“በሽብርተኝነት” ተጠርጥረዋል ተብለው በተያዙት ጋዜጠኞች እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ የምስክርነት ቃል ቀረበ

11 Nov

For PDF file Click here: 1Terrorism2

ከሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በአቶ መለስ መንግሥት በሽብርተኝነት ወንጀል በተከሰሱትና በእሥር ላይ በሚገኙት ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባል እና ግለሰቦች ላይ ዐቃቤ- ሕግ የሰው ምሥክሮችን ትላንት ዕረቡ ጥቅምት 29 ቀን 2004 አሰማ።

በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ ፋይል በተከሰሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢብዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌ እና የፍትህ ጋዜጣ ዓምደኛ እና መምህርት ርእዮት ዓለሙ ላይ የዐቃቤ- ሕግ ምስክር ሆነው የመጡት ድምፃቸው በድንጋጤ የሚርገበገብ፣ ለሚጠየቁት ነገር እንደ ቴአትር ስክሪፕት የተሸመደደ የሚመስል የተጠና ንግግር ያደረጉት የአብቶቡስ ተራ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሶፍት ወረቀት ሻጭ፣ ሊስትሮ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ዐቃቤ- ሕግ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው አንደኛው ምስክሬ በሁለተኛው ተከሳሽ ላይ የሚያስረዱት በአዲስ አበባ በተለያየ ጊዜ በለሊት ገንዘብ እየከፈሏቸው ”በቃ፣ ይበቃል፣ መለስ በቃ‘ እያሉ በመርካቶ፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ፣ ተክለሃይማኖት አካባቢ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ሲያስጽፉና ገንዘብ ሲከፍሉ፣ ሦስተኛ ተከሳሽን ጨምሮ የተለጠፉትን ቦታዎች ፎቶግራፍ ሲያነሳ እንደነበር የሚያሳዩልኝ ሲሆን ተከሳሾች ያለምንም ጫና ከኢሜላቸው ሠነዶችን ፕሪንት እያደረጉ ሲያወጡ እንደነበር የሚገልጹልኝ ታዛቢ ምስክሮችንም አቀርባለሁ ብሏል፡፡

የዐቃቤ- ሕግ የመጀመሪያ ምስክር ሆኖ የቀረበው አብርሃም ተሰማ የተባለ የቀን ሰራተኛ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ- አቡቶቡስ ተራ አካባቢ አልጋ ተከራይ መሆኑን እና ቋሚ አድራሻ እንደሌለው ገልፆ ከግንቦት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ቦና ታከለ በሚባል የአቡቶቡስ ተራ ሊስትሮ አሰባሳቢነት ከጀርባ በአቶ ዘሪሁን ገ/እግዚሃብሄር እየተመራ በአንድ ለሊት 70 ብር እየተከፈለው በቀይ ቀለምና በቡርሽ በቃ የሚል ጽሑፍ በአቡቶቡስ ተራ- አዳራሽ አካባቢ፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ፣ ጊዮርጊስ የባስ ፌርማታው ላይ እና ጥቁር አንበሳ አካባቢ ሲጽፍ እንደነበር ጠቅሶ በሦስተኛው ቀን ግን አብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) የመለስ ትልቅ ፎቶ ላይ ”መለስ በቃህ‘ ብሎ ለመጻፍ ፖሊሶች ስለነበሩ ፈርተን ትተን ተመለስን፣ በቀጣይም ወደ ክፍለ- ሀገር በማምራት ነቀምት፣ ጅማ፣ ደሴ እና ጋምቤላ ትሄዳላችሁ፣ መኪና ይመቻቻል ተብለን ነበር ብሏል፡፡

በአብዛኛዎቹ የዐቃቤ- ሕግ ምስክሮች ላይ የ2ተኛ፣ የ3ተኛ እና የ4ተኛ ተከሳሾች ጠበቃ ደርበው ተመስገን መስቀለኛ ጥያቄ የለኝም በማለት ያለፉት ሲሆን በችሎቱ ላይ የተሰየሙት ሦስት ዳኞች ማነው የሚልካችሁ፣ ማነው የሚያዘው የሚሉ የማጣሪያ መስቀለኛ ጥያቄ አድርገው ነበር፡፡

ሁለተኛው የዓቃቤ- ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረበው ጉችዬ ላቀው በላይ በአብቶቡስ ተራ አካባቢ ጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን ገልፆ እርሱንም ቦና ታከለ የሚባል ሊስትሮ የሚሰራ ሰው የግርግዳ ጽሑፍ እንፃፍ እንዳለውና ከአብርሃም ጋር በመሆን ከምሽቱ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ እየተዘዋወሩ እንደፃፉ ገልፆ ከመጀመሪያው ምስክር ጋር በጋራ የተጠና የሚመስል ነጥቦችን በዐቃቤ- ሕግ ጠያቂነት መስክሮ ተከላካይ ጠበቃ መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ እንደማይፈልጉ በመናገራቸው ዳኞቹ የራሳቸውን ጥያቄዎች ለምን የክፍለ- ሀገር ጉዟችሁ ቆመ፣ ቦናን የሚልከው ማነው የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው ጠይቀዋል፡፡

የዐቃቤ- ሕግ ሦስተኛ ምስክር ሆኖ የቀረበው ቦና ታከለ ሲሆን ዕድሜው 20 መሆኑን፣ ሥራው ሊስትሮና ሶፍት መሸጥ እንደሆነና ከአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ አልጋ ተከራይቶ እንደሚኖር ለፍርድ ቤቱ ገልፆ ተከሳሾችን ታውቃቸዋለህ ለሚለው የዐቃቤ- ሕግ ጥያቄ አቶ ዘሪሁን ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ጫማ ያስጠርገኝ ስለነበር አውቀው ነበርና የአንድነት ፓርቲን መታወቂያ ስጠኝ ብዬው መቶ አምሳ ብር ያስከፍላል ብሎኝ ሃያ- ሃያ ብር እያደረግኩ ሰጠሁትና የአባልነት መታወቂያውን አመጣልኝ በማለት ውብሸትን ግን በመልክ ብቻ ነው የማውቀው ከአቶ ዘሪሁን ጋር አንድ ቀን መጥቷል ብሏል፡፡

በዚህ ትውውቃችን አቶ ዘሪሁን መጥቶ 350 ብር እከፍልሃለው በቃ እያልክ በከተማው ውስጥ በየለሊቱ ፃፍ አለኝ ያለው የዐቃቤ- ሕግ ሦስተኛ ምስክር ቦና ታከለ እኔም አብርሃምን 130 ብር እሰጥሃለሁ ፃፍ አልኩት፣ የመጀመሪያው ቀን አብቶቡስ ተራ ተፃፈ ዘሪሁን መጥቶ አይቶ ከፈለኝ፣ በሚቀጥለው ቀን አብዮት አደባባይ ሂድና የመለስ ፎቶ ላይ በቃ ብለህ ፃፍ 1100 ብር እከፍልሃለሁ አለኝና ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ወደዚያ ሄደን ፖሊሶችን አይተን ፈርተን ተመለስን፣ ቀጥሎ ግንብ ላይና ላሜራ ላይ ጊዮርጊስ፣ ተክለሃይማኖትና ጥቁር አንበሳ አካባቢ ፃፍን- ቦታዎችን ሁሉ መርጦ የሚነግረን ዘሪሁን ነው፡፡

በዚህ መሐል አብቶቡስ ተራ አካባቢ አብርሃም ካፌ ውብሸት መጣ እና ዘሪሁን ሄዶ ፎቶ እናንሳ ሲለው ውብሸት ደግሞ ተነስቷል አለው፤ ከዚያም ዘሪሁን በመጀመሪያ 200 ብር ቀጥሎ 300 ብር ሰጠኝና በቀጣይ የትራንስፖርት ብር እሰጥህና አምቦ፣ ሻሸመኔ እና ጋምቤላ እንሄድና በቃ እያልክ ትጽፋለህ አለኝ ብሏል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ባነሱት መስቀለኛ ጥያቄ ላይ ውብሸትን የማውቀው በመልክ ብቻ ነው ብለሃል ስሙንስ ሲሉት መርማሪ ፖሊስ ነው የነገረኝ፣ እኔ የማውቀው አንድ ቀን ለዘሪሁን ስደውልለት ፎርቱን ካፌ ነኝ አለኝና በአጋጣሚ ውብሸትም መጣ፣ ቀኑንም ፣ወሩንም አላስታውስም ሰዓቱ ግን ጠዋት ነው ሲል የፓርቲውን መታወቂያ ለምን አወጣህ ሲሉት ዝም ብዬ ነው ያወጣሁት ጓደኞቼ ሱዳን የሚሄዱ ነበሩ አውጣ ስላሉኝ አወጣሁ ሲል ጠበቃው ጥያቄዬን ጨርሻለው አሉ፡፡

ዘግይቶ የነበረው የዐቃቤ- ሕግ 4ተኛ ምስክር በመሐል መጥቶ ቃለ መሐላ የፈጸመ ሲሆን የፌዴራል አቃቤ- ሕግ ብርሃኑ ወንድማገኝ ምስክሩ 4ተኛ ተከሳሽ ሂሩት ክፍሌ የኢህአዴግ መንግሥት ይብቃን የሚሉት የአዲስ አበባ ተወካይ እንደነበረችና በአሜሪካን አገር ከሚኖረው ኤሊያስ ክፍሌ ጋር እንደምትገናኝ የተለያዩ ሥራዎች እንዲሰራ ክፍያ የፈጸመችና የተዋዋለች እንደነበር ይመሰክርልኛል ብሏል፡፡

4ተኛው የዐቃቤ- ሕግ ምስክር ጌታሁን ዮሐንስ በሥሙ የሚጠራ የተሸከርካሪ ጋራጅ እንዳለውና ሂሩትን የማውቃት ሚያዚያ 2003 ዓ.ም መኪና ልታሰራኝ መጥታ ሲሆን ቀደም ሲል እኔ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሬ በታሰርኩበት ወቅት እርሷም ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ታስራ በዓይን አውቃት ነበር፣ በይቅርታ መለቀቋንም አውቃለሁ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ጋራጄ መኪና ልታሰራ መጥታ ለአንድ ሥራ እፈልግሃለሁ አለችኝና በቃ ተብሎ በየአደባባዩ እንደምትጽፍና እኔም የሀዋሳንና የደቡቡን ክልል እንዳስተባብርና እዛ ከሚጽፉ ልጆች ጋር እንድገናኝ ጠየቀችኝ፡፡ ለቀለም መግዣም 2 ሺህ ብር ከፍላኛለች፣ ትዕዛዝ የምትሰጠውም እርሷ ናት፣ ሥሙን ካሌብ ከአሜሪካ ካለኝና (በኋላ ኤልያስ ክፍሌ) መሆኑን ካወቅኩት ሰው ጋር ካዛንችስ- አቧሬ ኢንተርኔት ቤት ወስዳ በስልክ አገናኝታኛለች ካለ በኋላ በአንድ ጊዜ ቀረቤታ እንዲህ ስትለኝ ደንግጬ ለፖሊስ አመለከትኩና አስያዝኳት በማለት የምሥክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

የተከላካይ ጠበቃ ደርበው በመስቀለኛ ጥያቄ ካሌብ ኤሊያስ ክፍሌ መሆኑን እንዴት አወቅክ፣ እርሷስ ከኤሊያስ ክፍሌ ጋር ስታገናኝህ ምን አለችህ እና ቀደም ሲል እስር ቤት ነው የማውቃት ብለሃል አሁንስ አንድ ላይ ናችሁ ሲሉት ምስክሩ ሥሙ ኤሊያስ መሆኑን ፖሊስ በምርመራ ላይ ነገረኝ፤ ከኤሊያስ ጋር በስልክ ስታገናኘኝም ይህ ሰው ከውጭ የሚረዳን ነው ብላኛለች፤ አሁን ሁኔታውን ለፖሊስ ያመለከትኩት እኔ በመሆኔ አልታሰርኩም፣ የወንዶችና የሴቶች እሥር ቤት የተለያየ ስለሆነ ቀደም ሲል በታሰርኩበት ጊዜ አንድ ላይ አልነበርንም ነገር ግን ቀደም ብሎ የግንቦት 7 የእርሷ አባሪ ታሳሪዎች ከኔ ጋር ስለነበሩ ስለእርሷኬዝ አውቅ ነበር ሲል ለዳኞች ጥያቄም መልስ ሰጥቷል፡፡

የዐቃቤ- ሕግ 5ተኛ ምስክር ጸጋዬ አዱኛ የወረዳ 5 ጸጥታ አስተባባሪ መሆኑን ገልጾ ለግል ጉዳዬ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አምርቼ በነበረበት ጊዜ ውብሸት ታዬ በፍላጎቱ ያለምንም ተጽዕኖ ከኢሜሉ ላይ በእንግሊዝኛ 50፣ በአማርኛ ደግሞ 20 ሠነዶችን ፕሪንት እያደረገ ሲያወጣ በታዛቢነት ተመልክቼ በእያንዳንዱ ገጽ ጀርባ ላይ ስለመታዛቤ ፈርሜያለሁ ያለ ሲሆን 6ተኛው የዐቃቤ ሕግ ምስክር አቶ ገብረመስቀል በድንጋጤ ድምፃቸው ከመጠን በላይ እየተርገበገበ እና የሽምደዳ ንግግር በማድረግ በ5ተኛ ተከሳሽ ርእዮት ዓለሙ ሰኔ 2003 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በፖሊስ ጣቢያ ቢሮ ቁጥር 26 ዘና ብላ፣ ሳትጨናነቅ፣ ያለምንም ተጽዕኖና አስገዳጅነት ከኢሜሏ ላይ የእንግሊዝኛ እና የአማርኛ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው 149 ሠነዶችን ፕሪንት እያደረገች ስታወጣና ፊርማዋን ስታስቀምጥ ተመልክቻለሁ፤ ከኔ ጋርም ኢዘዲን አሊ የተባለ ታዛቢ ነበር ብለዋል፡፡

የ5ተኛ ተከሳሽ የእርዮት ጠበቃ ሞላ ዘገየ አለመጨናነቋን ደጋግመው ተናግረዋል የሥነልቦና ባለሙያ ነዎት፣ 149 ሠነዶችን ይዘት አይቻለሁ ብለዋል አንብበውታል፣ ኢሜሉስ ለምን እንደተላከ ከማን እንደተላከ ተመልክተዋል ሲሉ መስቀለኛ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ምስክሩ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ አለመጨናነቋን ፊቷን ስለተመለከትኩ ነው የተረዳሁት፣ ሠነዶችን አላነበብኩም ርዕሶችን ብቻ ተመልክቼ ነው ይዘቱን የተረዳሁት፣ኢሜሉ ከማን ለምን እንደተላከ እኔ አላውቅም ሲሉ ዐቃቤ- ሕግ ምስክሬን እያጨናነቁብኝ ነው ሲል ስሞታ አሰማ፤ ዳኞቹም ምስክሩን ተረጋግተው እንዲመልሱ ተናገሯቸውና ጠበቃው ጥያቄዮን ጨርሻለሁ አሉ፡፡

በመጨረሻም ዐቃቤ- ሕግ 7ተኛው ታዛቢ ምስክሬ የተለየ ስለማይናገሩ በማስቀረት በ9ነኛ የምስክርነት ተራ ቁጥር የተቀመጡትን ወ/ሪት ሣምራዊት ፍሰሃ በማቅረብ ያስመሰከረ ሲሆን ከእርዮት ጋር ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ እንደሚተዋወቁና እንደሚቀራረቡ በመግለጽ ርእዮት ማህበራዊ ጉዳይ ሲኖራት፡- ልደት፣ ምርቃት ካሜራ ጓደኛዬ ስለሆነች ትዋሰኝ ነበር ብላ መስክራለች፡፡

ዐቃቤ- ሕግም የሰው ምስክር ማስረጃ ማጠናቀቁን ገልፆ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠኝ ቀጠሮ የድምጽና የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎቼን አቀርባለሁ ብሏል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ የድምጽና የምስል ማስረጃ የተባሉትን ቀደም ብሎ እንዲደርሳቸው፣ ኪኢንተርኔት ነው የወጡት የተባለው ሠነዶች የትኛው ሠነድ ለየትኛው ተከሳሽ እንደሆነ ዐቃቤ- ሕግ በግልጽ አላስቀመጠም፣ ተከሳሾች በፖሊስ ጣቢያ ከሦስት ወር በላይ ታስረው በተጽዕኖ፣ በማስፈራራት እና በግርፋት የሰጡት ቃል ለፍርድ ቤቱ እንደማስረጃ መቅረቡ አግባብነት የለውም ውድቅ ይደረግልን በማለት ያቀረቡትን ጥያቄዎች ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

የ5ተኛ ተራ ቁጥር ተከሳሽ የርእዮት ጠበቃ ሞላ ዘገየ ከደንበኛዬ ኢሜል ወጣ የተባለው የእንግሊዝኛ ሠነድ የአማርኛ ትርጉም መፋለስ ስላለው ፍርድ ቤቱ በሚያስተረጉምበት የትርጉም ቤቶች በትክክል ይተርጎምልን ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ- ሕግ ያስተረጎመው የሕግ ፈቃድ ባለው ትርጉም ቤት ስለሆነ ችግር የለውም ነገር ግን ተፋለሰ የምትሉትን ለይታችሁ አቅርቡ በማለት የድምጽና የምስል ማስረጃዎችን ለመመልከት ለዓርብ ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ADDIS NEGER

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: