Tag Archives: seifu fantahun

“አንገት ከሚሰበር፤ ባይበላስ ቢቀር!” መቲ ሸዋዬ ይልማ

14 Aug

You can also have the PDF format:

https://jontambek.wordpress.com/wp-content/uploads/2011/08/doc991.pdf

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሳያት ደምሴ አሜሪካ ላይ በነበራት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ መዝፈን ሲገባት እሷ ግን እየዘፈነች በማስመሰል ማይም ስታደርግ ታዳሚው እንዳወቀባትና ተቃውሞ እንዳቀረበ እሷም እንዳለቀሰች ባልደረባችን ሰይፉ ፋንታሁን ከአሜሪካ በስልክ ከዘገበ በኋላ በጉዳዩ ላይ ከተወልደ በየነ (ተቦርነ) ጋር ቀልደውበታል፡፡ ምንም እንኳን መረጃው እውነት እንደሆነ ቢታወቅም ከልጅቷ ቤተሰቦች ቅሬታ በመቅረቡ ይቅርታ እንድንጠይቅ በቃልም በፅሁፍም ከሸገር ሀላፊዎች ጥያቄ ቀርቦልናል፡፡ እንዲያውም የይቅርታው ቃል በእጅ ተፅፎ እንድናነበው በጣቢያው የፕሮግራም ሀላፊ በአቶ ተፈሪ አለሙ ተሰጥቶናል፡፡

አንብቡ ተብሎ የተሰጠን የይቅርታ ፅሁፍ ይኸውና፡

“ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና ሰኞ ዕለት ባስተላለፍነው ፕሮግራም አሜሪካ ስለቀረበ ኮንሰርት አንስተን ሳያት ደምሴ ስላጋጠማት ጉዳይ ተጨዋውተን ነበር፡፡ የችግሩ መንስኤ ማንም ይሁን ማንም ተፈጥሮ የነበረው ነገር ሁሉ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ወሬ ስናቀርብ ለማዋዛት ብለን ቀልድ ቢጤ በመጨመር ዘፈንም ጋብዘን ነበር፡፡ እኛ ይህን ያደረግነው በቅን ልቦና ቢሆንም በሳያት ደምሴና በቤተሰቦቿ ላይ ቅሬታ ሊፈጥር ችሏል፡፡

እኛ እንኳን በሞዴልነቷና በተዋናይነቷ የምናከብራትን ሳያት ደምሴ ይቅርና ማንም ሰው ቢሆን ቅር እንዲሰኝብንም እንዲያዝንብንም አንፈልግም፡፡ ሳያት ደምሴን አግኝተን እስክናነጋግራት ድረስ ለተፈጠረው ሁሉ ሳያት ደምሴንም ሆነ ቤተሰቦቿን ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ የሳያት ደምሴ ዜማ ይቀጥላል፡፡”

እዚህ ፅሁፍ ላይ እንካችሁ አንብቡ ተብሎ ከመሰጠቱ በተጨማሪ አንድ ችግር ይታየኛል፤ ያሰመርኩባቸውን ቃላት ይመለከታል፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው ቅር እንዳይሰኝብንና እንዳያዝንብን የሆነ ሙያ ባለቤት መሆን አለበት? ሰው በመሆኑ ብቻ የሚያገኘው ክብርስ? እንኳን እሷን ይቅርና ማንም ሰው ቢሆን ተብሎ መለየቱ ጣቢያው በሰዎች መካከል የሆነ ክፍፍል አለው አያስብልም? በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በሸገር ሬዲዮ ላይ የሚበላለጡበት የሰውነት መስፈርት አላቸው ማለት ይሆን? ሌላ ሰው ላይ ይህ ነገር ደርሶ ቢሆን ኖሮ ግን ይህንን ያህል ትኩረት አይሰጠውም ነበር ማለት ነው? ለመሆኑ የሷና የሌላው “ማንም ሰው” የሚባለው ጎራ ልዩነት ምንድነው? እንደው ከየትኛው ጎራ እንደሆንን እንድናውቀው ያህል ቢነገረን…

እኛም በጊዜው የነበርነው የታዲያስ አዲስ አዘጋጆች መቲ ሸዋዬ ይልማ፤ ዳዊትና ተስፋዬና ተቦርነ መልሳችንንና አቋማችንን በቃልና በፅሁፍ ገልፀናል፡፡ ለሸገር ሬድዮ ጣቢያ ሀምሌ 16 ቀን 2003 ዓ.ም. የላክነው ደብዳቤ ቅንጫቢ እነሆ፡

“…ይቅርታ እንድንል የተሰጠን ተጽፎ ነው፡፡ ይህ ከምንም በላይ የማንቀበለውና ያዘንንበት አካሄድ ነው፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ሀላፊነት የሚሰማን ማመዛዘንና ማሰብ የምንችል ሆነን ሳለን ይህንን አንብቡ ተብሎ መሰጠቱ ቅሬታ ፈጥሮብናል፡፡

…ለፕሮግራሙ ከፍተኛ የአድማጮች ቁጥር ያስገኘለትና ተወዳጅ ያደረገው አንዱ መገለጫው የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ከመዝናኛ ጋር የተያያዙ ወሬዎች ከቀረቡ በኋላ በጉዳዮ ዙሪያ መቀለድ ነው፡፡ ይህም ከሁለት አመት ተኩል በላይ በሸገር የሬድዮ ጣቢያ በሁሉም የስነጥበብ ዘርፍ ባለሙያዎች ዙሪያ ፕሮግራማችንን የምናቀርብበት አንዱ ገጽታ ሆኖ ቆይቷል፡፡የሳያትን ጉዳይ ከከዚህ ቀደሞቹ የሚለይበት አንድም ነገር ባይኖርም ለሷ ይቅርታ እንድንጠይቅ መባሉ እንግዳ ሆኖብናል፡፡

…በመጨረሻ ልናስታውሰው የምንሻው ስለሀገር ውስጥ ጉዳዮች ፕሮግራሞች መስራት እንፈልጋለን፤የአቅማችንን ያህልም እንሞክራለን፡፡ ጥሩ የተሰራ አስደሳችና አርኪ ስራ ስናይ የምናሞግሰውና በርቱ የምንለውን ያህል ትክክል ያልሆነ ድርጊት ሲፈጸም (የሳያት የአሜሪካ ድረጊት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆን እያስታወስን) እንዲሁም ደረጃውን ያልጠበቀ ስራ ካጋጠመን እንናገራለን እንተቻለን፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚወድሱበትና የሚደሰቱበት ካልሆነ እውነተኛ መረጃ እንኳን ቢሆን ባለጉዳዮቹና የሚቀርቡዋቸው ሰዎች ይቀየማሉ፤ ይቅርታ እንድንጠይቃቸውም ይፈልጋሉ፡፡ እውነቱ እኛ ጋር እንኳን ቢሆንም ይቅርታ በሉኝ ባይ በመጣ ቁጥር መሸማቀቅ፤ ጊዜና ጉልበታችንን ማባከን፤ እንዲሁም መወቀስ ስለማንፈልግ ሳንወድ የሀገር ውስጥ ወሬዎቻችንን ቁጥር ለመቀነስ ተገደናል፡፡ ይህ ፕሮግራሙንም ሆነ የአየር ሰአቱን የሰጠውን ጣቢያ እንደሚጎዳው እሙን ነው፡፡”

የታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ከሁለት አመት በላይ በሳምንት ለ5 ቀናት (ለ11 ሰአታት)በቀጥታ የሚተላለፍ ፕሮግራም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቅዳሜ ምሽት አድማጮች እየደወሉ በቀጥታ በስልክ መስመር እናወራለን፡፡ በቀጥታ የሚተላለፍ ፕሮግራም ላይ ማንኛውም አይነት ስህተት ቢከሰት ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ይህንን ትልቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን ሀላፊነታችንን መቼም ዘንግተነው አናውቅም፡፡ ከቀጥታ ፕሮግራማችን በተጨማሪ በራሳችን ስቱዲዮ ቀርፀን የምናስተላልፋቸው ፕሮግራሞችም አሉን፡፡ በአካል አግኝተን መጠየቅ የማንችል ሲሆን ደግሞ በስልክ ቃለምልልስ አድርገን እናስተላልፈዋለን፡፡ ልክ ሰይፉ ከሀገር ውጪ ሆኖ ወሬዎችን ሲነግረን እንደምናደርገው፡፡ ሆኖም ግን ከሰሞኑ በተፈጠረው ሁኔታ ሳቢያ በአቶ ተፈሪ አለሙ ሀምሌ 15 ቀን 2003 ዓ.ም. ተፈርሞ የደረሰን ደብዳቤ ግን እስከዛሬ የነበረንን ሀላፊነት ሳያምኑበት ነበር የሰጡን እንዴ ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል፡፡

“… ምንም አይነት በስልክ የሚመጡ ዘገባዎች በጣቢያው ኃላፊዎች ይሁንታን ሳያገኙ እንዳይተላለፉ እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ቢገኝ ግን ጣቢያው ፕሮግራሙን ሙሉ ለሙሉ ለማገድ የሚገደድ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡”

ሳንሱር የቀረ ነበር እኮ የሚመስለን፡፡ ለካ አንዳንድ ቦታዎች አሁንም አለ፤ ያውም ያለ ሳይመስል፡፡

የታዲያስ አዲስን አቋም ግልፅ ካደረግን በኋላ የሸገር ሀላፊዎች በራሳቸው ይቅርታውን ሊያቀርቡ በመወሰናቸው ለኛ ተሰጥቶን አናነብም ያልነው ፅሁፍ በአቶ አበበ ባልቻ ተነቦ በታዲያስ አዲስ የአንድ ሳምንት ፕሮግራም ላይ ለ5 ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ እንዲተላለፍና ከእያንዳንዱ ይቅርታ በመቀጠል የሳያት ዘፈን አብሮ እንዲሰማ ተወሰነ፡፡ በዚህ ውሳኔ የተነሳ በሌላ መሰረታዊ መርህ ላይ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ እነሱ ላልጠፋ ጥፋት ይቅርታ ማለት ከፈለጉ ይበሉ ብለን እሺ አልን፡፡ የሷ ዘፈን እንዲተላለፍ የተሰጠንን ውሳኔ ግን በጭራሽ እንደማንቀበለው በቁርጠኝነት ተናገርን፡፡ የማንቀበልበት ሁለት ምክንያቶች አሉን፡፡

የመጀመሪያው የሙያ ክልልና ነፃነት (Professional Space and Freedom) ማክበርን ይመለከታል፡፡ ከሸገር ጋር ያለን መግባባትና የሙያው ስነምግባር የሚፈቅደው ፕሮግራሙን በሙሉ መብትና ሀላፊነት የምንሰራበት እንደሆነ፤ ከማንኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነን በፕሮግራሙ ውስጥ የሚካተተውን ይዘት ሙዚቃ ጨምሮ የምንወስነው እኛ አዘጋጆቹ ብቻ እንደሆንን ነው፡፡ ከአቶ አበበ ባልቻ ይቅርታ በኋላ የሳያትን ዘፈን ማሰማት አለባችሁ የሚለው ትዕዛዝ ግን ይህንን ሙያዊ ክልላችንን የሚጥስና ነፃነታችንን የሚጋፋ በመሆኑ ተቃውመናል፡፡ ዛሬ የሚፈልጉትን ሙዚቃ አሰሙ ሲሉን እሺ ካልን ነገ ይህንን አውሩ ሲሉን በምን አፋችን አይሆንም እንላለን? የዛሬው ግፊያ ነገ የት ላይ ሊጥለን እንደሚችል ስናስበው ፀንተን መቆሙ አማራጭ የሌለው ውሳኔ በመሆኑ በእምቢታችን ገፋንበት፡፡ በመካከላችን የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብና ፕሮግራሙ እንዳይቋረጥ በነሱ አፍ የተነበበውን ይቅርታ በፕሮግራማችን እንዲቀርብ የዘፈኑን ጉዳይ ግን በጭራሽ እንደማንስማማበት ሰኞ ሀምሌ 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ተነጋገርን፡፡ በማግስቱ ማክሰኞ ለመደበኛው ስራችን በእለቱ የነበርነው አዘጋጆች እኔና ዳዊት ስቱዲዮ ስንገኝ ግን ከተስማማንበት ውጪ ዘፈኑም አብሮ እንደሚተላለፍ ትዕዛዝ እንደተሰጠ ተነገረን፡፡ ለአቶ ተፈሪን ደውዬ ዘፈኗ እንዲተላለፍ በጭራሽ እንደማንፈቅድ በቁርጠኝነት ተናገርኩ፡፡

ሁለተኛው የሳያት ሙዚቃ በታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ላይ እንዳይተላለፍ የወሰንንበት ምክንያት የሙዚቃውን ደረጃ ይመለከታል፡፡ በታዲያስ አዲስ ላይ የሚቀርቡት ሙዚቃዎች በተወሰነ ደረጃ ጆሮ-ገብ መሆን ይኖርባቸዋል ብለን አዘጋጆቹ እናምናለን፡፡ አድማጮቻችን እኛን ለማድመጥ የሚሰጡንን ጊዜ አክብረን በግጥም፤ በዜማ፤ በቅንብርና በአዘፋፈን ቢያንስ ከነዚህ በአንዱ እንኳን ደረጃውን የጠበቀ ስራ መርጠን ለማቅረብ እንጥራለን፡፡ ስለዚህም የሳያት ዘፈኖች ለአቅመ-አድማጭ ጆሮ አይመጥኑም ብለን ትተናቸዋል፡፡ እኛ ለመስማት ጀምረን ለመጨረስ ያቃተንን ዘፈኖች እንዴት ብለን ነው ለአድማጮቻችን እንካችሁ የምንለው?

በመሆኑም በታዲያስ አዲስ ላይ ከኛ ከአዘጋጆቹ መልካም ይሁንታና ፍቃድ ውጪ ፕሮግራምም ሆነ ሙዚቃ እንዳስተላለፍ ትእዛዝ ሲሰጠኝ ለመቀበል የኢትዮጵያዊነት ክብሬ፤ የግል አመለካከቴም ሆነ የሙያ ስነምግባሬ ስለማይፈቅድልኝ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ከስቱዲዮ ለመውጣት ወስኛለሁ፡፡

ሰይፉ መጥቶ ከሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ሀላፊዎች ጋር እስኪነጋገር ድረስም ፕሮግራሙ ሊቋረጥ ግድ ሆነ፡፡ የሰይፉን መምጣት ተከትሎም ከዚህ በፊት በተወሰኑት የጣቢያው ሀላፊዎች ላይ ያየነውና የታዲያስ አዲስ አዘጋጆች በብርቱ የታገልነው የከፋፍለህ ግዛ አካሄድ ይፋ ወጣ፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜያት በአካልም ሆነ በስልክ የተወሰኑት የሸገር ሀላፊዎች በተናጠል የታዲያስ አዲስ አዘጋጆችን ያነጋግሩን ነበር፡፡ ዝርዝሩን ልተወውና የሚነግሩን በአብዛኛው ስለኛ (ስለተደወለልን) ግለሰቦች ጥሩ ስለሌሎቹ አዘጋጆች ግን ጥሩ ያልሆነ ነገር ነበር፡፡ ይህንን አንድን ቡድን ለማፍረስ የሚደረግ የከፋፍለህ ግዛ አካሄድ ከዚህ በፊት ሌሎች ሲያደረጉት አንብበናል፤ ሰምተናል፤ አይተናል፡፡ ስለዚህም በተናጠል ስለሰይፉ፤ ስለተቦርነ፤ ስለዳዊትና ስለእኔ ለሌላችን የሚነገረንን እኛ በአንድ ላይ እየተነጋገርን በቀጣይነት ምን ማድረግ እንዳለብን እየተመካከርን አንድነታችንና ጓደኝነታችን እንዳይበታተን መበርታት ጀመርን፡፡ ከሰይፉም ጋር በስልክ እየተነጋገርን በአቋማችን ገፋንበት፡፡ ሰይፉ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላም ከሬድዮ ጣቢያው ጋር መስማማት ላይ ደርሰን ወደስራችን ልንመለስ የምንችለው ከዚህ በፊት የተፈጠሩትን አይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ቅሬታችንን ፍቀን፤ የአሰራር ደንብና አካሄድ ላይ ተነጋግረን ከተግባባን በኋላ ብቻ መሆን እንዳለበት አራታችንም የታዲያስ አዲስ አዘጋጆች ተስማማን፡፡ ብዙም አልዘለቀም እንጂ፡፡

የሸገር ሀላፊዎች በመገናኛ ብዙሀን እንደገለፁትም ጉዳዩ እልባት የሚያገኘው ሰይፉ ከመጣ በኋላ በመሆኑ እሱ ሲመጣ ለብቻው አነጋገሩት፡፡ እንደለመዱትም ትእዛዝ ሰጡት፡፡ እሱም ተቀበላቸው፡፡ ከውሳኔዎቹ መካከል ሰይፉ ስለተፈጠረው ሁኔታ ሳይናገር ውሾን ያነሳ ውሾ ብሎ ምንም እንዳልተፈጠረ ፕሮግራሙን እንዲቀጥል፤ ተቦርነ ስራውን መቀጠል እንደሚችል (በነገራችን ላይ ለኔና ለሰይፉ ከሀላፊዎቹ በአንዱ በግል ከተነገሩን ጉዳዮች መሀል አንዱ የዚህ ችግር ዋነኛ አባባሽና በጣቢያው ላይ ለሚነሱት ሌሎች ብዙ ቅሬታዎች ዋና መንስኤ ተቦርነ በመሆኑ አግዱት የሚል ነበር)፤ ታዲያስ አዲስ ስቱዲዮ ረግጦ እንዲወጣና ስራ እንዲያቆም ያደረገው ዳዊት በመሆኑ እሱ በጭራሽ እንዳይገባ (ውሳኔው የኔ መሆኑን እነሱም ያውቃሉ እኔም ተናግሬያለሁ)፤ እኔ ደግሞ ለአንድ ወር ከስራ እንድታገድ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ከዳዊት ጋር ከዚህ ቀደም የሚያገናኛቸው ሌላ ቁርሾ ከሌላቸው በስተቀር በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ዳዊት ብቻውን ያደረገው የተለየ ነገር እንደሌለ የሁላችንም ልብ ያውቀዋል፡፡ ታዲያ እሱን ለብቻው ማገድ ምን አመጣው? የከፋፍለህ ግዛ አካሄዳቸው አንዱ መገለጫ ካልሆነ በስተቀር፡፡

እኛስ ብንሆን አንዱ የስራ ባልደረባችን ታግዶ ሌሎቻችን ብንሰራ ምን አይነት ሰው ያደርገናል? ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ተሸነፍን እነሱ እንደፈለጉት ተከፋፍለን ተገዛን ማለት አይደል? ስንሰራም ሆነ ስንታገል የነበረው በአንድነት ነው፡፡ ካገዱን አንድ ላይ ካስገቡንም አንድ ላይ መሆን እንዳለበት ተነጋግረን ነበር፡፡ እኔ አሁንም በባለሙያዎች አንድነትና የትግል አጋርነት (Professional Solidarity) አምናለሁ፡፡ ከውስጣችን አንዳችንን ሲያጎድሉን የተረፍነው መደሰት የለብንም ምክንያቱም ድክመታችንን ስላሳየናቸው አወቅኩሽ ናቅኩሽ ይመጣል፡፡ ቀስ በቀስ ይሸረሽሩናል፡፡ በዚህና በቀደምት ጉዳዮች የታዘብነው አመለካከታቸውንና ማንነታቸውን በመሆኑ ነገም ተመሳሳይ መርህ መጣስና መብት መጋፋታቸውን እንደሚቀጥሉ ጥርጥር የለኝም፡፡ ዛሬ ለባልደረባችን ካልወገንን ነገስ ለኛ ማን ይወግንልናል?

በነገራችን ላይ ፌስ ቡክ ገፄ ላይ አንድ ፅሁፍ አስቀምጬ ነበር፡፡ ይህንን ፅሁፌን የሸገር ሬድዮ ጣቢያ ሀላፊዎች የኔ ፌስ ቡክ ላይ አይተውት ነበርና ለአንድ ወር እንድቀጣ ከወሰኑበት ምክንያቶች አንዱ እሱ ነው አሉ፡፡ ታዲያ ስለነዚህ ሰዎች መርህ የመጣስና መብት የመጋፋት አባዜ መናገሬ ተሳሳትኩ? ይኸው አንድ ሚድያ ሊያከብረውና ሽንጡን ገትሮ ሊከራከርለት የሚገባውን መሰረታዊ መብት ሊጋፉኝ እየሞከሩ እኮ ነው፤ ሀሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴን… ያውም በገዛ ፌስ ቡኬ ላይ፡፡

የኔ ውሳኔ ስራቸውን ከቀጠሉት ባልደረቦቼ ከሰይፉና ከተቦርነ የተለየ ነው፡፡ ባንዘልቅበትም ጀምረነው የነበረውን አንድነትና ለእምነቴ መቆምን እገፋበታለሁ፡፡ ከመካከላችን አንዱን እንኳን ሊነጥሉ ቢሞክሩ አብሬ ታግዬ በሬዲዮ ጣቢያቸው ሊያፍኑት የሞከሩትን ድምፃችንን ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ አሰማለሁ እንጂ አቋሜን ቀይሬ፤ ቃሌን በልቼ፤ ባልደረባዬን አጋፍጬ ዞር አልልም፡፡ ጥፋቱን አጥፍታችኋል የተባሉት ሁለቱ ወደስራቸው እንዲመለሱ ተደርጎ የለም አላጠፉም ብለው ሲከራከሩላቸው የነበሩት ጓደኞቻቸው መታገድ ካልገረማቸው ይገርመኛል፡፡ “ገንፎ እፍ እፍ ቢሉሽ ሊውጡሽ” አሉ፡፡ ከምንም በላይ ግን ውሳኔያች እድሜ ልካችንን አንገታችንን ቀና አድርጎ የሚያኖረን ሊሆን ይገባል እንጂ የሚያሸማቅቀን መሆን የለበትም፡፡ “አንገት ከሚሰበር፤ ባይበላስ ቢቀር” ብሎ የለ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፡፡

PDF file can be found here under:

https://jontambek.wordpress.com/wp-content/uploads/2011/08/doc991.pdf