“ሽሚያው” የት ያደርሰናል?! Awramba times – Wubeshet Taye [‘Before his ter……..attack’ June 2011].

22 Jul

ዜናው በቀላሉ የሚታመን አይነት አልነበረም። የጠ/ሚ/ሩ የቀኝ እጅ የነበሩ ቁጥራቸው ወደሃያ የሚጠጋ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ዕውቅ ‹ነጋዴዎች› ፈጽመውታል ተብለው በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ዘብጥያ ወረዱ። ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ከሕዝቡ ላይ ዘርፈውታል የተባለው የገንዘብ መጠንም በዶላርና በብር እየተመነዘረ ተሰልቶ በመረጃ መረቦች ይፋ መሆን ያዘ። ይህንኑ ተከትሎ አንድ ድረ ገፅ ‹ኢትዮጵያ በሙስና እየተደረመሰች ነው› የሚል ዘገባ አቀረበ።ስፍር ቁጥር የሌለው የአገርና የሕዝብ ኃብት በዚህ መጠን በጣት ለሚቆጠሩ ግለሰቦች የዋለው በአንድ ጀምበር ሳይሆን ‹ተጠርጣሪዎቹ› አድራጊ ፈጣሪ ሆነው በቆዩባቸው ረዥም ዓመታት ውስጥ በመሆኑ ክንውኑ የፈጠረው አንድምታ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። መረጃው የደረሳቸውና በሁኔታው የተደናገጡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በስልክ እየተደዋወሉና ያሉትን የመገናኛ መንገዶች እየተጠቀሙ ‹ምን እየተደረገ ነው? ባለስልጣናቱ አገራችንን ምን እያደረጓት ነው?› ሲሉ በተጠቂነት ስሜት አፅንኦት ሰጥተው ተጠያየቁ። የአገር ውስጥና የውጭ ሜዲያዎች ክስተቱን ከየራሳቸው የአተያይ አቅጣጫ እየመዘኑ የውይይት መድረክ ፈጠሩ። የፖለቲካ ተንታኞች ጠ/ሚ/ሩ የዚህ አይነት ባለስልጣኖቻቸውን አሁንም በአፍንጫቸው ስር ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ጠቆሙ። ወቅቱ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነበር። መንግስት የተወሰደው እርምጃ አገሪቱ በቀጣይ ጊዜያት ለምታደርገው ሙስናን የመዋጋት ጦርነት የመጀመርያው ደረጃ ብቻ መሆኑን ቃል በመግባት የሙሰኞች ምሽግ እየተደረመሰ መሆኑን ገለጸ። ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለሙስና ምንም ታጋሽት አይኖረንም /Zero tolerance for corruption/ ሲሉ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን አበሰሩ። ይሁንና የዚህ ብስራት ተግባራዊ መገለጫዎች በእርግጥ ሙሰኞችንና ሙስናን ከምንጩ የሚያደርቁ ሆነዋል ወይስ የደባው ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ ከድርበቡ በሚጨልፍ ገርገብ የማድረጊያ ስልት አገሪቱን ራሷን በሂደት ቦርቡሮ የሚደረምስ? የሚለው ጥያቄ መፈተሽ የጀመረውም በትክክል ከዚህ ጊዜ በኋላ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ከተባለበት የ‹ዜሮ ቶለረንስ› ጊዜ አንስቶ የተጓዝንበትን መንገድ በሳይንሳዊ የግምገማ ስልት ስንፈትሸው ከአስደንጋጭ እውነታ ጋር እንደምንጋፈጥ በዓለም ዓቀፍ ተቋማትና በዘርፉ ጠበብቶች እየቀረቡ ያሉ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ባገባደድነው ዓመት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የዓለም የኢኮኖሚ ነፃነት ኢንዴክስ አገራችን ከ179 አገራት በ144 ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ‹ከሙስና ነፃ በመሆን› በሚለው መመዘኛ ደግሞ ከመቶ ያገኘችው ውጤት 27 ብቻ ነው።
‹‹ይህ ማለት…›› ይላሉ የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እያሱ ይመር የአሃዙን አንድምታ አስመልክቶ
ለአውራምባ ታይምስ ሲገልጹ ‹‹… ስልሳ ሰባት በመቶ ያህል ኮረፕትድ /የሙስና ሰለባ/ ሆነናል ማለት ነው። ባለፉት ተከታታይ
ዓመታት የነበርንበት ደረጃ ብዙ ከዚህ የተለየ አይደለም። ለነገሩ ተቋሙ አገራቱ ስላሉበት የሙስና ደረጃ በየዓመቱ ያወጣል እንጂ በንጽጽር የሚያይበት መርሕ የለውም።›› ከላይ የተጠቀሰው ተቋም ወንጀሉ በሕጉ የተደነገገ ቢሆንም በርካታ የመንግስት ሹማምንት በዘፈቀደ ሕጉን ስለሚተላለፉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመጠን በላይ በተሰራጨ የሙስና ወረርሽኝ ሁለንተናዊ ዕድገቱ እየመከነ መሆኑን ጠቁሟል። የሙስና መንስኤዎች ምንድናቸው? በፖለቲካውና በማሕበራዊው ዘርፍ የሚያስከትለውና እያስከተላቸው ያሉት ምስቅልቅሎች ምን ይመስላሉ? በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራበት ይገባል በሚባለው ማሕበረሰባዊ ግንባታ ላይ እያደረሳቸው ያሉት ውድመቶችስ ምንድናቸው? ለምንድነው የአገርንና የሕዝብን አንጡራ ኃብት በሚቦጠቡጡ የመንግስት ባለስልጣናትና ኃላፊዎች መዳፍ ስር ወድቀን አገራችን ወደ ገደል እየተገፈተረች ያለችው?
ሁኔታው ወዴት ያመራናል? ብዙዎችን የሚያሳስብ ጥያቄ ሆኗል።

እንደ “ሙሴ” መሆን ይህ ሐረግ ያለቦታው የገባ መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በፊት
ከተፈጸመ አንድ ክስተት ጋር ተያይዞ የሚነሳ እንደሆነ የቋንቋና የስነ መለኮት ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። በቅዱስ መጽሐፍ ‹ዘሁልቁ› ተብሎ በሚጠራው ክፍል /ምዕ.21 ላይ/ ሙሴና አሮን ከግብጽ ባርነት ወደ ተስፋይቱ ምድራቸው በሚያደርጉት ጉዞ ውኃ በእጅጉ ለተጠማውና በምድረ በዳ ለነበረው ነገደ እስራኤል ተአምራዊ በሆነ መንገድ ውኃ ከድንጋይ አፍልቀው ማጠጣታቸው /በፈጣሪ ኃይል/ ተገልጻDል። ምንም እንኳ ዋናው መሪ የነበረው ሙሴ የተአምራዊው ኃይል ምንጭ እሱ
እንዳልሆነ ቢያውቅም የማይገባውን ክብር ለማግኘት በመፈለግ ብቻ ውኃውን እሱ እንዳፈለቀው አድርጎ ተናገረ። በዚህ የማይገባውን ጥቅም የመፈለግ ጥፋት ግቡ አድርጎ ይጓዝባት ወደነበረችው የተስፋይቱ ምድር /ከነአን/ እንዳይገባ ቅጣት ተጣለበት። ሙስናን ኃላፊነትን ወይም አጋጣሚን ተጠቅሞ በማንኛውም መንገድ የማይገባ ጥቅምን ለራስ ወይም ለሌሎች መሻት ነው የሚለው የተጠቃለለ ኃሳብ በፌዴራል የስነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ፕሮፋይል የዚህ ዓመት ዕትም ላይ ካገኘነው ትንታኔ ጋር ይመሳላል፡፡
ተቋሙ ‹‹ሙስና ማለት በአንድ አካል ወይም በአባላቱና ኃላፊዎቹ አንድን ተግባር የመፈፀም ወይም ያለመፈፀም ሁኔታ ላይ ተገቢ
ያልሆነ ተጽዕኖ ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማስገኘት ሲባል ውለታ፣ የተስፋ ቃል፣ እጅ መንሻና ጥቅማጥቅም መስጠት ወይም መቀበል፤ በቃላት ወይም ከዚህ ውጭ በሆነ ሁኔታ ዛቻ ወይም ማስፈራራት ማድረግ እንዲሁም ስልጣንን ያለ አግባብ በመገልገል ተጽዕኖ ማሳደር ነው።›› ሲል የሚተረጉመው ሲሆን መገለጫዎቹን ደግሞ ፤- ‹‹ማታለል፣ ምዝበራ፣ ማጭበርበር፣ በሥልጣን ያለ አግባብ መገልገል፣ በዝምድናና በወዳጅነት መስራት (አድልዎ)፣ ስርቆት፣ እምነት ማጉደል፣ ሰነድ መደለዝ እና ጉቦ መስጠትና መቀበል ዋና ዋናዎቹ የሙስና መገለጫዎች ናቸው።›› ካለ በኋላ ከእነዚህ መገለጫዎች መካከል አብዛኛዎቹ በኮሚሽኑ የእስከአሁን የሥራ እንቅስቃሴ በተግባር የታዩ መሆናቸውን ገልጻDል።
ለሙስና መንስኤነትና ስር መስደድ የተለያዩ ግብአቶች አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይገለጻል። በጀርመን የ‹ዴቨሎፕመንት› ኢኮኖሚክስ
መምሕርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ፍቃዱ በቀለ የፓርላሜንታዊ
ዴሞክራሲ ዕጦትን በዋንኛነት ያነሳሉ።

‹በአገራችን ያለው ችግር ዕውነተኛ የፓርላሜንተሪ ዴሞክራሲ ያለመኖርና
በፓርላሜንቱ ውስጥ ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ መቀመጫውን የያዘው
ራሱ ገዢው ፓርቲ ስለሆነ መንግስትና ፓርላሜንቱ እጅና ጓንት መሆናቸው
ነው።›› እንደ ዶ/ር ፍቃዱ እምነት በእንደዚህ አይነት የአሰራር ግልጽነት
በሌለበት አገርና የአንድ ፓርቲ የበላይ ፈላጭ ቆራጭነት በሰፈነበት አገር
ሙስናን የሚዋጉ ተቋማት ቢፈልጉ እንኳ ተግባራቸውን ሊወጡ በፍጹም
አይችሉም ።

ቀደም ሲል የጠቀስነው የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ፕሮፋይል በበኩሉ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎችን በመጥቀስ ‹‹የዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር በሚፈለገው ደረጃ አለመጎልበት፣ ተቋማዊ ቁጥጥር በሚፈለገው ደረጃ አለመጎልበት፣ ድህነት፣ ሙስናን የሚያበረታቱ ጎጂ ባህሎች መኖር፣ የፕራይቬታይዜሽን ሂደት፣ በሚፈለገው መጠን ያልተገነባ የፋይናንስ ስርዓት፣ በኦዲትና በአካውንቲንግ ዘርፎች የሚታየው የእውቀትና የክህሎት ማነስ እንዲሁም የመልካም ሥነ ምግባር እሴቶች መሸርሸር በዋና ዋና መንስኤነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው።›› ሲል ይዘረዝራል።
በመጨረሻ ላይ ያነሳው ግን በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያለውን ለምዝበራ የሚያጋልጥ ብልሹ የአሰራር ስርዓት ነው። ‹‹ምንም እንኳን
ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እየታየበት ቢመጣም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታየው የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘት ለሙስና መንስኤነት የሚጠቀስ ነው›› ይለዋል። ይህ ሁኔታ በየዓመቱ ለፓርላማ በሚቀርበው የዋና ኦዲተር ሪፖርት ውስጥ ገዝፎ ይንጸባረቃል።

የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት
በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ያለፈውን በጀት ዓመት ሂሳብ የፌዴራል መንግስት መ/ ቤቶች ኦዲት ሪፖርት አቅርቦ ነበር። ሪፖርቱ እንደሁልጊዜው ሁሉ የመንግስት ተቋማትን ገመና ገልጦ ያሳየ ተብሎለታል። ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለምዝበራና ብክነት መንገድ የሚከፍቱ ካላቸው የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ምርመራዎች ውዝፍ የሰነድ ሂሳብ (በ43 የፌ/መ/ቤቶች)፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ ወጪ የተደረገ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ (በ16 መ/ቤቶች)፣ ደንብና መመሪያ ሳይከተል በተደረገ ግዥ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ /በ32 መ/ቤቶች/፣ ደንብና መመሪያ ሳይከተል ያለአግባብ የተፈፀሙ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ /በ22 መ/ቤቶች/፣ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጭ የተመዘገበ፣ የንብረት ገቢ
ደረሰኝ ያልቀረበበት፣ ወዘተ፣… በዝርዝር ቀርቧል።
በተለይ የኦዲት ሪፖርቱ ምርመራ ለምዝበራና ብክነት በር የሚከፍት ግኝት ላይ ደረስኩባቸው ያላቸው ተቋማት ማንነት የብዙዎችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፣ በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ዳይሬክቶሬትና የመሳሰሉት የኦዲት ግኝት ይፋ ሲደረግ ‹ምንም አንታገስም› በሚል ከአስር ዓመታት በፊት በቁርጠኝነት እንደተጀመረ የተነገረለት ሙስናን መዋጋት በዝርክርክና ለምዝበራ በእጅጉ በተመቻቹ አሰራሮች መምከኑን አመልካች ነው ተብሏል። የዋና ኦዲተር ሪፖርት ለፓርላማ የሚቀርብበት ጊዜና የሚሸፍናቸው ጉዳዮች የተሟሉ ያለመሆንም ችግሩን ድርብርብ አድርጎታል የሚል ቅሬታ ይቀርባል። ከኦዲተር መ/ቤቱ በተጨማሪ የፀረ- ሙስና ኮሚሽን በየጊዜው የሚደርስበትን የምርመራ ግኝትና ችግሮች ለፓርላማ ማቅረብ ቢኖርበትም የዚህ አይነቱ አሰራር ያልተተገበረበት ምክንያት ይተቻል።__

ዶ/ር ፍቃዱ በቀለ ‹‹በመሰረቱ እንደዚህ አይነቱ ኮሚሽን በፓርላሜንቱ ቁጥጥር ስር መሆን ያለበትና የስራውን ውጤትና በየጊዜው በየመስሪያ ቤቱ የሚገጥመውን ችግርና ችግሩን ለመቅረፍ መወሰድ ስለሚኖሩባቸው እርምጃዎች በሪፖርት አጠናቅሮ
ለፓርላሜንቱ ማቅረብ ነበረበት።›› ካሉ በኋላ ይህ በተጨባጭ አልሆነም ስላሉበት ምክንያት ሲገልጹ፤- ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ መታየትና መመርመር ያለበት ጉዳይ እራሱ የስነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ይህንን ከፍተኛ ኃላፊነትና ያለበትን
የጠቅላላውን ሕዝብ ህይወት የሚነካ ተግባር ለመወጣት የሞራል ብቃት ኖሮት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይችላል ወይ?›› ሲሉ ይጠይቃሉ። የዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ምሁሩ በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ አይነት ኮሚሽን በመንግስት ቁጥጥር ስር ከሆነና ተጠሪነቱም ስልጣንን ለጨበጠው አገዛዝ ከሆነ ኃላፊነቱን በብቃትና ስነ-ምግባር በተሞላበት ሁኔታ ሊወጣ እንደማይችል ያሰምሩበታል።

“በአሮጌው ጨርቅ
ላይ አዲስ እራፊ…”
ሪፖርቱ ሲቀርብ
በስፍራው የነበረው የአውራምባ ታይምስ የፓርላማ ዘጋቢ ለዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አጠቃላይ የሀገሪቱን በጀት አጠቃቀም የኦዲት ውጤት በሪፖርቱ ውስጥ ለምን እንዳልተካተተ ጠይቋቸው ከሚኒስቴር
መ/ቤቱ ጋር የመውጫ ስብሰባ ባለመደረጉ መሆኑን መግለጻቸው ለብዙዎች ሚዛን የሚደፋ ምላሽ አልሆነም፡፡
ይህ ‹‹የመውጫ ስብሰባ›› የሚደረገው በኦዲተሮች ‹‹ግኝት›› ተብለው የተለዩ ጉዳዮች ላይ በቂ ማብራሪያ ሚኒስቴር መ/ ቤቱ እንዲያቀርብ ዕድል መስጠት ስላስፈለገ መሆኑን ቢገልጹም ያለፈው ዓመት በጀት በአስደንጋጭ የአሰራር
ምስቅልቅሎች ተተብትቦ ባለበት ሁኔታ የቀጣዩን ዓመት በጀት ለማጽደቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚ ባለሙያዎች “በአሮጌው ጨርቅ ላይ አዲስ እራፊ እንደመጣፍ” ሆኖባቸዋል።

የሪፖርቱ መዘግየት

ወይም በ11ኛው ሰዓት መቅረብ ግን የዋና ኦዲተር መ/ ቤት ጥፋት ተደርጎ መወሰድ የለበትም ሲሉ አቶ ገመቹ ተከራክረዋል። መከራከርያቸው ‹‹እኛ ሪፖርት የምናቀርበው ም/ቤቱ በሚያወጣው መርኃ- ግብር መሠረት ነው። ቀደም ብለው ቢጠይቁ ኖሮ ሚያዚያ ላይም ማቅረብ እንችል ነበር።›› የሚል ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው አጠቃላይ የሀገሪቱን በጀት አጠቃቀም የኦዲት ውጤት ያላካተተው የኦዲት ግኝት በራሱ እንኳ በአገሪቱ አንገብጋቢ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ አውታሮች ላይ የሰፈፈውን የድርመሳ ሽሚያ በግልጽ አመልካች ተደርጎ ተወስዷል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሲገለጥ… ያለአገልግሎት ከተቀመጡትና ከአቅም በታች እያገለገሉ ካሉት ውጪ የኃይል እጥረት እንዲያቃልሉ በሚል ምክንያት ኮርፖሬሽኑ 60 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ጀነሬተሮች ተከራይቶ ለኪራይ 10 ሚሊዮን 368 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ ቢያደርግም
ኮርፖሬሽኑ የራሱ ንብረት የሆኑትን ጀነሬተሮች በሙሉ አቅማቸው ቢጠቀምባቸው ኖሮ 62 ሜጋዋት ማመንጨት ይችሉ እንደነበርና ለኪራይ የወጣውን የውጪ ምንዛሪ ሊያስቀር ይቻል እንደነበር በጎፋ፣ በድሬ ዳዋ፣ በሻሸመኔና በሐዋሳ በሚገኙ
ዕቃ ግምጃ ቤቶች በመጋዘን ውስጥ ሊቀመጡ የማይችሉ ንብረቶች ለፀሐይና ለዝናብ ተጋልጠው እና በግቢው ውስጥ ቢጠፉ እንኳን በማይታወቅበት ሁኔታ ተዝረክርከው ሳር በቅሎባቸውና አቧራ ለብሰው ተቀምጠው መገኘታቸው… ወዘተ የሚሉት ግኝቶች በሕዝብ
ኃብት ላይ የሚፈጸመውን ውድመትና የተጠየቅ አልባነት መንሰራፋት ያጋለጠ ሆኗል።
ሌላው ሲዘርፍ እኔም
አብሬ ልዝረፍ
ዶ/ር ፍቃዱ የሚባክኑት ኃብቶችና የሚዝጉት ዕቃዎች የህዝብ ሀብት በመሆናቸው ማንኛውም ሰራተኛ በመንግስት ወይም መንግስት ነክ መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ ቢሰራም የህዝብ አገልጋይ መሆኑን መርሳት እንደሌለበት የሚያሳስቡት በዚህ ዓይነቱ የተዝረከረከና ኃላፊነት የጎደለው አሰራሩ ለታዳጊው ትውልድም መጥፎ አርአያ እንደሚሆንና ምናልባትም ከመንግስት ጋር መቃቃር ማለት ከህዝብ ጋር መጣላት አለመሆኑን ማንኛውም የመስሪያ ቤት ሰራተኛ መረዳት እንዳለበት በማስታወስ ነው።
ኤ ች . አ ይ . ቪ / ኤ ድ ስ ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚል ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ በሚገኝ ወገኖች ስም የሚሰባሰበው ገንዘብና ቁሳቁስም እንዴት እየዋለ እንዳለ መመልከቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል። አሁንም ከፓርላማ ዘጋቢያችን ሐተታ
ስንቀነጭብ፤-

‹‹…የሀገር አቀፉን የማስተባበሪያ ዘዴ ቢሮ ፈቃድ ሳያገኝ በአጠቃላይ 201 ሚሊዮን
449 ሺህ 630 የኢትዮጵያ ብር እና አንድ ሚሊዮን 623 ሺህ 466 የአሜሪካ ዶላር
በተለያዩ መ/ቤቶችና በክልል ጽ/ቤቶች ከተፈቀደለት ተግባር ውጭ ወደሌላ እንዲተላለፍ
ተደርጓል። የተለያዩ የመንግስት ሴክተሮችና አስፈፃሚ አካላት ለፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ተግባራት
የተላከላቸውን ገንዘብ በወቅቱ እንደማይጠቀሙ፣ ተገቢውን ክትትል እንደማያደርጉና
የማወራረጃ ጊዜ ገደብ ሲቃረብ ብቻ በመሯሯጥ ገንዘብ ለመጠቀም ጥረት ስለሚያደርጉ
አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ መሆኑ ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።…›› የሚል እናገኛለን።

እየገለጥን ስንሄድ የዝቅጠቱን ጥልቀት በቀላሉ እንመለከተዋለን። የፖለቲካ ተንታኞች አጠቃላይ ሁኔታውን ከገመገሙ በኋላ በየክልሉ የተዋቀሩት ተቋማትና አስተዳዳሪዎቹም ራሳቸው ከታች እስከላይ ድረስ በሙስና የተበከሉ መሆናቸው እንደዚህ ዓይነቱ ሃላፊነት የጎደለውና አገርን የሚያጠቃ አሰራር ለመስፈኑ ምክንያት መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው ይላሉ። አያይዘውም ሌላው ሲዘርፍ እኔም አብሬ ልዝረፍ የሚለው የድርመሳ ሽሚያ ከግድ የለሽነት አልፎ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ወገኖች የመጣን ዕርዳታና የተመደበን ባጀት ሳይቀር ማባከኑ ስርዓቱ ለሌላው ሰው ሩህሩህነትና ኃላፊነት የማይሰማው እንዲሁም ወገን በሞት አፋፍ ላይ እያለ እንኳ የሚመዘብር ልሂቅ እየፈለፈለ መሆኑን ጠቋሚ ብለውታል። ከሪፖርቱ ጭብጥ አኳያ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በቀጣይነት ምን ሊያደርግ እንደሚችል ኃላፊዎቹን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አብዛኞቹ ‹ስልጠና› ላይ ናቸው በመባሉ አልተሳካም።__

Advertisements

2 Responses to ““ሽሚያው” የት ያደርሰናል?! Awramba times – Wubeshet Taye [‘Before his ter……..attack’ June 2011].”

 1. Hiya! I simply want to give a huge thumbs up for the
  nice data you’ve gotten here on this post. I will be coming again to your blog for more soon.

 2. www.overhaulinforums.com August 6, 2013 at 10:37 pm #

  Hello there, I found your blog by way of Google whilst searching for a comparable matter,
  your website got here up, it appears great. I’ve bookmarked it in my google bookmarks.
  Hello there, simply turned into aware of your weblog through Google, and located that it is truly informative. I’m going to watch out
  for brussels. I will appreciate when you proceed this in future.
  Lots of other people can be benefited out of
  your writing. Cheers!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: