Tag Archives: Professor Getachew Haile

የፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፤ አባ ባህሪይ

10 Mar

የፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፤

አባ ባህሪይ

Click here below to download the document:

Yeabba_Bahriy_Dirsetoch.main

Advertisements

ቀዳሚ ቃል:- መስፍን ወልደማርያም /ፕሮፌሰር/

2 Sep

The PDF format for “Introduction to Dekekee Estifano’s Pain” by Professor Mesfin Woldemariam

በፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተተረጎመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ሰቆቃ ያስደነግጣል፤ ያሳዝናል፤ ያስቆጣል፤ የማናውቀውን ራሳችንን እርቃናችንን ያሳየናል፡፡ ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላም ፍንክች አለማለታችን ውስጣችንን እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ ይህንን መጽሐፍ ሳነብብ ምዕራባውያን (በእንግሊዝኛ) “ቶርቸር” (የግዕዝ ፀሐፊዎች “ኩነኔ”) የሚሉትን ሰውን የማሰቃየትን ዘዴ እኛ የፈጠርነው መሰለኝ፡፡ ቻይናውያን በዚህ ክፉ ዘዴ እንደሚታሙ አውቃለሁ፤ እኛም ሆንን ቻይናውያን የታሪካችንን ርዝመትና ያለንበትን የደኽነት አዘቅት ለመገንዘብ ይህ የክፋት ዘዴአችን ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ይመስለኛል፡፡ ከሰዎች በፊት በስልጣኔ በራፍ ላይ ደርሰን ከኋላችን የመጡት በአዳራሹ ሲገቡ እኛ አሁንም ውጭ ቆመን መቅረታችንና በልመና የምንኖር መሆናችን የገዥዎቻችን የአፈና ተግባር የማይቀር ውጤት ሆኖ ነው፡፡ በህገ አራዊት እየተመራን የሰውነት ሀብታችንን፣ አእምሮአችንና መንፈሳችንን ታፍነን ኑሮአችንን የምናሻሽልበትን ዘዴ ለመፍጠር አልቻልንም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ወኔ የነበራቸውና ሃሳባቸውንና እምነታቸውን ማንንም ሳይፈሩ በአደባባይ ለማውጣት የቻሉ ሰዎች መገኘታቸው ከአፈናው ባሻገር ጭራሹን ባዶ አለመሆናችንን ያሳየናል፡፡ ትልቁ ነገር የነዚህን የደቂቀ እስጢፋኖስን ሃሳብና እምነት መቀበል ወይም አለመቀበል አይደለም፤ ትልቁ ቁምነገር አባ እስጢፋኖስ በማንም አፋአዊ ኃይል ተመርተው ወይም ተገድደው ሳይሆን በራሳቸው የውስጥ የአእምሮ ብርሃን ተጉዘው ከ..ሲወርድ ሲዋረድ.. አስተሳሰብ ተላቅቀው ወደ አንድ መደምደሚያ ላይ መድርሳቸው ነው፡፡ ለማንም ማህበረሰብ ለትምህርትና ለእውቀት፣ ለእድገትና ለመሻሻል፣ ለልማትና ለብልጽግና አዲስ ፈርን እየቀደዱ አዳዲስ ደረጃ ላይ የሚደርሱት እንደዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ሰዎች እንደተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ እያሉ ድርግም በማለታቸው አገሪቱ ከነሱ ልታገኝ የምትችለውን ዘለቄታ ያለው ጥቅም አጣች፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት “ሲወርድ ሲዋረድ” በሚል በማያስብና በማያሳስብ የቁልቁለት አስተሳሰብ ለብዙ ምእት ዓመታት ተጓዙ፤ ውጤቱ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የቤተክህነት ትምህርት አእምሮን የመሳል ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው አያጠራጥርም፡፡ የተሳለና የሰለጠነ አእምሮ በጥልቀት ያስባል፤ ትክክለኛ የአስተሳሰብ ስልት በመከተልም አዲስ ሐሳቦችን ያፈልቃል፤ አዲስ ሐሳቦች አዲሱን ትውልድ ወደ አዲስ የእድገት ደረጃ ላይ ያወጡታል፤ አዲስ ሐሳቦች ከቆዩ ሐሳቦች ጋር እየተጋጩ በህገ ኃልዮት ያሸነፈው ይቀጥላል፤ የተሸነፈው ይሞትና ወደታሪክ ማህደር ይገባል፡፡ ወይም አዲሱና አሮጌው ተፋጭተው ከሁለቱም ውህደት ሌላ አዲስ ሀሳብ ይወጣል፡፡ የምዕራቡ ህብረተሰብ የተጓዘበት እውቀትን የማስፋት መንገድ ይህ ነው፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስ ሰቆቃ በግልፅ የምናየው ግን በእኛ ማህበረሰብ አዲስ ሀሳብ ጠላት ሆኖ መታየቱን ነው፤ ህገ ኀልዮት በህገ አራዊት መደቆሱን ነው፡፡ ሀሳብን በሀሳብ መቋቋም የማይችሉ የስልጣን ጉጉት የአእምሮ ስንኩላን ያደርጋቸው የሚቀናቸውና የሚቀልላቸው የሚጠሉት ሐሳብ ማህደር የሆነውን ሰው ማጥፋቱ ነው፡፡ የኖረውን ያለውን በግድ ተቀበሉ እየተባለ አዲስ ነገርን ማሰብና መግለጽ አደገኛ ተግባር እየሆነ ይሄዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ማሰብን ማስቀረት የማይቻል ቢሆንም ሐሳብን በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ማውጣቱ ለኢትዮጵያውያን እስከዛሬ አስቸጋሪ ነው፤ ስውርና የተለባበሰ አነጋገር እስከዛሬም ባህላችን ሆኖ የቆየ ይመስለኛል፡፡
ስለደቂቀ እስጢፋኖስ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክና ባህል በአዲስ መንፈስ እንደገና እንድንመረምር የሚጋብዘን ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን የአይሁድ አገር ለማድረግ፣ የእስላም አገር ለማድረግ የጠፋው የሰው ህይወት፣ የፈሰሰው የሰው ደም፣ የወደመው ንብረት ለህገ አራዊት እንደተገበረ መስዋዕት ልንወስደው የምንችል ይመስለኛል፡፡ የሚያሳዝነው ለህገ አራዊት መገበሩ ገና ዛሬም አለማብቃቱ ነው፡፡ ይህ ነው እያንዳንዳችን ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን፤ ምንድን ነው በእኛ ውስጥ ወይም በባህላችን ውስጥ ሐሳብን እንደጦር የሚፈሩ ሰዎች አናታችን ላይ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው? በተራው ኢትዮጵያዊም ዘንድ ቢሆን ይኸው ሐሳብን የመፍራት አዝማሚያ እንዴት ባህል ሆነ? ጭቆናን የኢትዮጵያውያን ባህርይ ያደረገው ምንድን ነው? ከምንም ህዝብ የተለየ የጭቆና ዝንባሌ የለንም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን እውነት ለመካድ መሞከሩ አይረዳንም፤ መድኃኒት የሚሆነን መቀበሉና መመርመሩ ነው፡፡
ጌታቸው በመግቢያው ላይ ደቂቀ እስጢፋኖስ ከማርቲን ሉተር ሰላሳ ዓመታት ቀድመው ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያመጡ ሰዎች ነበሩ ይላል፡፡ ይህ ትልቅ ነጥብ ነው፤ ማርቲን ሉተር በአውሮፓውያን አእምሮ ላይ ያመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ በሃይማት ላይ ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በዓለማዊው ጉዳይ ላይ የነበረው ተፅእኖ ማክስ ቬበር በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መሀከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማሳየት በዘገበው አንድ የቀልድ አባባል ይገለጣል፤.. ..ወይ በደንብ ብላ፤ ወይ በደንብ ተኛ፡፡.. Max Weber (tr. Talcott parsons), The protestant Ethic and the spirit of capitalism, ለዚህ የቬበር መጽሐፍ ቀዳሚ ቃሉን የጻፈው የእንግሊዙ የኢኮኖሚክስ ታሪክ ሊቅ ታውኒ ፕሮቴስታንትነት በአመጣው ለውጥ “ስራ የኑሮ ዘዴ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዓላማም አገኘ” ይላል፡፡ ይላል በዚሁ በማክስ ቬበር መፀሀፍ ገፅ ሶስት ላይ አእምሮ ከአፈና ሲወጣና ነፃነትን ሲያገኝ ከሰው ልጅ ውስጥ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይወጣል፤ ወሰኑ የማይታወቅ የመፍጠር ችሎታ በተጨባጭ ተግባር ይገለጣል፡፡ በዓለም ውስጥ ዛሬ በበለፀጉትና በሚደኸዩት አገሮች መሀከል ያለው ትልቁና ዋናው ልዩነት የአእምሮ ነፃነት ነው፡፡ ለምሳሌ በሚደኸዩት አገሮች ውስጥ ባለው ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት ይበልጥ የሚጠቀሙበት የበለፀጉት አገሮች ናቸው፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስም ላይ ቢሆን የአእምሮ ነፃነት ከሃይማኖት አጥር ውጭ ያለውን ዓለም የማሻሻል ችሎታን እያሳየ ነበር፤ አባ ዕዝራ ስለተግባረ እድ ተጠይቀው ሊያደርጉ የሚችሉትን ሁሉ ሲዘረዝሩ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ በውስጣቸው መኖሩን ያልተገነዘበው የንጉሱ መልእክተኛ መልስ “ይህን ሁሉ አደርጋለሁ የምትለው እግዚአብሔር ነህ እንዴ?” የሚል ነበር፡፡
አንድ ተጨማሪ ነጥብ መነሳት ያለበት ይመስለኛል፤ ከእለት ተእለት የኑሮ ትግል በቀር ማሰብን እንደሙያ የያዙ ሰዎች ከሃይማኖት ውጭ በኢትዮጵያ ነበሩ ለማለት ያስቸግራል፤ እነዚያውም በሃይማኖት አጥር ውስጥ ሆነው የማሰብ ችሎታቸውን ያሳዩ ሰዎች …እንደ አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው፣ ከዚያም በኋላ እንደፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ያሉት..ለስደትና ለስቃይ መዳረጋቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብ የተከለከለ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ትምህርቱ በተራቀቀበት በሃይማኖቱ አጥር ውስጥ ማሰብ ከተከለከለ ትምህርት በሌለበት ከሃይማኖቱ አጥር ውጭ ማሰብ ጨንገፎአል ማለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በሃያኛው ምእት አመት የዘውዱ ስርዓት ከፈጠረውና ከብዙ ዓመታት ትግል በኋላ የኢትዮጵያ መካነ ኀልዮት ከሆነው ደርግ ቢያዳክመውም ካልገደለው ዩኒቨርስቲ ወያኔ አርባ መምህራንን ማስወጣቱና ብዙዎቹን ለስደት መዳረጉ የሚያመለክተው አለመለወጣችንን ብቻ አይደለም፤ ከሃያኛው ምእት አመት ወደኋላ ተመልሰን አሁን በኢትዮጵያ ማሰብ የተከለከለ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም እኩይ የወያኔ ማን አለብኝነት ዩኒቨርስቲውን ቢያንስ ሰላሳ ዓመታት ወደ ኋላ እንደመለሱት ማሰብ ስለሚሳናቸው ሊገባቸው አይችልም፤ የአገሪቱን ዓይን እንደማጥፋት የሚቆጠር ነው፡፡
ጌታቸው ስለደቂቀ እስጢፋኖስ “አበባቸውን አረገፉት፣ የእንቅስቃሴያቸውን ነበልባል ውሐ ቸልሰውበት ሳይቀጣጠል ቀረ” ሲል የደቂቀ እስጢፋኖስን ሐሳብና እምነት መዳፈን በሚገባ ይገልጠዋል፡፡ ውጤቱ ግን በደቂቀ እስጢፋኖስ የተወሰነ አልነበረም፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የአእምሮ ነፃነት ተዳፍኖ እንዲቀርና ኢትዮጵያ በልጆቿ የአእምሮ ኃይል እንዳትጠቀምበት ሆኗል፡፡ ይህም ደኽነታችንንና ኋላቀርነታችንን ፍንትው አድርጎ የሚያስረዳን ይመስለኛል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ባንቱስታን መሰል የጎሳ ክፍፍል በሚታመስበትና በጥላቻና በመፈራራት መንፈሳዊ ውሳኔ ተሙዋጥጦ ባለበት ጊዜ የደቂቀ እስጢፋኖስ ታሪክ ልዩ መልእክት አለው፤ አገዛዙ ምንም ያህል በህገ አራዊት ላይ የተመሰረተ ክፉ ጭካኔ ቢያሳይም የሰው ልጅ መንፈስ የማይበገርና እምቢ ባይ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ቁም ነገሩ ደቂቀ አስጢፋኖስ መሸነፋቸው አይደለም፤ ቁምነገሩ እየተሰቃዩ መታገላቸው ላይ ነው፤ ለህገ አራዊት አንንበረከክም ማለታቸው ነው፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ነገር አንድም የደቂቀ እስጢፋኖስ አባል ሲሞት ሞተ አለመባሉ ነው፤ “ሰማዕትነቱን” ወይም “ገድሉን ፈጸመ” ይላሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጥልቅ መልእክት ያለው ሆኖ ይሰማኛል፡፡ የሰው ልጅ ህይወት እንደእንሰሳ ህይወት አይደለም፤ ዓላማ አለው፤ መልእክት አለው፡፡ ቁም ነገሩ ዓላማውን ወይም መልእክቱን መፈጸም ነው እንጂ መኖር ብቻ አይደለም፤ ሐሳብንና እምነትን እንደያዙ በነፃነት ማለፍ ሐሳብንና እምነትን አስረግጦ ከመኖር የተሻለ ነው ብለው የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ ለዛሬው ትውልድ ይህ ኃይለኛ መልእክት ነው፡፡
የዛሬው ትውልድ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ባለውለታ ነው፤ እነዚህ ለአዋቂው ለውጪው ዓለም ክፍት ሆነው፤ ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተቆልፈውበት የነበሩ ጽሑፎች ናቸው፡፡ እስከዛሬ አንድም ንጉስ ወይም ፕሬዚዳንት እነዚህን ታሪካዊ ሰነዶች አላስተረጎመና አላሳተመም፡፡ ጌታቸው በራሱ ጥረት ብቻ እነዚህን ጽሑፎች በአማርኛ እየተረጎመ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ ስላበቃቸውና ስለራሳችን እንድንማር በሩን ስለከፈተልን ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ በበኩሌ የምጨምረው በዚህ ሳያበቃ እግዚአብሔር እድሜውንና ብርታቱን ሰጥቶት ሌሎቹንም እንዲያበረክትልን ነው፡፡

ፍትህ

%d bloggers like this: