አይቴይና የአፍሪካ ዲክታተር መሪዎች (በአርቲስት ደበበ እሸቱ)

13 Sep

For Amharic PDf file click here: Debebe Eshetu

በቅድሚያ እንኳን ለዘመን መለወጫው አዲስ ዓመት አደረሳችሁ! መጪው ዘመን መብላትን አስበን ሳይሆን እህል በልተን የምንጠግብበት፤ መዳንን ተመኝተን ሳይሆን ታክመን የምንድንበት፤ከሰቀቀን ኑሮ ተላቀን እፎይ የምንልበት፤ የጎሪጥ ከመተያየት ይልቅ ተሳስበን የምንወያይበት፤በፍራቻ ሳይሆን በመምረጥ የምንኖርበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

ሃገራችን በየወቅቱ ከሚጋረጥባት እጦት ተገላግላ ራሷን የምትችልበት፤የሚሸሽባት ሳትሆን የምንሰባሰብባት፤ የምናፍርባት ሳትሆን የምንኮራባት ኢትዮጵያ እንድትሆን ሁላችንም ለሃገራችን እንደ የአቅማችን እንጣር፡፡ ለዚህ ደግሞ የዜግነት ግዴታና መብትም ነውና የማንም ፈቃድ ሳያስፈልገን፤ ድርሻችንን ለመወጣት የምንተጋበት ዘመን ይሁንልን፡፡

ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም ካነበብኩት ላካፍላችሁ፡፡

አይቴይና የአፍሪካ ዲክታተር መሪዎች

የተከበረው ጋናዊ ኤኮኖሚስት ጆርጅ አይቴይ ያለጥርጥር ሕዝባዊ ከሚባሉት 100 ምሁራን አንዱና (የሚያነሳቸውና የሚሟገትላቸው ሃሳቦች ማንኛውም የትምህርት ስርአት ከሚጠይቃቸው የምሁራን መለኪያ በእጅጉ የላቁና የተከበሩም ናቸው) ዓለም ለለውጥ ከሚንቀሳቀስባቸውና ሂደቱን ለማስተካከል ከሚጥርባቸው የትግል ስርአት ጋር የወገነ ክቡር ምሁር ነው፡፡ በዚህም ሂደቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ከተፈጠሩት በዝባዥ ዲክታተሮች ጋር ግብግብ ገጥሞ እየሞገታቸውና ማንነታቸውን ይፋ እያወጣ ነው፡፡

እ አ አ በ1960 የአፍሪካን ምሁራን፤ጠበቆች፤ ሃኪሞች፤መምህራን ‹‹የፖለቲከኞች መንጋዎች እራሳቸውን በአፍሪካ ለሚገኙ ዲክታተሮች ፤በፈቃደኛነት በመሸጥ፤በገዢዎቻቸው በመደፈር፤በመጠቃት፤እነዚህኑ የህዝብ ጠላቶችና ደም መጣጮች ለማገልገል በአገልጋይነት የተሰለፉና አቅማቸው ሁሉ በሚችለው ሕዝቡን ካስጨቆኑና ተስፋ ካስቆረጡ፤ መሳርያ ሆነው ካስደበደቡና ካስጨፈጨፉ በኋላ፤ እንደታኘከ ሸንኮራ ለመጣል ይበቃሉ፡፡ ወዲያው ደሞ በነዚህ እግር ለመተካትና ለማገልገል፤ ያለፉት መሰሎቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፤ ሃገርና ወገንን ለማሰቃየት በእውቀት ነጋዴነት አንዱ ባንዱ ላይ እየተደራረቡ ሩጫ ይይዛሉ፡፡

ስለ አፍሪካዊያን ዲካታተሮችም ሆነ ስለ የምእራቡ ዓለም የጡት አባቶቻቸው፤ ከአይቴ በተሸለ የሚገልጻቸው የለም፡፡በቅርቡ በኦስሎ በተካሄደው ‹‹በዓለም የነጻነት ፎረም›› ላይ ተገኝቶ የአፍሪካን ሰው በላ የሆኑ ዲክታተሮች ለመዋጋትና ለማስወገድ እቅድ ነድፎ ለታዳሚዎቹ አቅርቦ ነበር፡፡

በ1960 ነጭ የቅኝ ገዢዎቻችንን ብንገላገልም ሃገራችንን ግን ከቅኝ ግዛት ተጽእኖ አላላቀቅንም፡፡ ነጩን ቅኝ ገዢ በጥቁር ቅኝ ገዢ ተካን እንጂ፡፡እነዚህ ጥቁር ገዢዎች ደሞ የስዊስ ባንክ ሶሻሊስቶች፤የአዞ አንቢዎችና ነጻ አውጪ ነን ባዮች፤በጩኸትና በቃላት ድርደራና በሃሰት ድርሰት የተሞሉና የገንዘብ መያዣ ሻንጣ ባንዳዎች፤ ሽፍቶች ናቸው፡፡አፍሪካውያን ስለነዚህ ሰዎች ሲናገሩ፤‹‹በረሮውን አባረን ካለፈው በባሰ ሰው በላ የሆነውን አይጥ ተካን›› ይላሉ፡፡

እነዚህ የአፍሪካ የዶላር ሻንጣ ሽፍቶች፤የወንጀል ድርጅቶች የሚመሩ ናቸው፡፡

ማስረጃውም

የናይጄርያው ሳኒ አባቻ፤ 5 ቢሊዮን ዶላር ዘረፈ፡፡ የስዊሱ ክፍተኛ ፍርድ ቤት በ2005 የአባቻን ቤተሰብ የወንጀለኞች ጥርቅም ብሎታል፡፡

የሱዳኑ ኦማር በሺር 7 ቢሊዮን ዶላር መንትፏል፡፡

ሆስኒ ሙባረክም የ40 ቢሊዮን ዶላር ክምር ዘርፏል፡፡

በንጽጽርም እስከ ኦባማ ድረስ የነበሩት የ 43 ፕሬዜዳንቶች ንብረት በድምሩ 2..5 ቢሊዮን ብቻ ነው፡፡

ይህስ ሆነ ግን የአፍሪካን ዲክታተሮች ታግሎ ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

የአፍሪካን ደም መጣጭ ዲክታሮች ለማስወገድ የአይቴ ‹‹ሕግ››፤ በየመንገዱ ላይ በጩኸት በተሞሉ ሰላማዊ ሰልፎች እነዚህ ዲክታተሮች ሊወገዱ አይችሉም፡፡ እንደ አይቴ እምነት እነዚህን ጭራቆች ለማስወገድ 3 ሁኔታዎችን ያመላክታል፡፡

1ኛ የሁሉንም የተቃዋሚ ድርጅቶች የሚያሰባስብና በአንድነት የሚያሰልፍ ህብረት ያስፈልጋል፡፡ይህንንም ለማድረግ ጥቂት ለህሊናቸው የቆሙ፤የሃገርና የወገን ጉዳይ ቅድሚያ እሳቢያቸው የሆኑ፤ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ያልወገኑ፤ ምንም አይነት የፖለቲካ ጠቀሜታ የሌላቸው ሰዎች ያሉበት ስብስብ መፍጠር፡፡ እነዚህም ተአማኒነት፤ዕውነትም ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

ጋና ውስጥ ይህን መሰል ተቋም ተፈጥሯል፡፡ ‹‹የለውጥ ጥምረት›› ይባላል፡፡

2ኛ. ጠላትን ለይቶ ማወቅ፤ አካሄዱን እቅዱን፤ጥንካሬና ድክመቱን፤……. ድክመቱን ካወቁ በኋላ በዚያ ላይ ማተኮር፡፡ሁሉም ፈላጭ ቆራጭ ጨቋኝ ገዢዎች የሲቪሉን ማህበረ ሰብ፤ መገናኛውን፤ፍትህን፤ የደህንነት ክፍሉን፤የምርጫ ቦርዱንና ባንክን በመያዝ ነው የሚገዙትና ጥቅማቸውንና ስልጣናቸውን የሚያቆዩት፡፡ ስለዚህም ከነዚህ የተቻለውን ያህል በሚመች መንገድ ተጠግቶ በመንቀሳቀስ ነው ቅዋሚያዊው ሂደት ሊሰምር የሚችለው፡፡

3ኛ. የማስተካከያውን ሂደት በሚገባ መንደፍ ያስፈልጋል፡፡

ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ውስጥ 10 ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ምርጫዎች ያሸነፉት እነዚያው ፈላጭ ቆራጮች ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ ምርጫውን የሚያሸንፉበት ምክንያት ተቃዋሚ ድርጅቶች በመከፋፈላቸውና ውህደት አጥተው በተናጠል በመንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ይህ የአይቴይ አባባል እውነትነት አለው? ስለዚህስ ‹‹የኢትዮጵያዊያን ጥምረት ለነጻነት›› የሚባል ግንባር መፈጠርስ ይቻላል? የፈላጭ ቆራጮች ድክመቶች ምንድን ናቸው? በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ሰጥተውና ትኩረታቸውን አሰባስበው አጢነው ሊወያዩበት የሚገባቸው ጉዳይ ይህ ነው፡፡

በፈላጭ ቆራጩ መነጽር መመልከት

ያለአንዳች ጥርጥር አይቴይ ፈላጭ ቆራጮችን ለማስወገድ ያሰመረው መስመር ልክ ነው፡፡ የአፍሪካን ፈላጭ ቆራጭ የቀን ጅብ መሪዎች ማንነታቸውን በሚገባ በመረዳትና በማወቅ ከነሱ በፈጠነ ሂደት ተግባራትን ማከናወን የግድ ነው፡፡የሚሰሩትን የሚያቅዱትን የሚያከናውኑትን ሁሉ በመመርመር እነሱን በኛ ሳይሆን በነሱው መነጽር በማየት መቅደም መቻል ያስፈልጋል፡፡የአፍሪካን ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች እንዲህ ያለውን በሰው ልጅ ህሊና ውስጥ የማይታሰብ ወንጀል የሚሰሩበትን ምክንያትና ሰበብ፤የሰው ልጅ ከሚገምተው በላይ የሚያደርሱትን ግፍና ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ለማሰቃየት ያበቃቸውን ጭካኔና ድፍረት ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ሕዝቡ በቃችሁ፤ እምቢ ሲላቸው እየሰሙና እያወቁ ያን እምቢ ያላቸውን ሕዝብ ለመግዛት ማሰብስ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው፡፡ የትም ያልታየና የማይታይ ፍልስፍናቸው እራሳቸውን እንኳ ማሳፈሩን እያወቁ ካፈርኩ አይመልሰኝን የመሃይም እምነት ይዞ ልግዛ ማለት ማፈሪያነት መሆኑን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

የአፈፍሪካን አምባገነን መሪዎች ባህሪ ከአእምሮ ችግራቸው፤ስሜታዊ ድንፋታቸው በመነሳት ሲመረመር ምንጩ ጥላቻ፤ንፉግነት፤ክፋት፤በቀል፤እኩይነት እና ራስ ወዳድ ሆኖ የበላይነትን ከመፈለግ ህመማቸው ጋር የተያያዘ ሆኖ አናገኘዋለን፡፡

ሕዝብን እንመራለን በማለት ፈንታ ረግጠን፤ ጨፍልቀን፤እምቢ ሲልም ደብዛውን አጥፍተን እንገዛዋለን በሚል ያረጀ ያፈጀ መመርያ ለመጓዝ መምረጥ የከፋና የማይሽር ሕዝባዊ ቁስልን መፍጠር በመሆኑ ‹‹አረኛ ምን አለ›› ወደ ሚለው አመለካከት መመለስ የግድ የሚሆንበት ዘመን ሳያልፍ ቶሎ ከአጉል ጎዳናቸው መመለስን ይጠይቃል፡፡

በቀደም ‹‹ከሥልጣኔ የሚያነሳኝ የሕዝብ ፍላጎት እንጂ የጎዳና ሰልፍ አይደለም፤ሕዝቡ እንደሚወደኝና ሲመርጠኝም ፈልጎኝ እንደሆነ ታይቷልና አርፋችሁ ተቀመጡ፤ ሃገሪቱን ለከፋ እጣ ልትጥሉ ስትነሱ በዝምታ መመልከት ሃገርን ለውድቀት መዳረግ ነውና እረምጃ ይወሰዳል›› በማለት ሙባረክ ሕዝብ አልብሶኛል የሚሉትን ‹‹ፍቅር›› አውጀው ሳይጨርሱ ከስልጣናቸው መነሳት ብቻ ሳይሆን የአልጋ ቁራኛ ሆነው በሰፈሩት ቁና ሊሰፈሩ ለፍርድ ቀረቡ፡፡

ማነህ ባለሳምንት ተባለና ጋዳፊም ‹‹ሕዝቡ ይወደኛል፤ ካለእኔ ሊቢያ የለችም፤ የዚህ እንቅስቃሴ ፈጣሪዎች የሊቢያና የሊቢያውያን ጠላቶች እንጂ ልጆቿ አይደሉም፤ ልጆቿማ ከኔ ጎን ተሰልፈው ሃገራቸውን ከታለመ ጥፋት ለማዳን ቆርጠው የተነሱት ናቸው፡፡ ሕዝቡ ይወደኛል፤ ምራን እያለኝ ነው! አለንልህ ሲለኝ ይሰማኛል!›› ሲሉ ልጃቸው ሰይፍ አሊም በበኩሉ ‹‹እነዚህን የጎዳና አይጦች ከነመሰሪ ሃሳባቸው ድራሻቸውን እናጠፋዋለን›› እንዳላሉ ሁሉ፤ ገሚስ ቤተሰባቸው ወደ ጎረቤት ሃገር ተሰደደ እሳቸውና ሰይፍ አሊም የገቡበት የዓይጥ ጉድጓድ አልገኝ አለ እንጂ እንደአይጥ ጉድጓድ ለጉድጓድ እንደሚሽሎከለኩማ እያየን ነው፡፡

እንዲሁ ናቸው ዲክታተሮች፡፡ ሕዝቡ ይወደናል፤ በኛ የመጣባቸው በአይናቸው የመጣባቸው ነው በማለት የሚጠላችውን ሕዝብ የግድ ውደደንና ኑር ማለት የጋራ ቋንቋቸው ነው፡፡ዲክታተሮች የትም ይሁኑ የት አንድ ናቸው፡፡ ሲናገሩ በድንፋታ፤ ሃቅ ሲባሉ አሻፈረኝ፤ እህ ሲባሉ አካኪ ዘራፍ፤ ከኛ በላይ ላሳር በማለት ሁሉን በጃቸው አድርገው ለዝንት ዓለም ለመኖር ከሕዝብም ከፈጣሪም ጋር አጉል ትግል ይገጥማሉ፡፡ ውጤቱ ግን ለመሸሸግ የአይጥ ጉድጓድ ፍለጋ ብቻ ነው የሚሆንባቸው፡፡ያን ጊዜ ደሞ ይረፍዳል……………፡፡ ይላል አይተይ፡፡

Listen to VOA about Debebe Eshetu & other reflections:
http://www.youtube.com/watch?v=sujufy9mZjc
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: