ከዚህም ፤ ከዚያ፤

12 Mar

For Amharic PDF: Click here

ምንድነው፤ ከዚህም ከዚያ አትሉኝም??? አንዱን ሳነሳ አንዱን ስጥል፤፤ ስለ ማሞ ውድነህ ፤ ብዬ የጀመርኩት ነገር አገራዊ ይዘት ቢይዝብኝ ፤ ሰፋ አድርጌ ፤ ከዚህም ከዚያ አደረኩት፤፤
ማሞን ሳስብ በህሊናዬ ቀድሞ የሚመጣው የኤርትራ ጉዳይ ነው፤፤ የኤርትራ ጉዳይ፤ ሲታሰብ ደግሞ፤ ፊት ለፊት ድቅን የሚሉት ጥቂት መፃህፍት ናቸው፤፤ ስለ ኤርትራ ጉዳይ በቀዳሚነት የማሞ ውድነህ መፅሃፍን የሚቀድም መፅሀፍ ያለ አይመስለኝም ፤ ሌሎቹ ደግሞ፤ የበአሉ ግርማ፤ ኦሮማይ እና ፤ የ ዘውዴ ረታ፤የኤርትራ ጉዳይ፤ መፅህፍት ጥቂቶቹ ናቸው፤፤ የዘውዴ ረታ አባት ፤የንግስት ዘውዲቱ ባለሟልና ፀሀፊ የነበሩ በመሆናቸው ጭምር የግብአት /RESOUCE/ ችግር አይታይባቸውም ፡፡
የማሞ ውድነህን፤ የኤርትራ ጉዳይ፤ መፅሀፍ ለየት የሚያደርገው፤ ለረጅም ዓመታት ፤ በ1960ዎቹ በኤርትራ (የቀድሞ የኢትዮጲያ ክፍለ-ሃገር) የመንግስት ፕሬስ ክፍል ሃላፊ ሆነው በሰሩባቸው አመታት፤ በኤርትራ ጉዳይ ላይ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ከፍተኛ ሰዎች (ጃንሆይን ጭምር)፤ ከበዓሉ ግርማ፤ኦሮማይ ይልቅ ፤አብሮ ሰርቶና በግንባር አግኝቶ መወያየት መቻላቸው ይመስለኛል፤፤ ለንፅፅር ያህል ከወሰድነው፤ በዓሉ ግርማ፤ እንደ ቀይ ኮከብ ዘመቻ፤ የቡድን አባል ሆኖ ያዘጋጀው ኦሮማይ፤ የፍቅር ትእይንት (፤አባቴ ይሙት ደደብ ነህ፤) ፤ ከመግባቱ በቀር፤ ከዘመቻው የስራ ሪፖርት ላይ መቀዳቱን፤ ለምን በዓሉን ገደላችሁት ሲባሉ ደርጎች የሚሰጡት ማስተባበያ እንደሆነ ቀጥሏል ፤፤ ይመስለኛል; ኮረኔል መንግስቱም፤ በትግላችን ውስጥ፤ የቀይ ኮከብ ዘመቻን ያላካተቱት፤ አንድም ቀድሞ የተቀዳ ስራ መሆኑን በመገንዘብ ላለመድገም ወይንም በቅፅ 2 አዘናግተውን ሊመለሱበት ፈልገውም ይሆናል፤፤ እንዲያው ለጨዋታችን አነሳነው እንጂ እሳቸውማ(ኮረኔል) ምን ያልደገሙት(ያልቀዱት) ነገር አለና፤፤ የአክሱማውያን ስልጣኔ፤ ፤ የኢማም መሃመድ ግራኝ ወረራ እና፤ ከዛጉዌ ስርወ መንግስት በኋላ የመጡ ስርወ መንግስታት የጠበቃቸው ስራና ፈተና፤ወዘተ፤ ወዘተ…. መንግስቱ ከ 17 ዓመት በኋላ እረፍት ሲያገኙ ያነበቧቸው ይሆኑ እንዴ…ሲል አንዱ፤ በሆነ ጋዜጣ ላይ አስተያየቱን ፅፎ አይቻለሁ፤፤
ካነሳነው አይቀር፤ ኮረኔል፤ እራሳቸውን፤ እንደጃንሆይ ደጋግመው፤ እኛ ሲሉ አስተውዬ፤ አይ፤ ብቻቸውን አለመሆናቸውን ለማስገንዘብ ፈልገው ነው የሚል ግምት ይዜ ነበር፤፤ አይ….አይ …አይደለም፤፤ ብቻቸውን ፤ንግግር ሲያደርጉ በሚያሳይ ፎቶ ግርጌ ስር፤ ስለ ሶማሊያ ጦርነት መግለጫ ስንሰጥ ፤የሚሉ ሃረጎች ሳይ ፤ በፈዛዛ የሚታለፍ ጉዳይ አለመሆኑ ገብቶኛል፤፤ ሌላው ደግሞ፤ ፕሮፌሰር መስፍንን በተደጋጋሚ ፤ ዶክተር መስፍን ወልደማሪያም ይላሉ፤፤ እርግጥ ነው ፤ ፕሮፌሰር መስፍን፤ የፃፉት አይደለም፤ እግረመንገዳቸውን ያወሩት ለ PHD መመረቂያ Thesis ሊሆናቸው ይችላል፤፤ ማንስ ደፍሮ ሊያስተምራቸው?? መምህሩ(ምናባዊው መምህር) በንዴት፤ ጭቅጭቅ ነው? ትምህርት? ብሎ ጥሎዋቸው እንደሚሄድ ግን ይታየኛል፤፤
ወደ ማሞ ስንመለስ፤
ማሞን በቀረበው ጊዜ ደግሞ፤ ከአክሱም አስመላሽ ኮሚቴ ጋርም አስታውሳቸዋለሁ፤፤ ስለ አክሱም ሀውልት ደግሞ ማንሳታችን ካልቀረ፤ ኢህአዲግ የሰራው የትግል ፍሬ እየመሰለን ብዙዎቻችን፤ ድጋፍም ባንሰጥ፤ ዝምታ ላይ ማተኮራችንን አስተውያለሁ፤፤ በጣልያን ሀገር ይገኝ የነበረውን የአክሱም ሃውልት ፤ ወደ ሃገሩ መመለሱ ታሪካዊ ፋይዳው ላቅ ያለ እንደሆነ እኔም የገባኝ፤ ጆን ስፔንሰር፤ ወደ ሃገሩ አለመመለሱን፤ የኢትዮጲያዊያን ድክመት እንደሆነ ፤በጥርስ የገባች አገር / Ethiopia at Bay / መፅሃፋቸው ላይ አፅንኦት ሰጥተው መፃፋቸውን በማንበቤ ይመስለኛል፤፤ አቶ መለስ በተደገጋጋሚ ፈረንጅ አያዋጣችሁምም……. ቢሉም አንዳንዶቻችን ግን ከፈረንጅ ካልሰማን አናምንምና፤፤
ማሞ ያልረገጡት መሬት፤ ያላዩት ዳገት ፤ ያልወረዱበት ቁልቁለት የለም ማለት ይቻላል፤፤በስለላ መፅኃፍት ላይ ማተኮራቸውም፤ ምክንያታዊ እንደሆነ ማሞ ሲያስረዱ፤ /ሀገሬ ከውጭ ጥቃት እራሷን ለመከላከል፤ ሌሎች አለማት የደረሱበትን የስለላ ታሪኮች፤ እኔም የገባኝን ያህል እንድታውቅ በመፈለጌ ነው/ ይላሉ ፤፤የስለላ ገሃዳዊ ትእይንቶችንም በራሳቸው ላይ እንዳዩም ሲያሳዩን፤፤ ለምሳሌም፤ የሻቢያው፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ታዋቂ ሽፍታ ከመሆኑ በፊት ፤ ከጀብሃ፤ እና ከመንግስት ጋር እየተመላለሰ Double Agent /የሁለቱ አለም ሰላይ/ በመሆን ሲያገለግል እንደነበር በአንድ ወቅት ከማሞ አንብቤያለሁ፤፤ በተያያዘ ዘገባም ፤ ጀብሃ፤ ማሞ የሚወዱትን ጥሬ ስጋ ቤት አጥንቶ የግድያ ሙከራም ቃጥቶባቸውም እንደነበረና፤ በእሳቸው ዳፋ ሌላው መግባቱን እንዲሁ ፤፤
ማሞ ፤ ሰው አይነኩም፤ ከነኳቸውም ወይም እንደሚነኳቸው ከጠረጠሩም አይለቁም፤፤ በአንድ ወቅት ፤ የትምህርት ሚኒስትራችን ፤ አጤ ኃይለስላሴ፤ ሲሆኑ ፤ ምክትላቸው እንዲሆኑ ደግሞ የፈቀዱላቸው፤ ክቡር ከበደ ሚካኤል ነበሩ አሉ፤፤ ከበደ ሚካኤል በወቅቱ አገሪቱ ከገባችበት የእውቀት አዘቅት ለማውጣት ከሚታትሩ ምሁራን መካከል አንዱ ነበሩም አሉ፤፤ ማሞ እና ከበደ ሚካኤልም አይመቻቹም ይባላልም ነበረ፤፤ ማሞ ከተመቻቸው በግልጥ ፤ በጋዜጣ ላይ ከበደ ሚካኤል፤ ከሰው ከመቅዳት ውጪ ምን አዲስ ነገር አላቸውስ ብለው ይሞግቱም ነበር፤፤ ከበደ ሚካኤል አፍልቀው መፃፍ እንደማይሆንላቸውም በመግለፅ፤፤ ማሞም በኋላው ላይ እንደ ከበደ ሚካኤል ወደ ትርጉም ስረው ላይ ጠቅለው ገቡበት እንጂ፤፤

ሰው ወደ ላይ ወጣ
መልሶም ወረደ
ቁልቁለት ሳይገታው
የሰው ልጅ ወረደ – ወረደ ነጐደ
አቀበት የወጣው
ጉልበቱ ደከመ – ሕይወቱ በረደ፡፡- ማሞ ውድነህ

ነብስ ይማር፤
Jonas Jontambek

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: