“በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች ገጦ የሚታየው ድህነት እንጂ እድገት አይደለም”

13 Dec

 For Amharic PDF file, click here: Befekadu Degefe

ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ የድምጽ ግርማ ሞገሳቸው ብቻ የሚበቃ ፤ በኢኮኖሚክስ መምህርነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ለረጅም አመታት አገልግለው ፤ ከ 40 ው የተባረሩ መምህራን አንዱ የሆኑ፤ በ1997 ዓ.ም ደግሞ ተማሪያቸው ከነበረው ፤ ሚኒስቴር፤ግርማ ብሩ ጋር ስለ ሃገራችን ኢኮኖሚ በተለያየ ጎራ የተከራከሩ እና ፤……ወዘተ. ወዘተ……

ከፍትህ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንሆ.፤

ፍትህ፡- የአገራችንን ኢኮኖሚ እንዴት ይገመግሙታል?

ፕ/ር በፍቃዱ፡- የወቅቱ የአገራችን ኢኮኖሚ ሁለት ገፅታ አለው፡፡ አንዱ የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው፡፡ በዚያው መጠን የሚያስተክዝና አንገት የሚያስደፋም ገፅታም ይስተዋልበታል፡፡
ከመልካሙ ገፅታ ለመጀመር የኢህአዴግ መስተዳደር ብዙ ሰናይ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ግብአትን ወደ አምራች፤ ምርትን ወደ ሸማች የሚያደርሰን መንገድ ቀደም ሲል ከነበረው በእጥፍ አሳድጓል፡፡ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ግድብ በመገንባት፤ የእንፏሎት ጉድጓድ በመማስ፤ የነፋስ መዘውር በመትከል ከታዳሽ ምንጮች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ገንብቷል፡፡ ፍፃሜው የሚያጓጓን እና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና በተለይም ስነ ልቡናዊ ፋይዳው ግዙፍ የሆነውን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት መነሳሳቱም የሚያስከብረው ነው፡፡
ከግብርና ውጭ ላለው ዘርፍ ትኩረት በመስጠቱ የመዋቅራዊ ለውጥ ጅማሮ እየታየ ነው፡፡ ለከተሜው ስራ፣ ለገጠሬው አማራጭ የገቢ ምንጭ መፈጠሩ ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡ ይህ ሂደትም መሰረታዊ የእድገት ገች የሆነውን የገበያ ችግርን በማስወገድ ለኢኮኖሚ እድገት ሰፊ አገራዊ እድል መኖሩን አስመዝግቧል፡፡ ለዚህም ሁነኛው ምስክር በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት ነው፡፡ እነዚህ ተግባራትና ውጤቶቻቸው ናቸው ኢኮኖሚውን አኩሪ ገፅታ የሰጡት፡፡ እንግዲህ እነዚህና መሰል ተግባራቱ ታሪክ ኢህአዴግን በበጎ ያስታውሰዋል፣ ያወድሰዋልም፡፡
አስደማሚውና አስደንጋጩ ክስተት መስተዳድሩ የዘረጋቸውንና ያፈራቸውን መሰረተ ልማቶች ተጠቅሞ ምርት በተለይም የምግብ ምርትን ለማሳደግ የሚያስችል ስርዓት ዘርግቶ በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት የሚፈልጉ አገራዊ አምራች ኃይሎችን በማዝመት ህዝብን ከችጋር፣ አገርን ከሰቆቃ ማዳን ሲችል ይህን አለማድረጉና የዚህም ቸልተኝነት ያስከተለው መከራ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች ገጦ የሚታየው ድህነት እንጂ እድገት አይደለም፡፡

ፍትህ፡- መንግስት ኢኮኖሚው በሁለት አሃዝ እያደገ ነው ይላል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት እርስዎ ድህነት ነው እንጂ ኢኮኖሚው አይደለም ያደገው የሚሉት?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- ተው፡፡ ያላልኩትን አታስብለኝ፡፡ ኢኮኖሚው አላደገም አላልኩም፡፡ ኢኮኖሚው አድጓል፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የ2003ን የበጀት አመት ክንውን ለፓርላማ ዘገባ ሲያቀርቡ ኢኮኖሚው በ11.4 በመቶ ማደጉን አብስረው ነበር፡፡ ይህ አኩሪ እድገት ነው፡፡ እኔም ከዚህ ቁጥር ጋር አልጣላም፡፡ ግን በዚያኑ አመትና እንዲሁም ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ጎልቶ የታየውና የሚስተዋለው የድህነት እድገት እንጂ የኢኮኖሚው እድገት አይደለም፡፡ በተለይ የከተማ ኗሪው ህዝብ የኑሮ ደረጃ እየቀነሰ ሳይሆን በከፍተኛ ፍጥነት እየወደቀ ነው፡፡ በምን ያህል ነው የኑሮ ደረጃው የቀነሰው ብትል መልሱ ዋጋ በሚንርበት መጠን ልትገምተው ትችላለህ፡፡
ፍትህ፡- አንድ ነገር ግልፅ እናድርግ፡፡ እርስዎ እያሉ ያሉት ኢኮኖሚው አድጓል ግን ህዝቡ አልተጠቀመም ነው፡፡ የዘመኑን አባባል ልጠቀምና እንዴት ነው ነገሩ ልበል?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- አዎ፡፡ ኢኮኖሚው አድጓል፡፡ ግን በዚህ ተመንዳጊ ኢኮኖሚ ውስጥ ምንድነው ያደገው እና የእድገቱ ትሩፋትስ የት ገባ የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ ከእድገቱ ትሩፋት ብትጀምር፡፡ የእድገቱ ውጤት ፍትሃዊ ክፍፍል አልታየበትም፡፡ እጅግ አናሳ የህብረተሰብ ክፍል ሀብታም ሲሆን ብዙሃኑ ግን ለድህነት የተዳረገበት ዘመን ነው፡፡ ወደ ኢኮኖሚው እድገት ስትመጣ ምንድነው ያደገው ለሚለው መልሱ ኢኮኖሚውን በዘርፍ በዘርፉ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር የ2003ትን ኢኮኖሚ ውጤት አደባባይ ባዋጠው ዘገባ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ካሉት ሶስት ዘርፎች ትልቁ ባለድርሻና ባለከፍተኛ እድገት ባለቤት የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ በ2003ዓ.ም ድርሻው 46.6 ሲሆን ያስመዘገበው እድገት 12.5 በመቶ ነው፡፡ ሁለተኛው ግብርና ነው፡፡ ድርሻው 41.1 ከመቶ ሆኖ በአመቱ ያስመዘገበው እድገት 9 በመቶ ነው፡፡ ባለአናሳው ዘርፍ ኢንዱስትሪው ሲሆን ድርሻው 13.4 ሆኖ እድገቱ ግን 15 በመቶ ነው፡፡ ይህ በግላቸው ያስመዘገቡት እድገት ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ እድግት ያበረከቱት ሲሰላ ግብርና 3.7፤ ኢንዱስትሪ 2.0 አገልግሎት 5.8 ይሆናል፡፡ የነዚህ ድምር ነው የ11.4 በመቶውን እድገት ያስገኘው፡፡ እነዚህ ቁጥሮች ኢኮኖሚው ያለበትን ሁኔታ በግልፅ ያስረዳሉ፡፡ በ2003ዓ.ም ፍጆታንና መዋእለ ነዋይን ያካተተ ፍላጐት ያደገው ኢኮኖሚው በዘመኑ ዋጋ ባደገበት በ32.9 በመቶ ነው (በትክክለኛው ስሌት ይሄ መጠን ትክክለኛውን ፍላጐት አይለካም፡፡ አገራዊ ወጪ ከገቢያችን ስለሚበልጥ..፡፡ ከዚህ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ፍጆታ ያደገው በ27 በመቶ ሲሆን የምግብ ፍላጐት ያደገው በ16 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ (እነዚህ ቁጥሮች ግምት መሆናቸውን አትርሳ፡፡ የምጠቀምበት ትክክል ናቸው ለማለት ሳይሆን የተፅእኖውን ምንጭና አቅጣጫ ለማመላከት ብቻ ነው፡፡) በዚያው አመት ግብርና (ለምግብና ለምግብ የማይሆነውንም ጨምሮ) ያደገው በ3.7 በመቶ ነው፡፡ ይሄ የግብርናው እድገት ሙሉ በሙሉ የምግብ ሰብል እድገት ነው ብንል እንኳን (የግብርና ምርት ሁሉ ለምግብ እንደማይውል እያወቅን) ከምግብ ፍላጎት ጋር ስታነፃፅረው እጅግ ትልቅ ክፍተት መኖሩን ያሳያል፡፡ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ክፍተት የተሞላው በዋጋ ንረት ነው፡፡ ቁምነገሩ በቂ አናመርትም፡፡ እግዚአብሔር ያሳይህ ስንዴ ከውጭ እየገዛን ነው፡፡ ጤፍ የሚያመርት አገር የለም እንጂ ቢኖር ጤፍም ከውጭ እንገዛ ነበር፡፡ የሚገርም ነው፡፡ እኛ አምርተን፤ በልተን ጠግበን ተርፎን ወደውጭ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ለማካበት የሚያስችሉንን ምርቶች ማምረት አቅቶን ሳይሆን ባልታወቀ ምክንያት ከውጭ እንገዛለን፤ እንለምናለን፤ በዚህ የምናገኘው ስለማይበቃን እንራባለን፡፡ እንደዚህ አይነት ተአምር ልታይ የምትችለው እዚህ አገር ብቻ ሳይሆን ይቀራል ብለህ ነው፡፡
ፍትህ፡- ግን እኮ ሌሎች የሚሉት ኢኮኖሚያችን በሁለት አሃዝ ስለሚያድግ የዋጋ ንረት የተከሰተው በምርት እጥረት ሳይሆን ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንሳፈፈው ገንዘብ ስለበዛ ነው ነው የሚሉት?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- ዛሬ በአገራችን ባለው ሁኔታ የዋጋ ንረት መንስኤ የገንዘብ ብዛት ነው ከሚሉ ኢኮኖሚስቶች ስብስብ ውስጥ አትጨምረኝ፡፡
ፍትህ፡- በሁለቱ መካከል ግንኙነት የለም ነው የሚሉኝ?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- በገንዘብና በዋጋ መካከል ያለው ቀጥተኛ ግንኙነት አንዱ የሌላው መገለጫ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በዋጋና በገንዘብ ብዛት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የለም፡፡ በሌላ አነጋገር ዋጋ የሚንረው ገንዘብ ስለበዛ አይደለም፡፡ ገንዘብ ቀንሶም ዋጋ ሊንር ይችላል፡፡ ገንዘብ ጨምሮ ዋጋ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ስለዚህም የአገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ ገንዘብ ቀንሱና ዋጋ ይረጋጋል የሚሉ ኢኮኖሚስቶች አሉ ብዬ ለማመን ያስቸግረኛል፡፡
ፍትህ፡- ግራ እያጋቡኝ እኮ ነው ፕሮፌሰር?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- በመጀመሪያ ገንዘብ በዝቷል ከሚል ብትነሳ፤ ከምን ጋር አነፃፅረው ነው ገንዘብ በዛ አነስ የሚሉት? ኢኮኖሚያችን አሁን ባለበት ሁኔታ ስንት ገንዘብ ነው ልክ የሚሆነው፡፡ ለዚህ መልስ አለኝ የሚል ከፈጣሪ በስተቀር ፍጡር የለም፡፡ ገንዘብ በዛ የምትለው ህዝብ ከሚፈልገው በላይ ከሆነ ነው፡፡ በአገራዊ ደረጃ ገና ገንዘብ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን አትርሳ፡፡ በነፍስ ወከፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገንዘብ ከሌሎች ሀገራት ጋር ብታስተያየው የኛው ኢምንት ሆኖ ነው የምታገኘው፡፡ በግለሰብ ደረጃም ብታስብ አንድ ሰው በእጄ ያለ ገንዘብ በዛ አነሰ የሚለው በአንፃራዊ ስሌት ነው፡፡ አሁን ለመሸመት የሚፈልገውን፤ ለመጠባበቂያ የሚያስፈልገውን፤ ሀብቱን እንዴት ለመያዝ እንደሚፈልግ፤ ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል ገምቶና በአጠቃይ ግራ ቀኙን አይቶና ገምቶ፤ አውጥቶና አውርዶ ነው የሚወስነው፡፡
ሁለተኛ ምንጊዜም እና የትም ቦታ የዋጋ ንረት ገንዘባዊ ክስተት ነው ይሉ የነበሩት (ነፍሳቸውን ይማረውና) ሚልተን ፍሪድማንና ደቀመዛሙርቶቻቸው እንኳን እዚህ ድምዳሜ የደረሱባቸው ታሳቢዎች (assumptions) አሉ፡፡ ከነዚህም አንዱና ዋነኛው ኢኮኖሚው ያለውን የማምረት ሃይል ሙሉ በሙሉ በመጠቀሙ ምርት ሊጨምር የሚችልበት እድል በፍፁም የለም የሚለው መሰረታዊ መነሻ ነው፡፡ የፍሪድማን መቼታዊ ፍሰት የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ሀ/ ገንዘብ ሲጨምር የሰው ገንዘብ የመያዝ ፍላጎት አይጨምርም፡፡ በመሆኑም በጁ የገባውንና የማይፈልገውን ገንዘብ ለምርት (ቁሳዊና አገልግሎታዊ) መሸመቻ ያውለዋል፡፡ ለ/ ኢኮኖሚው የማምረት ሀይሉን ሙሉ በሙሉ በመጠቀሙ ተጨማሪውን ፍላጐት የሚያስተናግድ ተጨማሪ አቅርቦት አይኖርም፡፡ ሐ/ስለዚህ ኢኮኖሚው ተጨማሪውን ፍላጐት የሚያስተናግደው ገንዘቡ ባደገበት መጠን ዋጋ በመጨመር ነው፡፡ ገንዘብ 10 በመቶ ቢያድግ ዋጋ 10 በመቶ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዋጋ እንዲረጋጋ ከተፈለገ የገንዘብን እድገት ግርድፉ አገራዊ ምርት በዘመኑ ዋጋ በሚያድግበት ልክ ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ነው የገንዘብተኞች (monterist) አቋም፡፡
ፍትህ፡- ታድያ ኢህአዴግ ለምን ይህንን አያደርግም?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- የገንዘብተኞች አስተሳሰብ ስህተት በመሆኑ፡፡ አንደኛ የገንዘብ መጠንን ለመቆጣር የማይቻል ባይሆንም እጅግ በጣም አዳጋች በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰሞን የገንዘብተኞችን መርሀግብር ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች አስከፊ ውጤት ነው የገጠማቸው፡፡ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በገንዘብተኞች አቋም የተጠመቁት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ሬገንና የእንግሊዝዋ ጠ/ሚኒስትር ታቸር የሊቃውንትን ምክር እምቢኝ ብለው የገንዘብን ብዛት እድገት ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ለማቆራኘት ሞከሩ፡፡ ውጤቱም ኢኮኖሚያቸውን ለአደጋ ማጋለጥ ሆነ፡፡ ችግሩ ከመባባሱ በፊት የገንዘብተኛ መርሀ ግባቸውን በመቀልበስ የገንዘብ ብዛት ሳይሆን የገንዘብን ዋጋ (ወለድ) በመቆጣር ላይ ቸከሉ፡፡ አሁን በአለም ላይ ያለው ገንዘባዊ መርሀ ግብ የሚተገበረው ወለድን ዝቅና ከፍ በማድረግ ነው፡፡
የገንዘብን መቀነስ እንደመፍትሄ የሚያስቀምጡት ለማለት የሚፈልጉት ሌላ ሳይሆን ፍላጐት ቀንሱ ነው፡፡ የገንዘብ መርሃ ግብን ተቅመህ ፍላጐት መቀነስ የምትችለው ባንኮች (ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ) የሚያበድሩትን እንዲቀንሱ በማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ሁለት መንገድ አለው፡፡ አንደኛው ወለድ ከፍ በማድረግ ብድርን ውድ ታደርጋለህ፡፡ በዚህም ሰዎች የሚበደሩትን ይቀንሳሉ፡፡ ሁለተኛው ባንኮች ሊያበድሩ የሚችሉትን መጠን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተወስናለህ፡፡ ይህን በማድረግ ፍላጎትን ቀንሰህ ከአቅርቦት ጋር ለማጣጣም ትሞክራለህ ማለት ነው፡፡
ይህን ታሪክ ወደእኛ አገር አምጣው፡፡ ሌሎችም ታሳቢዎች ትክክል ናቸው ቢባል እንኳ (ይህም አጠያያቂ ነው) እጅግ ከፍተኛ የምርት ምንጮች በስራ ላይ ባልዋሉበት በኛ አገር ይህ አስተሳሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ በአገራችን ሰርቼ ልብላ ብሎ የተዘጋጀ ሰራተኛና የምንበላውን ምግብ ለማምረት ምቹ መሬት በሞላበት አገር የምግብ ዋጋ መናር የተከሰተው ገንዘብ ስለበዛ ነው የሚል ኢኮኖሚስት የለም፡፡
ፍትህ፡- ታድያ ፍላጎትን ለምን አንቀስንም?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- አደገኛና አላስፈላጊም ስለሆነ፡፡ አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ ፍላጎትን መቀነስ ከህሊና፤ ከኢኮኖሚው እድገት፤ ከማህበራዊ እርጋታና ከፖለቲካ ስክነት አኳያ ስታየው ዘግናኝና አደገኛም ነው፡፡ እስቲ አስብ ፍላጐት እንቀንስ ስትል የማንን ፍላጐት ነወ ለመቀነስ የሚዳዳህ፡፡ የሀብታሙን ፍላጐት አትቀንስም፡፡ የፈለከውን ብታደርግ አቅሙ ስላለው የፈለገውን ከማድረግ አትከለክለውም፡፡ ልትቀንስ የምትችለው የሰርቶ አደሩን ፍላጐት ነው፡፡ በትክክል ለመናገር የምትቀንሰው የሰርቶ አደሩን ፍላጐት ሳይሆን ፍላጐቱን ለማሟላት የሚችልበትን አቅም ነው የምትቀንሰው፡፡ ዛሬ ሰርቶ ባገኘው ደመወዝ ቆሎ በልቶ የሚያድረውን ነገ ከስራ ታባርረዋለህ፡፡ ከስራ ያስወጣኸው ተባራሪ ይርበዋል፡፡ ይጠማዋል፡፡ የምግብ ፍላጎቱን አትቀንስም፡፡ ሲርበው የሚበላውን እንዳይገዛ ነው የምታደርገው፡፡ ሰርቶ ለመብላት የሚፈልግን ሰራተኛ ህዝብ ስራ ነስተኸው ለችጋር አጋልጠኸው ዋጋ ብታረጋጋ የህሊና ፀፀት ነው የሚሆነው ትርፉ፡፡ ከኢኮኖሚ አንፃር ብታየው ስራ ፈት በማብዛት ሁለት ጉዳት ይኖርብሃል፡፡ አንደኛው ስራ የፈታውን ብታሰራው ኢኮኖሚው በዚያው መጠን ያድጋል፡፡ ሁለተኛም ስራ ያለው ሰው ምርት ስለሚሸምት ለአምራቾች ገበያ ይፈጥራል፡፡ ይህም እድገት ያመጣል፡፡ ቆሎ ሻጭዋ ብዙ ገዥ ካላት ብዙ ገብስና ሽንብራ ትገዛለች፡፡ ሽንብራና ገብስ የሚያመርቱ ገዥ ስላገኙ ምርቶቻቸውን ለመጨመር ሰራተኛ ይቀጥራሉ፡፡ የኢኮኖሚ እድገት ማለት ይኸው ሰንሰለታዊ ሂደት ነው፡፡ ሌላ ሚስጢር የለውም፡፡ ስራ አጥ ሲበዛ ፍላጎት አይቀንስም፡፡ ግን አይረካም፡፡ ሰው ይቸገራል፡፡ ይከሳል፣ ይታመማል፣ ወንጀል፣ ልመና ይጨምራል፡፡ እነዚህና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ይበረታሉ፡፡ ሰው ሳይመቸው ሲቀር በመስተዳደር ላይ ያምፃል፡፡ ይህም የፖለቲካ ቀውስ ይፈጥራል፡፡ ፍላጎት ይቀንስ የሚሉት እነዚህን ውጤቶች የሚልጉ አይመስለኝም፡፡
ፍትህ፡- ታድያ መፍትሄው ምንድነው?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- መፍትሄው በጣም ቀላል ነው፡፡ በአገራችን ጣምራ ችግር ነው ያለን፡፡ ሰርቶ ለመብላት የሚፈልግ ህዝብ ስራ ማጣትና የዋጋ ንረት ናቸው፡፡ ሁለቱንም በትክክለኛ የእድገትና የልማት መርሀ ግብር ልናስወግድ እንችላለን፡፡ መስተዳደሩ የጀመረውን የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ማቆም ቀርቶ መቀነስ የለበትም፡፡ ይህ መሰረተ ልማት ከመዘርጋት ሌላ ሰርቶ ለመብላት ለሚፈልግ የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ ግን ከዚህ በተጓዳኝ መስተዳደሩ ኢትዮጵያውያን አምራቾች በተለያዩ የተግባር መስኮች በተለይም በምግብ እህል ምርት እንዲሰማሩ ማበረታታት ይገባዋል፡፡ ለምና ድንግል መሬት እያለንና እንዲያውም የምናደርግበት ስላጣን የውጭ ድርጅቶችና ሰዎች መተው ቢፈልጉ አበባ፤ ካሻቸውም ጉሎና ተልባ አምርቱበት ብለን እየለመንን በነፃ በምንሰጥበት አገር፤ የስራ ማስኬጃ ገንዘብም ከቸገራችሁ እኛው እንሰጣችኋለን እያልን፤ ያመረታችሁትንም ብትፈልጉ ለኛ ካልፈለጋችሁም የፈለጋችሁበት ልትወስዱ ትችላላችሁ ብለን በምንለማመጥበት አገር ለኛ ምግብ እንዲያመርቱ ለምን አይደረግም፡፡ ለኢትዮጵያውያንስ ለምን ተመሳሳይ ማበረታቻ አይሰጥም፡፡ የኛ ሰው ሰርቶ ለመክበር እድሉን ለምን ይነፈጋል፡፡ እኔ እርግኛ ነኝ እድሉ ከተሰጠው ኢትዮጵያዊ ገበሬ የምግብ ዋጋ ንረትን ለመግታትና ብሎም ለማረጋጋት ከሁለት ግፋ ቢል ከሶስት መኸር አያልፍም፡፡
ፍትህ፡- ታዲያ ኢህአዴግ ለምን ይህን ተግባራዊ አያደርግም?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- ይሄ የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡ መልሱን የምታገኘው ከኢኮኖሚስት ወይም በኢኮኖሚክስ ሳይሆን ከፖለቲካው ነው፡፡ ኢኮኖሚው በገበያ የሚመራ ከሆነ አምራቹ የገበያ ዋጋ የሚሰጠውን መረጃ ተመርኩዞ ማምረት አለማምረቱን ይወስናል፡፡ መስተዳደሩ ምን እንደሚመረት፣ ማንና የት እንደሚያመርት ማን ምን እርዳታና እገዛ ማግኘት እንደሚገባው አመራር በሚሰጥበት እንደኛ ባለ አገር ውሳኔው ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው የሚሆነው፡፡ አበባ፣ ጐሎ ዘይትና ሩዝ በሰፊው አምርተው የውጭ ገበያ እንዲያውሉ የውጭ ድርጅቶችን የጋበዘ መስተዳደር አገሬው የሚበላውን ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ፤ ገብስና ማሽላ በሰፊው እንዲመረት ለማድረግ ከፈለገ ምንም አይገደውም፡፡ መፍትሄው ለአበባ፤ ለሩዝና ለባዮ ጋዝ አምራቾች ግብአት እንዲያመርቱ የተደረገውን ያህል እንኳን ባይሆን በምግብ ዘርፍ ለተሰማሩ ወይም ሊሰማሩ ለሚፈልጉ እገዛ፣ ማበረታቻ ቢደረግ ችግሩ በአጭር ጊዜ ይፈታል፡፡ በዚህም በአገራችን የተከሰተውን የችጋርና በተለይም በስፋት ናኝቶ የአገሪትዋን ገፅታ ካደበዘዘ ጠኔ በቀላሉ ልንገላገል እንችላለን፡፡
ፍትህ፡- ይሄ ሁሉ ችግር እያለ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የማሰለፍ የኢህአዴግ ዕቅድስ?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- በአሁኑ አያያዝ አገሪትዋ መካከከኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልትቀላቀል ትችላለች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በአለም እጅግ ደሃ ከሆኑት ተርታ አይወጣም፡፡
ፍትህ፡- እንዴት እንዲህ ይሆናል?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- አሁን በተያዘው ስልት አልሚዎቹና የልማቱ ባለቤቶች የውጭ አገር ዜጎች ስለሚሆኑ ከልማቱ የሚገኘውንም ጥቅም አጋባሾች እነሱ ይሆናሉ፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት ስርዓቶች የውጭ ዜጋ የመሬት ባለቤት አይሆንም ነበር፡፡ አባቶቻችን ኢትዮጵያን ሊወር የመጣን ላት ለመዋጋት ክተት ሰራዊት ብለው ህዝብን የሚያዘምቱት በሶስት ምክንያቶች ነው፡፡ ሚስት፣ ሃይማኖትና መሬት ናቸው፡፡ አሁን የመሬት ባለቤት መንግስትና ህዝብ ሳይሆኑ መስተዳደሩ ነው፡፡ እሱም ለፈለገው ይሰጣል፡፡ ካልፈለገው ይነሳል፡፡ የውጭ ዜጋ የፈለገው አካባቢ የፈለገውን መሬት በሚፈልገው መጠን ለመያዝ የሚያስፈልገው መፈለጉን ለሚመለከተው ባለስልጣን መንገር ብቻ ነው፡፡ ከዚያም ህዝቡ ከአካባቢው ተባሮ መሬቱ ይሰጠዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሬትን ከውጭ ባለሀብት ጋር ተጫርቶ ሊይዝ ስለማይችል ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን አትሆንም፡፡ አዲሶቹ ባለቤቶች በተፈናቀለው ህዝብ እንዳይቸገሩ አስፈላጊው ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡
አዲሶቹ ባለቤቶች አዲሱን አገራቸውን ያለማሉ፡፡ አገሬው እድለኛ ከሆነ በኩሊነት ይቀጠራል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም መዋቅራዊ ለውጥ ይካሄድበታል፡፡ አድጎ ተመንድጎና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች እኩል ይሆናል፡፡
ፍትህ፡- ወደ ፖለቲካው ልውሰዶትና ሰሞኑን የአንድ ወቅት የትግል ጓደኞችዎ ጭምር በሽብር ታስረዋል፡፡ ይህንን ነገር እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- ኢህአዴግ አገሪትዋን የሚገዛው እርጋታ በማሳጣት ነው፡፡ ጭር ሲል የሚወሰድ አይመስለኝም፡፡ በቅርቡ በአ ባይ ግድብ አ ስፈነደቀን፡፡ እጅግም ፍንደቃ አደጋ መስሎት ነው መሰለኝ አሸብሮ አኮማተረን፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ በጉጉት መጠበቅ ነው፡፡ ገምት ብትለኝ የሚቀጥለው የሚያኮማትር ሳይሆን የሚያስደስት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ደስታና ሀዘን ይፈራረቁ የለ? ስለሽብር ካነሳህ አይቀር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሁሉ በሽብር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ያልተሸበረ የለም፡፡ ሰርቶ ያላለፈለት ህዝብ ስራ ቢያጣ ምን እንደሚሆን እያሰበ ይሸበራል፡፡ የሚያገኘው ደመወዝ ለሱና ለቤተሰቡ ጉርስ መብቃቱን አለመብቃቱን ሲያስብ ይሸብራል፡፡ ኃብታሙም የሽብርቋት ነው፡፡ ሀብቱን እንዴት እንዳገኘ ሲያስብ ይሸበራል (ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በንፅህና ሰርቶ የከበረ ያለ አይመስለኝም..፡፡ የፖለቲካው መረጋጋት ያሸብረዋል፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ይመጣ ይሆን ብሎም ይሸበራል፡፡ በቃሊቲም ሲያልፍ ይሸበራል፡፡ ፊቱን (እጁን) ባለማስመታቱ ይሸበራል፡፡ ያስመታም እንደሆን መጠኑ ያሸብረዋል፡፡ እንዴት ይቺ ብቻ ወይስ ለካ ይሄን ያህል አለህ ይሉኛል ብሎ ይሸበራል፡፡ በስልጣን ያለውም የሚቀማኝ መጣ ብሎ ይሸበራል፡፡ ያልተሸበረም ምን አግኝቶ ወይም ሰምቶ ነው ያልተሸበረው ይሉኝ ይሆን ብሎ ይሸበራል፡፡ የቀረውም በሽብርና በተሸበሩ መካከል በመኖሩ ጤንነቱ እንዳይቃወስ መሸበር አለበት፡፡ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት በተሸበረበት አገር አሸባሪዎች መታሰራቸው ነው የሚገርመኝ፡፡ መደረግ ያለበት የሽብርን ምንጭ ነው ማድረቅ ነው፡፡
ፍትህ፡- ኤርትራን ማለትዎ ነው?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- አይ አንተ ደግሞ፡፡ ይሄ ሁሉ ገዥ የሚሰጠው ምክንያት ነው፡፡ አፄ ኃ/ስላሴ ላይ ተማሪ ሲያምፅ የውጭ እጅ አለበት አሉ፡፡ ደርግ ገንጣዮችና አስገንጣዮች የሚያዘምቱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሲል ነበር፡፡ ጋዳፊ በራሱ ጥፋት ሳይሆን በውጭ ጠላቶቹ አመካኘ፡፡ የሶሪያው አሳድም እንዲሁ፡፡ መሪዎች ችግሩ እነሱና ከነሱ አካባቢ መሆኑን አምነው የእርምት እርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ ያኑ የውጭ እጅም ቢኖር አገር ውስጥ የሚይዙት ሲያጡ አርፈው ይቀመጣሉ፡፡ በኔ እይታ የኢህአዴግ ዋነኛ ጠላት ግንቦት ሰባት አይደለም፡፡ ኦነግ አይደለም፡፡ ኦብነግ አይደለም፡፡ አልሸባብ አይደለም፡፡ አልቃይዳ አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ዋነኛ ጠላት ኢህአዴግ እራሱ ነው፡፡ እራሱን መፈተሽ፤ መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ጉልታዊ አስተዳደሩን ዴሞክራሲያዊ ባይሆንም በህግ የበላይነት ስር ማዋቀርና ለህግ ተገዥ ስርዓት መፍጠር አለበት፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር እስከመሃል ከቀበሌ እስከ ላይኛው የስልጣን አካል ያሉት ገዥዎቻችን ሕግ የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ የራሳቸው ጥቅምና ፍላጐት ነው ሕግ፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን መስተዳደራቸው የገባበትን ማጥ የተገነዘቡ አይመስለኝም፡፡ እውነቱን ደፍሮ የሚነግራቸው ስለሌለ፡፡ መንበራቸው እንዳይናጋና አልጋቸው እንዳይደፈር ከፈለጉ ማየት ያለባቸው ውጭ ሳይሆን እውስጥ ነው፡፡
ፍትህ፡- መንግስት ወገናዊ ነው፣ ያዳላል ተብሎ ይታማል?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- መስተዳደር ሁል ጊዜ ወገናዊ ነው፡፡ ለማን እንደሚያዳላ የሚወስነው ለማን ጥቅም ነው የቆምኩት ብሎ ሲያስብ ነው፡፡ የአገራችን አስተዳደር ከጥንት ከጠዋት የተመሰረተው በህግ ሳይሆን በጉልበት ነው፡፡ እንደ ተቋም ስርዓቱ ጠን ካራና ስር የሰደደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የተረጋጋ መስተዳደር በማያውቅ ህብረተሰብ የኢትዮጵያ መንግስት ለዘመናት የዘለቀው፡፡ የመስተዳደሩ ባለቤት ጉልበተኛው ነው፡፡ ሲሸነግሉን በጉልበት ነው የምገዛህ አይሉም፡፡ አፄ ኃ/ስላሴን እግዚአብሔር መርጦና ቀብቶ እንደራሴ አደረገኝ አሉና ገዙ፡፡ ፕሬዘዳንት መንግስቱና ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ህዝብ መረጠን አሉ፡፡ ከጥንት እስከዛሬ ያለውን ፖለቲካዊ ህብረተሰብ ካጤንክ ህዝቡን በሶስት ትከፍለዋለህ፡፡ እነዚህም ገዢ፣ አስገዥና ተገዥ፡፡ ገዥ ያው ስልጣን የያዘው ክፍል ነው፡፡ አስገዥ (አንዳንዶች ስማቸውን ሲያጠፉ ተላላኪ ይሏቸዋል) በተቋም ደረጃ ገዥውን ፓርቲ፤ ፓርላማውን፣ ፍርድ ቤቶችን፤ ከማእከል እስከ መንደር የተዘረጋውን አስተዳደራዊ ሰንሰለት፤ ደሕንነቱን፤ የመከላከያ፤ ፌደራልና ክልላዊ ፖሊስን ያካትታል፡፡ የአስገዥዎች ሚና ህዝቡን ቀጥ ሰጥ አድርገው ማስገዛት ነው፡፡ ስርዓቱ ጉልታዊ የሚባለው ነው፡፡ በገዥና በአስገዥ መካከል ያልተፃፈ ውል አለ፡፡ ገዥው አስገዥውን ህዝብ እንዳያምፅብኝ ቀጥ ሰጥ አድርገህ አሳድር ብሎ ህዝብ ላይ ይጎልተዋል፡፡ ጉልተኛው ምንም ጠያቂ ሳይኖርበት ህዝብን እንዳሻው ያደርጋል፡፡ ህዝብ ዜጋ ሳይሆን የአስገዥዎች ንብረት ነው፡፡ ገዥ ለመሆን ካለው ትግል የበለጠና የከፋ ፉክክር የሚካሄደው በአስገዥዎችና አስገዥ ባለመሆን በሚፈልጉ መካከል ነው፡፡ ያለውን አስገዥ ነቅሎ እራሱን ለመትከል ትልቅ ሽኩቻ ይካሄዳል፡፡ እኔ የተሻልኩ አስገዥ ነኝ በማለት፡፡ ችግሩ ለገዥው የሚደርሰው ተገዥው ህዝብ በደሉን የሚሰማውን አጥቶ ሲያምፅ ነው፡፡ ኢህአዴግ እዚህ አፋፍ ላይ ነው የተንጠለጠለው፡፡ ከዚህ ነው መጠንቀቅ ያለበት፡፡
ፍትህ፡- ህዝቡ ስለተከፋፈለ ነው የተገዛው የሚባለውስ?
ፕ/ር በፍቃዱ፡- እኔ ሶስት አይነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አይቻለሁ፡፡ በዘውድ ዘመን ህዝብ አንድ ነበር፡፡ የሀብት ልዩነት ቢኖር በስርዓቱ አታማርርም፡፡ የአርባ ቀን እድልህ በመሆኑ፡፡ ትንሽ ትልቁ ተከባብሮ፤ ያኘውን ተካፍሎ ዘርና ሃይማኖት ሳይለየው የኖረ አንድ ህዝብ ነበር፡፡ ሁሉም በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ ነው የኖረው፡፡ በደርግ ኢሰፓ ዘመን ህዝብን መከፋፈል ተጀመረ፡፡ በቆርቋዥና ተቆርቋዥ፤ በአቀባባይና በተቀባይ ከበርቴ፤ በፋዶ ቡርዧ በቡርዧ፤ በገዥና በተገዥ ወዘተ ከፋፍለው፡፡ ኢህአዴግ መጣና በዘር ከፋፍለው፡፡ በአንድነት ይኖር የነበረው ህዝብ የኢህአዴግ የመጀመሪያ አመታት አብሮ መኖር ጀመረ፡፡ ቀጥሎ ተቻችሎ መኖር መጣ፡፡ አሁን ያለው የችሎ መኖር ዘመን ነው፡፡ የሚቀጥለውን ለማየት እድሜ ይስጠን ነው ፀሎቴ፡፡
ፍትህ፡-ፕ/ር በፍቃዱ ለሰጡን ጠለቅያለ ኢኮኖሚያዊ ማብራሪያ በአንባቢዎችን ስም እናመሰግናለን፡፡
ፕ/ር በፍቃዱ፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: