የአፍሪካ ኀብረት ዓለም በቃኝ ገባ

6 Feb


ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
የዛሬ አርባ ዘጠኝ ዓመት ግድም በአፍሪካ አዳራሽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው የአፍሪካ ኀብረት) ሲመሠረት ተመልካች ሆኜ ገብቼ እዚያው አድሬአለሁ፤ የዛሬዎቹ ወጣቶች ያቺን ኢትዮጵያና እነዚያን ኢትዮጵያውያን የሚያውቋቸው አይመስለኝም፤ አንዳንዴ ሳስበው ግምትም ያላቸው አይመስለኝም፤ የነሱ ጥፋት አይደለም፤ ሥርዓት ባለው መንገድ ሥራዬ ብሎ፣ የአገር ጉዳይ ነው ብሎ ያስተላለፈላቸው የለም፤ ዛሬ የንክሩማ ሐውልት በአፍሪካ ኀብረት ግቢ ቆመ የሚል ወሬ ስሰማ ደርግ በአፍሪካ አዳራሽ መግቢያ ላይ የሌኒንን ሐውልት መትከሉን አስታወሰኝ፤ ዛሬ ደግሞ ወያኔ ከማን አንሼ ብሎ የንክሩማን ሐውልት በአፍሪካ ኀብረት ግቢ ውስጥ ተከለ፤ ንክሩማ ትልቅ አፍሪካዊ ነው፤ ነገር ግን ለአገሩም አልበቃም፤ በምንም ዓይነት መንገድ አጼ ኃይለ ሥላሴን አይተካም፤ ኢትዮጵያ ሰው አጥታ ከጋና መበደርዋ ኢትዮጵያ የወረደችበትን አዘቅት ያሳያል፤ እነማን ይዘዋት እንደወረዱም ግልጽ ነው፤ አንድ ሰው ብቻ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ የተዋረዱ እንዳይመስለን፤ የተዋረደችው ኢትዮጵያ ናት፤ እንደተለመደው ጠምዝዘው ጋናን ማጣጣል ወይም የጋናን ክብር መቀነስ አድርገው የሚያቀርቡት ይኖሩ ይሆናሉ፤ የምለው ጋና ከኢትዮጵያ አትቀድምም፤ ንክሩማም ከአጼ ኃይለ ሥላሴ አይቀድምም ነው፤ ንክሩማም ቢኖር በአፍሪካ ኀብረት ጉዳይ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ለውድድር አይቀርብም ነበር፤ ጋና ነጻ በወጣችበት እለት በዓሉን ለማድመቅ የሄዱት ልዑል ሣህለ ሥላሴና አቶ አበበ ረታ ነበሩ፤ ከተመለሱ በኋላ አቶ አበበ በብሔራዊ ቤተ መጽሐፍት ስለጋና ንግግር አድርገው አዳምጫለሁ፤ ኢትዮጵያኮ በኢጣልያ ወረራ ጊዜም የአርበኞችዋን ነፍስ ይማርና ሰንደቅ ዓላማዋ ሲውለበለብባት የነበረች አገር ናት፤ የአርበኞችዋን ነፍስ ይማር! ሐውልት ባናሠራላቸውም ሲናቁብን በአርምሞ ልናልፈው አንችልም፡፡
አርበኞችን ወደዳር ማስወጣትና የሥልጣን ወንበሮችን በባንዳዎች ማስያዝ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጀመሩት ቢሆንም ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ የአገር ውርደት መሆን የለበትም፤
በቅርቡ ሪፖርተር በርእሰ አንቀጹ የሀሳብ ማጠራቀሚያ (ቲንክ ታንክ) በሚል ርእስ ጽፎ ነበር፤ ከሹሞቹ ውጭ ሰዎች መኖራቸውን፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው መሆኑን፣ ሀሳባቸውን የሚያዳምጥ መኖሩን ካላረጋገጥን ሀሳቦች ዋጋ የላቸውም፤ የንክሩማን ሐውልት በኢትዮጵያ ለመትከል ወይም የሌኒንን ሐውልት በኢትዮጵያ ለመትከል ከአንድ ሰው በቀር አይወስንም፡፡

የአፍሪካ አንድነት የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1963ዓ.ም. ነው፤ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ከፍ ያለና የተከበረ ስም ነበራት፤ በአፍሪካ ያለምንም ጥርጥር ቀዳሚዋ አገር ነበረች፤ ኢትዮጵያን ለዚህ ያበቃት ረጅም የነፃነት ታሪክዋ፣ የህዝቡ ጨዋነት፣ የመሪዎቹ፣ በተለይም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ግርማና ሞገስ አንድ ላይ ሆነው ኢትዮጵያን የተከበረችና የተፈራች አገር አድርገዋት ነበር፡፡
ለአፍሪካ ኀብረት የተሰበሰቡት በዘመኑ የነበሩ ታላላቅ መሪዎች፣ አገሮቻቸውን ከቅኝ አገዛዝ ያወጡ ሰዎች ነበሩ፤ መሪዎቹ በየሰፈራቸው የጎረቤቶች መኀበር እያቋቋሙ ለትልቁ የአፍሪካ አንድነት እምብዛም ግድ አልነበራቸውም፤ ምናልባትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በማቋቋም እያንዳንዳቸው በየአገራቸው ያላቸው ሥልጣን የሚ¬¬¬-ቀነስባቸው መስሎአቸው የነበረ ይመስለኛል፤ አብዛኛዎቹ እናጥናው፣ እናብላላው በማለት የድርጅቱን ምሥረታ ለማስተላለፍ በፓም ይጥሩ ነበር፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግን የድርጅቱ ሰነድ ሳይፈረም ማናችንም ከአዳራሹ አንወጣም ብለው ገትረው ያዙአቸው፡፡
የአጼ ኃይለ ሥላሴ ትልቅነትና የኢትዮጵያ የመንፈስ መሪነት በገሀድ ታየ፤ እንደናስርና እንደቤን ቤላ ያሉ አብዮተኞች ሳይቀሩ ከጃንሆይ ጋር ሲነጋገሩ ጎንበስ ብለውና እጆቻቸውን ወደኋላ አጣምረው ነበር፤ መቼም የዚህ ፊልም አንድ ቦታ ይኖራል ብዬ ተስፋ አለኝ፤ የዛሬ ወጣቶች ሁሉ ሊያዩት የሚገባ ነው፤ እምቢተኞቹንና አፈንጋጮቹን ሁሉ አንድ በአንድ እያነጋገሩ፣ እንደኒዬሬሪና አሚን ተጣልተው የማይነጋገሩትን እያስታረቁ ሰነዱ ሳይፈረም መውጣት የለም አሉ፤ እንደማስታውሰው ሰነዱ ከሌሊቱ በስምንትና በዘጠኝ መሀከል ተፈርሞ አለቀና ሲነጋ በየቤታችን ገባን፡፡
የአፍሪካ አንድነት በጋዳፊ (ነፍሱን ይማረውና) ውትወታ የአፍሪካ ኀብረት ተባለ፤ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ነው፤ ዓላማው የአፍሪካን ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ የአፍሪካ አገሮችን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለመጠበቅና ከማናቸውም ዓይነት ቅኝ አገዛዝና ቄሣራዊ ተጽእኖ ለመከላከል ነበር፤ ነበር፤ ነበር፤ በአገሮች መሀከል የሚከሰቱ ችግሮችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲገኝላቸው ማድረግ ነበር፤ ነበር፤ ነበር፡፡
እንደዚያ ዕለት በኢትዮጵያዊነቴ ኮርቼ አላውቅም፤ ስለዚህም የኢትዮጵያውያን የዩኒቨርስቲ መምህራን ማኀበር ስብሰባ ጠራሁና ያየሁትን ገልጬ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ የምስጋና ደብዳቤ እንጻፍላቸው የሚል ሀሳብ አቀረብኩ፤ አንዳንድ ተቃውሞ ተነሥቶ ከተከራከርንበት በኋላ እንዲጻፍላቸው ተወሰነ፤ ዳብዳቤውን ጽፌ ለጃንሆይ እንዲሰጥልን ለዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ለልጅ ካሣ ወልደማርያም አስረከብሁት፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠራኝና አንተው ወስደህ ብትሰጥ ይሻላል አለኝ፤ የምሄድበትን ቀንና ሰዓት ነገረኝ፤ ወስጄ በእጃቸው ሰጠኋቸው፤ እንዳነበቡት ወይም እንደተነበበላቸው ፍልቅልቅ ባለ ደስታቸው ይታይ ነበር፡፡
ዛሬ የአፍሪካ አንድነት (ኀብረት) በቻይና ቸርነት ፎቅ ተሠርቶለት ዓለም በቃኝ ገባ አሉ፤ የአፍሪካ መሪዎችም እዚያው ተሰበሰቡ፤ አቶ መለስም ለቻይና አስተዋጽኦ ዋጋ ለመክፈል ለማኦትሴ ቱንግ ተማሪ ሐውልት አስተከለ፤ ቀጥሎም የአፍሪካ መሪዎች በምን ምክንያት ወደ አውሮፓ ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ በማለት አቶ መለስ ተቆጥቶ በዓለም-በቃኝ ፎቅ ውስጥ የአፍሪካ ፍርድ ቤት ማቋቋም እንችላለን የሚል ሀሳብ አቀረበ ተባለ፤ ማን በማን ላይ እንዲፈርድ ይሆን? የአውሮፓ ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት የተፈራው ምኑ ነው? ወይስ የዓለም-አቀፍ ትርጉም ችግር ሆኖ ነው? መቼም የአፍሪካ ፍርድ ቤት ዓለም-አቀፍ ደረጃ ላይ ይውጣ ማለት…ምን ማለት ይሆን? የተባበሩት መንግሥታትስ መቼ ነው ተለይቶ ‹‹አፍሪካዊ›› የሚሆነው?
ለማናቸውም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሆነው የሚመለከቱን የኢትዮጵያ አርበኞች ይቅር ይበሉን፤ ለኢትዮጵያም ከሌኒን ያወጣት አምላክ ያውቃል!

Advertisements

2 Responses to “የአፍሪካ ኀብረት ዓለም በቃኝ ገባ”

  1. Abelo February 10, 2012 at 1:35 pm #

    it is a good explanation but our current leaders present the country for the retail market this is what the current situation looks like .

    • hayelom May 21, 2013 at 12:49 pm #

      u shit!!!u want only power but no one will give u zat///

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: