝና ጥማት ማርኪያ ‘ምንዱባን’ እዬዬ እላለሁ፤ አምርሬ አለቅሳለሁ፡፡

…..ዋ ‘ኔን ‘ኔን፤

አወይ ጅል መሆን፤

ይሄዳሉ ቢሉኝ ‘ሚመጡ መስሎኝ

ድንጋይና ኮረት

እንጨትና ኩበት

አንድ ማቴ ጭነት

ጎምት ተሸክሜ፤…ቆሜ ጠበኩኝ፤…

ዋ! ይብላኝልኝ!

መልካምሰው አባተ thesecondsky2020@gmail.com

ጥቁሩ ዊሊያም

11 Jul

እኔና ጥቁሩ ዊሊያም ከአዲስ አበባ ቤተክርስቲያናት በአንዱ እንገኛለን፡፡ እሱ እያስተማረ እኔና ሌሎች ምዕመናን ደግሞ እየተማርን፡፡ ዊሊያም ሃይለኛ ሰበካ ላይ ነው፤ እኔ ደግሞ ሃሳብ ላይ ነኝ፡፡ የዊሊያም ሃሳቦች የሚያመጧቸው ሌሎች ሃሳቦች ይዘውኝ ጭልጥ ይላሉ፤ ብዙ ቦታ፡፡

‹‹…መጀመሪያ ኖህ ውሃው መጉደሉን እንዲያጣራ አሞራን ላከው፤ አሞራው ተመልሶ መርከቧ ላይ በማረፍ አለመጉደሉን ለኖህ ነገረው፤…..ሶስተኛ ጊዜም ኖህ እርግቢቱን ላካት፤ እርግቢቱም በዚያው ቀረች፤ ኖህም ውሃው መጉደሉን አውቆ ከመርከቢቱ ወጣ፡፡ እንደርግቢቱ ያርጋችሁ ምዕመናን፤ እንደርግቢቱ ሁኑ፤…›› ብሎ መረቀን ዊሊያም፡፡ እኔ ምርቃቱ አልተዋጠልኝም፤ በምሳሌው መሰረት እኛ ምዕመናን መሆን የነበረብንማ እንደ አሞራው ነው፤ እርግቢቱማ መልዕክቷን ሳታደርስ በዚያው የውሃ ሽታ ሆና አይደል የቀረችው፡፡ ‹‹ነጭ ሆኖ መገኘት ምንኛ መልካም ነገር ነው፤ እርግቧ መልዕክት ይዛ የተሰወረች ብትሆንም ነጭ ስለሆነች ነው መሰል እነሆ ምስጋና ይደርሳታል፤….›› ስል አሰብኩ፡፡ (በራሴ አተረጓጎም ተደነኩ!)

ምዕመናን እንደሚያውቁት ዊሊያም መልኩ ጥቁር ቢሆንም ደሙ በመቶኛ ቢሰላ ዘጠና በመቶውን ነጭ የደም ሴሎች ይይዛሉ ተብሎ ይገመታል፤ ጥቁር ቆዳውን ነጫጭ ልብሶቹ፤ ጥቁር ሃሳቡን ነጫጭ ሃሳቦቹ ሸፍነውበ(ለ)ታል፡፡ በአጠቃላይ ዊሊያም (ወላጆቹ ያወጡለት ስም ዋለልኝ ነበር) ጥቁር ማንነቱ በነጭ ማንነቱ 2 ለ 1 እየተመራ መሆኑ ገባኝ፤ ብዙ ጊዜ ነጭ ስለራሱ ብዙ ስለሚያወራ ደስ ስለማይለኝ ዊሊያምንም አልሰማህም አልኩት፡፡ እናም ሰበካውን ትቼ ሌላ ስፍራ ሄድኩ፤ በሃሳቤ፡፡….

እንደሚታወቀው አለም ሊጠፋ ሲል እግዜር ነገረውና ኖህ ከቤተሰቡ ጋር በመርከቡ ብቻውን ቀረ፤ ካም፤ ሴምና ያፌት ከተሰኙ ልጆቹ ጋር፡፡ ሴም የአብርሃም መስመር ነው፤ እስከ ዳዊት ይዘልቃል፤ ፈጣሪ አዳምን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው ባለው መሰረት ከድንግል ማሪያም ደርሶ እየሱስ ክርስቶስን የመሰለ የሰው ሁሉ ቁንጮ ይወልዳል ወይም ይወለዳል፡፡ ካም ኖህ በረገመው ልጁ ከነዓን በኩል ሄዶ እስከ ጥቁሩ ዊሊያም ይዘልቃል፡፡ ….የነጭ አፈ ታሪክ እንደሚለው ከሆነ ‹‹ኖህ ከነዓንን ስለረገመው የልጅ ልጆቹ አረቦችና ጥቁሮች እነሆ የነጮች የዘላለም ቅኝ ተገዢ ይሆኑ ዘንድ ተገደዱ፤…››፡፡ ወይ ነጮች! ዝም ብለን መገዛት እንደሚኖርብን መለኮታዊ ትዕዛዝ መኖሩን እየነገሩን እኮ ነው፤ አይገርሙም? በጣም የሚያበሳጨው ደግሞ ይህን ጉዳይ ልክ ነው ብለው የሚከራከሩ አረቦችም ጥቁሮችም ብዙ መሆናቸው ነው፡፡ ከእነኚህ ውስጥ ጥቁሩ ዊሊያም አንዱ ነው፡፡

በደንብ አልሰማውም እንጂ ጥቁሩ ዊሊያም መስቀሉን በእጁ ይዞ እየወዘወዘ በስሜት ማስተማሩን ቀጥሏል፤ እኔም የራሴ ሃሳብ ይዞኝ እንደሄደ አልመለሰኝም፡፡

አዳኙ (ጠበቅ አድርጎ ያነበበ ተጠያቂው ራሱ ነው) ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሰው በሁለት ይከፈላል፤ ህዝብና አህዛብ፡፡ ህዝብ ማለት እስራኤል ማለት ነው፡፡ እስራ = ህዝብ፤ ኤል = እግዚአብሄር፤ በአንድ ላይ፤ የእግዚአብሄር ህዝብ! ሌላውስ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ግን ለመልሱ መቼኮል አያስፈልግም፤ ምክንያቱም አሪፍ አይቸኩልም፡፡ ‹‹…በዚህ አለም ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ፤ ህይወት ራሷ ችኩል ናት፣…›› ብሏል ደግሞ በዓሉ ግርማ፡፡

አባቶቻችን እንደሚነግሩን በብሉይ ዘመንም ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሄር የተወደዱ ናቸው፤ በህገ ልቦና ያመልኩት ስለነበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያውያን እንደ ሰዱቃውያን ወይም ፍልስጤማውያን አህዝብ አልነበሩም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን አገባ፡፡ ወንደሙ አሮንና እህቱ ማሪያም (ማሪያሞችን ለማያውቁ ይህቺኛዋ ማሪያም የእዬሱስ እናት ድንግል ማሪያም አለመሆኗን ይገነዘቡ ዘንድ መንገር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው) ሙሴ አህዛብ አገባ ብለው ለእግዜር ክስ አቀረቡ፡፡ እግዜርም ተበሳጭቶ ‹‹ህዝብንና አህዛብን የምለዬው እኔ ወይስ እናንተ!›› ብሎ ቀጣቸው፡፡ እነ ማሪያም ለምፃም ሆኑ፤ ደግ ስለሆነ በኋላ ማራቸው እንጂ፤….. ይህ ማለት ምን ማለት ነው፤ አህዛብነት አብርሃማዊነትን በማጣቀስ ወይም በደም ውርስ የሚገኝ ሳይሆን የሙሴ ታቦትን ከፍልስጤማውያኑ ጣዖት ዲጎን በማስቀደም የሚጎናጸፉት የማመን ፀጋ ነው፡፡ በብሉይ ዘመን እስራኤላውያን ታቦተ ፂዮንን ይዘው ጠላቶቻቸውን ብዙ ጊዜ አሸነፉ፡፡ ከአድዋ ድል መልስ እቴጌ ጣይቱ ምን አሉ ‹‹የእስራኤል አምላክ በኛ ላይ አድሮ እንጂ እኛማ ምን አቅም ኖሮን፤…››፡፡ ታዲያ ጽላተ ሙሴ ከአድዋ በጥቂት ኪሎሜትር ርቀት አክሱም ፅዮን ማሪያም ቤተክርሰቲያን ውስጥ ተቀምጦ የምኒሊክ ጦር ሊሸነፍ ኖሯል ወይ? የአድዋን ጦርነት ኢትዮጵያውያን በልምጭም የሚያሸንፉት ይመስለኛል፡፡ የጣሊያን ጦር ደካማ ነበር ማለት ሳይሆን በብሉይ ዘመን የነዳዊት የሃይል ምስጢር የነበረው እግዜሩ በምድር (ፅላተ ሙሴ) አጠገባቸው ስለነበር ጠላትን ለመርታት አይቸገሩም ለማለት ነው፡፡

ልብ አድርጉ ጥቁሩ ዊሊያም እያስተማረ ነው፤ እኔ ግን አልሰማውም፤ የመጀመሪያው ምሳሌ ስላልጣመኝ ቀጣዩ ሀተታውም እንቶ ፈንቶ መስሎኛል፤ first impression matters ይላሉ እንግሊዞች፤ ‹‹ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል!›› ወይም ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ!›› ማለታቸው ነው፡፡

በ አ ጠ ቃ ላ ይ

እግዜር እስራኤላውያንን ከሌላው ለይቶ ለምን ህዝቤ አላቸው? ብሎ ለሚጠይቅ ሁሉ ፈጣሪ የሚወዱትን ይወዳል ይመስለኛል መልሱ፡፡ ‹‹ቀናተኛ አምላክ ነኝ!›› ብሎ የለ እንዴ?!

አርቆ ከወሰደኝ ሃሳብ ተመለስኩ፡፡ ጥቁሩ ዊሊያም አሁንም እያስተማረ ነው፡፡ ሃሳቤ በጥቁሩ ዊሊያም ሃሳቦች እንዳይወረስ ቶሎ ብዬ ሄድኩ እንደገና፤ ራቅ ብዬ፤ ወደ አውሮፓ መካከለኛ ዘመን፡፡ በነገራችን ላይ የጥቁሩ ዊሊያም እንዲያ መወራጨት እሱን ዘመን ያስታውሰኛል፡፡

ከ5ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን የሚዘልቅ ነው፤ የአውሮፓ መካከለኛ ዘመን (Medieval period, Europe)፤ ከሱ በፊት የብረት ዘመን ይባል ነበር፡፡ የብረት ዘመን ሲጠናቀቅ ለመካከለኛው ዘመን እጁን እንደሰጠው ሁሉ በመጨረሻው የመካከለኛ ዘመን ፊውዳሊዝም ለካፒታሊዝም እጁን እንደሰጠ ያኔ የነበርን ሰዎች እናስታውሳለን፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ዘጠኝ የመስቀል ጦርነቶች (አስራ አንድ የሚሉ አሉ) የተካሄዱባት ቅድስት ከተማ እየሩሳሌም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡ በዘመነ ብረት ወይም ከዛ በፊት በምዕራብ ኢምፓዬር ስር የሚጠቃለሉት ፍራንክ፤ ስላቭ፤ ቡልጋር፤ ሃንስ፤ ጎስ፤ …ወዘተ የሚል ወለነገድ የነበራቸው በአደንና በእርሻ የሚተዳደሩ አውሮፓውያን በሮማን ካቶሊክ ኢምፓየር ግዛት ስር ተደራጁ፤ ተደራጅተው አሻግረው ወደ ምስራቅ ሲመለከቱ የሮማ ካቶሊክ ኢምፓዬር የተገነጠለችበትና ክርስትናን በቀጥታ ከሃዋርያት የተቀበለችው የቤዛንታይን ኦርቶዶክስ ኢምፓዬርን ቆስጠንጢኒዮስ ከተማ ላይ ተመለከቱ፡፡ አውሮፓውያን ገበሬዎችና ጫከኞች ናፍቆትና ትዝታ የሚመስል ስሜት ሰውነታቸውን ውርር አደረጋቸው፡፡ ደግሞ ከቆስጠንጢኒዮስ ከተማ ወዲህ በመሃመዳውያን ሃይሎች የተወረረችው የእየሱስ ከተማ እየሩሳሌም አለች፡፡ ‹የክርስቶስ ከተማ በመሃመዳውያን? አይደረግም!› ብለው ዛቱ፡፡ ክርስቲያናዊ ቁጭት በረታ፡፡ አውሮፓውያኑ ከወንድሞቻቸው ቤዛንታይናውያን ጋር አበሩ፡፡ ከግሪክ የተወረሰ፤ በሮማን ኤምፓየር አስተዳደር የሚኮተኮት ስልጣኔ እየመጣላቸው የሚገኙት የተባበሩት የአውሮፓ ጎሳዎች የመስቀል ጦርነት አወጁ፤ ወደ እየሩሳሌም ከተማ፡፡ …እና በመካከለኛው ዘመን ታሪክ ዘጠኝ የሚደርሱ ወይም የሚያልፉ የመስቀል ጦርነቶች ተካሄዱ፤ በክርስቲያንና እስላም መካከል፤ በእየሩሳሌም ጉዳይ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ድሉ የማን ነበር? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ በውነቱ ድሉ የነጋዴዎች ነበር፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ‹‹አትቼኩል፤ በዚህ ዓለም ላይ ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ፤ ህይወት ራሷ ችኩል ናት›› ይላል ሰማዕቱ በዓሉ፡፡ በጣም ከቸኮልክ ግን ምክንያ እነሆ፡-

የመስቀል ጦርነት የፈጠረው ብቸኛው መልካም ነገር የከተሞችና የንግድ መስፋፋት ነው፡፡ የመስቀል ጦርነቶች ዋና ምክንያት እየሩሳሌምማ ዛሬም ድረስ የማን እንደሆነች አይታወቅም፡፡ የጣሊያን ከተሞቹ ቬነስ፤ ሲሲሊና ሌሎች የካቶሊክ ወታደሮች በተጓዙባቸው መስመሮች ያሉ ከተማዎች የመስቀል ጦርነት ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ወታደር የነበረው ጭሰኛና ጫከኛ ሁላ የከተማ ሰውና ነጋዴ ሆኖ አረፈው፡፡ አዳዲስ መዶቦች ተከሰቱ፤ ቡርዦ፤ ጭሰኛ፤ ሰራተኛ ወዘተ….(አንድ ወዳጄን ‹የሰራተኛው መደብ አሸናፊነት ታይቶኝ ከሰራተኛው ጋር ነበርኩ እኔ ያኔ!.› ስለው ‹…..ህም! .ወይ ጉድ!…..ከአቅሙ በላይ ድንች የተሸከመ ስልቻም እንደዚህ ተቀዶ አያውቅ!› ብሎ አሽሟጠጠኝ፡፡ ደስ አይልም!?)

ም………

መካከለኛው ዘመን ስፍራውን ለህዳሴ ዘመን (renaissance) ለቀቀ፡፡ እነ ኮፐርኒከስ፤ አይዛክ ኒውተን፤ ሼክስፔር፤ ጋሊሊዮ ትንሽ ቆይቶ በ18ኛው ክ/ዘመን ደግሞ የኤኮኖሚክስ ቲዬሪ ሞተሮቹ አዳም ስሚዝና ባልንጀሮቹ ተከሰቱ፡፡ የኔ አንበሳ ካርል ማርክስም ቀጥሎ መጣ፤ ማርከስ ብላድሚር ሌኒንን ተክቶ አለፈ፡፡ ሌኒን ማንን ተካ? ብላድሚር ፑቲን እንደማትሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ፑቲን በካራቴ እንጂ በርዕዮተ አለም እንኳን አይታማም! በርዕዮተ ዓለም ጉዳይስ ከፑቲን ይልቅ መንጌ ይሻላል፤ የመንጌ ችግር ምንድን ነው፤….የምስራቅ ጀርመንን ርዕዮተ ዓለም ካራማራ ተራራ ላይ ሆኖ በጦር ሜዳ መነፅር ሊያይ መሞከሩ ነው፤ በዚህ ምክንያት ምስሉን ሳይሆን ብዥታውን ብቻ ሊያይ ቻለ፡፡ ብዥታው እውነተኛ ምስል መሰለው እና በቃ ተሸወደ!…..መንጌን ሃጢያት ሰርቼ አላውቅም የሚል ይውገረው!

…እና ለማንኛውም በአውሮፓ ኢንዱስትሪ ተስፋፋ፤ አውሮፓ በሚያስደንቅ ፍጥነት በስልጣኔ ወደ ፊት ተሸቀነጠረች፡፡ አደን የደላቸው አፍሪካውያን ግን ይህን ሁሉ አያዩም፤ ይህን ሁሉ አይሰሙም፤ እዛው እነበሩበት ናቸው፡፡ ኢትጵያውያን ደግሞ ያኔ የሚገዳደሉበት ቀስት እየሰሩ ነበር፡፡…..

ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ ርዕዮተ አለም መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በመሆኑም አውሮፓውያን አትርፎ ሻጭ፤ ቆጣቢ፤ ቆጣሪ፤ ቋጣሪ፤ ሆኑ፡፡ ይሄ የመሸጥ የመለወጥ ክፍ አባዜያቸው ሰውንም ከመሸጥ አደረሳቸው፡፡ እና በዚህ የተነሳ ካፒታሊዝም የአፍሪካ ጠላት ነው እላለሁ፡፡ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይ፤ ጣሊያንና ሌሎች በካፒታሊዝም የማከማቸት ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ ተጠምቀው ስስት ሰውን ሸጦ እስከመለወጥ ሲያደርሳቸው የማርክዚስም እምነት አቀንቃኝ የነበሩት ሶሻሊስት ራሺያና ምስራቅ ጀርመን ግን ቅኝ ግዛትን እጅግ ይጠየፉት ነበር፡፡ እግዜር ይስጥልን፡፡ (ማርክስን ዝም ብዬ አልነበረም ለካ የወደድኩት፡፡ ያኔ አውሮፓ አፍሪካን ሲቀራመት ራሺያና ጀርመን ተጨምረው ቢሆን ኖሮ ፍዳችን በስንት በመቶ ያድግ ነበር በገብሬል!?…..)

ነገሩ ሲጠቀለል የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ከሶሻሊዝም ፍልስፍና ጋራ የሚጣላ ከካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም ጋር ደግሞ የሚስማማ ነው፡፡…..ለክፉ ክፉ ይስጠውና አፍሪካ በሰው ሽያጭ ተጥለቀለቀች፡፡ የአውሮፓ የካፒታሊዝም አብዮት ለአውሮፓ ስልጣኔን ሲያመጣ ለአፍሪካውያን ደግሞ ጥሬ ዕቃ መሆንን ይዞ ከተፍ አለ፡፡ የግብፅና የአክሱም ስልጣኔን ያልተጠቀምንበት፤ የግሪክ ስልጣኔ ያልደረሰን፤ የአፍሪካ መሬት ውብ አየር ሰነፍ ያደረገን እኛ አፍሪካውያን ለቅኝ ግዛት ተመቻችተን ጠበቅን፡፡ ….እናም ተሸጥን፤ ተለወጥን፡፡ ቅኝ ግዛት አዳም ከተፈጠረ በኋላ የሰው ልጆች ከሰሩት ሃጢያት ሁሉ እጅግ የከፋው ነው ይባላል፡፡

እስራኤላውያን ለህያው እግዚአብሔር አዶናይ፤ ፍልስጤማውያን ለጣኦት ዲጎን፤ ግሪካውያን ለነኤሪስ፤ ግብፃውያን ደግሞ ለነሃቶር ይሰግዱ እንደነበሩት ሁሉ አውሮፓውያን ከስልጣኔ አልፈው አለምን እስከመቀራመት፤ የአፍሪካን ሰባ በመቶ ሃብት እስከመዝረፍ ላደረሷቸው ለሚከተሉት ሶስት ጣኦቶቻቸው ይሰግዳሉ፡፡

የፈረንሳይ አብዮት
የእንግሊዝ አብዮት
የፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽን

በ1517 ዓ.ም. ጀርመን ዊተንበርግ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን የካቶሊክ ቄስ የነበሩት ማርቲን ሉተር ወደ 95 የወረዱ የተሃድሶ መመሪያዎችን (ዶግማዎቻቸውን) ቤተክርስቲያኑ በር ላይ ለጠፉ፡፡ ጊዜው ደግሞ መጥፎ ነበረ፡፡ ፊውዳሎችና ጭሰኛ ገበሬዎች (መካከለኛው መደብ) የተፋጠጡበት ነው፡፡ የአውሮፓን አንድ ሶስተኛ መሬት ይዛ የነበረችው ፊውዳሏ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በፊውዳል ጎራ፤ ኩትልክና የመረረው የቤተክርስቲያን ተሃድሶ አቀንቃኝ (Reformist) ማርቲን ሉተር ደግሞ በአማፂው መደብ ጎራ ተሰለፉ፡፡ ሉተር ለአማፂያኑ መፈክር የሚሆን የመፅሃፍ ቅደስ ጥቅስ አቀበላቸው፡፡ ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልም፡፡ ‹‹ክርስቶስ ነፃነት ነው! እየሱስ እኩልነት ነው፤…›› ወዘተ ያኔ ለመፈክር ያገለገሉ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅሶች ነው፡፡ ነገሩ እየከረረ ሲመጣ ደግሞ ሉተር ለመካከለኛው መደብ ወዳጆቹ እንዲህ አለ፡-

>

‹‹ክፉዎቹን ለመቅጣት መልካሞቹን ለመጠበቅ እግዚአብሄር ሃይልን ይቀባል፡፡ ቅጣቱ ለክፉዎቹ ይሆን ዘንድ ጳጳስ፤ ቄስ፤ መነኩሴ፤ እመምኔት፤ አበምኔት፤ ዲያቆን ወዘተ፤….የሚል ምርጫ ሳይኖር፤ ሁሉም ይደመሰሳሉ፤….››

ከጠሉ አይቀር እንደዚህ ነው፡፡

ይህን የሰሙ የሮማ ካቶሊኮች ከክርስቶስ መወለድ በኋላ ክርስቲያን በክርስቲያን ላይ ጦርነት ሲያውጅ ይህ የመጀመሪያው ነው አሉ፡፡ ምንም ቢሉ የትም አልደረሱም፤ ድምጥማጣቸው ጠፋ ማለት ይቻላል፡፡ ሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከሁለት ተከፈለች፡፡ ፊውዳሊዝም ስፍራውን ለስልጡን ልጁ ካፒታሊዝም ለቀቀ፡፡ ካፒታሊዝምና ተሃድሶ እጅና ጓንት ሆኑ፡፡ ካፒታሊዝም ባህር ተሻግሮ አፍሪካና አሜሪካ ሲደርስ ኢምፔሪያሊዝም ሊሆን ቻለ፡፡ በነገራችን ላይ በፊውዳሊዝምና በካፒታሊዝም መካከል የጊዜ እንጂ የግብር ልዩነት የለም፤ በፊውዳሊዝም ጥቂት ሰዎች በርካታ ሰፊ መሬቶችን ይይዛሉ፤ በካፒታሊዝም ደግሞ ጥቂት ሰዎች ብዙ ገንዘብ ይይዛሉ፡፡ በሳዳም ሁሴን እና በኡዴይ ሳዳም መካከል ምን ልዩነት አለ? ሁለቱም ሰው ይገድሉ ነበር፡፡

የፈረንሳይ አብዮት የንጉስ ሄንሪ ሚስት እቴጌ ሜሪ አንቶኒ የፈረንሳይ ረሃብተኞችን ‹‹ዳቦ ካጡ ለምን ኬክ አይበሉም?!›› ያለችበት ነው፡፡ የእንግሊዝ አብዮት ደግሞ የፊውዳሉ ሚስተር አዳምስ ጭሰኛ የነበረው ጀምስ የኢንዱስትሪያሊስቱ ሚስተር ጆንስ አሽከር የሆነበት ነው፡፡ የፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽን ደግሞ ማርቲን ሉተር ‹‹ሁሉም ሰው እኩል የማጠራቀም መብት በነፃነት አምላክ ተችሮታል፤ ማጠራቀም በእግዚአብሄር ዘንድ ሞገስን ያስገኛል!›› ሲል ፀረ – ፊውዳሊስቶችን ያበረታታበት ነው፡፡ ብቻ ሶስቱ ነገሮች አውሮፓን ወደ ፍፁም የካፒታሊዝም ዓለም የለወጡ ናቸው፡፡ የካቶሊክ ቄስ የነበሩት ማርቲን ሉተር ከካቶሊክ አለም ሲወጡ ሰማያዊውና እና ምድራዊው አለም የአንድ ሳንቲም ሁለታ ገፅታዎች ናቸው ብለው ነው፡፡ ሰማይ ቤት ለመድረስ እዚህ ምድር ላይ የሚተከል መሰላል ያስፈልጋል ብለዋል፤ መሰላሉ ደግሞ ያለ ገንዘብ አይተከልም፡፡ እናም ያኔ የሉተር ተከታዮች ከአባታችን ሆይ ቀጥሎ ገንዘባችን ሆይ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡

እዬሱስ ክርስቶስ አንዱን የይሁዳ ሃብታም ሰው ‹‹ንብረትህን በሙሉ ትተህ እኔን ተከተል አለው፤…›› ሰውየውም ‹‹ሃብቴን በሙሉማ እንዴት አድርጌ ትቼ እከተልሃለው፤ ከተከተልኩህም ከንብረቴ ጋር ነው እንጂ፤…›› ብሎ መለሰ፡፡ እየሱስም አለ ‹‹ሃብታም ከሚፀድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ትሾልካለች፤…››፡፡ ካቶሊካውያንም አሉ ‹‹በቃ! ሃብታም አይፀድቅም!››፡፡ ሉተራውያንም አሉ ‹‹እንዲያውም ሃብታም መሆን በእግዚአብሄር ዘንድ ግርማ ሞገስ ማግኘት ማለት ነው፤ ክርስቶስ በሃዲስ ኪዳን ገመል በመርፌ ቀዳዳ አሾልኳልና!››፡፡ የአውሮፓ ፖለቲከኞችም አሉ ‹‹ወግድ ካቶሊክ፤ እኛ በሉተር አቅጣጫ ነን!›› እነሆ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ሃይማኖት አልባው ገንዘብ የአውሮፓ ሃይማኖት ሊሆን በቃ፡፡ ….እናም ዛሬ አውሮፓ ውስጥ ሶስት ዋና ዋና ሃይማኖቶች አሉ፡፡ እነሱም ገንዘብ፤ ፐሮቴስታንትና ካቶሊክ ይባላሉ፡፡ ….ነገር ግን የኋልኞቹ በምዕመናን እጦት ቤተመቅደሶቻቸውን ስለዘጉ በግብረሰዶማውያን ማህበራት ተተክተዋል፡፡ ለነገሩ አውሮፓውያን የቅኝ ግዛት መሳሪያ ያደረጉትን ሃይማኖት አፍሪካ ውስጥ ተክለዋል ቢባል እውነት ነው፡፡ ….ግን ደግሞ ሌላ ጥያቄ አለ፤…ቅኝ ግዛት የተባለ ወረርሽኝ ነክቶን አያውቅም የሚሉት 13% ኢትጵያውያን በምን ምክንያት የፈረንጅ ሃይማኖት ተከታይ ሊሆኑ ቻሉ?

ይሄን ጥያቄ መልሼ ከወዳጆቼ ጋር ከምቀያየም ጥያቄውን ብተወው ይሻለኛል፡፡ ይልቅስ በተስኪያን ወዳስገባኝ ጉዳይ ልመለስ፡፡

…ጥቁሩ ዊሊያም ሰበካውን ቀጥሏል፡፡ ጥቁር ካባ ለብሷል፤ ደረቱ ላይ ነጭ መስቀል ደምቋል፡፡ ከፊቱ መፅሃፍ ቅዱስ አለ፡፡ አቤት አንደበት፡፡ ምዕመናን በእንቅልፍና በንቃት መካከል ሆነው ይሰሙታል ወይም አይሰሙትም፡፡

‹‹….እየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው፤….›› አለና ምዕመናኑን በትኩረት አጤናቸው፡፡ ድንገት ከእንቅልፋቸው እንደነቁ አፈጠጡበት ‹‹…አማላጅ ነው የሚሉ ተሳስተዋል›› ብሎ አረፍተ ነገሩን በመደምደም አረጋጋቸው፡፡ …..ምዕመናኑ እንደገና ተኙ፡፡ ዊሊያም ሰበካውን ቀጠለ፡፡

‹‹…መቼም ይገርማል! እህቶች ባል ፍለጋ ትንከራተታላችሁ፤ እንኳን እናንተ ማሪያምም ባል አልነበራት፤ …ድንግል ሁኑ ክርስቶስን መውለድ፤….›› አለና ዝም አለ፡፡ አሁን የሚለው ጠፋው፡፡ የተፋውን መላስ ሆነበት፤ ደነገጠ፡፡

‹‹መውለድ ምን?? ጨርሰው!›› አለ ከጀርባ የተቀመጠ አንድ ወጣት፡፡ ከፊት ለፊት ተቀምጠው የነበሩ ሁለት ወጣቾች ደግሞ ድንገት ተነሱ፡፡ ጥቁሩ ዊሊያም ነገሩ አላማረውም፡፡ ገልመጥ ገልመጥ ብሎ ተመለከተ፡፡ እየተከበበ መሆኑ ገባው፡፡ ጋዜጠኞች እንዲህ አይነቱን ጉዳይ ‹‹ጮማ ወሬ!›› ይሉታል፤ እኛ ፀሃፊዎች (ፀሃፊ ነህ ካላችሁኝ) ደግሞ ‹‹ሾርባ ወሬ›› እንለዋለን፡፡ የአሁኑ ነገር ግን ሾርባ ሳይሆን ሹርባ ነው የሆነብኝ፤ በጣም የተጠላለፈ፤ የተተበተበ፤ ውል አልባ ነገር፡፡

‹‹የጀመርካትን አረፍተ ነገር ጨርሳት እንጂ፤…›› አለው ከኋላ የተቀመጠው ወጣት፤ ከተቀመጠበት እየተነሳ፡፡ ምዕመናን ተደናገጡ፡፡ ጥቁሩ ዊሊያም ፊትና ኋላውን ተገላምጦ አዬ፡፡

ከኋላ የቆመው ወጣት ‹‹እናንተም ክርስቶስን መውለድ ብሎ ምን?…ጨርሳታ!›› ብሎ አፈጠጠበት፡፡ ዊሊያም አረፍተ ነገሩን ጨረሰው፡፡ ‹‹………..መውለድ ትችላላችሁ!›› ሲል ጨርሶት እግሬ አውጭኝ አለ፡፡ የሰበካ ፕሮግራሙ ወደ አባሮሽ ተለወጠ፡፡ ወጣቶቹ ዊሊያምን ያባርሩት ያዙ፡፡ እኔም የመጨረሻውን ለማወቅ ተከትልኋቸው፡፡

ጥቁሩ ዊሊያም ሲሮጥ ወጣቶቹ ሲከተሉ፤ እኔም ስከታተል፤ ቦሌ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ደረስን፡፡ ዊሊያም በተስኪያኑ ገብቶ ቆሌ ይላል ብዬ ስጠብቅ አልፎት ሄደ፡፡ ወጣቶቹ ተከተሉት፡፡ እኔም!…. የቀለበት መንገዱ ከመድረሱ በፊት ግን ሌላ ቸርች አገኛና እዚያ ገብቶ ቆሌ አለ፡፡ ወጣቶቹም በር ላይ ቆሙ፡፡ የሰው ቤተክርስቲያን መድፈር አልወደዱም፡፡ ማሪምን! በጣም አከበርኳቸው፡፡ ‹‹ክርስትና የራስን በር መጠበቅ እንጂ እንደ አውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የሰውን ቤተ መቅደስ መውረር አይደለም፤ የአረማዊው ናቡከደነፆር ጦር እንኳ የሰሎሞን ቤተመቅደስን ከማርከስ ተቆጥቧል!›› ስል በቀደም አባ መልከጼዴቅ ሲናገሩ የሰማሁትን ለራሴ ነገርኩት፡፡ ወጣቶቹ ከቸርቹ በር ተመለሱ፡፡ የአባሮሹ መጨረሻ መሆኑ ሲገባኝ እንኳን የፅሁፌን መደምደሚያ አገኘሁት እንጂ፤….ብዬ እኔም ወደ ቤቴ መጓዝ ጀመርኩ፡፡ አቤቱ ሰላም አግባኝ እቤቴ!

thesecondsky2020@gmail.com

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ታላቅ ስህተት

7 Jul

(ይህን ፅሁፍ ከወራት በፊት አንድ ጋዜጣ እንዲያወጣው ሰጥቼው ነበር፤ ነገር ግን ጋዜጣው የፕሮፌሰር መስፍን ወዳጅ ስለሆነ ሳያወጣው ቀረ)

ይህን ፅሁፍ ስፅፍ በሬውን ለማከል ስትንጠራራ ፈንድታ የሞተችውን እንቁራሪት እያሰብኩ ነው፡፡ እየተንጠራራሁ ስለሆነ አቅምን ባለማወቅ ከሚከሰተው እብጠትና ዕብሪት ብሎም ፍንዳታ እተርፍ ዘንድ የዕብጠት ሚዛኔን መጠበቅ ሳይኖርብኝም አይቀርም፡፡ ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው የተባለው ሃሰት አይደለምና በተለይ ደግሞ አሁን አሁን እንደምንታዘበው ባገራችን አምስት ገፅ አንብቦ አምስት ሺ ገፅ የመፃፍ አርበኝነት በርትቷልና ከእንዲህ አይነቱ ይዞ ጥርግ ከሚል ‘ሱናሚ’ ለማምለጥ እሱ ይጠብቀኝ ዘንድ ሱባኤ ሰንብቻለሁ፤ ዝምም ብያለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ዝም የማያሰኙ ነገሮች ስለሚከሰቱ ስሜትን ጨቁኖ መተኛት ትርፉ ራስ ምታትና ማቅለሽለሽ ስለሚሆን ዝም አይባልም፡፡ በመሆኑም ዛሬ መድፈር የማይገባኝን ሰው ልደፍር ነው፡፡

ዝሆንና አይጥ አንድ ላይ ሆነው ድልድይ ይሻገራሉ አሉ፡፡ ከተሻገሩ በኋላ አይጢት ሆዬ የተሻገሩትን ድልድይ በኩራት ዞራ እየተመለከተች ‹‹ፓ! አነቃነቅነውኮ!›› አለች አሉ፡፡ እሷን ብሎ ድልድይ አነቃናቂ! እኔም በዚህች አነስተኛ ፅሁፍ የዝሆን ሃሳብ ላነቃነቅ መሆኑ ነው፡፡

አስቀድሜ በራሴ ላይ ሂስ ካደርኩ ዘንድ ተንደርድሬ ወደ ነጥቡ ብገባ አንድም ፌስቡከኞቼን አላሰለችም፡፡

ከዶክተር ከበደ ሚካኤል ተረትና ምሳሌ እንዲሁም ከዶስቶቭስኪ ካራማዞቭ ወንድማማቾች መፅሃፍት በኋላ ራቴን ያሰረሳኝ መፅሃፍ ቢኖር የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ስልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ የተሰኘ መፅሃፍ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ሁለት መፅሃፍትን አንድ ላይ ባወጡበት ስራቸው በቀዳሚው አንጀቴን አራሱት በተከታዩ ደግሞ አንጀቴን አቆሰሉት፡፡ እንደኔ እምነት ከሆነ መቶ ፐርሰንት በሃቀኛ መረጃ የተደገፈ እውነት እናገራለሁ ብሎ ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት ቢደረስ ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን ተሳካ አያስብለውም፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ነገራን መፃፍ ዕቅድን መፃፍ ስላልሆነ ነው፡፡ (ለምሳሌ ሰሞኑን የኢህአዴግ ሰዎች የአምስት አመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጋነነ (ambitious) ነው ብለው ከወዲሁ ተስፋ ቆርጠው ተስፋ በማስቆረጥ ከአምስት አመታት በኋላ አልስኬቱ ድንገት ሲነገር ተደናግጠን እንዳናምፅ ካሁኑ ያለሳልሱን ይዘዋል፡፡ አቅደን እንጂ አሳክተን አናውቅምና የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም እንዲሉ እኛ የሀበሻ ልጆች አይሞቀን አይበርደን፤ አያስፈራን፤ አያሳፍረን፡፡)

ታሪክን የመሰለ ነገር የሚፅፍ ሰው ከመቶ ዘጠና ዘጠኝ ቢሳከለት ፈተናውን ወድቋል ብያለሁ፤ እውነቴን ነው፡፡ አንድ በርሜል ወይን ጠጅ ውስጥ አንድ ማንኪያ መርዝ ቢጨምሩበት በርሜሉ የወይን ጠጅ በርሜል መባሉ ይቀርና መርዝ የበከለው በርሜል ተብሎ ሊጠራ ግድ ይለዋል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ስልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ መፅሃፍ እንደዚህ ነው የሆነብኝ፤ ትንሽ በምትመስል ስህተት የተነሳ፡፡ ነገሬ ግልፅ እንዲሆን የፕሮፌሰሩን አስገራሚ የታሪክ መላምታዊ ስሌት እንደደሚከተለው ላስቀምጠው፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ~ መንግስቱ ሃይለማሪያም ^መለስ ዜናዊ

በፕሮፌሰር አስተሳሰብ መንግስቱ ሃይለማሪያምና ወያኔ (አቶ መለስ ማለታቸው ነው መሰለኝ) የቴዎድሮስ ደም የማፍሰስ ክፉ አመል ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ሁለቱም መግደልን የተማሩት ከመቶ አምሳ አመታት በፊት ይኖር ከነበረው ካሳ ሃይሉ የተባለ የቋራ ሽፍታ ነው፡፡ ‹‹…..የጎንደር ነገስታት ሎሌ የነበረው ቀጥሎም የሸፈተው ካሳ ሃይሉ አጤ ነኝ ብሎ ለሰሎሞንና ሳባ የዘር ተዋረድ ብቻ የሚገባውን ዘውድ ሲደፋ የጭካኔ በትሩን አንገዛም ባሉት ወገኖቹ ላይ ያሳርፍ ቀጠለ፡፡ የዱላ ቅብብሉም ሲወርድ ሲዋረድ መንግስቱ ሃይለማሪያምና መለስ ዜናዊ ከተባሉ የባህሪ ልጆቹ ጋር ደርሶ እነሱም ዱላውን ተቀብለው ይህንን መከረኛ ህዝብ ይጠልዙት ያዙ፤…›› ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ ፕሮፌሰር እንዲህ ማለታቸው መብታቸው ሆኖ ሳለ አስቂኝና አናዳጅ የሆነብኝ ነገር ስለ ዱላ ቅብብሉ ያሰቀመጧቸው ማስረጃ ተብዬዎች ማስጠላት ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በግምት ወደ ኋላ ተጉዘው ቴዎድሮስን የሳሉበት መንገድ ሳጤነው ከዘመን ተሻጋሪ ነገረኛ ግጥሞች ባለፈ ከማናውቀው የቴዎድሮስ የጭካኔ አፈታሪክ ይልቅ ፕሮፌሰር የጨበጡት ብዕርና የተደፈነ አጭር አረፍተ ነገር ምን ያህል እንደሚዎጋና ጨካኝ እንደሆን ነው የተሰማኝ፡፡ ከላይ የተናዝዝኩት የቅድመ ይቅርታ ኑዛዜ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶልኝ አንድ ነገር ልበል፤ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ እንደ አንዳንድ መንደረኛ ታሪክ ፀሃፊዎቻችን ያልጠራ ግንዛቤ አላቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቴዎድሮስን የጭካኔ ፈጣሪ አድርጎ በአነስተኛ አረፍተ ነገር መደምደም ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ ይበልጥ አብሻቂ የሆነው ነገር ፕሮፌሰር መስፍንን ያህል ሰው ቴዎድሮስ እጅግ አረመኔ ነበረ ብሎ ለመደምደምና ከነመንግስቱ ጋር ለማነፃፀር የተጠቀሟቸው ማስረጃዎች የእረኞችንና የአዝማሪዎችን ግጥሞች መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ቴዎድሮስ ባገር ውስጥ የዛጉዌ ስርወ መንግስት ሙቀት በሚሰማው ዋግሹም ጎበዜ፤ የኦሮሞ ልዕልቶቹ ጥሩወርቅና ውቢት ከልጃቸው ኢዮአስ ሞት በኋላ ያጡትን የጎንደር ቤተመንግስት እንደገና ለመቆጣጠር እና ዮሃንስ አራተኛ ደግሞ ባላቸው የሰሎሞን ዳይናስቲ የዘር ሃረግ ምክንያት ያን ‘’የኮሶ ሻጭ ልጅ’’ እንጦርጦስ አውርደው ዘውዱን በራሳቸው አናት ላይ ደፍቶ የሰሎሞን ስርዎ መንግስትን ለመመለስ ቴዎድሮስን በሶስት አቅጣጫ ወጥረውታል፡፡ ታዲያ ከዮሃንስ፤ ከዋግሹም ጎበዜና ከጥሩወርቅ መንደር በኩል ‹‹እሳት መጥቶ ከቋራ፤ ድፍን አበሻን በላ፤…›› ተብሎ ቢገጠም ምኑ ይደንቃል? የኛ ሰው እንኳን በቴዎድሮስ ላይ በእግዜሩ ላይስ ገጥሞበት የለ?

ሁለቱን ታማለህ አንዱን ትገድላለህ፤

የሴት ልጅ ነህና ፍርድ የት ታውቃለህ፤…

ተብሎ የተገጠመበት ማነው? እየሱስ ክርስቶስ አይደለም እንዴ? መዓት የሚያመጣውን ይህንን አይነት ግጥምስ የገጠመው ማነው? ፈረንጅ ነው? አይደለም፤ በሁለቱም ልጆቻቸው መታመምና መሞት እርር ድብን ያሉ የኛው የድሮ እናታችን ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ለቴዎድሮስ ለምን እንደሚያቅራራለት ይገርማቸዋል፤ ይሄ ማለት አልገባቸውም ማለት ነው፡፡ ታዲያ ለምን እኔ አልነግራቸውም?

እንግሊዛዊው የስነፈለክ (astronomy) ሊቅ ፕሮፌሰር ስቴፈን ሃውኪንግ የዘመኑ አልበርት አንስታይን ሲባል ይወደሳል፡፡ ሃውኪንግ የአንስታይን ደቀመዝሙር ነው፡፡ አንስታይን በቲዬሪ ደረጃ አስቀምጧቸው ያለፋቸውን ንድፈ ሀሳቦች አሻሽለውና አጎልብተው ወደ ተግባር የሚያመጧቸው ሃውኪንግና ሌሎች ጓደኞቹ ናቸው፡፡ ወይም እንዲህ እንልበል፡፡ የአንስታይን መላምቶች በተለይም አንፃራዊነት ቲዬሪ ዛሬ ለምንገለገልባቸው ኮምፒዩተር፤ ሳተላይት፤ ቴሌቪዝን፤ ጂ.ፒ.ኤስ.፤ ሞባይል…ወዘተ መሰረት ነው፡፡ አንስታይን ግን አንድም ቀን ኮምፒዩተር ሳይገለገል ነበር ያለፈው፤ ቴሌግራም ፈጣሪው አሌክሳንደር ግርሃም ቤል አንድም ቀን በቴሌግራም ተነጋግሮ እንደማያውቀው ማለት ነው፡፡ አጼ ምኒልክን ስቴፈን ሃውኪንግ አፄ ቴዎድሮስን አንስታይን አድርጌ ለማስቀመጥ ፈልጌ አይደለም፡፡ ስለ ቅብብሎሹ ማውራት ስለፈለኩ ነው፡፡ አባቶቻችን ስልጣን ለመያዝ እርስ በርስ ቢተጋተጉም ያንዱን መልካም ስራና ባህሪ የመውረስ ፍጥነታቸው እንዲህ አይነት ባህሪ ፍፁም ያልፈጠረባቸው የቅርቦቹና የአሁኖቹ መሪዎቻችን ሊቀኑበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ የአገር ውስጥና የውጭ የተባሉ ፖሊሲዎች ነበሩት፡፡ እንደሚገባኝ የቴዎድሮስ የውጭ ፖሊሲ ከአፄ ዘራ ያዕቆብ የሰሜን ፖሊሲ የተወሰደ ነው፤ ቴዎድሮስ ከልብነ ድንግልና ንግስት ኢሌኒ የተጀመረውን የውጭ ግንኙነት ሊቀጥለው ፈልጎ ወዳጅነቱን ከእንግሊዝ ጋር ማድረግ ጀመረ፤ ከንግስት ቪክቶሪያ ጋር የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነቶችን ለመፈፀም እጅግ ይጥር ነበር፤ ምክንያቱም ምፅዋን የያዙት ኦቶማን ቱርኮች መስፋፋት ለቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኑ አለም በጠቅላላ እጅግ አስጊ ነበርና ነው፡፡ (ቱርኮቹ ለአህመድ ግራኝ የጦር መሳሪያ ሰጥተው የኢትዮጰያን ስልጣኔ ማሽመድመዳቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡) ቴዎድሮስ አጼ ልብነ ድንግል ላይ የደረሰው እሱም ላይ እንዲደርስ አልፈለገም፤ እናም ከእንግሊዞች ጋር በኋላ በፀብ የሚቋጭ ወዳጅነትን ቀጠለ፤ እንግሊዞች ደግሞ የስትራቴጂ ጉዳይ ሆኖባቸው ከሃያሏ ቱርክ ጋር መጣላት አልፈለጉም፡፡ ንግስት ቪክቶሪያ ቴዎድሮስን መካድ ግድ ሆነባቸው፤ ቴዎድሮስም መገንፈል ነበረበት፡፡

የቴዎድሮስ የአገር ውስጥ ፖሊሲ የተባለውን ስንመለከት ደግሞ የምኒልክ አያት ሳህለ ስላሴ ንጉሰ ሸዋ የጀመሩትን ነበር ቴዎድሮስ ያጠናከረው፤ ዛሬም ድረስ ቡዳ፤ ቀጥቃጭ ስንል የምናጣጥላቸውን የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ቴዎድርስ ከመኳንንቱ ከፍ ያለ ክብር ሰጣቸው፤ ከቅልውጥ መንጋ ደብተራ ይልቅ የጥበበኞች እጅና አዕምሮ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የዕድገትና ስልጣኔ መሰረት እንደሆን ገብቶታል፤ የመኳንንቱንና የቤተ ክርስቲያናትን መሬት እየቀማም ለድሃ ገበሬዎች ይሰጥ ነበር፡፡ (እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን መንግስቱ የቴዎድሮስን ጭካኔ ወረሰ ካሉ አይቀር የመንግስቱ መሬት ላራሹ አዋጅም ከቴዎድሮስ የተወረሰ ነው ማለት ነበረባቸው፤ አላሉትም እንጂ…፤ ችግሩ ያለው ቴዎድሮስን አንጋዶ ለማዬት ከመወሰኑ ላይ ነው፡፡)

ከላይ እንዳልኩትና ከተነሱት ምሳሌዎች አንፃር አባቶቻችን ዘውድ ለመጫን ቢራኮቱም እንኳ አንዱ የአንዱን መልካም ሃሳብ ይዞ የመጓዝ አስደናቂ ባህሪ እንደነበራቸው ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ስለምትባል አገር ሳስብ ፊቴ ላይ ድንቅ የሚሉብኝ እምዬ ምኒልክ የቴዎድሮስን ራዕይ አልተጋሩም ማለት አይቻልም፡፡ ያፈጠጠው ሃቅም ይሄው ነበር፡፡ ምኒልክ የቴዎድሮስን በጎ ራዕይ ተቀብለው መሃሪነታቸውንና ደግነታቸውን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ ያወረሱትን የፈሪሃ እግዜአብሄር ፀጋቸውን ተጠቅመው ትነስም ትብዛ ይቺን ታክል አገር በክብር አስረክበውናል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ፉርሽ የሚሆን የፕሮፌሰር መስፍን ሃሳብ አለ፤ የዱላ ቅብብሉ ነገር፡፡ ቴዎድሮስ አረመኔ ነበር ብለን እናስብ፡፡ ከነ ቀዳማዊ እያሱና አፄ ዘራ ያዕቆብ የተቀበለውን ራዕዩን ብቻ ሳይሆን ራሱም ይፍጠረው ከሌላም ይውረሰው አረመኔነቱንም ለምኒልክ አቀብሏል ልንል ነው፡፡ ምኒልክን በትክክል የሚያውቅ ሰው ካለ ግን ዱላ ቅብብሉ እሳቸው ላይ መቆሙን ይገነዘባል፡፡ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ባልነበረበት ዘመን ምኒልክ የለዬላቸው ዴሞክራት ነበሩ፤ በጥበብ እንጂ በሃይል የማያምኑ ታላቅ ሰው፡፡ ታዲያ የካሳ በትር በዬት በኩል አልፎ መንግስቱና መለስ ላይ እንደደረሰ ራሳቸው ፕሮፌሰር በድምደሜ ሳይሆን በእውነትና አመክንዮ ተመስርተው ቢያስረዱን የተሻለ ይሆናል፡፡ በ’ውነቱ ቅር የሚያሰኝ ነገር ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውርደትሽን አያሳዬኝ!…›› ብሎ ራሱን ያጠፋን ሰው፤ ኢትዮጵያን ለአስራ ሰባት አመት በጨለማ ካኖረ እና ከኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝብ አስተሳሰብ በተቃራኒ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል አለመሆኗን በግድ ሊያረጋግጥ ከሚሯሯጥ ሰው ጋር ማነፃፀር እጅግ በጣም ነውር ነው፡፡ ቴዎድሮስ የስልጣን ጥመኛ ቢሆን ኖሮኮ ያኔ ራሱን ከመግደል ይልቅ ከመቅደላ ጥቂት ዞር ብሎ እንደገና ራሱን ካደራጀ በኋላ ተመልሶ አፄነቱን ለመቆናጠጥ መፋለም ይችል ነበር፡፡ የቴዎድሮስ አላማ አገር ማበልጸግ እንጂ አገር መግዛት አይደለም፡፡

በስልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ ገፅ 2 ላይ እንዲህ የሚል ፅሁፍ አለ፡፡ ‹‹…ቴዎድሮስ ምን ሰሩ? አንደኛ የዘመነ መሳፍንትን ኢትዮጵያን የመከፋፈል አዝማሚያ አገዱ፤ ሁለተኛ፤ ባይሳካም የኢንዱስትሪ ስራ እንዲጀመር ሞከሩ፤ አንድ ጊዜ ተተኩሶ የበቃው መድፍ አሰሩ፤ ያንን መድፍ መቅደላ ላይ አወጡት፤ ይህ ቀላል ነገር እንዳይመስላችሁ፤ ዛሬ ያንን መድፍ ከመቅደላ ማውረድ አይቻልም፤ ሶስተኛ ራሳቸውን ገደሉ፤ ከዚህ ሌላ ስለቴዎድሮስ የሚተረክ የለም፤….››

እኔ በፕሮፌሰር መስፍን ውስጥ ለአፍታ ልቀመጥና ከላይ ያስቀመጡትን አይነት ጥሬ ሃሳብ ልናገር ‹‹…ክርስቶስ ምን ሰራ? መጀመሪያ ተወለደ፤ በድንግል ማሪያም ዕቅፍ ውስጥ አዬነው፤ ከዚያ በኋላ የለም፡፡ የ5፤ 10፤ 15፤ 20፤ እና 25 ዓመቱ ጎረምሳው እዬሱስ የት ነበር? ድንገት 30ኛ ዓመቱ ላይ ከተፍ አለና ጥቂት ሃዋርያቱን ሰብስቦ ላስተምር አለ፤ ብዙ ሳይቆይ የገዛ ዘመዶቹ ያዙና አሰሩት፤ ወንጀለኛ ብለው ገረፉት፤ ሰቀሉት፤ ከዚህ ሌላ ስለ ክርስቶስ የሚተረክ ነገር የለም፤…..››

ፕሮፌሰር ክርስቶስን ፈርተው አልፃፉትም እንጂ ስለ ክርስቶስ እንደዚህ ያለ ሃሳብ በውስጣቸው አለ፡፡ ፕሮፌሰር የሳቱት ታላቅ ቁምነገር አለ፤ ይኸውም ታላላቅ ሰዎች አለምን የለወጧት በቃል ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ክርስቶስ በሞቱ ለህዝበ አዳም ትንሳኤን አመጣ፡፡ እኔ ቴዎድሮስን ከክርስቶስ የማነፃፅር ጅላጅል ባልሆንም የቴዎድሮስ ራስን መግደል ኢትዮጵያውያን ለእምነታቸውና ሀገራቸው ክብር እስከምን ድረስ መሄድ እንዳለባቸው የሚያስተምር ወደር የሌለው ተምሳሌትነት ነው፤ የአድዋ ጀግኖቻችን ገድል የነቴዎድሮስ እምቢ ለሃገሬ ባይነት መንፈስ የለበትም አይባልም፡፡

ምን ሰራ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ በአጠቃላይ ሃሳቡ እጅግ አከራካሪ ይሆናል፡፡ ከአጼዎቻችን መካከል የሰሩት ስራ እርክት አድርጓቸው ያለፉት ምኒልክ ብቻ ናቸው ብዬ አምናለሁ፤ እርሳቸውም ቢሆኑ ትክክለኛ ተቀባይ ስላልነበራቸው መንፈሳቸው የሚያርፍ አይመስለኝም፡፡ አብዛኛዎቹን የምናከብራቸው ለማንነታችን መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ጠብቀው አስተላልፈውልን ስላለፉ ነው፡፡

ስለ ዘመነ መሳፍንት!

የዘመነ መሳፍንት ወቅት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ያልነበረችበት ሁሉም የራሱን አምባ ይዞ አምባገነን የሆነበት ዘመን ነው፡፡ የአምባ መኳንንትና ሹማምንት ቆይታ ለጥቂት አመታት ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ላስታ፤ በጌምድር፤ ሸዋ፤ ትግሬ፤ ጎጃም…ወዘተ የሚባሉ አገራት እንጂ ሁሉንም አቅፋ የያዘች አንዲት ኢትዮጵያ ባልኖረች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመሃመድ ግራኝ ዘመን የእሳት ዘመን ነው፤ የዘመነ መሳፍንት ዘመን ደግሞ የበረዶ ዘመን ነው፡፡ በረዶውን ፕሮፌሰር አንድ ሽፍታ ሲሉ ያጣጣሉት ቋረኛው ካሳ አቀለጠው፡፡ በረዶው መቅለጡ ብቻ አልነበረም ቁምነገሩ፤ ገደል አፋፍ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ ወደ ደልዳላው ተመለሰች፡፡ ይህ እንግዲህ እንደሚዛናችን ትልቅ ወይም ትንሽ አሊያም ምንም ነጥብ ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ለእኔ ግን ለኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንት ክፍፍል ውጭ ከባሰ አደጋ ውስጥ የገባችበት ዘመን አለ ብዬ አላስብም፤ የግራኝ ጥፋትና የጣሊያን ወረራ ከዚህ ጋር ሊተካከሉ ይችላሉ፡፡ ቴዎድሮስ ከዚህ አኳያ ትልቅ ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ስለሃገር ዕድገት ከማውራታችን በፊት መጀመሪያ አገር የምትባለው ነገር መኖር መቻል አለባት፡፡ እኔ ፕሮፌሰርን ብሆን ኖሮ በአዕምሮዬ ፈጥኖ መምጣት የነበረበት ጉዳይ የቴዎድሮስ ሎሌነትና ሽፍታነት አይደለም፤ ይልቅስ አንድ ተራ የነበረ ሰው ያንን ከሰለሞንና ሳባ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እጅግ ግዙፍ የተራራ ጎምት ድንጋይ እንዴት ደፍሮ ሊጋተረው ቻለ? የሚለው በሆነ ነበር፡፡ ከሆነ ነገር ተነስቶ ታላቅ መሆን ቀላል ነው፤ እንደ ቴዎድሮስ ከምንም ተነስቶ አጼ መሆን ግን እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ለነገሩ ፕሮፌሰር ሰው ናቸውና ሚዛናቸውም ሰውኛ ነው፡፡ አንድ ተራ ሽፍታ በርግጥም ዘሎ የማይታሰበውን ዘውድ ሲጭን ያኔ እነ እቴጌ ምንትዋብ እንደሆኑት ሁሉ ፕሮፌሰርም ደንግጠው ይሆናል፡፡ ወደ ታላቁ መፅሃፍ ስንመጣ ፈጣሪ በሰው መንገድ አይሄድምና መሾም ያለበትን ይሾማል፤ እግዚብሄር ባይሆን ኖሮ አፈቀላጤው አሮን እያለ ዱዳውን ሙሴን ማን ለመሲህነት ይመርጠው ነበር?

የቴዎድሮስ ጭካኔ ማለት ምን ማለት ነው ?

የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች ባልተፈጠሩበት ዘመን የአለም አገዛዝ ሁኔታ አንድ አይነት ነበር፤ በጉልበት፡፡ መጀመሪያ አንድ ሰው አገር የመምራት ራዕይ ይኖረዋል፤ እንደ አድያም ሰገድ እያሱ ዕድለኛ የሆነ ከዙፋን ቤተሰብ ይወለዳል፤ እንድ ቴዎድሮስ ያለው ዕድለቢስ ደግሞ እነ ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት ኮሶ ከምትሸጥ ድሃ እናት ይወለድና ሌሎች ቢሰሙ የሚያስቃቸውን አገር የመምራትን ራዕይ ይሰንቃል፡፡

ቀጥሎ ከራዕይ በኋላ ተከታይ ማፍራት ነው፤ ከዚያ ሰራዊት ማደራጀት፤ አገር ለመምራት የሚቀናቀኑትን ባላጋራዎች ሁሉ መምታት፤ ድል ከቀናም እያስገበሩ መግዛት ነው፡፡ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት ነበረ እንዴ ያኔ? ቢኖርስ በጊዜው ከነበረው ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ አኳያ ያዋጣ ነበር ወይ?

በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ነገስታትና መሪዎች ታሪክ ሳይገድል ስልጣን ላይ የወጣ፤ ስልጣን ይዞም ያልገደለ የለም፡፡ ከዚህም በባሰ ለዙፋን ሲሉ አባቶቻቸውን የገደሉም አሉ፤ ቀዳማዊ እያሱ የተገደለው ዙፋን በጠማው ልጁ ተክለሃይማኖት ነበር፡፡ እጅ እዬቆረጡ ገደል በመጨመር መግደል የጥንት የኢትዮጵያ ነገስታት የአገዳደል ዘይቤ ነው፤ ሃይለስላሴ አቀለልኩት ብለው ወደ አደባባይ ሰቀላ ለውጠውታል መሰለኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የኢትዮጵያን ታሪክ በሚገባ ለመረመረ ጭካኔ የተሞላበትን አገዳደል ሁሉም ይተገብሩት ነበር፤ በአስከፊ ሁኔታ፡፡ ከዚህ አንፃር ቴዎድሮስ ከሌሎች ነገስታት ተለይቶ የጭካኔ ተምሳሌት የሆነበት ምስጢር ምንም ሊገለጥልኝ አልቻልም፡፡ ሁለት ነገሮችን ግን እጠራጠራለሁ፤ አንደኛ ቴዎድሮስ እጅግ የማይገፉት ጦረኛ እየሆነ ሲመጣ ተቀናቃኞቹ ግጥም ማስገጠምን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፤ ወይ ደግሞ ቴዎድሮስ ሲገድል ተደብቆ አልበረም፤…

ሌላው ፕሮፌስር መስፍን ሊያውቁት የሚገባ ነገር የጥንት ነገስታት አባቶቻችን በእምነታቸውና በአላማቸው ወይም በሃገራቸው ጉዳይ ምንም ድርድር የማያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ልበ ብርሃኑ አጼ ዘራ ያዕቆብ ልጆቹ ባዕድ አምላኪ በመሆናቸው ምክንያት በህዝብ ፊት አደባባይ አውጥቶ እስኪሞቱ ገርፏቸዋል፡፡ ‹‹….የእግዚአብሄር ክብር ከሚጎድፍ ልጆቼ ይጥፉ!›› ማለቱ ነው ዘራ ያዕቆብ፡፡ ሁላችንም እግዚአብሄርን ከልጆቻችን እንደምናስበልጥ ጥርጥር የለውም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ይሄንንም ጭካኔ ካሉት ከፍልስጤማውያን ምርኮ የተመለሰውን ፅላተ ሙሴ በደስታ ብዛት በእጁ የነካው ኦዛ በአምላክ ተቀስፎ ስለሞተ ይህንም የእግዜር ጭካኔ እንበለው?

አፄ ዘራ ያዕቆብ ልጆቹን ሲያጠፋ ያስተላለፈው መልዕክት አንድ ነው፤ ሃገርና እግዚአብሄር ከራስ ልጆች ይበልጣሉ፡፡ ቴዎድሮስ ከጨከነ የጨከነባቸው ጠቃሚ ራዕዩን ሊያከሽፉበት ፊቱ ላይ በተደነቀሩት ሰዎች ላይ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ለድሃ የቆመ ሰው ነበር፤ ድሃን አልገደለም፤ ሊገድሉት የመጡትን ግን ምን ያድርጋቸው? እጅ ወደ ላይ ብሎ ይጠብቃቸው? ወይስ ስለ መቻቻል ፖለቲካ ሰብኮ ያሳምናቸው? ፕሮፌስር መስፍን ቢመልሱት ይሻላል፡፡

መቼም የፕሮፌሰርን አስተሳሰብ አምኖ ቴዎድሮስን ከፕሬዚደንት መንግስቱ ሃይለማሪያምና ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የማነፃፀሩን ነገር እውነት ነው ብሎ የሚቀበል ችኩል ተከታይ አይጠፋም፡፡ ለእንዲህ አይነቶቹ እኔ አንድ መልዕክት አለኝ፡፡ መቼም ከፕሮፌሰር መስፍን ይልቅ እኔን አምነው የለም! ቴዎድሮስማ እርስዎ እንዳሉት አይደለም ብለው ይሞግታሉ ብዬ አላምንም፡፡ በትምህርት፤ በእድሜና በልምድ ትልቅ የተባለ ሰው ያጣመመውን በትምህርት፤ በእድሜና በልምድ ትንሽ የሆነ ሰው አመታትን ቢጥር አያቃናውም፡፡ ቢያንስ ግን ቴዎድሮስ ከመንግስቱና መለስ እጅግ የተራራቀ አስተሳሰብ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ ንግስት ቪክቶሪያ የጦር መሳሪያ እንዲልኩለት የጠዬቀው በኦቶማን ቱርኮች የተያዘችውን ምፅዋን በሃይል ለማስለቀቅ ነበር፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ደግሞ ሰሞኑን ኤርትራ ላይ ጦርነት እንደሚደረግ ፍንጭ የሰጡት ምፅዋን ለማስመለስ አይደለም፤ መድረኮችና አረናዎች እንዳሉት ምፅዋም ሆነ አሰብ የኢትዮጵያ አለመሆናቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለአለምአቀፍ ማህበረሰብ አረጋግጦ የኢትዮጵያን ህዝብ እንቁልልጭ በማለት የእናት አገራቸውን ለማስደሰት ነው፡፡ እስቲ በሞቴ ቴዎድሮስና መለስን ምን አመሳሰላቸው? ያኛው ሃሳቡ እስከ እዬሩሳሌም ይሄኛው ሃሳቡ እስከ አዲስ አለም፡፡ ቴዎድሮስ በዘመኑ ስለ ኢንዱስትሪ አብዮት የሚያስብ ልዩና አስገራሚ ሰው ነው፡፡ ዛሬ በእኛ ዘመን በእኛ አገር የኢንዱስትሪ አብዮት ማለት እንደ ቴዎድሮስ ሃሳብ አይደለም፤ ስልጣን ማቆያ ጥበብ ነው፤ አራት ነጥብ!

መንግስቱ ሃይለማሪያም ደግሞ አጥናፉ አባተን ገድሎ ስልጣን ላይ ከመውጣት፤ አማን አብዶን ገድሎ የኤርትራን ፖለቲካ ከማበላሸት ያላለፈ ተራ ወመኔ ነው፡፡ መንግስቱ ሃይለማሪያም ከተወለደበት ዘመን ብዙ ዓመታት ወደ ኋላ ቆጥሮ መወለድ የነበረበት የስልጣኔ ፋራ ነው፤ ቴዎድሮስ ደግሞ ሰራተኛ እጆችን እያጣጣሉ የኢትዮጵያን ስልጣኔ ማምጣት አይቻልም ብሎ የነገስታት የህልውና ሞተር የሆኑትን የሃይማኖት ሰዎች የተገዳደረ በመሆኑ ወደፊት መወለድ የነበረበት ሰው ነው፡፡ እሱና መንግስቱ ዘመን መቀያዬር ነበረባቸው፡፡ ለነገሩ ቴዎድሮስ ዛሬ ቢወለድስ ምን ያመጣል? እንደነ ዋግሹም ጎበዜ ሁሉ እን ፕሮፌሰር መስፍን ግጥም ያስገጥሙበት ነበር፡፡

በመጨረሻም የምለው ነገር፤ ፕሮፌሰር መስፍን ዙሪያችን ገደልና ጨለማ በሆነብን በዚህ ዘመን በጠባብ ሽንቁር ብልጭ የሚሉልን የግዙፉ ጨለማ ብርሃናችን ነዎትና ይፃፉ ነው፤ ልክ በክህደት ቁልቁለት ላይ እንዳስቀመጡት ከሃዲውንና እውነተኛውን እንለይ ዘንድ ይልፉልን፡፡ ሲፅፉ ካልተጠነቀቁ ግን መቼስ ምን ይደረግ ከእውነት አይበልጡምና ዝም ማለት የማንችል ዝም አንልም፡፡

አሜሪካውያን ታሪክ አልባ በመሆናቸው ምክንያት ታሪክን ሆሊውድ ላቦራቶሪ ውስጥ ፈጥረው በሌለ ታሪክ ኤቨረስት ተራራን የሚያክል አሜሪካዊነትን በትውልዳቸው ልብ ውስጥ ሊፈጥሩ ይጥራሉ፡፡ የኛ ታሪክ ፀሃፊወች ደግሞ {ነጋድራስ ገብረህይዎት ባይከዳኝ ይመስሉኛል እንዳሉት} አንዱን ለማጉላት አንዱን እንጦርጦስ ከማውረድም ባለፈ ጥሩ የሰሩትንም ገልብጠው በተቃራኒው እንዲሳሉ ያስቀምጧቸውና ፈጣሪም ይቅር የማይለውን ሃጢያት ይሰራሉ፡፡ ብልጦቹ የውሸት ታሪክ ፈጥረው ጠንካራ ትውልድ ለመፍጠር ይሞክራሉ፤ እኛ ጠንካራ ታሪክ ሰሪዎቻችን አንኳሰን ትውልዱን በድቡሽት ላይ የቆመ መሰረት አልባ ልናደርገው እንታትራለን፤ እኔ በበኩሌ ፕሮፈሰር ከእንዲህ አይነቱ ጎራ ውስጥ ከማያቸው እንደ መይሳው ይሄንን አላይም ብዬ ሽጉጥ ብጠጣ እምርጣለሁ፡፡ ጨርሻለሁ!
Melkamsew Abate

%d bloggers like this: