ለዲሞክራሲ እና ለመልካም አስተዳደር ገፅታ ግንባታ፤ ምርጫ ቦርድ በመድረክ የባንክ ሂሳብ ውስጥ 3,598 ብር አስቀመጠ፤፤

12 Mar

ኢሕአዴግ የሀገሪቱን ሀብት በብቸኝነት ጠቅልሎ መያዙ አልበቃ ብሎታል – መድረክ
የተመድ የልማት ፕሮግራም የሰጠውን ገንዘብ ኢሕአዴግ ወዳጅ እየገዛበት ነው – አቶ ገብሩ አሥራት


ኢሕአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲ፣ እንደ መንግሥትና እንደ ነጋዴ፤ የሀገሪቱን ሀብት በብቸኝነት ጠቅልሎ መያዙ አልበቃ ብሎት፣ በዴሞክራይታዜሽን ስም ከለጋሽ ሀገሮች ወይም ከመንግሥት ካዝና በፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ስም የሚመጣውን ገንዘብ ጠቅልሎ መውሰዱ ሳያንሰው ለአጋሮቹና ለታማኝ ተቃዋሚዎቹ በመስጠት፣ ወዳጅ እንዲገዛበት መፈቀዱ፣ ኢሕአዴግንም ሆነ ቦርዱን በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በታሪክ ፊት የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑን መድረክ ገለፀ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የስራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ አስራት፤ ቦርዱ ለአምስቱ ፓርቲዎች ስላከፋፈለው ገንዘብ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ2004 ዓ.ም፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተግባር ማከናወኛ፣ 10 ሚሊዮን ብር ማስፈቀዱንና 7.5ሚ ብር ለኢህአዴግ እንደተሰጠ ተናግረዋል፡፡ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት” በሚል ለተቋቋሙት አምስት ፓርቲዎች “ከኢሕአዴግ ድርሻ የተቆነጠረ ነው” ተብሎ፣ 1 ሚሊዮን ብር እንደተከፋፈለ ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ለዚህ የሰጠው ምክንያት ደግሞ ገንዘቡን ፓርቲዎቹ ለ2002 ዓ.ም ምርጫ ባቀረቧቸው ዕጩዎች ብዛት መሰረት ሲያከፋፍል፣ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ ዕጩዎችን ለ2002 ዓ.ም ምርጫ አቅርቦ ውጤቱን ለተቀማው የስድስት ፖለቲካ ፓርቲዎች ድርጅት ስብስብ ለሆነው መድረክ ግን ምንም ገንዘብ አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡
የአትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመድረክ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ስላስገባው 3598 ብር እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተግባር ማከናወኛ ከመንግሥት ካስፈቀደው 10 ሚሊዮን ብር ላይ በአንድ መቀመጫ አስልቶ ስላስገባለት ገንዘብ በሚመለከት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ፤ “አምና ለተመሳሳይ ተግባሮች ማከናወኛ ተብሎ ያለ ፍላጐታችን በባንክ ሂሳብ ቁጥራችን ገቢ ያደረጋችሁትን 3698.41 ብር፣ ክፍፍሉ ኢፍትሃዊና አድሎአዊ ሆኖ በማግኘታችን በመልሶ መለኪያ ተጨማሪ ወጪ አውጥተን ለቦርዱ ተመላሽ ማድረጋችን እየታወቀ፣ ለ2004 ዓ.ም በጀት ዓመትም ያችው ብር 3598.41 ያለ ፍላጐታችን በባንክ ሂሳባችን ገቢ መደረጉና ይህንንም ገንዘብ ገቢ ከተደረገልን የድጋፍ ገንዘብ፣ ከሦስት እጥፍ በላይ ወጪ አውጥተን፣ የውጭ ኦዲተር ቀጥረን፣ በኦዲተር የተረጋገጠ የፋይናንስ ሂሳብ ሪፖርት እንድናቀርብ መጠየቃችን ተገቢ አይደለም” በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ፓርቲው ያለፍላጐቱ በባንክ የሂሳብ ቁጥሩ የገባውን ገንዘብ አምና እንዳደረገው ሁሉ ለቦርዱ ተመላሽ ማድረጉን በደብዳቤ ጠቅሶ፤ ለወደፊትም ቢሆን የድጋፍ ገንዘቡ ክፍፍል አፈፃፀም ከአድሎአዊነት እስካልፀዳ ድረስ፣ ቦርዱ በመድረኩ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ማድረጉን እንዲያቆም በደብዳቤ ጠይቀውታል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ቦርዱ ያለ መድረክ ፍላጐት፣ በባንክ ሂሳብ ቁጥር፣ ገንዘቡን ገቢ ቢያደርግ፤ መድረክ ገንዘቡን ለመመለስ ወይም ደግሞ ገቢ ከተደረገው ገንዘብ እጥፍ በላይ ወጪ አውጥቶ እና ኦዲተር ሾሞ፣ የፋይናንስ አጠቃቀምን ሪፖርት ለማቅረብ የማይገደድ መሆኑን ለቦርዱ በደብዳቤ አስታውቋል፡
1 ሚሊዮን ብሩ ተከፋፍሎ የተሰጣቸው የጋራ ምክር ቤት አባላቱ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣ የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኤዴፓ) እና የኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሰዴፓ) አምና በወጣው መስፈርት መሠረት ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል የሚከፋፈል 20 በመቶ፣ በ2002 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ባቀረቡት ዕጩ ብዛት 60 በመቶና በዚሁ ምርጫ ወቅት ባቀረቡት የሴት ዕጩ 20 በመቶ ድርሻ እንዲከፋፈል በመደረጉ፣ ፓርቲዎች ተቃውመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስለ ጉዳዩ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ገብሩ፤ “ገንዘብ መስጠቱ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ኢሕአዴግ ለእነዚህ ፓርቲዎች ገንዘብ እየሸለማቸው እና ወዳጅ እየገዛበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሙስና ነው፡፡” ብለዋል፡፡
Addis Admas.

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: