Archive | Professor Mesfin RSS feed for this section

የአፍሪካ ኀብረት ዓለም በቃኝ ገባ

6 Feb


ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
የዛሬ አርባ ዘጠኝ ዓመት ግድም በአፍሪካ አዳራሽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው የአፍሪካ ኀብረት) ሲመሠረት ተመልካች ሆኜ ገብቼ እዚያው አድሬአለሁ፤ የዛሬዎቹ ወጣቶች ያቺን ኢትዮጵያና እነዚያን ኢትዮጵያውያን የሚያውቋቸው አይመስለኝም፤ አንዳንዴ ሳስበው ግምትም ያላቸው አይመስለኝም፤ የነሱ ጥፋት አይደለም፤ ሥርዓት ባለው መንገድ ሥራዬ ብሎ፣ የአገር ጉዳይ ነው ብሎ ያስተላለፈላቸው የለም፤ ዛሬ የንክሩማ ሐውልት በአፍሪካ ኀብረት ግቢ ቆመ የሚል ወሬ ስሰማ ደርግ በአፍሪካ አዳራሽ መግቢያ ላይ የሌኒንን ሐውልት መትከሉን አስታወሰኝ፤ ዛሬ ደግሞ ወያኔ ከማን አንሼ ብሎ የንክሩማን ሐውልት በአፍሪካ ኀብረት ግቢ ውስጥ ተከለ፤ ንክሩማ ትልቅ አፍሪካዊ ነው፤ ነገር ግን ለአገሩም አልበቃም፤ በምንም ዓይነት መንገድ አጼ ኃይለ ሥላሴን አይተካም፤ ኢትዮጵያ ሰው አጥታ ከጋና መበደርዋ ኢትዮጵያ የወረደችበትን አዘቅት ያሳያል፤ እነማን ይዘዋት እንደወረዱም ግልጽ ነው፤ አንድ ሰው ብቻ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ የተዋረዱ እንዳይመስለን፤ የተዋረደችው ኢትዮጵያ ናት፤ እንደተለመደው ጠምዝዘው ጋናን ማጣጣል ወይም የጋናን ክብር መቀነስ አድርገው የሚያቀርቡት ይኖሩ ይሆናሉ፤ የምለው ጋና ከኢትዮጵያ አትቀድምም፤ ንክሩማም ከአጼ ኃይለ ሥላሴ አይቀድምም ነው፤ ንክሩማም ቢኖር በአፍሪካ ኀብረት ጉዳይ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ለውድድር አይቀርብም ነበር፤ ጋና ነጻ በወጣችበት እለት በዓሉን ለማድመቅ የሄዱት ልዑል ሣህለ ሥላሴና አቶ አበበ ረታ ነበሩ፤ ከተመለሱ በኋላ አቶ አበበ በብሔራዊ ቤተ መጽሐፍት ስለጋና ንግግር አድርገው አዳምጫለሁ፤ ኢትዮጵያኮ በኢጣልያ ወረራ ጊዜም የአርበኞችዋን ነፍስ ይማርና ሰንደቅ ዓላማዋ ሲውለበለብባት የነበረች አገር ናት፤ የአርበኞችዋን ነፍስ ይማር! ሐውልት ባናሠራላቸውም ሲናቁብን በአርምሞ ልናልፈው አንችልም፡፡
አርበኞችን ወደዳር ማስወጣትና የሥልጣን ወንበሮችን በባንዳዎች ማስያዝ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጀመሩት ቢሆንም ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ የአገር ውርደት መሆን የለበትም፤
በቅርቡ ሪፖርተር በርእሰ አንቀጹ የሀሳብ ማጠራቀሚያ (ቲንክ ታንክ) በሚል ርእስ ጽፎ ነበር፤ ከሹሞቹ ውጭ ሰዎች መኖራቸውን፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው መሆኑን፣ ሀሳባቸውን የሚያዳምጥ መኖሩን ካላረጋገጥን ሀሳቦች ዋጋ የላቸውም፤ የንክሩማን ሐውልት በኢትዮጵያ ለመትከል ወይም የሌኒንን ሐውልት በኢትዮጵያ ለመትከል ከአንድ ሰው በቀር አይወስንም፡፡

የአፍሪካ አንድነት የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1963ዓ.ም. ነው፤ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ከፍ ያለና የተከበረ ስም ነበራት፤ በአፍሪካ ያለምንም ጥርጥር ቀዳሚዋ አገር ነበረች፤ ኢትዮጵያን ለዚህ ያበቃት ረጅም የነፃነት ታሪክዋ፣ የህዝቡ ጨዋነት፣ የመሪዎቹ፣ በተለይም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ግርማና ሞገስ አንድ ላይ ሆነው ኢትዮጵያን የተከበረችና የተፈራች አገር አድርገዋት ነበር፡፡
ለአፍሪካ ኀብረት የተሰበሰቡት በዘመኑ የነበሩ ታላላቅ መሪዎች፣ አገሮቻቸውን ከቅኝ አገዛዝ ያወጡ ሰዎች ነበሩ፤ መሪዎቹ በየሰፈራቸው የጎረቤቶች መኀበር እያቋቋሙ ለትልቁ የአፍሪካ አንድነት እምብዛም ግድ አልነበራቸውም፤ ምናልባትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በማቋቋም እያንዳንዳቸው በየአገራቸው ያላቸው ሥልጣን የሚ¬¬¬-ቀነስባቸው መስሎአቸው የነበረ ይመስለኛል፤ አብዛኛዎቹ እናጥናው፣ እናብላላው በማለት የድርጅቱን ምሥረታ ለማስተላለፍ በፓም ይጥሩ ነበር፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግን የድርጅቱ ሰነድ ሳይፈረም ማናችንም ከአዳራሹ አንወጣም ብለው ገትረው ያዙአቸው፡፡
የአጼ ኃይለ ሥላሴ ትልቅነትና የኢትዮጵያ የመንፈስ መሪነት በገሀድ ታየ፤ እንደናስርና እንደቤን ቤላ ያሉ አብዮተኞች ሳይቀሩ ከጃንሆይ ጋር ሲነጋገሩ ጎንበስ ብለውና እጆቻቸውን ወደኋላ አጣምረው ነበር፤ መቼም የዚህ ፊልም አንድ ቦታ ይኖራል ብዬ ተስፋ አለኝ፤ የዛሬ ወጣቶች ሁሉ ሊያዩት የሚገባ ነው፤ እምቢተኞቹንና አፈንጋጮቹን ሁሉ አንድ በአንድ እያነጋገሩ፣ እንደኒዬሬሪና አሚን ተጣልተው የማይነጋገሩትን እያስታረቁ ሰነዱ ሳይፈረም መውጣት የለም አሉ፤ እንደማስታውሰው ሰነዱ ከሌሊቱ በስምንትና በዘጠኝ መሀከል ተፈርሞ አለቀና ሲነጋ በየቤታችን ገባን፡፡
የአፍሪካ አንድነት በጋዳፊ (ነፍሱን ይማረውና) ውትወታ የአፍሪካ ኀብረት ተባለ፤ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ነው፤ ዓላማው የአፍሪካን ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ የአፍሪካ አገሮችን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለመጠበቅና ከማናቸውም ዓይነት ቅኝ አገዛዝና ቄሣራዊ ተጽእኖ ለመከላከል ነበር፤ ነበር፤ ነበር፤ በአገሮች መሀከል የሚከሰቱ ችግሮችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲገኝላቸው ማድረግ ነበር፤ ነበር፤ ነበር፡፡
እንደዚያ ዕለት በኢትዮጵያዊነቴ ኮርቼ አላውቅም፤ ስለዚህም የኢትዮጵያውያን የዩኒቨርስቲ መምህራን ማኀበር ስብሰባ ጠራሁና ያየሁትን ገልጬ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ የምስጋና ደብዳቤ እንጻፍላቸው የሚል ሀሳብ አቀረብኩ፤ አንዳንድ ተቃውሞ ተነሥቶ ከተከራከርንበት በኋላ እንዲጻፍላቸው ተወሰነ፤ ዳብዳቤውን ጽፌ ለጃንሆይ እንዲሰጥልን ለዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ለልጅ ካሣ ወልደማርያም አስረከብሁት፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠራኝና አንተው ወስደህ ብትሰጥ ይሻላል አለኝ፤ የምሄድበትን ቀንና ሰዓት ነገረኝ፤ ወስጄ በእጃቸው ሰጠኋቸው፤ እንዳነበቡት ወይም እንደተነበበላቸው ፍልቅልቅ ባለ ደስታቸው ይታይ ነበር፡፡
ዛሬ የአፍሪካ አንድነት (ኀብረት) በቻይና ቸርነት ፎቅ ተሠርቶለት ዓለም በቃኝ ገባ አሉ፤ የአፍሪካ መሪዎችም እዚያው ተሰበሰቡ፤ አቶ መለስም ለቻይና አስተዋጽኦ ዋጋ ለመክፈል ለማኦትሴ ቱንግ ተማሪ ሐውልት አስተከለ፤ ቀጥሎም የአፍሪካ መሪዎች በምን ምክንያት ወደ አውሮፓ ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ በማለት አቶ መለስ ተቆጥቶ በዓለም-በቃኝ ፎቅ ውስጥ የአፍሪካ ፍርድ ቤት ማቋቋም እንችላለን የሚል ሀሳብ አቀረበ ተባለ፤ ማን በማን ላይ እንዲፈርድ ይሆን? የአውሮፓ ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት የተፈራው ምኑ ነው? ወይስ የዓለም-አቀፍ ትርጉም ችግር ሆኖ ነው? መቼም የአፍሪካ ፍርድ ቤት ዓለም-አቀፍ ደረጃ ላይ ይውጣ ማለት…ምን ማለት ይሆን? የተባበሩት መንግሥታትስ መቼ ነው ተለይቶ ‹‹አፍሪካዊ›› የሚሆነው?
ለማናቸውም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሆነው የሚመለከቱን የኢትዮጵያ አርበኞች ይቅር ይበሉን፤ ለኢትዮጵያም ከሌኒን ያወጣት አምላክ ያውቃል!

Advertisements

ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ ይባል ነበር ዱሮ ወግ ነው ምርጫ ማሸነፍ ሆነ ዘንድሮ! አስተሳሰብና ጉልበት (ሕገ አራዊት)

31 Jan

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

በረከትን በደንብ የሚያውቀው ያሬድ ጥበቡ ሙልጭ አድርጎ ነግሮታል፤ ያሬድ ከዚህ በፊትም ስለበረከት ጽፎ ነበር፤ አሁን ከጻፈው ጋር ሳስተያየው አንድ ግጥም ትዝ ይለኛል፤ አንዲት የቸገራት ሴትዮ ያንጎራጎረችው ይመስለኛል፡-

ወደድኩህ ወደድከኝ፤ ጠላሁህ፤ ጠላኸኝ፤
እንደሚጣራ ጠጅ እየጣልክ አታንሣኝ!

ያሬድ ስለበረከት በሚጽፈው ሁሉ እያነሣ የመጣልና እየጣለ የማንሣት ዝንባሌን ያሳያል፤ እስከዛሬ በናፍቆት የሚጠብቀውን ወዳጁን ሸፍጥንና የአእምሮ ሕመምን ሲያለብሰው ማንኛቸው መቼ እንደተለወጡ ለመረዳት ያስቸግራል፤ ለማናቸውም የዲክንስን መጽሐፍ ያሬድ እንደሚለው በረከት ከመጀመሪያው ገጽ በላይ አነበበም አላነበበ እንግሊዝኛው ትርጉም መሆኑን የተረዳሁት ከያሬድ ነው፤ ለምን ወደ እንግሊዝኛ እንደተሄደም አልገባኝም፡፡

በዚህ ዓመት ታላላቅ የአገር መሪዎች የሚያስተምሩን ነገር ባይኖራቸውም ‹‹የታሪክ››መጽሐፍት የሚሉትን አሳትመዋል፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና አቶ በረከት ስምዖን፤ ሁለቱ ሰዎች በብዙ ነገር የሚመሳሰሉ ቢመስሉም እውነትን በመናቅና በመጥላት አንድ ናቸው፤ ዛሬ እኔ ላነሣ የፈለግሁት ግን በአስተሳሰብ ግድፈት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

በ1997 የፖለቲካ ክርክር ላይ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ሠላሳ በመቶ የሚሆነው ስለሰብዓዊ መብቶች የሚናገር ስለሆነ ይህ ቀረው የሚባል አይደለም፤ ችግሩ በተግባር የምናየው ሕገ አራዊት መሆኑ ነው ብዬ የተናገርሁትን ጉልበተኛው በረከት ወዲያው ቀለብ አድርጎ ‹‹ሕገ መንግሥቱን ሕገ አራዊት ነው አለ፤›› ብሎ ወነጀለኝ፤ ለጉልበተኛው ሕገ ኀልዮትም ሆነ ሕገ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ አይደሉም፤ ዛሬ ረዳቱ የሆነውም ጠበቃው የገዛ ጆሮውን ከድቶ በጉልበተኛው የተነገረውን እያስፋፋ በፍርድ ቤቱ አስተጋባ፤ ዳኞቹም ጠበቃውን ሰምተው ፈረዱ፤ ዛሬ እነሱ አንገታቸውን አጎንብሰው ይሄዳሉ፡፡

ዛሬም ያው አስተሳሰብ (አስተሳሰብ ካልነው) እንደተለመደው ቃላትን እየዘለዘለ ለውንጀላ ያቀርባል፤ አንዱዓለም አራጌ ‹‹የአምባ ገነን አገዛዝ ባለበት የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው፤›› አለ ይባላል፤ ጉልበተኛው እንደለመደው መጀመሪያ የተባለውን ቀንጭቦ ኪሱ ከተተና (!)አንዱ ዓለም ‹‹የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው›› አለ ብሎ ለውንጀላ ያመቻቸዋል፤ የአንዱ ዓለም መታሰር እሱ ራሱ ያለውን ያረጋግጣል? ወይስ አለ የተባለውን ያረጋግጣል? ወይስ ሁለቱንም ያረጋግጣል? በመሠረቱ አንዱ ዓለም ያለው ሙሉ ቃልና ጎዶሎው ልዩነት የላቸውም፤ የጉልበት አገዛዝ ባለበት የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው፤ የሚለውና ያለመነሻ የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው፤ የሚለው በአንድ ነገር ይመሳሰላሉ፤ ጀግናን የጥቃት ኢላማ በማድረግ ይስማማሉ፤ ከዚያም አልፎ ጀግንነትን መጠቃት አድርገው የሚያቀርቡት ይመሳሰላሉ፤ የተዛባ አስተሳሰብ!

ቀጥዬ የምጠቅሰው ምሳሌ ከላይ ከተጠቀሱት የባሰ የአስተሳሰብ ግድፈትን የሚያመለክት ነው፤ አቶ መለስ ‹‹የተሃድሶ እንቅስቃሴያችንን በከፍተኛ ፍጥነት ከሚወርድና በየደቂቃው ፍጥነት እየጨመረ ከሚጓዝ ናዳ አምልጦ ወደ ጠንካራ ከለላ ለመግባት ከሚሮጥ ሰው ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡›› ሲል ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ውስጥ ተናግሮአል፤ በ1997 ምርጫ አቶ መለስ ብዙ አጃቢዎቹ (አቶ በረከትን ጨምሮ) ስለዌደቁበት የናዳውን ኃይል በትክክል ገምቶ የተናገረ ይመስለኛል፤ መለስ የተናገረው ወደበረከት ስምዖን ጆሮ ሲደርስ ግን ሌላ ሆኖ ነበር፤- ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ! መለስ ወደፊት ሂድ! ሲል በረከት ስምዖን ቀኝ-ኋላ ዙር! ይላል፤ ወደፊት አልሮጥም የማለት መብት አለው፤ ጥያቄው ይህ አይደለም፤ የአስተሳሰብ ግድፈቱ ወደፊት ሂድ ማለትና ቀኝ-ኋላ ዙር ማለትን አንድ ማድርጉ ላይ ነው፤ በወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን የመጣ የአፈፃፀም ጉድለት የሚባለው ነገር ምንጩ እንዲህ ያለ የግንዛቤ መዛባት መሆኑ ነው፡፡

ለምራቂ አንድ ሌላ ግድፈት ላቅርብ፤ የመጽሐፉ ዋና ርዕስ ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› ነው፤ ምን ማለት ነው? ወግ የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም አለው፤ አንዱ ትርጉም ወሬ ነው፤ ሁለተኛው ትርጉም ሥርዓት ማለት ነው፤ ከሃምሳ ዓመታት በፊት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ በራስ ቢትወደድ እንዳልካቸው የተደረሰ ጨዋታ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ታይቶ ነበር፤ አቶ አሐዱ ሳቡሬ ሲተቹ ድራማ ብለውት ነበር፤ እኔ ግን ጨዋታ ነው ብዬ ‹‹አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም›› ለዚያ ለሞተ ጨዋታ ተስማሚ ስም ነው በማለት ጽፌ ነበር፤ እንዲሁም የሁለት ምርጫዎች ወግ በሁለቱም የወግ ትርጉሞች ተስማሚ ስም የተሰጠው ተረት ነው፤ እውነቱ ጸሐፊው በዚያ ምርጫ መውደቁ ነው፤ እውነቱ ጸሐፊው እንደገና በልዩ ዝግጅት ተመረጠ መባሉ ነው፤ ታሪክን፣ ያውም የቅርብ ታሪክን ወደተረት ለመለወጥ ለጉልበተኛም ቢሆን አስቸጋሪ ነው፤ ተዋንያኑ ሁሉ ገና በሕይወት አሉ፤ ጸሐፊው ልማድ ሆኖበት አላነበባቸውም እንጂ አንዳንዶቹም ስለምርጫው ከወግ ባለፈ ጽፈዋል፡፡

ስለ2002 ምርጫ በቅርቡ እንኳን በአሐዝ የተደገፈ ጥናት ወጥቷል፤ አንደኛ ከአጠቃላይ የየክልሉ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ የመረጡትን ስናይ ምርጫው ወግ ብቻ እንደነበረ ገሀድ ይሆናል፤ ለምሳሌ ከየክልሉ የመረጡት በኦሮሚያ 31 ከመቶ፣ በአማራ 33 ከመቶ፣ በደቡብ 27 ከመቶ፣ በትግራይ 39 ከመቶ፣ በአዲስ አበባ 19 ከመቶ፣በአፋር 66 በመቶ፣ ከዚያ ደግሞ በድሬደዋ 57 ከመቶ ሲሆኑ በሐረርና በኦጋዴን ደግሞ ለወግም የማይመች በመሆኑ አልተገለጸም፤ ናዳው የምርጫውን ወግ እንኳን እንደደፈጠጠ በተለይ የአፋርና የድሬዳዋ የመራጮች አሐዝ ምስክር
ነው፤ እድሜያቸው የማይፈቅድላቸው ሁሉ ካልመረጡ በቀር፤ ወይም በእነዚህ ክልሎች አብዛኛው ሕዝብ በልዩ ተአምር እድሜው ከ18 ዓመት በላይ ካልሆነ በቀር ከላይ የተገለጸውን ያህል መራጭ ሊያገኙ አይችሉም፤ እንዲሁም በመረጡት ወንዶችና ሴቶች መሀከል በየክልሉ የሚታየው ድርሻ ወንድና ሴቱ እኩል እንዲሆን ተደርጎ የተደለደለ መሆኑ ይታያል፤ ይህንን ሁሉ የዘነጋ ከታሪክ ይልቅ ወደተረት ያዘነበለ ጨዋታ ነው፤ ተረቱ የሚጣፍጠው ከተገኘ!

ሁለተኛ አቶ ኡስማን አሊ የሚባል ሰው 368,211 ድምጽ፣ አቶ ሽመልስ ከማል ብርሃን የሚባል ደግሞ 19,647 ድምጽ ለወጉ አግኝተው ተመርጠዋል፤ ከተመራጮቹ 64 በመቶ ያህሉ ያገኙት ድምጽ ከ50,000 በታች ነው፤ መለስ ዜናዊ ያገኘው 40,302 ነው፤ በትግራይ ወይዘሮ አልማዝ የሚባሉ 87,185 ድምጽ ማግኘታቸው ቱባ ቱባ ባለስልጣኖቹ ካገኙት ጋር ሲወዳደር ሰማይ ያደርሳቸዋል ስለ2002 ምርጫ በአገቱኒ ውስጥ ዝርዝር መረጃ ቀርቦአል፡፡

መጽሐፍ ያውም የታሪክ መጽሐፍ ለመጻፍ ለእውነት ክብር መስጠትና ለእውነት ተገዢ መሆን ያስፈልጋል፤ አለዚያ ጉልበትና የአቶ አላሙዲንን ገንዘብ ማጥፋት ነው፡፡

Feteh

ሽብር ማለት የየካቲት 12 ሽብር

5 Dec

For Amharic PDF file visit here: Terrorism

መስፍን ወ/ማርያም /ፕሮፌሰር/

የኢትዮጵያ ህዝብ ለልጆቹ ስም ሲያወጣ ሽብሩ፣ አሸብር፣ ወንድይራድ፣ ያየህይራድ ይላል፤ ሽብርን ፈልጎ አይደለም፤ ሽብርን ራሱን አስፈራርቶ ለማስቀረት ነው፤ ጥቃትን ለመከላከል የፈጠረው ዘዴ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሽብር ጠላት መሆኑን አንድ ማስረጃ ላቅርብ፤ ስለችጋር ሳጠና በችጋር ጊዜ ሽብር፣ ዝርፊያና ቅሚያ፣ ረብሻ የማይታይባት ኢትዮጵያ ብቻ ነች፤ በችጋር ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብርና ዝርፊያ ያየ ሰው ቢነግረኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ አሁን ወደ የካቲት 12 ሽብር ልግባ፤ ሽብር እንደማናውቅ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡

ኢያን ካምቤል የሚባል ብሪታንያዊ በየካቲት 12/1929 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣልያን እንደራሴ፣ ግራዚያኒን ለመግደል ስለተደረገው ሙከራ አንድ መጽሐፍ አሳትሞአል፤ በመጀመሪያ አንድ ነገር መናገር አለብኝ፤ መንግስት ቢኖር፣ ወይም ለታሪክ ክብር የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን ምሑራን ቢኖሩ እስከዛሬ ድረስ ጉዳይ ብለን ሳናጠናው የተውነውን ትልቅ ጉዳይ ኢያን ካምቤል ስለጻፈልን በጣም የሚመሰገን ነው፤ እኛን ግን በጣም የሚያሳፍረን ነው፤ እኔማ ብዙዎቹ ሰዎች በቅርቤ የነበሩ ዘመዶችና ወዳጆች ስለነበሩ ይበልጥ ያሳፍረኛል፡፡
ስለ የካቲት 12 ሽብር፣ ስለ አብርሃ ደቦጭና ስለ ሞገስ አስገዶም ላይ ላዩን እሰኪበቃን ሰምተናል፤ ዋናውንና ዝርዝሩን ጉዳይ ግን ሳናውቀው ቆይተን ነበር፤ ሁለቱ የኤርትራ ወጣቶች በኢጣልያ የቅኝ አገዛዝ መስሪያ ቤት ውስጥ ታማኝ አገልጋዮች ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፤ በአንድ በኩል ውስጣቸው የተቀበረ የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ በሌላ በኩል ከኤርትራ ተከትሎአቸው የመጣው የፋሺስት ኢጣልያኖች ንቀትና ማዋረድ አንገፍግፎአቸው ክፉ ጥላቻ በውስጣቸው አሳደረባቸውና በፋሺስት እንደራሴው ላይ ጉዳት ለማድረስ ወስነው ተነሱ፤ ተዘጋጁ፡፡
ለየካቲት 12 የኢጣልያ አገዛዝ የኢትዮጵያ ህዝብ የማስገበሪያ ልዩ ዝግጅት አድርጎ በቤተ መንግስት (በኋላ የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርስቲ) በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ግቢውን ሞልተውት ነበር፤ ለፋሺስት ኢጣልያ እንዲገብሩ የተጠሩት ታላላቅ የኢትዮጵያ መሳፍንትና መኳንንት፣ የተማሩ ወጣቶች፣ የተማሩ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ የኢጣሊያን ታላቅነትና ቸርነት እንዲቀምሱ የተጠሩ በሺህ የሚቆጠሩ ደሀዎች፣ አካለ ስንኩላን፣ ዓይነ ስውሮች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ሁለት ሁለት ጠገራ ብር ምጽዋት ለመቀበል ተኮልኩለው ነበር፤ እንግዲህ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በሀጂ በዳሶ በኩል ከድሬዳዋ የመጣላቸውን ቦምባቸውን ታጥቀው በሰገነቱ ላይ ነበሩ፤ የመጀመሪያውን ቦምብ ሲጥሉና መሬት ሲጨልም ግራዚያኒ ሲሸሽ ሌላ ቦምብ ወረወሩና ከኋላው ክፉኛ አቆሰሉት፤ ቁስሉን ሁለት ወር ተኩል ያህል በራስ ደስታ ሆስፒታል (ያኔ የኢጣልያኖች ሆስፒታል ነበረ) ተኝቶ ቢታከምም እስከ ህይወቱ መጨረሻ ከውስጥም ከውጭም ህመምተኛ ነበር፤ ከግራዚያኒ ጋር ብዙ የፋሺስት ሹሞች ቆስለዋል፤ ከኢትዮጵያውያን መሀከልም ራስ ኃይለ ስላሴ ጉግሳና ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስም ቆስለዋል፡፡
ከቦምቡ በፊት ግራዚያኒ ባደረገው ዲስኩር የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያን ለማዳን እግዚአብሔር የላከው እንደሆነና የአማራን የአረመኔና የግፍ አገዛዝ እስከዘላለም ለማስወገድና አማራዎች ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡
ሁለት ሰዎች ቦምብ ስለወረወሩና ምንአልባትም ከአሥር የማይበልጡ ሌሎች ሰዎች ስለተባበሩአቸው ምንም አይነት ምርመራ ሳያስፈልግ፣ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይሰበሰብ በመጀመሪያ እዚያው ግቢ ውስጥ ለማዳመቅና ለመገበር የተሰበሰቡት መሳፍንትና መኳንንት፣ ለምጽዋት የተጠሩ ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ድሆች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ አካለ-ስንኩላን ተጨፈጨፉ፤ ቀጥሎም የተማሩ የተማሩ ሰላማዊ ወጣቶች፣ የጦር መኮንኖችና ነቃ ያሉ ካህናት፣ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በሙሉ እየተለቀሙ ተጨፈጨፉ፤ ሽብር ይህ ነው፤ ኢትዮጵያውያንን በቤት ውስጥ እያስገቡ ከውጭ ቆልፈው ቤንዚን እያርከፈከፉ አቃጠሉአቸው፤ ሽብር ይህ ነው፤ ጠመንጃ የሌለው ፋሺስት በአካፋ፣ በዶማ፣ በመጥረቢያ በተገኙበት ኢትዮጵያውያንን እየቆራረጠ የደረቀውን የበጋ መሬት የኢትዮጵያውያንን ደም አጠጣው፤ ሽብር ይህ ነበር፡፡ የፋሺስቱ ሰራዊት ደብረ ሊባኖስን ከነመነኮሳቱ አቃጠለው፤ ይህ ሽብር ነበረ፤ አዲስ አበባ ሬሳ በሬሳ ላይ የተከመረባት፣ የደም ጎርፍ የሚወርድባት፣ ዓየሩ በተቃጠለ የሰው ሥጋና በሬሳ ሽታ ተበክሎ መተንፈስ አስቸጋሪ የነበረባት ከተማ ነበረች፤ ሽብር ይህ ነው፤ ኡኡታው፣ ለቅሶው፣ ዱብ ዱብ እያለ ከደም ጋር የሚደባለቀው እንባ.. ይህ ነው ሽብር.. ወደ ሰማይ የሚከንፈው ጩኸት አምላክን ሲያስከፋና ሲያሳዝን፣ይህ ነው ሽብር..
ግራዚያኒ ትንሽ ሲያገግም ከአማራ መኳንንት ጋር ለመገላገል ከዚህ የተሻለ ዕድል አይኖርምና ሁሉንም ጨርሱ፤ ብሎ አዘዘ፤ ሽብር ይህ ነው..
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በፋሺስት ተይዘው ሊሰቀሉ ሲሉ አብርሃ ደቦጭ ..የወንድሜን ስቅላት አላይም፤ እኔን መጀመሪያ ስቀሉኝ.. ስላለ እንደፈለገው ሊሰቅሉት ሲዘጋጁ ..ለአገሬ በአደረግሁት ነገር ሁሉ እኮራለሁ፤ አሁንም በደስታ ለአገሬ እሞታለሁ…. ብሎ ሲናገር የፋሺስቱ አዛዥ በንዴት ተበሳጭቶ አብርሃንም ሞገስንም በሽጉጥ ገደላቸውና ሬሳቸውን ሰቀለ፤ እብደት የሽብር መጨረሻ..
ፋሺስቱን አዛዥ ምን አሳበደው? ያቺን ጠምዝዞና ጨምቆ፣ ዳምጦና ፈልቅቆ ከውስጣቸው አስወጥቻለሁ ብሎ የገመተው ኢትዮጵያዊነት ፊት ለፊት ገጠመው.. ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ፋሺስቱ አዛዥንም ሞትንም እያዩ በአንድ ላይ ተጋፈጡአቸው፤ ኢትዮጵያዊነት የተሸፈነበትን የፋሺስት መንጦልያ ቀዳዶ ወጣ.. ፋሺስቱንም ሞትንም ናቀ.. ለሞት የተዘጋጀ ሰው ሲንቅ፣ ለመግደል ለተዘጋጀው ሰው የመንፈስ ሞት ነው..
በዚያው እለት ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጋፍጦ የአበደው የፋሺስት አዛዥ ቀኛዝማች ወርቁ በሚባሉ አርበኛ ጦር ተመትቶ አብርሃ ደቦጭንና ሞገስ አስገዶምን ተከትሎ ሄዶአል፤ የሽብር መጨረሻው ይህ ነው..
ፈሪሃ እግዚአብሔር አለውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽብር ይፈጸምበታል እንጂ ሽብር አይፈጽምም፡፡

የአስተሳሰብን ህግ ካልጠበቅን ለመግባባት ያቅተናል – Professor Mesfin Woldemariam

11 Oct

For Amharic pdf file click here: Professor Mesfin

ለብዙ ዓመታት የማውቀው ወዳጄ ገብሩ ታረቀኝ በፍትህ ጋዜጣ ላይ፣ የማላውቀው አቶ ዓሥራት በአድማስ ጋዜጣ ላይ በትግሬነታቸው ተቆርቁረውና እኔን ባዕድ አድርገው የጻፉትን አንብቤ ሁላችንንም የሚያውቁ ሌሎች ሰዎች አስተያየት እንዲሰጡበት በማለት መልስ ከመስጠት ተቆጥቤ ቆየሁ፤ ሆኖም እስካሁን ከአንድ ሰው በቀር የደረሰልኝ የለም፤ ስለዚህ እኔው ልጋፈጠው፡፡
ገብሩ ወዳጄ ነው የምለው ሰው ስለሆነ የጋለ ስሜቱን ይዞ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ከእኔ ጋር ጉዳዩን አንስቶ አለመወያየቱ ከሚችለው በላይ የሆነ ግፊት ቢያጋጥመው መስሎ ታየኝ፤ እንዲያውም ሌላ ሰው እሱ ያለውን ሲናገር ቢሰማ ለእኔ ቆሞ ይከራከራል ብዬ የምገምተው ሰው ነበር፤ አንድ ሳይካያትሪስት (የአእምሮ ሐኪም) ሲናገር እንደሰማሁት የጎሳ አስተሳሰብ የጎሳን ድንበር ጥሶ ወዳጅነት የሚባል ነገር አያውቅም ያለውን አስታወሰኝ፤ ይህ እንደማይሆን ተስፋ አለኝ፡፡
በምን ላይ እንደጻፍሁት ሳልናገር ለሁለቱም የትግራይ ተቆርቋሪዎች የሚከተሉትን አጫጭር ነጥቦች ላመልክታቸው፡-
1. ወያኔ ..ከሚኒልክ በፊት ኢትዮጵያ አገር አልነበረችም ሲል የአፄ ዮሐንስንና የራስ አሉላን ትግሬነትና ኢትዮጵያዊነት በመካድ.. ጀመረ፤
2… የጎንደርን በሬ፣ የጎጃምን በሬ፣ የሸዋንም በሬ፣
ባንድ አርጎ ጠመደው የትግሬው ገበሬ..
(የትግራይን የኢትዮጵያዊነት መሰረት ለማስረዳት የጠቀስሁት)
3. ..የትግሬ ዘር (ኤርትራውያንን ጨምሮ) የኢትዮጵያ መሰረት ነው፤ የትግሬ ዘር የኢትዮጵያን ታሪክ ተሸካሚ ነው፤ እንኳን በኢትዮጵያዊነታቸው ያሉትን ትግሬዎች የተገነጠሉትንም ለማጥፋት ማሰብ በምድርም በሰማይም ይቅርታ የማያስገኝ ወንጀል ነው፡፡ ከኤርትራውያን ጋር የተደረገውንም የወንድማማቾች ጦርነት አጥብቄ የተቃወምሁት በዚህ ምክንያት ነበር፤ በሰሜን ያሉትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከመቅጽበት ወደባዕድነት ለውጠን አሁን ደግሞ የተረፍነውን አጥፊና ጠፊ አድርጎ መፈረጁ ለማንም የሚበጅ አይሆንም፡፡..
ብዙ ሌሎችንም መጥቀስ እችላለሁ፤ ልብ ላለው ይበቃል፡፡
በደርግ ዘመን በዩኒቨርስቲ ውስጥ ስናወራ ስለ የአእምሮ ወዝ-አደር ስናገር አንዱ ካድሬ የአእምሮ ወዘ-አደር የሚባል ነገር የለም ብሎ ተቆጣ፤ አብረውን የነበሩት ሁሉ በስምንት ተኩል እኔ ቢሮ እንዲመጡ ጋበዝሁና መጽሐፉን ይዤ መጣሁና ለካድሬው አሳየሁት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌኒን ተናዶ በደርዘን የሚቆጠሩ ካድሬዎችን በአንድ ትጉህና ታታሪ ባለሙያ የሚለውጠኝ ባገኘሁ ብሏል ስል ያው የማይማር ካድሬ ተቆጣና ..አይወጣውም…. አለ፤ መቶ ብር ከኪሴ አወጣሁና አንድ ጊዜ በነፃ አስተምሬሃለሁ፤ አሁን ግን መክፈል አለብህ፤ የሌኒንን ጽሑፍ ካላመጣሁልህ መቶ ብር ታገኛለህ፤ ካመጣሁ ግን መቶ ብር ትከፍላለህ ብለው አሻፈረኝ ብሎ በስሀተቱ ጸና፤ አቶ ዓሥራት ብዙውን ጽሑፎቾን አንብቤአለሁ ሲል እውነት እንዳልሆነ ስለማውቅ ውርርድ ላቀርብለት ፈልጌ ነበር፤ ስለአማራ የተናገረው እኔ የጻፍሁትን እንዳላነበበ ጥሩ ማስረጃ ነው፤ ሳያውቁ በእርግጠኛነት አዋቂ መስለው ለሚቀርቡ ቀላሉ መንገድ በአደባባይ ውርርድ ነው፤ ገብሩ ታረቀ እንኳን በአሜሪካ የፈረንጅ ልጆች ሲያስተምር ስለኖረ በአገር ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ ማንበቡ አጠራጣሪ ነው፡፡
ለነገብሩና ለነዓሥራት ትልቁ ፍሬ ነገርና ቁም-ነገር ትግሬነታቸውን ለብቻቸው የያዙት መስሎአቸው ነው፤ በትግሬነታቸው ውስጥ አነሱንና እኔን የሚያያይዙ ብዙ ከባድ ሰንሰለቶች መኖራቸውን አያውቁም፤ ለነሱ ትግሬ ከትግሬነት ሌላ ፋይዳ ወይም ትርጉም የለውም፤ እንደዚህ ያለ ክርክር መነሳቱ ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል እንደላላ የሚያመለክት ነው፡፡
..ማወቅ ወደ እርግጠኛነት የሚያመራው በመጠራጠርና በመጠየቅ ነው፤ አለማወቅ ግን ምንጊዜም ወደጠን ካራ የጨለማ እርግጠኛነት የሚመራ ነው፤ አለማወቅ ከኃይል ጋር ሲጋባ የአምላክን ቦታ ይይዝና እስመ አልቦ ዘይሰአኖ ይሆናል፡፡..
ሁለቱም ሰዎች፣ ፕሮፌሰር ገብሩም አቶ ዓሥራትም ባሳዩዋቸው ሁለት የእውቀት ጉድለቶች ልጀምር፤ ይህንን ማድረጉ አያስደስተኝም፤ ነገር ግን አለማወቅን ወደ እውቀት እየለወጡ ሰዎችን ማሳሳቱ፣ ከዚያም አልፎ በትግራይ ማህበረሰብ ላይ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የጥላቻ መርዝን ለመንዛት የሚደረገውን ሙከራ አገርን የሚጎዳ ነውና ሊታለፍ አይገባም፤ ፕ/ር ገብሩም አቶ ዓሥራትም በሂሳብ ትምህርታቸው ስለ Set theory ትንሽ ቢያውቁ ..የኤርትራና የትግራይ ዜጎች..ያልሁት ደማቸውን አያፈላውም ነበር.. ትግራይ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ውስጥ ይገኛሉ፤ የኔ ስህተት የአንባቢዎችን ደረጃ ከፍ አድርጌ መመደቤ ነው፡፡
ሌላው የእውቀት ልዩነት ሰው የመሆን ግንዛቤያችን ነው፤ ለእኔ ሰው በቁና የሚሰፈር፣ ወይም በከረጢት የሚታሰር አይደለም፤ እያንዳንዱ ሰው በነጠላ ለራሱ ስራ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤ እንኳን በ2004ዓ.ም ጥንትም ቢሆን ጽድቅም ሆነ ኩነኔ የግል ነው፤ በጎሳ ወይም በጅምላ አይመጣም፤ የሰው ልጅ እንደ አይጥና እንደድመት አይደለም፤ እንኳን አብሮ የኖረና የተዛመደ፣ አንዱ ለሌላው የመጨረሻ መስዋዕትነት የከፈለ ቀርቶ እንግዳም ቢሆን አንዱ ለሌላው መሰረታዊ ጠላትነት የለውም፤ ፕ/ር ገብሩና አቶ ዓሥራት እንጀራቸውን ለማብሰል ለትግሬዎች ዘብ የቆሙ መስለው ባልገባቸው ነገር ሁሉ ደማቸውን ያገነፈሉት እኔን ባዕድ በማድረግ ለመጠቀም ነው፤ ለእነሱ አዝናለሁ፤ የትግራይ ህዝብ እኔን በነሱ ዓይን እንደማያየኝ አምናለሁ፡፡
ፕ/ር ገብሩ ..እኔም እንደአስገዶም ገ/ስላሴ የወዲያ ማዶ ልጅ ነኝ.. ይላል፤ ወዲያ ማዶ ስል ትግራይ ማለቴን ማን ነገረው? ስብሐት ነጋን ወዲህ ማዶ ሳደርገው በገብሩ ግንዛቤ ትግሬ አይደለም ማለቴ ነው መሰለኝ.. ገብሩን ወዴት ከፍ ከፍ እለዋለሁ.. ገብሩ የወዲያም የወዲህም ልጅ አይደለም፤ የባህር ማዶ ልጅ ነው..
ሁለተኛ ስለኤርትራውያን የተናገረው መልካም ስሜቱን ከመግለጽ በቀር መጽሐፉን ቢያነብበው ኤርትራውያን በስሜት ሳይሆን በተግባር እሱ ..እስረኞች.. ያላቸው ሰዎች የገለጹትን እውነት ያስተባብለዋል፤ በተጨማሪም ለታሪክ ባለሙያው መንገር ካልሆነብኝ የሠርጸ ድንግልን ዜና መዋዕል ቢያነበው ከወራሪ መከላከል እንደሚችሉ ሊገነዘብ ይችላል፡፡
ሶስተኛ፣ ..የሞራል ሉዓላዊነት.. በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ አልገባኝም፤ አላግባብ ተሰካክቶ የተደነቀረ ነገር ነው፡፡
አራተኛ፣ ለኢጣልያ ገብረው የጠላት ወታደር በመሆን ወገናቸውን የወጉት ኤርትራውያን እጅና እግር መቆረጡ በአሁኑ ጊዜ ላለነው የሚዘገንን ነው፤ ነገር ግን ፕ/ር ገብሩ በዓድዋ ጦርነት በምኒሊክ አገዛዝ የተደረገውን ሲናገር በቅርቡ በማይጨው የደጃዝማች ኃ/ስላሴ ጉግሳን ሆነ በሌላ የተፈፀመን ቅጣት አለማንሳቱ፤ በአገራችንም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን አልሰማም ይሆን? የአጼ ዮሐንስንስ አልሰማም ይሆን? ወይስ እኔ እንዳነሳለት ፈልጎ ይሆን? አንዳንድ ነገሮችን እየነቀሱ በማውጣት ታሪክ እንደማይጻፍ ለፕ/ር ገብሩ መንገር አያስፈልግም፤ የምኒልክን ሀጢአት ለማበራከት ከሆነ ከሸዋ ሳይወጣ በጧፍ ያነደዱትን ሊጨምርበት ይችላል፡፡
አሁን ከባድ ወደሚመስሉኝ ነጥቦች ልምጣ፤ ለእኔ እንደሚገባኝ ታሪክ ሁነትን በመግለጽ ይጀምራል፤ በትክክል ለተመዘገበው ሁነት ፍቺ መስጠት፣ ወይም ጥሩና መጥፎነቱን በመግለጽ ፍርድ መስጠት በኋላ የሚመጣ ነው፤ በሌላ አነጋገር ፍርድ ሁነትን ተከትሎ ይመጣል እንጂ የሁነቱ ፍቺ ወይም በሁነቱ ላይ የሚሰጠው ፍርድ አይቀድምም፤ ይህ ከሆነ ፈረንጆች እንደሚሉት ፈረሱን በጋሪው ለመጎተት እንደመሞከር ይሆናል፤ አጉል ድካም ነው፤ አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ለሁለት ጊዜ ገብሩ ለማድረግ የሚፈልገው ይህንን ነው፤ ምን እንደተናገርሁ ለአንባቢው ሳይነግር፣ በራሱ ግምት የተናገርሁ ለመሰለው ነገር ፍቺና ፍርዱን መስጠት ይጀምራል፤ ይህ የእውቀትና የእውነት ፈላጊ ምሁር የአጻጻፍ ስርዓት አይደለም፤ በዚህ ጉዳይ አቶ ዓሥራት እኔ ያልሁትን በትክክል ጠቅሶ ወደራሱ አስተያየት ይሻገራል፤ ይህ ተገቢ ነው፡፡
ገብሩ ግን ..ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በትግራይ ዜግነት መተካትዎ ምን ቢያስቡ ነው?.. ይለኛል፤ መጀመሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ ምን እንደተናገርሁ አይገልጽም፤ የተገነጠለውን ኤርትራን ይገድፍና ዘልሎ ትግራይን ለማስገንጠል የፈለግሁ ለማስመሰል ..ምን ቢያስቡ ነው?.. ይለኛል.. ኤርትራን የጨመረ እንደሆነ ተንኮሉ ይበላሻል.. ለኢትዮጵያውያን ነግሮ ሊያስወነጅለኝ ፈልጎ ነው? ወይስ ለአስገንጣዮቹ ነግሮ ሊያስሸልመኝ.. ለተገንጣዮቹና ለአስገንጣዮቹ በስሜት ማንኛችን እንቀርባለን?
ከላይ እንደጠቀስሁት በሂሳብ ወይም በፍልስፍና ንባብ ቢደገፍ እዚህ ስህተት ላይ አይወድቅም ነበር፤ ..ምን አስበህ ነው?.. የሚለው ለመወንጀልና ለማስወንጀል የተቃጣ ለማንም ግልጽ የሆነ ንጹህ ተንኮል ነው፤ ከኢትዮጵያ ዜግነት የተለየ የትግራይ ዜግነት መኖሩን ሊነግረኝ ያሰበ ይመስላል፤ እንዲህ ያለ መያዣና መጨበጫ የሌለው ነገር እኔ አልተናገርሁም፤ በ1998 ጓደኞቼና እኔ ከተከሰስንበት አንዱ የትግሬን ዘር ለማጥፋት መሞከር የሚል ለጆሮም የሚቀፍ ነገር ነበር፤ በ1998 ፍርድ ቤት በቀረብንበት ጊዜ የዛሬው የገብሩ ጽሑፍ ቢገኝ ትልቅ ማስረጃ ሆኖ ይቀርብ ነበር፤ እግዚአብሔር ሲያወጣን ገብሩ በዚያን ጊዜ ከእኛ ጣጣ ተከልሎ በአሜሪካው ነበር፤ ዛሬም 1998 እየሸተተ ነውና ገብሩ ስራ አያጣም፡፡
አንድ የታሪክ ባለሙያ ፕ/ር ትናንት በጋዜጣ የተጻፈውን በትክክል መድገም ሲሳነው ከአስር፣ ከሃምሳ፣ ከመቶ ወይም ከዚያ በላይ የቆዩ ጉዳዮችን እንዴት አስታውሶ እውነቱን ሊናገር ነው? እኔ የጻፍሁትን እሱ በመሰለው ተርጉሞ ከአገርና ከዘመድ ጋር የሚያጣላ ከባድ ነገር ሲለጥፍብኝ በጣም ያሳዝናል፤ መቼም ኢትዮጵያ ሆነና ነው እንጂ በሌላ አገር ቢሆን የጋዜጣው አዘጋጅ ያልተባለ ነገር ተቀብሎ አያሳትመውም ነበር፤ ከዚያም በላይ ገብሩና እኔ ስለምንተዋወቅ እሱ የጻፈውን ሌላ ሰው ቢጽፈው ገብሩ ይቃወማል ብዬ ሙሉ እምነት ነበረኝ፤ እንዲህ ዓይነት ጭራሽ ትርጉም የሌለው ነገር እኔ አልወጣኝም፤ ከኢትዮጵያ የተለየ የትግራይ ዜግነት የሚባል ነገር መኖሩንም አላውቅም፤ ዜግነት ምን እንደሆነና ከጎሳዊነት የተለየ መሆኑን አውቃለሁ፤ ዜግነትን በጎሰኛነት የሚተኩት እነማን እንደሆኑ ገብሩ አላወቀም ማለት ነው፤ ወይም አምስት መቶ ዶላር ኪራይ የሚከፈልበት ጊዜያዊ ዜግነት ከሌለው በቀር ወደ ቀበሌ መታወቂያ ለማውጣት ሲሄድ ያስረዱታል፤ እኔ ግን ዜግነትንና ጎሰኛነትን አላነካካቸውም፤ ዜግነቴንም እንዲያው በዋዛ አላየውም፡፡
* ..የኤርትራና የትግራይ ዜጎች.. ያልኋቸው ኢትዮጵያውያን ካልሆኑና የዜግነት ግዴታ ከሌለባቸው ኃላፊነቱን ከየት አምጥቼ ጫንሁባቸው?
* ገብሩስ የኢትዮጵያ ዜግነታቸውን ተገፈፉ ብሎ ወደቁጣና ወደመከፋት ያመራው ዜግነታቸውን ከዜግነታቸው ግዴታ እንዴት ለይቶ ነው?
የዜግነት መብትና ግዴታ በእያንዳንዱ ግለሰብ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው፤ ዘርን ወይም ጎሳን ከዜግነት ጋር ማገናኘት ግልጽ ስህተት ነው፤ በ1969 ሶማልያ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ አንድ የትግራይ ዜጋ በራሱ ፈቃድና ወጪ አዲስ አበባ መጥቶ ለመዝመት መወሰኑን በቴሌቪዥን አይተናል፤ የኢትዮጵያ ዜጋ ስላላልሁት በተግባር የገለጠውን የዜግነት ግዴታ ይፍቀዋል የሚል የጎሳ ህመም የያዘው ብቻ ነው፡፡
እጅግ የሚያስደንቀውና ከገብሩ በጭራሽ የማልጠብቀው የቼኮዝላቫኪያውን ጸሐፊ የሀበሻ ጀብዱ የሚለውን መጽሐፍ ገና ሳያነብበው መጥላቱ ነው፤ እኔ ሰውዬውን ጎበዝ በማለቴም የተበሳጨ ይመስላል፡፡
..የትግሬ ሽፍቶች.. በሚለውም ጥቅስ ተበሳጭቷል፤ የእሱ መበሳጨት አንሶ ሌሎችን ለመቆስቆስ ..በዚህ አባባልዎ ብዙዎች ዜጎችን ሳያስከፉ እንዳልቀሩ ሳልጠቅስ ለማለፍ አልፈልግም.. ይላል፤ ብዙ ሰዎችን የሚያስከፋው አባባሌ ምን እንደሆነ የታሪክ ፕ/ሩ አልተናገረም፤ የእኔን ጽሑፍ ያላነበበ ሰው አንድ መጥፎ ነገር የተናገርሁ ይመስለዋል፤ እኔ ያልሁት ስላልተጠቀሰ አንባቢው የራሱን ፍርድ ለመስጠት እንዳይችልና የገብሩን ፍርድ ብቻ ተቀብሎ መስመር እንዲይዝ ይጋብዘዋል፤ ከገብሩ እኔ የምጠብቀው አንደኛ ምንም ያህል ቢያስከፋ እውነትን ለመቀበል ዝግጁ መሆንን ነበር፤ ሁለተኛ ፀሐፊው የጠቀሳቸውን የትግሬ ሽፍቶች ለትግራይ ህዝብ በሙሉ ማልበስ አጉል ጎሰኛ አስተሳሰብ ነው፤ ትዕግስትና ፍላጐት አድሮበት መጽሐፉን ቢያነብበው የራስ ስዩምም ጦር ከራስ ካሣ ጦር ጋር ተሰልፎ ሲዋጋ እንደነበረ መረዳት ይችል ነበር፤ በህገ ኀልዮት (ሎጂክ) ለጥቂቶች የተነገረውን ለጠቅላላው ማልበስ ልዩ ስም ያለው የአስተሳሰብ ጉድለት ነው፤ ነገር ግን ፕ/ር ገብሩ በዚህ በህገ ኀልዮት ስሀተቱ እኔን ለማቄል ..በሽፍቶች አሳበው መላውን ትግሬ ለመፈረጅ ነው የሚል እሳቤ የለኝም ይላል፤.. እንኳን ይቺንና የዝንብ ጠንጋራ እናውቃለን ሲባል አልሰማም መሰለኝ..
በፍትህ ጋዜጣ ከአቶ ስብሓት ነጋ ጋር የተጀመረው ክርክር በአንድ ጉዳይ ላይ ነበር፤ ከዚያ ክርክሩ እየወረደ የጎሳ ሽታ ይዞ መጣ፤ የኔ የመጨረሻ ጥረት ይህንን የጎሳ ሽታ ለማስወጣት ነበር፤ ሐጎስ እርገጤ ሌባ ነው ሲል በላቸው የሚናደድ ከሆነ፣ እርገጤ ሐጎስ ሌባ ነው ሲል ጥዑም የሚናደድ ከሆነ እንደሰዎች ለመነጋገር የምንችልበት ጊዜ አልደረሰም ማለት ነው፤ በግላችንም ሆነ በህዝብነታችን የሚያዳክመን አጉል መሸፋፈንና ድብብቆሽ ነው፤ እውነቱን ለማወቅና እውነቱን ለመናገር ድፍረቱን ከአገኘን ሳንጎዳዳ እንደልብ ለመነጋገር እንችላለን፤ ለጋዜጦቹም ሆነ ለአንባቢዎች አንድ ለመግባቢያ የሚረዳን ሀሳብ ላቅርብ፤ INTERNET ውስጥ ገብተን LOGICAL FALLACY ብለን ብንጠይቀው በምንነጋገርበትም ጊዜ ሆነ በምንጽፍበት ጊዜ ሊረዳን የሚችል ትምህርት የምናገኝ ይመስለኛል፤ በገለባ እየለወጥን የምናውቀውንም የማናውቀውንም እያደባለቅን ብንነታረክ ዋጋ የለውም፤ ከዚያም በላይ እያንዳንዳችን ተምረናል፤ አውቀናል፤ ብለን በውስጣችን ያለውን መርዝ ከምንነዛው በውስጣችን ይዘነው እኛኑ እንዳደረገ ያድርገን፡፡

Feteh.

%d bloggers like this: