በስዊድን ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ የፍርድ ቤቱ መቀመጫና መነጋገሪያ ተለወጠ፤ ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ለታሕሳስ 11 ተቀጠሩ

8 Dec

ረቡዕ ህዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም፡- ፍትሕ ሚኒስቴር ከሲዊዲን ኤምባሲ የገንዘብና የቁሳቁስ (ማቴሪያል) እርዳታ ማግኘቱን ምንጮች ለአዲስ ነገር አስታወቁ፡፡ እርዳታው በምሥጢር የተያዘ ሲሆን በዋናነትም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ እና ሦስተኛ ወንጀል ችሎቶች አዳራሽ ማሻሻያ እንዲውል ከሥምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ማንነታቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ አንድ የፍርድ ቤት የማኔጅመንት ክፍል ሠራተኛ ለሪፖርተራችን እንደተናገሩት በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት እና ለሽብርተኞች ድጋፍ ሰጥታችኋል በሚል ወንጀል የተከሰሱት ሁለት ሲዊድናዊያን ጋዜጠኞች እና በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእሥር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላትን የክስ ሂደት የሚያስችሉት ችሎቶች የሚሠየሙባቸው አዳራሾች የድምጽና የምስል ግብዓቶችን በአግባቡ ለማድመጥና ለመመልከት የሚያስችሉ ዘመናዊ የሳውንድ ሲስተምና የምስል መመልከቻ መሳሪያዎችን ጨምሮ ለምቹ ወንበሮች መግዢያ የሚሆን ለጊዜው ቁጥሩ ያልታወቀ ገንዘብ ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ በእርዳታ (ትብብር) መልክ ተቀብሏል ብለዋል፡፡

ትናንት እና ዛሬ በዋለው የሁለቱን ሲዊዲናዊያ ጋዜጠኞች ማርቲን ካርል ሽብየ እና ጁዋን ከርል ፐርሹን የክሥ ሂደት የሚታይበት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የሚስተናገድበት አዳራሽ ወንበሮች ሙሉ ለሙሉ በአዳዲስ ምቹ ወንበሮች የተቀየሩ ሲሆን ዘመናዊ የድምጽ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ከነሙሉ የድምጽ ማይክራፎኖች፣ የምስል መመልከቻ ኦቨር ሔድ ፕሮጀክተር ከነኋይት ቦርድ፣ ዘመናዊ የችሎት የምሥል መቅረጫና መቅረጸ ድምጽ ይገኝበታል ብለውናል፡፡

ይሁን እንጂ የፍርድ ቤቱ የድምጽ ባለሙያዎች ከመሣሪያዎቹ ጋር በቀላሉ መግባባት ባለመቻላቸው የትናት ከሰዓት በኋላው የችሎት ውሎ እንደታሰበለት የድምጽ ጥራቱ ሊጠበቅና በመላ አዳራሹ ሊደመጥ ባለመቻሉ የተከሳሽ ቤተሰቦች፣ የሲዊድን እና የአውሮፓ ኅብረት የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ፣ የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ይህን እርዳታ በዚህ ወቅት መቀበሉ “ቢያንስ በቲዎሪ ደረጃ የጥቅም ግጭት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል” ሲሉ አንድ የህግ ባለሞያ ለሪፖርተራችን ተናግረዋል።

ስለዚህ የፍርድ ቤት ድራማ በስዊድን ቴሌቪዥኖች በሚቀርቡ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ የሚታየው ምስል በውሃ ፍሰት የተበላሸው የችሎቱ የውጭ ገጽታ ነው። ተሰብሮ ያለተጠገነው በፍርድ ቤቱ ደጃፍ ያለው ባለመብራት ጽሑፍ በስዊድን ተመልካቾች ዘንድ የፍርድ ቤቱ ወካይ ምስል ወደመሆን ተቃርቧል።

ትናንት ማክሰኞ እና ዛሬ ረቡዕ የሲዊዲናውያኑ ጋዜጠኞች ጠበቆች ሁለት የመከላከያ ምሥክሮችን የሲዲ የድምጽ እና የጽሑፍ ማስረጃዎችን ቀርበዋል፡፡

የተከላካይ ጠበቆች የመከላከያ ምሥክሮች ጭብጥ የሚያተኮረው ዐቃቤ ሕግ በ2ተኛ እና በ4ተኛ ክሦች ላይ ያመለከተውን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ ጉዳት ለማድረስ እንደመጡ አድርጎ ያቀረበውን ክስ ለማስተባባል ያለመ ነው። ሁለቱ ምሥክሮች ከጋዜጠኞቹ ጋር አብረው የሚሰሩና ዓላማቸውንም ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆኑ ተከሳሾቹ ነጻ የጋዜጠኝነት ሥራ እንደሚሰሩ እውነታውን ያመለክቱልኛል ብለዋል፡፡

ተከሳሽ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤቱን የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው የተፈቀደላቸው ሲሆን በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በቀር ምንም ዓይነት የሽብር ወንጀል አለመሥራታቸውንና በሙያቸው አንቱ የተባሉ ምስጉን የምርመራ ጋዜጠኞች መሆናቸውን፣ ሙያው የሚጠይቀውን መሰናክሎችና መስዋትነት በመክፈል ሙያዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡ አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህ ሙያዊ ተግባር በኬንያና ሶማሊያ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጸው፣ በሶማሊያና በኦጋዴን ቆይታቸውም አካባቢው ያልተረጋጋ በመሆኑ ማንኛውም የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም የምግብ ድርጅት ሠራተኞች በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ እንደሚያደርጉት ሁሉ እነርሱም ጠባቂ ወታደሮች መቅጠራቸውን በመግለጽ በአቃቤ- ሕግ የክስ መዝገብ ግን በኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ሠራዊት አባላት እንደታጀብን አድርጎ ማቅረቡ ሐሰት ነው ብለዋል፡፡

“አብረውን በተመሳሳይ መዝገብ በአንደኝነትና በሁለተኝነት የተከሰሱት የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ሠራዊት አባላት ነን ብለው አምነዋል ተብሎ በችሎቱ 17 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው የተባሉት አብዲወሊ መሀመድ እስማኤል እና ከሊፍ አሊ ዳሂርን እኛ አናውቃቸውም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየናቸውና ከእኛ ጋር የቀላቀሏቸው በኢትዮጵያ ሠራዊት ተይዘን በታሰርን በሁለተኛው ቀን ላይ ነው” ብለዋል፡፡

የተከሳሽ አንደኛ የመከላከያ ምሥክር በዓመት ስድስት ጊዜ የሚታተመው የ Filter reportage magazine ዋና አዘጋጅ የሆኑት ሚስተር ማቲያስ ጆሃንሰን፣ ሁለተኛው ምሥክር ደግሞ የ Kontinent Picture Agency ዋና ስራ አስኪያጅ እና የጆሃን አለቃ የሆኑት ማግነስ ሉፓ (Magnus Laupa) ናቸው። ማርቲን እና ጆሃን ፍሪላንስ የምርመራ ጋዜጠኞች መሆናቸውንና፣ የሲዊዲን የነዳጅ ፍለጋ ካምፓኒዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ላይ በሚፈጠሩ ግጭቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው በሙያዊ ሥራ እንደሚመረምሩ፣ የሲዊድን ሕዝብም ስለኩባንያዎቹ የማወቅ ፍላጎት እንዳለው ለችሎቱ አስረድተዋል።

አፍሪካን ኦይል የተባለው የሲዊዲን የነዳጅ ፍለጋ ካምፓኒ ከዚህ ቀደም በሱዳን ባደረገው የነዳጅ ፍለጋ እንቅስቃሴ ላይ ሰዎችን ያለፍቃዳቸው ከአካባቢያቸው በማፈናቀልና ሠራተኞቹም ሴቶችን በግዳጅ የመድፈር ድርጊቶች ፈጽመዋል በመባል በሲዊዲን ሕዝብ ይከሰስ እንደነበር አውስተዋል። ይህን የሚገልጽም መጽሐፍ በሲዊዲን ተጽፎበት ስለነበር ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያም ሲመጣ በኦጋዴን አካባቢ ነዋሪዎች ላይ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን ስለመፈጸሙ ስሞታዎች ከአካባቢው ከተሰደዱ ሰዎች በመሰማቱ ጋዜጠኞቹ በቦታው በመገኘት ተጠቂዎቹን የአካባቢው ሰዎችን በማናገር የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ ለመሥራትና ለሲዊዲንና ለእስካንዲኒቪያን ሕዝብ ለማስነበብ በተከለከለውና በጦርነት እንቅስቃሴ ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ግዛት ኦጋዴን ውስጥ ገብተዋል በማለት መሥክረዋል፡፡ ተከሳሽ ጋዜጠኞቹ ከዐቃቤ- ሕግ እና ከፍርድ ቤቱ ለቀረበላቸው መስቀለኛ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡
አድሪያን ብሉምፊልድ የተባሉት ሌላው ምስክር የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጠኛ ናቸው። ግጭት ባለባቸው ቦታዎች የሚሰማሩ ጋዜጠኞች በተለያየ ምክንያት ወደ ተከለከሉ ቀጣናዎች ያለፈቃድ እንዲገቡ የሚገደዱበት ሞያዊ አጋጣሚ የተለመደ መሆኑን፣ ይህን ሲያደርጉም ከአንዱ ወይም ከሌላው ወገን ሰዎች ጋራ ሊጓዙ እንደሚችሉ አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት ግን ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ተከሰው አያውቁም፣ ሊከሰሱም አይገባም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምስክርነት ተናግዋል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች የመከላከያቸውን ዝርዝር በጽሑፍ እንዲያስገቡ አዝዞ ብይን ለመስጠት ለታሕሳስ 11 ቀጠሮ ሰጥቷል።

(ሙሉ ገ./ addisnegeronline.com)

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: