እውነት ግን ይህ አገር የማነው ?

22 Nov

For Amharic PDF file visit here: whose country is this?

በትናንትናው ዕለት ይህንን መጣጥፍ እየጻፍኩ
እያለ ቢሮ ውስጥ ‹‹ድንገት›› መብራት ይጠፋና
ለግማሽ ቀን ያህል ስራችን ይስተጓጎላል፡፡ አንዱ
ባልደረባችን ‹‹አሀ! ለካ ዛሬ ዕለቱ ዓርብ ነው››
አለ፡፡ ከመስከረም ወር ወዲህ በዕለተ አርብ (ዕለቱ
ጋዜጣችን ወደ ማተሚያ ቤት የምትገባበት
ቀን መሆኑ ይታወቃልና) ክስተቱ ሁሌም
የሚያጋጥምና የተለመደ ሆኗል፡፡ እኔም ሆንኩ
ባልደረቦቼ ይህንን (ሆን ተብሎ የሚደረገውን)
ሴራ ጠንቅቀን ስለምንረዳ ማድረግ የሚገባንን
ጥንቃቄ አስቀድመን በመከወን ጋዜጣዋ ቅዳሜ
ማለዳ አንባቢ ጋር እንድትደርስ እናደርጋለን፡፡ይህ አይነቱ ክስተት ተራ አሊያም የአጋጣሚ
ነገር ሊመስል ይችላል፤ግን አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ባለፈው ሳምንት የገባንበት አዲሱ ቢሮ
እንኳን፤ ከገባንበት ቀን አንስቶ ተመሳሳይ ዕጣ ሊገጥመው ግድ ሆኗል፡፡ የአካባቢው ሰዎች
እንደነገሩኝ ከሆነ እኛ ከመምጣታችን በፊት ዓርብ ብቻ ተመርጦ መብራት የሚጠፋበት
ሁኔታ ጨርሶ አልተለመደም፡፡ የዚህችን አገር ፖለቲካዊ ሴራ በተለይ
ደግሞ የኢህአዴግ መሪዎችን ባህሪ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው በመሰል ነገሮች ብዙ ባይደነቅም
‹‹ይህ አገር የማነው›› ለማለት ያህል ግን በቂ ግብአት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ መጣጥፌ መነሻ
ግን የሰሞኑን የክስና የስደት ሱናሚ ነው፡፡ ነጻነትን ለመሸመት – ስደት
የሙያ አጋራችንና ጓደኛችን አቤ ቶኪቻው ባለፈው ዓርብ ወደ አውራምባ ታይምስ
ዝግጅት ክፍል ጎራ ብሎ ያጋጠመውን ሁሉ ሲያጫውተን በቀጣዮቹ ቀናት ወይ የመሰደዱ
አሊያም የመታሰሩን ዜና እንደምንሰማ ሁላችንም እርግጠኞች ነበርን፡፡ እናም በማግስቱ
ከጠረጠርነው አንዱ (የመሰደዱን ዜና) ልንሰማ ግድ ሆነ፡፡ ነገስ የማን መታሰር አሊያም
የማን ስደት እንሰማ ይሆን? አዎ! ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማንም እርግጠኛ ሆኖ
መናገር አይችልም፡፡ ሰው በገዛ አገሩ የነጻነት እጦትና የረዳት አልባነት ስሜት ሲሰማው፤
መንግስት ለራሱ ህዝብ አለኝታና ጥላ ከለላ ከመሆን ይልቅ የስጋትና የፍርሀት ምንጭ
ሲሆን፣ ዜጎቹ ነጻነት ፍለጋ ሌላ መሸሸጊያ መፈለጋቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ታዋቂው
ጣሊያናዊ ጋዜጠኛና ጸሐፊ ኢታሎ ካልቪኖ እንዳለው “The ideal place for me is the
one in which it is most natural to live as a foreigner” ነውና፡፡ ሰው በአገሩ እንደ
ዜጋ ሊያገኝ የሚገባውን ተፈጥሮአዊ ነጻነት እንዳያጣጥም ገዢዎቹ ጋሬጣ ሲሆኑበት እንደ
ጣሊያናዊው ጋዜጠኛ ‹‹መወለድ ቋንቋ ነው›› ብሎ ከባዕድ መንግስታት ነጻነት ለመሸመት
ስደትን አማራጭ ቢያደርግ የማያስወቅስ ውሳኔ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ የማን ናት?
የጋዜጠኝነት ሙያ፣ ‹‹ህገመንግስታዊ መብት›› ወይስ ‹‹ወንጀል››
ይህችን አጭር መጣጥፍ ስሞነጫጭር በርካታ አስጨናቂ ነገሮች በአእምሮዬ እየተመላለሱ
ነበር፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ፤ በአንድ በኩል ‹‹ህገመንግስታዊ መብት›› በሌላ
በኩል ደግሞ ‹‹ወንጀል›› እንደሆነ በግልጽ እየተነገረን ነው፡፡ መብት አሊያም ወንጀል
መሆኑ የሚወሰነው ኢህአዴግ ለግለሰቡ (ለጋዜጠኛው) ባለው አዎንታዊ አሊያም
አሉታዊ አመለካከት ብቻ ነው፡፡ ከወራት በፊት ‹‹እከሌ የታሰረው በጋዜጠኝነት ሙያው
በሰራው ስራ ሳይሆን፣ ከጋዜጠኝነት ሙያው ውጪ በሽብር ድርጊት በመሳተፉ ነው›› የሚል
ዜና ነበር የሚስተጋባው፡፡ አንድ የዋህ ጋዜጠኛ በዚህ አባባል ተታልሎ፤ ‹‹በጋዜጠኝነቴ
በሰነዘርኩት ትችት የማልታሰር ከሆነና ሙያዬ እውነትም ህገመንግስታዊ ከለላ አለው››
ብሎ መንግስትን የማያስደስት መጣጥፍ ካሰፈረ ከላይ የጠቀስነው አባባል ይቀየርና
‹‹የጋዜጠኝነትን ሙያና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንደሽፋን በመጠቀም…››
በሚል ርዕስ ስክሪፕቱ ተቀይሮና ፕሮዳክሽኑ ተሰናድቶ በእነ አቶ ሽመልስ በኩል ለሚዲያ
ፍጆታ ይውላል፡፡
እስክንድርን በቃሊቲ ባለፈው ቅዳሜ ታዋቂው ጋዜጠኛና የፖለቲካ
ተንታኝ እስክንድር ነጋን ለመጎብኘት ወደ ቃሊቲ አቅንቼ ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት 2004 ከገባ
ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይኑን ማየቴ ነበር፡፡  ለወትሮው በአገራዊና አለማቀፋዊ የማይጠገብ
ትንታኔው የሚማርከኝ እስክንድር ቃሊቲ ሳገኘው በዝምታ ተውጧል፡፡ በመጠኑም ቢሆን
ገጽታው ላይ የመጎሳቆል ነገር ቢስተዋልበትም፣ ደብዘዝ ባለው ፈገግታው ውስጥ ግን እልህና
ቁጭት ይታይበታል፡፡ ‹‹እንግዲህ ለታሪክ ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር፤ እየቀረቡብን ያሉ
ማስረጃዎች ሙያዊ ግዴታችሁን በመጠቀም በጥልቀት ብትመረምሯቸው መልካም ነው››
አለኝ፡፡ በስፍራው የነበሩ ሲቪል የለበሱ ‹‹የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች›› ግን ይህ አይነቱ ውይይት
ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መልካም ፈቃዳቸው አልነበረም፡፡ ‹‹ይህንን ትታችሁ በማህበራዊና
ቤተሰባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብትወያዩ አይሻልም›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡን፡፡
በእርግጥ እስክንድር ይህ አይነቱ እስርና መጎሳቆል ሊመጣ እንደሚችል ጠንቅቆ
ያውቃል፡፡ ቀደም ብሎም ተዘጋጅቶበታል፡ ፡ ከመጠየቂያው ቅጥር ግቢ ወጥቼ ትንሽ
እንደተራመድኩ ባለቤቱ አለምአቀፍ ተሸላሚዋ ሰርካለም ፋሲል፤ እስር ቤት ከተወለደው
ልጇ ናፍቆት እስክንድር ጋር ተመለከትኳት፡ ፡ እናም ስምንት ወራት በትዝታ ወደ ኋላ
ተጉዤ እስክንድር በመጋቢት ወር የነገረኝን አስታወስኩ፡፡ ‹‹መታሰር ብቻ ሳይሆን ከዛም
በላይ ዋጋ ሊያስከፍለኝ የሚችልን ነገር ለመቀበል ወስኛለሁ፤ ውሳኔው ደግሞ የብቻዬ
አይደለም፡፡ ከባለቤቴ ጋር ነው የወሰንነው፡፡ የእሷ ጠንካራ ድጋፍም አለኝ፡፡ ልጄን በጣም
ነው የምወደው ባየሁት ቁጥር በጣም ነው የምንሰፈሰፈው፡፡ ያለብኝን የዜግነት ኃላፊነት
በመወጣቴ ምክንያት መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ካለም ለመክፈል ዝግጁ ነኝ››

እውነት ግን ይህ አገር የማነው? ነበር ያለው በወቅቱ፡፡ እኔ ግን የእስክንድርን
አንድና ብቸኛ ልጅ ሳየው፣ ቀድሞ ወደ ህሊናዬ የመጣው እዚያው ቃሊቲ መወለዱ
ነው፡፡ እስር ቤት የተወለደው ይህ ሕፃን፣ ዕድገቱን የሚጨርሰው እዚያው እስር ቤት
በመመላለስ ነው ማለት ነው፡፡ በመወለድ ያገኘው ዜግነታዊ ‹‹መብቱስ›› እስር ቤት
መመላለስ ብቻ ነው? ለመሆኑ ይህ ልጅ፣ የመጪውንና የአዲሱን ትውልድ አስተሳሰብ
እንደምን ባለ መልኩ ይቀርፀው ይሆን? ከአዲሱ ትውልድስ ምን ይማራል፤ መሪዎቻችን ስለ
አዲሱ ትውልድ ግንባታ ሲያወሩ የዚህ ልጅ ጉዳይ አይመለከታከታቸውም ይሆን?
ሁለት አመት የዘገየው ‹‹ድግስ›› ከእስክንድር በተቃራኒ ነጻነትና መሸሸጊያ
ፍለጋ ለስደት የተዳረጉት የአዲስ ነገሮቹ አብይ ተክለማሪያምና መስፍን ነጋሽም፤ ያኔ
የተደገሰላቸው ምን እንደነበረ በሚያሳብቅ መልኩ ዛሬ ከሁለት አመት በኋላ ድግሱ
በሌሉበት እውን ሆኗል፡፡ ሁለቱም ጋዜጠኞች በክሱ እጅግ እንደተገረሙ በፌስቡክ ገጾቻቸው
ላይ ያሰፈሩት ሀሳብ ይመሰክራል፡፡ ዐብይ ተክለማርያም ‹‹በማለዳ ተነስቼ ስለአገሬ
ባሰላሰልኩና በተወያየሁ፣ አገሬ ቃልኪዳኖቿን እንድታሳካና እምቅ አቅሟን እንድትጠቀም
ባለምኩኝ፣ በአቶ መለስ ዜናዊ የሽብርተኝነት ክስ ተደገሰልኝ›› ብሏል፡፡ መስፍን በበኩሉ
‹‹በአቶ መለስ መጽሐፍ መሰረት የኔ ይፋዊ ማንነት ተቀይሮ ወደ ተፈላጊ አሸባሪነት
ተለውጧል፡፡ ይህ ግን ሁላችንንም ለተሻለ ነገር ያነሳሳናል እንጂ ተስፋ ይቆርጣሉ
ብላችሁ እንዳትጠብቁ›› በማለት ገልጾአል፡፡ እጅግ የሚገርመው፣ ከሁለት ዓመት
በፊት ጠ/ሚኒስትር መለስ ስለ አዲስ ነገር ጋዜጠኞች መሰደድ ተጠይቀው
‹‹በጋዜጣ ሒስ ቀረበብን›› ብለው መሰደድ አልነበረባቸውም የሚል ‹‹ምንም አላሰብንም››
ዓይነት አንደምታ ያለው ማስተባበያዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ እነሆ የአዲስ ዘመን በሂስ
የተጀቦነ ዲያቢሎሳዊ አቅጣጫ ዘግይቶም ቢሆን በገሃድ እየታየ ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ
አይነቱ የመጠፋፋት፣ የመጠላለፍና የ‹‹ሰዶ ማሳደድ›› ፖለቲካ ማብቂያው የት ይሆን?

Advertisements

3 Responses to “እውነት ግን ይህ አገር የማነው ?”

 1. MELAKU MINAS November 29, 2011 at 4:36 pm #

  Interesting ideas,good lookings,

 2. ዮስፍ November 30, 2011 at 10:40 pm #

  ዳዊት መጨረሻ ለጠየካት ጥያቄ እጠር ያለ መልስ ብሰጥህ ደስ ይለኛል ‘መቼ ይሆን የሚያበቃው” ላልከው የሚያበቃው’ማ አንተ’ና መሰሎችህ ቀስ በቀስ ከጭዋታ ውጭ ስትሆኑ [ስትከስሙ]ያኔ ያበቃል

  • Melaku Minas December 1, 2011 at 10:45 am #

   Hi,Yosef,how could you use awarded like this?Dawit is the man who awarded the International CPJ prize.He a truthful journalist.He is a real Ethiopian who wishes to make his country undivided democrat state.It is a man who leaves his beloved Ethiopia,cause fighting for freedom and equality……………… So you must not use a word like this. But if you are DJ of “EPRDF” go to hell.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: