ሽብር ማለት የየካቲት 12 ሽብር

5 Dec

For Amharic PDF file visit here: Terrorism

መስፍን ወ/ማርያም /ፕሮፌሰር/

የኢትዮጵያ ህዝብ ለልጆቹ ስም ሲያወጣ ሽብሩ፣ አሸብር፣ ወንድይራድ፣ ያየህይራድ ይላል፤ ሽብርን ፈልጎ አይደለም፤ ሽብርን ራሱን አስፈራርቶ ለማስቀረት ነው፤ ጥቃትን ለመከላከል የፈጠረው ዘዴ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሽብር ጠላት መሆኑን አንድ ማስረጃ ላቅርብ፤ ስለችጋር ሳጠና በችጋር ጊዜ ሽብር፣ ዝርፊያና ቅሚያ፣ ረብሻ የማይታይባት ኢትዮጵያ ብቻ ነች፤ በችጋር ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብርና ዝርፊያ ያየ ሰው ቢነግረኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ አሁን ወደ የካቲት 12 ሽብር ልግባ፤ ሽብር እንደማናውቅ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡

ኢያን ካምቤል የሚባል ብሪታንያዊ በየካቲት 12/1929 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣልያን እንደራሴ፣ ግራዚያኒን ለመግደል ስለተደረገው ሙከራ አንድ መጽሐፍ አሳትሞአል፤ በመጀመሪያ አንድ ነገር መናገር አለብኝ፤ መንግስት ቢኖር፣ ወይም ለታሪክ ክብር የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን ምሑራን ቢኖሩ እስከዛሬ ድረስ ጉዳይ ብለን ሳናጠናው የተውነውን ትልቅ ጉዳይ ኢያን ካምቤል ስለጻፈልን በጣም የሚመሰገን ነው፤ እኛን ግን በጣም የሚያሳፍረን ነው፤ እኔማ ብዙዎቹ ሰዎች በቅርቤ የነበሩ ዘመዶችና ወዳጆች ስለነበሩ ይበልጥ ያሳፍረኛል፡፡
ስለ የካቲት 12 ሽብር፣ ስለ አብርሃ ደቦጭና ስለ ሞገስ አስገዶም ላይ ላዩን እሰኪበቃን ሰምተናል፤ ዋናውንና ዝርዝሩን ጉዳይ ግን ሳናውቀው ቆይተን ነበር፤ ሁለቱ የኤርትራ ወጣቶች በኢጣልያ የቅኝ አገዛዝ መስሪያ ቤት ውስጥ ታማኝ አገልጋዮች ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፤ በአንድ በኩል ውስጣቸው የተቀበረ የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ በሌላ በኩል ከኤርትራ ተከትሎአቸው የመጣው የፋሺስት ኢጣልያኖች ንቀትና ማዋረድ አንገፍግፎአቸው ክፉ ጥላቻ በውስጣቸው አሳደረባቸውና በፋሺስት እንደራሴው ላይ ጉዳት ለማድረስ ወስነው ተነሱ፤ ተዘጋጁ፡፡
ለየካቲት 12 የኢጣልያ አገዛዝ የኢትዮጵያ ህዝብ የማስገበሪያ ልዩ ዝግጅት አድርጎ በቤተ መንግስት (በኋላ የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርስቲ) በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ግቢውን ሞልተውት ነበር፤ ለፋሺስት ኢጣልያ እንዲገብሩ የተጠሩት ታላላቅ የኢትዮጵያ መሳፍንትና መኳንንት፣ የተማሩ ወጣቶች፣ የተማሩ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ የኢጣሊያን ታላቅነትና ቸርነት እንዲቀምሱ የተጠሩ በሺህ የሚቆጠሩ ደሀዎች፣ አካለ ስንኩላን፣ ዓይነ ስውሮች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ሁለት ሁለት ጠገራ ብር ምጽዋት ለመቀበል ተኮልኩለው ነበር፤ እንግዲህ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በሀጂ በዳሶ በኩል ከድሬዳዋ የመጣላቸውን ቦምባቸውን ታጥቀው በሰገነቱ ላይ ነበሩ፤ የመጀመሪያውን ቦምብ ሲጥሉና መሬት ሲጨልም ግራዚያኒ ሲሸሽ ሌላ ቦምብ ወረወሩና ከኋላው ክፉኛ አቆሰሉት፤ ቁስሉን ሁለት ወር ተኩል ያህል በራስ ደስታ ሆስፒታል (ያኔ የኢጣልያኖች ሆስፒታል ነበረ) ተኝቶ ቢታከምም እስከ ህይወቱ መጨረሻ ከውስጥም ከውጭም ህመምተኛ ነበር፤ ከግራዚያኒ ጋር ብዙ የፋሺስት ሹሞች ቆስለዋል፤ ከኢትዮጵያውያን መሀከልም ራስ ኃይለ ስላሴ ጉግሳና ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስም ቆስለዋል፡፡
ከቦምቡ በፊት ግራዚያኒ ባደረገው ዲስኩር የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያን ለማዳን እግዚአብሔር የላከው እንደሆነና የአማራን የአረመኔና የግፍ አገዛዝ እስከዘላለም ለማስወገድና አማራዎች ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡
ሁለት ሰዎች ቦምብ ስለወረወሩና ምንአልባትም ከአሥር የማይበልጡ ሌሎች ሰዎች ስለተባበሩአቸው ምንም አይነት ምርመራ ሳያስፈልግ፣ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይሰበሰብ በመጀመሪያ እዚያው ግቢ ውስጥ ለማዳመቅና ለመገበር የተሰበሰቡት መሳፍንትና መኳንንት፣ ለምጽዋት የተጠሩ ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ድሆች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ አካለ-ስንኩላን ተጨፈጨፉ፤ ቀጥሎም የተማሩ የተማሩ ሰላማዊ ወጣቶች፣ የጦር መኮንኖችና ነቃ ያሉ ካህናት፣ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በሙሉ እየተለቀሙ ተጨፈጨፉ፤ ሽብር ይህ ነው፤ ኢትዮጵያውያንን በቤት ውስጥ እያስገቡ ከውጭ ቆልፈው ቤንዚን እያርከፈከፉ አቃጠሉአቸው፤ ሽብር ይህ ነው፤ ጠመንጃ የሌለው ፋሺስት በአካፋ፣ በዶማ፣ በመጥረቢያ በተገኙበት ኢትዮጵያውያንን እየቆራረጠ የደረቀውን የበጋ መሬት የኢትዮጵያውያንን ደም አጠጣው፤ ሽብር ይህ ነበር፡፡ የፋሺስቱ ሰራዊት ደብረ ሊባኖስን ከነመነኮሳቱ አቃጠለው፤ ይህ ሽብር ነበረ፤ አዲስ አበባ ሬሳ በሬሳ ላይ የተከመረባት፣ የደም ጎርፍ የሚወርድባት፣ ዓየሩ በተቃጠለ የሰው ሥጋና በሬሳ ሽታ ተበክሎ መተንፈስ አስቸጋሪ የነበረባት ከተማ ነበረች፤ ሽብር ይህ ነው፤ ኡኡታው፣ ለቅሶው፣ ዱብ ዱብ እያለ ከደም ጋር የሚደባለቀው እንባ.. ይህ ነው ሽብር.. ወደ ሰማይ የሚከንፈው ጩኸት አምላክን ሲያስከፋና ሲያሳዝን፣ይህ ነው ሽብር..
ግራዚያኒ ትንሽ ሲያገግም ከአማራ መኳንንት ጋር ለመገላገል ከዚህ የተሻለ ዕድል አይኖርምና ሁሉንም ጨርሱ፤ ብሎ አዘዘ፤ ሽብር ይህ ነው..
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በፋሺስት ተይዘው ሊሰቀሉ ሲሉ አብርሃ ደቦጭ ..የወንድሜን ስቅላት አላይም፤ እኔን መጀመሪያ ስቀሉኝ.. ስላለ እንደፈለገው ሊሰቅሉት ሲዘጋጁ ..ለአገሬ በአደረግሁት ነገር ሁሉ እኮራለሁ፤ አሁንም በደስታ ለአገሬ እሞታለሁ…. ብሎ ሲናገር የፋሺስቱ አዛዥ በንዴት ተበሳጭቶ አብርሃንም ሞገስንም በሽጉጥ ገደላቸውና ሬሳቸውን ሰቀለ፤ እብደት የሽብር መጨረሻ..
ፋሺስቱን አዛዥ ምን አሳበደው? ያቺን ጠምዝዞና ጨምቆ፣ ዳምጦና ፈልቅቆ ከውስጣቸው አስወጥቻለሁ ብሎ የገመተው ኢትዮጵያዊነት ፊት ለፊት ገጠመው.. ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ፋሺስቱ አዛዥንም ሞትንም እያዩ በአንድ ላይ ተጋፈጡአቸው፤ ኢትዮጵያዊነት የተሸፈነበትን የፋሺስት መንጦልያ ቀዳዶ ወጣ.. ፋሺስቱንም ሞትንም ናቀ.. ለሞት የተዘጋጀ ሰው ሲንቅ፣ ለመግደል ለተዘጋጀው ሰው የመንፈስ ሞት ነው..
በዚያው እለት ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጋፍጦ የአበደው የፋሺስት አዛዥ ቀኛዝማች ወርቁ በሚባሉ አርበኛ ጦር ተመትቶ አብርሃ ደቦጭንና ሞገስ አስገዶምን ተከትሎ ሄዶአል፤ የሽብር መጨረሻው ይህ ነው..
ፈሪሃ እግዚአብሔር አለውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽብር ይፈጸምበታል እንጂ ሽብር አይፈጽምም፡፡

Advertisements

One Response to “ሽብር ማለት የየካቲት 12 ሽብር”

  1. Last second Hotel Reservations May 29, 2013 at 3:01 pm #

    This article will help the internet users for building up new webpage or even a weblog from start to end.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: