ዳንዲ – የነጋሶ መንገድ [Preview]

27 Jul

እጅግ በጣም አስቸኳይ
..ለአቶ መለስ ዜናዊ
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ርዕሰ መስተዳደር
አዲስ አበባ
በህወሓት አመራር ውስጥ በተፈጠረው የአመራር ክራይስስ መንግስት በማያገባው የህወሓት የውስጥ ችግር ውስጥ እንዲገባና የህወሓት ሊቀመንበር የመንግስት ስልጣኑን በመጠቀም ፀረ-ህገ መንግስት፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ፣ ህገ ወጥና ሰብአዊ መብትን የሚገፉ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡
በተለይ እኔን እንደ አንድ ዜጋም ሆነ እንደርዕሰ ብሔርነት መብቶቼን የሚገፉ እርምጃዎችን የህወሓት ሊቀመንበር እያካሄደብኝ ነው፡፡ በዚህም መሰረት
ሀ/ ዜጐች ገብተው እንዳያገኙኝ እየተደረገ ነው፡፡
ለ/እኔ የምፈልጋቸውን ዜጐች እንዳላገኝ እየተደረገ ነው፡፡
ሐ/ እንደ ርዕሰ ብሔርነቴ በስፖርት መክፈቻ በዓል ላይ እንዳልገኝ ተደርጐአል፡፡
መ /የኔ ጠባቂዎች ከመደበኛ ስራቸው ተነስተው ሌላ ስራ እንዲሰሩና የዜጐችንና የእኔንም መብቶች በሚገፋ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህ (እኔን በተመለከተ) ህገወጥ፣ ፀረ-ህገ መንግስት፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ሰብአዊ እርምጃዎች እንዲቆሙ ለቋስሰበቈሽ..ቨእና ለመከላከያ መዋቅሮች የተላለፈው መመሪያ ባስቸኳይ እንዲነሳ አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት
…..ብታምኑም ባታምኑም ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የሚያስፈራራ እና የሚያዝ ደብዳቤ የፃፉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ.. ናቸው፡፡ የሚገርመው የዶ/ሩ ደብዳቤ የተፃፈው በ9/07/93 (ዶ/ሩ የኤፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳሉ) ነው፡፡
…ከስልጣን ከተነሱ እና ከገዥው ፓርቲ አመራርነትም ሆነ አባልነት ከለቀቁ ከ10 ዓመት በኋላ የቀድሞው የኦህዴድ የስራ አስፈፃሚ አባል እና የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በርካታ ሰነዶች፣ ሚስጥሮች፣ መረጃዎችን እና የህይወት ታሪካቸውን የያዘ መጽሐፍ ..ዳንዲ – የነጋሶ መንገድ.. በሚል ርዕስ በዚሁ ሳምንት ጀባ ብለውናል፡፡
መጽሐፉ በ384 ገፅ የተዋቀረ ሲሆን በስድስት ምዕራፍ ተከፍሏል፡፡ በእርግጥ ስድስተኛው ክፍል ..አባሪ ዶክመንት..የያዘ ነው፡፡ እነዚህ ኦርጅናል ዶክመንቶች የያዙት መረጃ ብቻውን ዳጎስ ያለ የታሪክ መፅሐፍ ይወጣዋል፡፡ ዶክመንቶቹ በተለይም ከ1983-1993 ስላለው የኢህአዴግ እና የኦነግ ፖለቲካ፤ እንዲሁም ስለ1993 የህወሓት ክፍፍል እና የእህት ድርጅቶች ተቋም የነበሩ ብዥታዎችን በሚገባ ያጠራሉ፡፡ አባሪ ዶክመንቶችን ከያዘው ክፍል ባሻገር ያሉት አምስቱ ክፍሎች በአዳዲስ መረጃ፣ በአንዳንድ ሚስጥሮች እና መሰል ጉዳዮች በእጅጉ የተብራራ እና መሳጭ ታሪክ እናገኛለን፡፡
ዶ/ር ነጋሶ መጽሐፉን አስኪብርቶ እና ወረቀት ይዘው አልፃፉትም ይልቁንም ለጋዜጠኛ ዳንኤል ተፈራ ተረኩለት እንጂ (ዳንኤል የፍትህ አምደኛ ነው..፡፡ እናም ዶ/ሩ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ስለነበረው የዘር ሀረጋቸው አንስተው እስከ መድረክ ድረስ ያለውን የፖለቲካ ጣጣ ፈንጣጣዎች አንድም ሳያስቀሩ መቅረፀ-ድምፅ ይዞ ለ3 ወራት ከቤታቸው ለከረመው ጋዜጠኛ ተረኩለት ጋዜጠኛውም እንደወረደ መጽሐፍ አደረገው ..ዳንዲ-የነጋሶ መንገድ.. ሲል ሰይሞ፡፡
መፅሐፉን አግኝቼ ከአነበብኩ በኋላ በያዘው መረጃ ተደመምኩ፡፡ ተደምሜም ሳበቃ ከአስደመሙኝ በርካታ ጉዳዮች ጥቂቱን ጨልፌ የፍትህ አንባቢዎችን ላስደምም አሰብኩ፡፡ እነሆም ሞልቶ ከፈሰሰው ታሪክ በማንኪያ ላቀብላ…
ዶ/ሩ ስለዘር ሀረጋቸው ከተረኩት ውስጥ ..ሞኙና ጀግናው ሰምበቶ ገዳ.. በሚል ንዑስ ርዕስ ስለቅድመ አያታቸው ሰምበቶ ገዳ የተረኩት ወግ ዘና የሚያርግ እና ጣፋጭ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በተለይም ደንቢዶሎ ውስጥ
..ሰምበቶ ገዳ ፈርዳ ሌንጂሳ
ፈፈቶ ዳዳ ነኮጄል ችሳ.. እየተባለ የሚዘፈንለት ሰንበቶ ገዳ የማታ ማታ ኩሬ በምትባለው መንደር የታወቀ ጀግና እና ፈረስ ጋላቢ ቢሆንም ከልጅነት እስከወጣትነት ድረስ ባለው እድሜው የሚታወቀው በሞኝነቱ ነው፡፡ እናም ሰንበቶ እንዲህ አደረገ እንዲህ ተናገረ እየተባለ የሚነገርለት ሰው ለመሆን በቃ፡፡ ከሰንበቶ ገጠመኞች አንዱን ብናየው ..አንድ ጊዜ ደግሞ ጥቅምት አካባቢ ሰምበቶ ገዳ ከእናቱ ጋር የጤፍ ማሳ ለማረም ይሄዳል የጤፍ ማሳ ሲያይ የመጀመሪያው ነበር፡፡ አረም እየነቀሉ እያለ ድንገት ንፋስ የጤፉን ዛላ ከላይ ታች ሲያምሰው የሚፈጥረውን ማዕበል መሰል ነገር ያያል፤እንዴ የእናቴ ጤፍ ወንዝ ሳይገባ ላስቁመው ብሎ በዱላው ..ቁም.. የት አባክ ልትሄድ ነው?.. ብሎ ጤፉን ደበደበው ይባላል.. እያሉ የቅድም አያቶቻቸውን ጣፋጭ ወግ ተርከዋል፡፡
…እንዲህ እያዋዛ የሚጀምረው የነጋሶ ታሪክ እንዴት የሲጋራ ሱሰኛ እንደሆኑ እየነገረን ይቀጥልና የፖለቲካ ጅማሯቸውን ያብራራል፡፡ ከሜጫና ቱለማ ማህበር እስከ ተማሪዎች ንቅናቄ ድረስ ያለውን የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ከነገሩን በኋላ ወደ ጀርመን ለታሪክ ትምህርት እንደሄዱ ይነግሩናል፡፡ ነጋሶ ወደ ጀርመን ለመጓዝ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሄዱ የሸኛቸው የቅርብ ዘመዳቸው እና የኦነግ መስራች የነበረው ሌንጮ ለታ ነው፡፡ ሌንጮ ነጋሶን ሲሸኛቸው እንደዋዛ ወግ ጀመሩ፡፡ እናም እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበላቸው
..ምን ለመማር ነው የምትሄደው?..
..ታሪክ….
..አንተ ሄደህ ታሪክ ተማር እኛ እዚህ ሆነን ታሪክ እንሰራለን..
ነጋሶ ጀርመን ገቡ፡፡ በጀርመንም አስከ ፒኤችዲ ዲግሪያቸው ድረስ ታሪክን አጠኑ፡፡ በወቅቱ በሀገር ቤቱ የፊውዳሉ ስርዓት በወታደራዊ ጁንታ ስርዓት ተቀይሮ ስለነበረ የፖለቲካው ግለት ጨምሯል፡፡ ነጋሶም በጀርመን በተለያዩ ማህበራት ሲሳተፍ ቆይተው የኦነግ አባል ሆኑ፡፡ ኦነግም በጀርመን ወኪሉ አደረጋቸው፡፡ ይህን በእንዲህ እንዳለ ደርግ ስለገደላቸው ቄስ ጉዲና ቱምሳ አዲስ መረጃ እናገኛለን፡፡ ደርግ ቄሱን የገደለው ..ኦነግ.. ብሎ ሲሆን ደርግ ከወደቀ በኋላ ደግሞ የቄሱ አስከሬን ከጅምላ መቃብር ወጥቶ በስርዓት በተቀበረበት ጊዜ ደርግ ቄሱን የገደለው የሃይማኖት ነፃነትን ለማፈን ነበር ተብሎ የተነገረውን ነጋሶ ይሽሩታል… ..በ1969ዓ.ም ቄስ ጉዲና ለቤተክርስቲያን ስራ ወደ ጀርመን ሲመጡ እግረ መንገዳቸውን ከኦነግ መልእክት ይዘው መጥተው ነበር፡፡ መልዕክቱን ለመንገር መጀመሪያ ዲማ ነገዎ ማስትሬት ዲግሪውን እያጠና ከነበረበት ሴኔጋል ወደ ጀርመን እንዲመጣ አደረጉና ከዚያ ፍራንክፈርት ከእኔ ጋር ተገናኙ፡፡ ለእሱ የመጣው መልዕክት ጀርመን ሀገር ቢሮ በመክፈት የኦነግ ወኪል ሆኖ እንዲሰራ የሚል ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ዲማን እንድረዳ ነበር የተፈለገው… ሌላው ቄስ ጉዲና የሰጡኝ መረጃ ኦነግ በመካከለኛው ምስራቅ አንድ ልዑክ እንደሚልክና ልዑኩ በባሮ ቱምሳ እንደሚመራ የሚጠቁም ነበር፡፡…ቄስ ጉዲናን ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘኋቸው ያኔ ነው፡፡ ደርግ ሀገር ቤት ሲገቡ እስር ቤት አስገብቶ ገደላቸውና ከሌሎች ጋር በጅምላ ተቀበሩ.. (ገጽ 110)
ከዚህ በኋላ ነጋሶ በጀርመን የነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ በስፋት ይተርክና በስተመጨረሻም ከኦነግ እንደወጡ እናያለን፡፡ ከዛስ? ..ዳንዲ.. ቀጥሎአል…ልክ ግንቦት 20 ቀን 1983 በሱዳን አቋርጠው ኢትዮጵያ ገቡ ..ሌላው መተማ፣ ጎንደርና ባህር ዳርን አልፈን ነቀምት እስክንደርስ ያስተዋልኩት ነገር የህወሓትን የበላይነት ነው፡፡ ሰራዊቱና አመራሩ በየመንገዱና በየኬላው ሁሉ የሚታየው ታጋይ የትግራይ ተወላጅ ነው… ያረፈበት ቤት ግድግዳ ላይ በትግረኛ የተፃፉ ጥቅሶች ተገጥግጠውበታል፡፡ እዚህ ኦሮሞዎች የሉም እንዴ? ብዬ አንዲቷን የቡድን መሪ ጠየኳት፡፡ ..አንድ ዘበኛ አለ.. አለችኝ.. የሆነ ሆኖ እዛው ኦሮሚያ ውስጥ ኦነግ የግድያ ሙከራ አድርጎባቸው ለጥቂት ከተረፉ በኋላ አዲስ አበባ መጡ፡፡ ከዛም ኦህዴድን ተቀላቀሉ፡፡
በአዲስ አበባም አዲስ መንግስት ተመስርቷል፡፡ ..የሽግግር መንግስት.. የሚባል ይሄ መንግስትም የሚተዳደረው ..የሽግግር ቻርተር.. በሚል ስያሜ በተዘጋጀ ደንብ ነው፡፡ ቻርተሩን ማን አዘጋጀው የሚለውን ነጋሶ ይነግሩናል ..መለስ ዜናዊ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ እና ሌንጮ ለታ.. ሲሉ አያይዘውም በወቅቱ ..ሻዕቢያ እና ህወሓት ከኦሮሚያ ብር ዘርፈዋል፡፡ የጦር መሳሪያም ወደ ትግራይ እና ኤርትራ በገፍ ጭነዋል.. ይሉናል፡፡
..የነጋሶ መንገድ.. መጽሐፍ ኦነግ ከሽግግር መንግስት ስለወጣበት ምክንያቶች በዝርዝር ይተነትናል፡፡ እናም ኦነግ እንዴት ራሱን ለኢህአዴግ እንዳጋለጠ እና የሰራቸውን ስህተቶች፣ ያደረገውን ጭፍጨፋ ቃል በቃል በመጽሐፍ ተገልጿል፡፡ ..በደኖ የኦህዴድ ደጋፊ የነበሩና ኦሮሞ ያልሆኑ ከ180 በላይ ግለሰቦች ወደ ገደል ተወርውረው በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል….ገፅ 149) በኦነግ፡፡ እዚህ ገፅ ላይ ሌላው አስደማሚ ታሪክ በወቅቱ የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የኦነጉ አቶ ደሜ ነገዋ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርብ የነበረው ፕሮግራም ነው፡፡ …..ትግራይ ፣የድንጋይ ሀገር፣፣ ጎጃም ፣የአህያ ነጂዎች ሀገር፣፣ ጉራጌ ፣የእንስሳት በሊታዎች ሀገር፣… የሚሉ አስነዋሪ የስድብ ሀተታዎች ፣ ዘረኛ ፕሮፓጋንዳዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻ ዎች ይተላለፉ ነበር፡፡ እኔን ፣ነጋሲ ግደይ፣ እያሉ ስሜን ሲያጎድፍ ነበር.. ሲሉ ነጋሶ የተረኩልን የመንግስት ጋዜጠኞችን ተግባር በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡
ሌላው ከነጋሶ የምናገኘው አዲስ ነገር አቶ በረከት ስምኦን የሚመለከት ነው፡፡ አቶ በረከት በጎንደር ተወልደው ያደጉ ቢሆንም ከኤርትራውያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው የነጋሶ መጽሐፍ ይተርካል ..የነፃነታቸው ቀን ሲከበር መለስ ኤርትራ ሄዶ በትግረኛ ንግግር ሲያደርግ እኔም ነበርኩ፡፡ እኔ፣ መለስ እና ኢሳያስ (ሲሊፐር ጫማ አድርጎ) ከተማ ውስጥ ዞረናል፡፡ በእውነት ትልቅ ነፃነት ነበር የተሰማኝ ሱቅ እየገባን ማታ ማታ እየዞርን አንድ ሁለት ቦታ መጠጥ እየተጎነጨን ተዝናንተናል፡፡ ያረፍነው በራስ ካሳ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ እነ በረከትም በበዓሉ ላይ ነበሩ፡፡ በረከት ከኤርትራም እንደሚወለድ ያወቅኩት ያን ጊዜ ነው፡፡ አንዳንዴ ዘመዶቼን ልጠይቅ እያለ ይሄድ ነበር… ኤርትራዊ መሆኑን እሱም ነግሮኛል፡፡ የመለስን ግን አላውቅም.. (ገጽ 176..፡፡
ነጋሶ ከኦነግ ከወጣ በኋላ የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ስለ ሁለት የስራ ኃላፊዎች ባህርይ ይነግሩናል፡፡ ስለ አማረ አረጋዊ (የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት) እና ተስፋዬ ገብረአብ፡፡ እንዲህ በማለት …..አንዳንዶቹ የአቅም፣ ሌሎቹ የሙያ፣ቀሪዎች ደግሞ የስነ ምግባር ችግር ነበረባቸው፡፡ ለምሳሌ ሙስናን መጥቀስ ይቻላል፡፡… ብዙዎቹ ወደ ኢህአዴግ ተቋማት ፋና፣ ዋልታ፣ ሲዛወሩ ተስፋዬ ገ/አብ ወደ እፎይታ መጽሔት ተልኳል ከናካቴው እንዳይባረሩ ደግሞ ሁሉም ታጋዮች ናቸው፡፡ በተለይ የማስታውሰው አሁን የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት የሆነውን አማረ አረጋዊን ነው፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ኀላፊነት አውርደን ወደ ኢዜአ ላክነው፡፡ ኢዜአ እያሉ አንድ ደብዳቤ ከኪራይ ቤቶች ተላከ፡፡ ደብዳቤው አቶ አማረ በ1983 ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ አንድ ቤት እንደተረከበና በሂደት ሌላ ቤት እንዲሰጠው መጠየቁን እነሱም ቤት አድሰው እንዲሰጡትና የቀድሞው ቤቱን ቁልፍ እንዲያስረክብ ሲጠይቁት ቁልፉን ለጓደኛው ሰጥቶ ስለነበረ አልመልስም ብሎ እየተሳደበ ሄደ፡፡አዲሱን ቤት ሰብሮ መግባቱ ስለሆነ መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ነው፡፡ እኛም አማረን ጠርተን የግለኝነት ስሜት አለብህ በጓደኝነት መስራት በራሱ ሙስና ነው፡፡ ስለዚህ ሂስህን ተቀበል አልነው… አልቀበልም አለምሰገድ ጋር እሄዳለሁ አለ፡፡ አለምሰገድ ደግሞ እነሱ ትክክል ናቸው ብሎ ሸኘው፡፡ እሱ ግን እንደገና አይ መለስ ጋር እሄዳለሁ አለ፡፡ ሂድ አልነው፡፡ ከቴሌቪዥን ወደ ኢዜአ፤ ከኢዜአ ወደ ህዝብ ግንኙነት ያዘዋወርነው በግምገማ ነው.. (ገጽ 182..፡፡ ..ተስፋዬ ገ/አብ በአቅም ማነስ ከፕሬስ መምሪያ ተባርሮ ወደ እፎይታ መጽሔት ከሄደ በኋላ ነው ቃለ መጠይቅ ያደረገልኝ፡፡አለምሰገድን አስፈቅጄ ወደ ነጋሶ ቢሮ ገባሁ ያለው ውሸቱን ነው.. (ገጽ 186)
ዶ/ር ነጋሶ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ አድናቂ እንደሆኑም ይናገራሉ፣ ..በዚያን ጊዜ የማደንቀው ሰው ነበር ታምራት.. (ገጽ 193..፡፡ እናም በገጽ 219 እና 220 ላይ ስለታምራት ክስ፣አቶ መለስ ያቀረቡትን ሪፖርት እና የእስር ጉዳይ ሰፋ አድርገው ዘርዝረውታል፡፡
ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭት መንስኤ፣ ጦርነት፣ መፍትሄ እና ተያያዥ ጉዳዮችንም የማናውቀውንም የምናውቀውንም አካተው ሰፋ አድርገው አብራርተውልናል፡፡ ከዚህ በኋላም ዶ/ሩ የህወሓትን ክፍፍል በሚገባ ተንትነውታል፡፡ በክፍፍሉ ወቅት ደኢህዴን እና ኦህዴድ ገለልተኛ እንደነበሩ ብአዴን ግን በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን የሁለተኝነት ቦታ ወደ አንደኝነት ለማስፈንጠር ሲል ከአቶ መለስ ጎን እንደቆመ ገልፀዋል፡፡ ..አንጃ በተባሉት ወገኖች ላይ ዘመቻ ሲያደርጉ ከነበሩት ሰዎች ቀንደኞቹ በረከት ስምኦንና አዲሱ ለገሰ ናቸው.. (ገጽ 235)
ነጋሶ አቶ መለስን ከመንግስቱ ኃ/ማርያም ጋር ያነፃፀሩበትን ምክንያት ሲገልፅም …..የዛን ቀን መለስ ከፊት ለፊታችን ተቀምጦ ሪፖርት ሲያደርግ እየፎከረ ነበር፡፡ ስለመቀሌ ውሳኔ ሲናገር ፣ጃኬታቸውን አስወልቀን ራቁታቸውን አባረርናቸው.. ነበር ያለው፡፡ ያን ጊዜ ንግግሩ አንድ ነገር አስታወሰኝ፤ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በተመስጦ እያየሁት ነበር፡፡ የግንቦት 20 በዓል በተከበረ ቁጥር የሚታዩ የደርግ ፊልሞች አሉ፡፡ ከነዛ ውስጥ የኢህአዴግ ሰራዊት ሰሜን ሸዋ የደረሰ ጊዜ መንግስቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተማሪዎችን ሰብስቦ ቂጣቸውን በሳንጃ….. እያለ ነውረኛ ፉከራ ሲያሰማ የሚያሳይ ፊልም አንዱ ነው፡፡ መለስም ጃኬታቸውን አስወልቀን….. እያለ ሲፎክር ያ የመንግስቱ ፉከራ ትውስ ብሎኝ እጄን አነሳሁና አስተያየት.. አልኩኝ፡፡ አከል አድርጌም ይቅርታ አነጋገርህ መንግስቱ ኃ/ማርያምን አስታወኝ፡፡ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ.. አልኩት፡፡ ቤቱ በድንጋጤ ተናወፀ፡፡ በተለይ ከጎኔ ተቀምጣ የነበረችው ገነት ዘውዴ እንዴት ከመንግስቱ ጋር ታወዳድረዋለህ? ብላ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች.. (ገጽ 240)
በገፅ 244 ላይ ደግሞ መለስ እኔን፣ ኩማ ደመቅሳን እና ግርማ ብሩን አያምነንም ሲሉ አስግራሚ ነገር ይነግሩናል፡፡ ነጋሶ ስለ ኤፈርትም ..ደስማይል.. ሲሉ የገለፁትን የአቶ መለስን መልስ ቃል በቃል ፅፈውታል፡፡ መለስ 10 አመት ሙሉ አታሎናል ይሉና ኢህአዴግ ወደ ካፒታሊዝም ዞሯል ያለበትን መንገድ ይተርካሉ፡፡
……..ከህወሓት ስብሰባ ረግጦ የወጣው አንጃ የኢህአዴግን ማህተሞች ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ዘርፎ በኢህአዴግ ሊቀመንበርነቴ በማህተሞቹ እንዳልጠቀም ስላደረገኝ በዚህ በኢህአዴግ ሊቀመንበርነቴ በምፅፈው ደብዳቤ ላይ የኢህአዴግ ማህተም ላሰፍር አልቻልኩም፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት የጋራችን የሆነውን የመንግስት ማህተም ያለበት ደብዳቤ ከዚህ ቀደም በመፃፌ በናንተ በኩል የቀረበውን ሂስ በመቀበል ማህተም የሌለው ደብዳቤ መፃፍ የሚያስከትለውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት በኢህአዴግ ሊቀመንበርነቴ በምፅፈው ደብዳቤ ላይ የማሰፍረው ማህተም በማጣት በህወሓት ማህተም ለመጠቀም ተገድጄአለሁ፡፡ ጓዶች ችግሩ አንጃው በውስጡ ህገ-ወጥ እርምጃ ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ተገንዝበው የጋራው ማህተማችንን ባለመጠቀሜ ይቅርታ እንደሚያደርጉልኝ እተማመናለሁ፡፡..

ፍትህ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: