ንግግራችን ትርፋማ እንዲሆን ከአሉባልታ እንውጣ

14 Aug

መስፍን ወልደማርያም /ፕሮፌሰር/

ሰሞኑን አልጀዚራ ላይ ካፌው ወይም የቡና ቤቱ በሚል ርዕስ አንዲት የኬንያ ጋዜጠኛ ከዚያው ከናይሮቢ የምታስተላልፈውን ፕሮግራም ስመለከት ምን ያህልና በስንቱ ነገር ወደኋላ መቅረታችን አሳዘነኝ፤ በአንጻሩ በረከት ስምዖንና ሽመልስ ከማል በእኛ አገር እንዲህ ያለነገር ባለመኖሩ እንዴት እንደሚደሰቱና እንደሚኮሩ አሰብሁ፡፡ አሁን እንኳን የፈለግሁት አቶ ስብሓት የአልጀዚራን ቡና ቤት እንዲጎበኘው ለመጋበዝ እንጂ ስለአፍ ጠባቂዎች ለመናገር አልነበረም፡፡
አቶ ስብሓት ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች እየሰራ ነው፤ በቀላሉ ልጀምር፤ በጽሁፉ ከባድ የሆነ የአስተሳሰብ ስህተት ይታያል፤ አንድ ምሳሌ፡-
…የውጫሌ ውል ለምን አስፈለገ… ጣልያን ኤርትራን ለምን ያዘ… የወቅቱን ጥያቄዎች አንስተን ትክክለኛ መልስ እንዲያገኙ ለታሪክ ባለሙያዎች ብንተወው ምናልባት መልሱ ኤርትራም በጣልያን አትያዝም ነበር፡፡ የአድዋ ጦርነትም አይኖርም ነበር ሊሆን ይችላል (……)
ይህ አባባል እምብዛም ትርጉም የለውም፡፡ ወተት ቢኖር በእንጀራ አምገህ ትበላ ነበር እንዳለችው ሴትዮ ነው.. ቢሆን ኖሮ በማለት ክርክሩን ለመለወጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በኤርትራና በትግራይ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራና የትግራይ ዜጐች ተግተው ኢጣልያንን ቢወጉ ኖሮ ከሐረር፣ ከሀድያና፣ ከሲዳሞ፣ ከሸዋ… ወደ ሰሜን መዝመት አያስፈልጋቸውም ነበር፤ ይህ ቢሆን ዛሬ ሌሎች ያልሞቱትን ሞት በመሞታቸው አይወቀሱም ነበር፤ ከኋላዬ ሁለት ተጨማሪ ዓይኖች ቢኖሩኝ፣ ቁመቴ አስር ሜትር ቢሆን፣ …እያሉ መከራከር የትም አያደርስም፡፡ ለልብ-ወለድ ስራ እንጂ ለታሪክ አይበጅም፤ የተዛባ አስተሳሰብ የሆነውንና ያልሆነውን፣ ያለፈውንና የሚመጣውን፣ እውነትና ሐሰትን ለይቶ በግልጽ እንዳያዩ አእምሮን ይጋርዳል፡፡ ስለዚህም አእምሮ ክፍት፤ ህሊና የፀዳ ሲሆን ለመግባባት ያመቻል፡፡
ስብሓት …..ታሪካችን ይጠና፣ ይመርመር፣ ይጻፍ፣ ህዝቦች ይወቁት….. የሚለው ትክክል ነው፡፡ ስለዚህም ነው ከማጥናትና ከመመርመር በፊት የሆነውን እንዳልሆነ፣ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ መናገር ወደ ስህተት የሚያመራው፤ የራሱን መመሪያ ቢከተል ከስህተት ይድን ነበር..
ሁለተኛው የሁነት ስህተት ነው፣ ይህም የሆነውን እንዳልሆነ፣ ያልሆነውን እንደሆነ እያደረጉ መናገር ነው፡፡ በአገር ጉዳይ በምንነጋገርበት ጊዜ ምንም ያህል የስልጣን ሰይፍ ብንታጠቅም በአገር ጉዳይ ሁላችንም እኩል ነን፡፡ ስለዚህም ለእውነት ምስክር የሚሆኑ ሰዎች አይጠፉምና እውነቱን በሻሽ መሸፈን እውነቱን ላይሸሽገው ተናጋሪውን ከባድ ትዝብት ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ስብሓት ስለአፄ ኃይለ ስላሴና ስለደርግ፣ እንዲሁም ታች ወርዶ ስለሽፈራውና ስለእኔ የሚናገረው እንኳን መመርመርና ማጣራት ቆም ብሎ ማሰብ የሌለበት አፍ ላይ የወጣውን መወርወር ነው፤ በማንአለብኝነት ጭልጥ ብሎ ወደስህተት መግባት፤ ለምሳሌ፤… በደርግ ዘመን የኤርትራ ..መሬትዋና ባህርዋ እንጂ ህዝቡ አያስፈልገንም የሚል በግልጽ ተዘመረ፤ የተግባር መመሪያም እሱ ሆነ፤.. ስብሓት ነጋ ይህንን የደርግ መመሪያ የሚለውን የሰማው በህልሙ ይመስለኛል፤ እውነት ከሆነ እኔን ትልቅ ነገር አምልጦኛል፡፡
እንዲሁም ቀደም ሲል በወጣው ጽሑፉ ላይ ሽፈራውና መስፍን ..ማህበረ ቅዱሳንን በጥናት ጉዳዮች ይደግፋሉ.. የሚለው የጤፍ ቅንጣት ያህል እውነት የለውም፡፡ እኔ ስለማህበሩ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ በመሬት ላይ የማውቀው ቅዱስም የለም፤ ከየት አንስቶ እንደለጠፈብኝ አላውቅም፡፡ መጥፎና ግልፅ ተንኮል ነው፡፡ የጎሳው ውንጀላ አነሰኝና አሁን ደግሞ የሃይማኖት ውንጀላ የሚጋብዝ ተንኮል ይመስላል፡፡ እኔ ይህንን መጨበጫ የሌለው አሉባልታ ከየት አገኘኸው ብዬ አጥብቀ አልጠይቅም፤ አቶ ተመስገን ለአቶ ስብሓት ጥያቄዎች በማስረጃ እንደመለሰው ስብሓት ሊመልስ አይችልም፡፡
ስብሓት ነጋ ስለወያኔ ድርጅት የሚናገረው እኛ ሃያ ዓመታት ሙሉ ከተከታተልነውና ከአወቅነው በፍፁም የተለየ ነው፡፡ ምናልባት እሱ ከፍ ብሎ ማማው ላይ ተቀምጦ የሚታየውና እኛ ታች ሆነን የሚታየን አይመሳሰልም ይሆናል፤ የምንሰማው ግን ጆሮአችንን ካልደፈንነው በቀር ሊለያይ አይችልም፤ ከወዲያ ማዶ እግዚአብሔር አቶ አስገደ ገብረ ስላሴ የሚባል ሰው አስነስቶ ያልተበረዘውን ደረቁን እውነት እንዲመሰክር እያደረገልን ነው፡፡ ስብሓት ነጋ ጥላሸት እንዳይቀባቸው እንጂ አንገፍግፎአቸው ከተሰደዱትም ምስክሮችን መጥራት ይቻላል፡፡ አቶ ስብሓት እናንተን ማየቱና እናንተን መስማቱ አቃተኝ ከአለ አቶ አስገደን ቢያዳምጥ እውነቱ ይገለጥለታል፡፡ ነገር ግን እውነቱ ቢገለጥለትም የማይቀበለው ከሆነ ለአክሱም ጽዮን እንሳልለታለን፡፡
አቶ ስብሓት ነጋ ህወሓት የሚማር ድርጅት ነው ሲል ህወሓት እንኳን መማርና የተማረ ሰው አጠገቡ እንደማያስደርስ ሃያ ዓመታት ሙሉ ያወቅነውን ሊያስክደን ነው? መማር የሚለው በተላላኪና በዶላር የሚገኘውን ዲግሪ ይሆን? ስብሓት ነጋ እየደጋገመ ስለታሪክ ይናገራል፤ የዛሬ መቶ ዓመትና ሁለት መቶ ዓመት የሆነውን ከማውራት የዛሬውን ምስክርነት ማስተካከሉ አይበልጥም ወይ? የህሊና ፍርድም ለመስጠት ከደረቁ እውነት መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የአድዋን ጦርነት እናንሳ አፄ ምኒልክ ከደቡብ፣ ከምዕራብና ከምስራቅ ጦራቸውን ሰብስበው ለጦርነት ሲዘጋጁ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባቸው? መንገዱ ምን ያህል ጊዜ ወሰደባቸው? የምኒልክ ጦር ከኢጣልያ ጦር ጋር ሲወዳደር ምን ያህል የሰለጠነ ነበር? የምኒልክ መሳሪያ ከኢጣልያ ጋር ሲወዳደር እንዴት ነበር? ስብሓት ሊመልሰው የሚገባ ሌላም በጣም በጣም ዋና ጥያቄ አለ፤ …አፄ ምኒልክ ጦራቸውን ሰብስበው በእግርና በበቅሎ ከደቡብ ተነስተው ትግራይ እስቲደርሱ ኤርትራና ትግራይ ምን አድርገው ጠበቁዋቸው? የኢጣልያ ጦር ትግራይን ሰንጥቆ አምባ አላጌ እስቲደርስ ማን ሊያቆመምው ሞከረ? የኢጣሊያ ጦር መቀሌ ገብቶ ሲመሽግ ማን ተከላከለው? ስብሓት እስከዛሬ ሳይገለጥለት ቀርቶ ከሆነ የኢጣልያንን ጦር ከአምባ አላጌ ያስወጣው የምኒልክ ጦር ነው፡፡ ከመቀሌም ምሽግ ያስወጣው የጣይቱ ዘዴና የምኒልክ ጦር ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ተሸፋፍኖ የቆየውን እናፍረጥርጠው ከተባለ ለማን አሳፋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡
ስለአድዋው ጦርነት ምስክርነት የሚሰጠን ገለልተኛ ታዛቢ እስክናገኝ ስለማይጨው ጦርነት የነበረ የዓይን ምክስር አንድ በቅርቡ ያነበብሁት መጽሐፍ ትዝ አለኝ፤ አንድ የቼኮዝላቫኪያ ጎበዝ የጻፈውን የሃበሻ ጀብዱ የሚል መጽሐፍ ተጫነ ጆብሬ መኮንን የተባለ ሰው የተረጎመውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳትሞታል፤ አቶ ስብሓት ብቻ ሳይሆን ማንበብ የሚችል ሁሉ ሊያነብበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፤ እኔ ፈረንጅ ስለኢትዮጵያ የፃፈውን ማንበብ ከተውሁ ብዙ ዓመታት ሆኖኛል፡፡ ይህንን ግን በአንድ ቀን ተኩል ጨረስሁት፤ የኢትዮጵያን ዘማቾች ከኋላ እያጠቁ ስለነበሩት ..የትግራይ ሽፍቶች.. ማን ይናገር? የነበረ፤ ነውና እንዲህ ይላል፡-
….የትግራይ ሽፍቶች) ለምን ወንድሞቻቸውን ይገድላሉ?… ከመሀል አገር ስድስትና ሰባት ወር ሙሉ ፍዳውን እያየ ሲጓዝ ከርሞ እዚህ የደረሰው ወንድማቸው፣ የነዚህን ምስኪኖች ህይወትና ንብረት ከጠላት ለመከላከል የገዛ ህይወቱን አልጋ ላይ ጥሎ፣ ቤት ንብረቱን በትኖ መከራውን ባየ ለምን ይገድሉታል?..
እነዚህ ሽፍቶች ወንድሙን የገደሉበት አብቹ የሚባል የአስራ ስድስት ዓመት የሰላሌ ዘማች በጣም ተናዶ የራሱን የግል ቡድን አቋቁሞ ያሳድዳቸው ነበር፡፡
ከዚያም በላይ እህል ውሃ ለዘማቹ እንዳይሸጡ ኢጣልያኖች በመከልከላቸው ዘማቾቹ ችግር ነበረባቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ለመናገር አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህንን እውነት ለመሸፈን በመሞከር የመሀል አገሩን ሰው መወንጀል ትክክል አይደለም፤ እውነት ተደብቆ አይቀርም፡፡
እንነጋገር ማለት አንድም ሆነ ሁለት የጋራ ችግር አለን ማለት ነው፡፡ እንነጋገር ማለት የጋረ አገር፣ የጋራ ወገን፣ የጋራ ሀብት፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ራዕይ አለን ብለን ማመን ነው፡፡ እንነጋገር ማለት እውነትን በማስረጃ አስደግፎ ነው፤ እንነጋገር ማለት እንግባባ ማለት ነው፤ እንግባባ ማለት ባንስማማም እንፋቀር፣ አንሸዋወድ፣ አናስሸብር ማለት አይደለም፡፡
በመጨረሻ ግራ ያጋባኝ ነገር አለ፤ አቶ ስብሓት ደጋግሞ ለኤርትራ መከታ መስጠት አለብን ሲል ከዝምድና ስሜት የመነጨ ነው ወይስ…፤ እንዲያውም ኤርትራን ..ከውጭ ወራሪ ለመከላከል እንኳን ገንዘብ ህይወትም መቆጠብ የለብንም.. ይለናል አቶ ስብሓት፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ይህንን ቢሰማ የሚቆጣ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አይቆጣም..
የእኔ አድናቆት ችግር እንዳያስከትል እንጂ ኢትዮጵያ እንደ አቶ አስገደ ገብረስላሴ ያለ ሰው እንዳታጣ የእግዚአብሔር በጎ መንፈስ አይለያት፡፡

The PDF file, hereunder:

https://jontambek.files.wordpress.com/2011/08/doc23.pdf

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: