የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ታላቅ ስህተት

7 Jul

(ይህን ፅሁፍ ከወራት በፊት አንድ ጋዜጣ እንዲያወጣው ሰጥቼው ነበር፤ ነገር ግን ጋዜጣው የፕሮፌሰር መስፍን ወዳጅ ስለሆነ ሳያወጣው ቀረ)

ይህን ፅሁፍ ስፅፍ በሬውን ለማከል ስትንጠራራ ፈንድታ የሞተችውን እንቁራሪት እያሰብኩ ነው፡፡ እየተንጠራራሁ ስለሆነ አቅምን ባለማወቅ ከሚከሰተው እብጠትና ዕብሪት ብሎም ፍንዳታ እተርፍ ዘንድ የዕብጠት ሚዛኔን መጠበቅ ሳይኖርብኝም አይቀርም፡፡ ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው የተባለው ሃሰት አይደለምና በተለይ ደግሞ አሁን አሁን እንደምንታዘበው ባገራችን አምስት ገፅ አንብቦ አምስት ሺ ገፅ የመፃፍ አርበኝነት በርትቷልና ከእንዲህ አይነቱ ይዞ ጥርግ ከሚል ‘ሱናሚ’ ለማምለጥ እሱ ይጠብቀኝ ዘንድ ሱባኤ ሰንብቻለሁ፤ ዝምም ብያለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ዝም የማያሰኙ ነገሮች ስለሚከሰቱ ስሜትን ጨቁኖ መተኛት ትርፉ ራስ ምታትና ማቅለሽለሽ ስለሚሆን ዝም አይባልም፡፡ በመሆኑም ዛሬ መድፈር የማይገባኝን ሰው ልደፍር ነው፡፡

ዝሆንና አይጥ አንድ ላይ ሆነው ድልድይ ይሻገራሉ አሉ፡፡ ከተሻገሩ በኋላ አይጢት ሆዬ የተሻገሩትን ድልድይ በኩራት ዞራ እየተመለከተች ‹‹ፓ! አነቃነቅነውኮ!›› አለች አሉ፡፡ እሷን ብሎ ድልድይ አነቃናቂ! እኔም በዚህች አነስተኛ ፅሁፍ የዝሆን ሃሳብ ላነቃነቅ መሆኑ ነው፡፡

አስቀድሜ በራሴ ላይ ሂስ ካደርኩ ዘንድ ተንደርድሬ ወደ ነጥቡ ብገባ አንድም ፌስቡከኞቼን አላሰለችም፡፡

ከዶክተር ከበደ ሚካኤል ተረትና ምሳሌ እንዲሁም ከዶስቶቭስኪ ካራማዞቭ ወንድማማቾች መፅሃፍት በኋላ ራቴን ያሰረሳኝ መፅሃፍ ቢኖር የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ስልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ የተሰኘ መፅሃፍ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ሁለት መፅሃፍትን አንድ ላይ ባወጡበት ስራቸው በቀዳሚው አንጀቴን አራሱት በተከታዩ ደግሞ አንጀቴን አቆሰሉት፡፡ እንደኔ እምነት ከሆነ መቶ ፐርሰንት በሃቀኛ መረጃ የተደገፈ እውነት እናገራለሁ ብሎ ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት ቢደረስ ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን ተሳካ አያስብለውም፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ነገራን መፃፍ ዕቅድን መፃፍ ስላልሆነ ነው፡፡ (ለምሳሌ ሰሞኑን የኢህአዴግ ሰዎች የአምስት አመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጋነነ (ambitious) ነው ብለው ከወዲሁ ተስፋ ቆርጠው ተስፋ በማስቆረጥ ከአምስት አመታት በኋላ አልስኬቱ ድንገት ሲነገር ተደናግጠን እንዳናምፅ ካሁኑ ያለሳልሱን ይዘዋል፡፡ አቅደን እንጂ አሳክተን አናውቅምና የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም እንዲሉ እኛ የሀበሻ ልጆች አይሞቀን አይበርደን፤ አያስፈራን፤ አያሳፍረን፡፡)

ታሪክን የመሰለ ነገር የሚፅፍ ሰው ከመቶ ዘጠና ዘጠኝ ቢሳከለት ፈተናውን ወድቋል ብያለሁ፤ እውነቴን ነው፡፡ አንድ በርሜል ወይን ጠጅ ውስጥ አንድ ማንኪያ መርዝ ቢጨምሩበት በርሜሉ የወይን ጠጅ በርሜል መባሉ ይቀርና መርዝ የበከለው በርሜል ተብሎ ሊጠራ ግድ ይለዋል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ስልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ መፅሃፍ እንደዚህ ነው የሆነብኝ፤ ትንሽ በምትመስል ስህተት የተነሳ፡፡ ነገሬ ግልፅ እንዲሆን የፕሮፌሰሩን አስገራሚ የታሪክ መላምታዊ ስሌት እንደደሚከተለው ላስቀምጠው፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ~ መንግስቱ ሃይለማሪያም ^መለስ ዜናዊ

በፕሮፌሰር አስተሳሰብ መንግስቱ ሃይለማሪያምና ወያኔ (አቶ መለስ ማለታቸው ነው መሰለኝ) የቴዎድሮስ ደም የማፍሰስ ክፉ አመል ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ሁለቱም መግደልን የተማሩት ከመቶ አምሳ አመታት በፊት ይኖር ከነበረው ካሳ ሃይሉ የተባለ የቋራ ሽፍታ ነው፡፡ ‹‹…..የጎንደር ነገስታት ሎሌ የነበረው ቀጥሎም የሸፈተው ካሳ ሃይሉ አጤ ነኝ ብሎ ለሰሎሞንና ሳባ የዘር ተዋረድ ብቻ የሚገባውን ዘውድ ሲደፋ የጭካኔ በትሩን አንገዛም ባሉት ወገኖቹ ላይ ያሳርፍ ቀጠለ፡፡ የዱላ ቅብብሉም ሲወርድ ሲዋረድ መንግስቱ ሃይለማሪያምና መለስ ዜናዊ ከተባሉ የባህሪ ልጆቹ ጋር ደርሶ እነሱም ዱላውን ተቀብለው ይህንን መከረኛ ህዝብ ይጠልዙት ያዙ፤…›› ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ ፕሮፌሰር እንዲህ ማለታቸው መብታቸው ሆኖ ሳለ አስቂኝና አናዳጅ የሆነብኝ ነገር ስለ ዱላ ቅብብሉ ያሰቀመጧቸው ማስረጃ ተብዬዎች ማስጠላት ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በግምት ወደ ኋላ ተጉዘው ቴዎድሮስን የሳሉበት መንገድ ሳጤነው ከዘመን ተሻጋሪ ነገረኛ ግጥሞች ባለፈ ከማናውቀው የቴዎድሮስ የጭካኔ አፈታሪክ ይልቅ ፕሮፌሰር የጨበጡት ብዕርና የተደፈነ አጭር አረፍተ ነገር ምን ያህል እንደሚዎጋና ጨካኝ እንደሆን ነው የተሰማኝ፡፡ ከላይ የተናዝዝኩት የቅድመ ይቅርታ ኑዛዜ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶልኝ አንድ ነገር ልበል፤ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ እንደ አንዳንድ መንደረኛ ታሪክ ፀሃፊዎቻችን ያልጠራ ግንዛቤ አላቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቴዎድሮስን የጭካኔ ፈጣሪ አድርጎ በአነስተኛ አረፍተ ነገር መደምደም ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ ይበልጥ አብሻቂ የሆነው ነገር ፕሮፌሰር መስፍንን ያህል ሰው ቴዎድሮስ እጅግ አረመኔ ነበረ ብሎ ለመደምደምና ከነመንግስቱ ጋር ለማነፃፀር የተጠቀሟቸው ማስረጃዎች የእረኞችንና የአዝማሪዎችን ግጥሞች መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ቴዎድሮስ ባገር ውስጥ የዛጉዌ ስርወ መንግስት ሙቀት በሚሰማው ዋግሹም ጎበዜ፤ የኦሮሞ ልዕልቶቹ ጥሩወርቅና ውቢት ከልጃቸው ኢዮአስ ሞት በኋላ ያጡትን የጎንደር ቤተመንግስት እንደገና ለመቆጣጠር እና ዮሃንስ አራተኛ ደግሞ ባላቸው የሰሎሞን ዳይናስቲ የዘር ሃረግ ምክንያት ያን ‘’የኮሶ ሻጭ ልጅ’’ እንጦርጦስ አውርደው ዘውዱን በራሳቸው አናት ላይ ደፍቶ የሰሎሞን ስርዎ መንግስትን ለመመለስ ቴዎድሮስን በሶስት አቅጣጫ ወጥረውታል፡፡ ታዲያ ከዮሃንስ፤ ከዋግሹም ጎበዜና ከጥሩወርቅ መንደር በኩል ‹‹እሳት መጥቶ ከቋራ፤ ድፍን አበሻን በላ፤…›› ተብሎ ቢገጠም ምኑ ይደንቃል? የኛ ሰው እንኳን በቴዎድሮስ ላይ በእግዜሩ ላይስ ገጥሞበት የለ?

ሁለቱን ታማለህ አንዱን ትገድላለህ፤

የሴት ልጅ ነህና ፍርድ የት ታውቃለህ፤…

ተብሎ የተገጠመበት ማነው? እየሱስ ክርስቶስ አይደለም እንዴ? መዓት የሚያመጣውን ይህንን አይነት ግጥምስ የገጠመው ማነው? ፈረንጅ ነው? አይደለም፤ በሁለቱም ልጆቻቸው መታመምና መሞት እርር ድብን ያሉ የኛው የድሮ እናታችን ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ለቴዎድሮስ ለምን እንደሚያቅራራለት ይገርማቸዋል፤ ይሄ ማለት አልገባቸውም ማለት ነው፡፡ ታዲያ ለምን እኔ አልነግራቸውም?

እንግሊዛዊው የስነፈለክ (astronomy) ሊቅ ፕሮፌሰር ስቴፈን ሃውኪንግ የዘመኑ አልበርት አንስታይን ሲባል ይወደሳል፡፡ ሃውኪንግ የአንስታይን ደቀመዝሙር ነው፡፡ አንስታይን በቲዬሪ ደረጃ አስቀምጧቸው ያለፋቸውን ንድፈ ሀሳቦች አሻሽለውና አጎልብተው ወደ ተግባር የሚያመጧቸው ሃውኪንግና ሌሎች ጓደኞቹ ናቸው፡፡ ወይም እንዲህ እንልበል፡፡ የአንስታይን መላምቶች በተለይም አንፃራዊነት ቲዬሪ ዛሬ ለምንገለገልባቸው ኮምፒዩተር፤ ሳተላይት፤ ቴሌቪዝን፤ ጂ.ፒ.ኤስ.፤ ሞባይል…ወዘተ መሰረት ነው፡፡ አንስታይን ግን አንድም ቀን ኮምፒዩተር ሳይገለገል ነበር ያለፈው፤ ቴሌግራም ፈጣሪው አሌክሳንደር ግርሃም ቤል አንድም ቀን በቴሌግራም ተነጋግሮ እንደማያውቀው ማለት ነው፡፡ አጼ ምኒልክን ስቴፈን ሃውኪንግ አፄ ቴዎድሮስን አንስታይን አድርጌ ለማስቀመጥ ፈልጌ አይደለም፡፡ ስለ ቅብብሎሹ ማውራት ስለፈለኩ ነው፡፡ አባቶቻችን ስልጣን ለመያዝ እርስ በርስ ቢተጋተጉም ያንዱን መልካም ስራና ባህሪ የመውረስ ፍጥነታቸው እንዲህ አይነት ባህሪ ፍፁም ያልፈጠረባቸው የቅርቦቹና የአሁኖቹ መሪዎቻችን ሊቀኑበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ የአገር ውስጥና የውጭ የተባሉ ፖሊሲዎች ነበሩት፡፡ እንደሚገባኝ የቴዎድሮስ የውጭ ፖሊሲ ከአፄ ዘራ ያዕቆብ የሰሜን ፖሊሲ የተወሰደ ነው፤ ቴዎድሮስ ከልብነ ድንግልና ንግስት ኢሌኒ የተጀመረውን የውጭ ግንኙነት ሊቀጥለው ፈልጎ ወዳጅነቱን ከእንግሊዝ ጋር ማድረግ ጀመረ፤ ከንግስት ቪክቶሪያ ጋር የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነቶችን ለመፈፀም እጅግ ይጥር ነበር፤ ምክንያቱም ምፅዋን የያዙት ኦቶማን ቱርኮች መስፋፋት ለቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኑ አለም በጠቅላላ እጅግ አስጊ ነበርና ነው፡፡ (ቱርኮቹ ለአህመድ ግራኝ የጦር መሳሪያ ሰጥተው የኢትዮጰያን ስልጣኔ ማሽመድመዳቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡) ቴዎድሮስ አጼ ልብነ ድንግል ላይ የደረሰው እሱም ላይ እንዲደርስ አልፈለገም፤ እናም ከእንግሊዞች ጋር በኋላ በፀብ የሚቋጭ ወዳጅነትን ቀጠለ፤ እንግሊዞች ደግሞ የስትራቴጂ ጉዳይ ሆኖባቸው ከሃያሏ ቱርክ ጋር መጣላት አልፈለጉም፡፡ ንግስት ቪክቶሪያ ቴዎድሮስን መካድ ግድ ሆነባቸው፤ ቴዎድሮስም መገንፈል ነበረበት፡፡

የቴዎድሮስ የአገር ውስጥ ፖሊሲ የተባለውን ስንመለከት ደግሞ የምኒልክ አያት ሳህለ ስላሴ ንጉሰ ሸዋ የጀመሩትን ነበር ቴዎድሮስ ያጠናከረው፤ ዛሬም ድረስ ቡዳ፤ ቀጥቃጭ ስንል የምናጣጥላቸውን የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ቴዎድርስ ከመኳንንቱ ከፍ ያለ ክብር ሰጣቸው፤ ከቅልውጥ መንጋ ደብተራ ይልቅ የጥበበኞች እጅና አዕምሮ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የዕድገትና ስልጣኔ መሰረት እንደሆን ገብቶታል፤ የመኳንንቱንና የቤተ ክርስቲያናትን መሬት እየቀማም ለድሃ ገበሬዎች ይሰጥ ነበር፡፡ (እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን መንግስቱ የቴዎድሮስን ጭካኔ ወረሰ ካሉ አይቀር የመንግስቱ መሬት ላራሹ አዋጅም ከቴዎድሮስ የተወረሰ ነው ማለት ነበረባቸው፤ አላሉትም እንጂ…፤ ችግሩ ያለው ቴዎድሮስን አንጋዶ ለማዬት ከመወሰኑ ላይ ነው፡፡)

ከላይ እንዳልኩትና ከተነሱት ምሳሌዎች አንፃር አባቶቻችን ዘውድ ለመጫን ቢራኮቱም እንኳ አንዱ የአንዱን መልካም ሃሳብ ይዞ የመጓዝ አስደናቂ ባህሪ እንደነበራቸው ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ስለምትባል አገር ሳስብ ፊቴ ላይ ድንቅ የሚሉብኝ እምዬ ምኒልክ የቴዎድሮስን ራዕይ አልተጋሩም ማለት አይቻልም፡፡ ያፈጠጠው ሃቅም ይሄው ነበር፡፡ ምኒልክ የቴዎድሮስን በጎ ራዕይ ተቀብለው መሃሪነታቸውንና ደግነታቸውን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ ያወረሱትን የፈሪሃ እግዜአብሄር ፀጋቸውን ተጠቅመው ትነስም ትብዛ ይቺን ታክል አገር በክብር አስረክበውናል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ፉርሽ የሚሆን የፕሮፌሰር መስፍን ሃሳብ አለ፤ የዱላ ቅብብሉ ነገር፡፡ ቴዎድሮስ አረመኔ ነበር ብለን እናስብ፡፡ ከነ ቀዳማዊ እያሱና አፄ ዘራ ያዕቆብ የተቀበለውን ራዕዩን ብቻ ሳይሆን ራሱም ይፍጠረው ከሌላም ይውረሰው አረመኔነቱንም ለምኒልክ አቀብሏል ልንል ነው፡፡ ምኒልክን በትክክል የሚያውቅ ሰው ካለ ግን ዱላ ቅብብሉ እሳቸው ላይ መቆሙን ይገነዘባል፡፡ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ባልነበረበት ዘመን ምኒልክ የለዬላቸው ዴሞክራት ነበሩ፤ በጥበብ እንጂ በሃይል የማያምኑ ታላቅ ሰው፡፡ ታዲያ የካሳ በትር በዬት በኩል አልፎ መንግስቱና መለስ ላይ እንደደረሰ ራሳቸው ፕሮፌሰር በድምደሜ ሳይሆን በእውነትና አመክንዮ ተመስርተው ቢያስረዱን የተሻለ ይሆናል፡፡ በ’ውነቱ ቅር የሚያሰኝ ነገር ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውርደትሽን አያሳዬኝ!…›› ብሎ ራሱን ያጠፋን ሰው፤ ኢትዮጵያን ለአስራ ሰባት አመት በጨለማ ካኖረ እና ከኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝብ አስተሳሰብ በተቃራኒ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል አለመሆኗን በግድ ሊያረጋግጥ ከሚሯሯጥ ሰው ጋር ማነፃፀር እጅግ በጣም ነውር ነው፡፡ ቴዎድሮስ የስልጣን ጥመኛ ቢሆን ኖሮኮ ያኔ ራሱን ከመግደል ይልቅ ከመቅደላ ጥቂት ዞር ብሎ እንደገና ራሱን ካደራጀ በኋላ ተመልሶ አፄነቱን ለመቆናጠጥ መፋለም ይችል ነበር፡፡ የቴዎድሮስ አላማ አገር ማበልጸግ እንጂ አገር መግዛት አይደለም፡፡

በስልጣን፤ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ ገፅ 2 ላይ እንዲህ የሚል ፅሁፍ አለ፡፡ ‹‹…ቴዎድሮስ ምን ሰሩ? አንደኛ የዘመነ መሳፍንትን ኢትዮጵያን የመከፋፈል አዝማሚያ አገዱ፤ ሁለተኛ፤ ባይሳካም የኢንዱስትሪ ስራ እንዲጀመር ሞከሩ፤ አንድ ጊዜ ተተኩሶ የበቃው መድፍ አሰሩ፤ ያንን መድፍ መቅደላ ላይ አወጡት፤ ይህ ቀላል ነገር እንዳይመስላችሁ፤ ዛሬ ያንን መድፍ ከመቅደላ ማውረድ አይቻልም፤ ሶስተኛ ራሳቸውን ገደሉ፤ ከዚህ ሌላ ስለቴዎድሮስ የሚተረክ የለም፤….››

እኔ በፕሮፌሰር መስፍን ውስጥ ለአፍታ ልቀመጥና ከላይ ያስቀመጡትን አይነት ጥሬ ሃሳብ ልናገር ‹‹…ክርስቶስ ምን ሰራ? መጀመሪያ ተወለደ፤ በድንግል ማሪያም ዕቅፍ ውስጥ አዬነው፤ ከዚያ በኋላ የለም፡፡ የ5፤ 10፤ 15፤ 20፤ እና 25 ዓመቱ ጎረምሳው እዬሱስ የት ነበር? ድንገት 30ኛ ዓመቱ ላይ ከተፍ አለና ጥቂት ሃዋርያቱን ሰብስቦ ላስተምር አለ፤ ብዙ ሳይቆይ የገዛ ዘመዶቹ ያዙና አሰሩት፤ ወንጀለኛ ብለው ገረፉት፤ ሰቀሉት፤ ከዚህ ሌላ ስለ ክርስቶስ የሚተረክ ነገር የለም፤…..››

ፕሮፌሰር ክርስቶስን ፈርተው አልፃፉትም እንጂ ስለ ክርስቶስ እንደዚህ ያለ ሃሳብ በውስጣቸው አለ፡፡ ፕሮፌሰር የሳቱት ታላቅ ቁምነገር አለ፤ ይኸውም ታላላቅ ሰዎች አለምን የለወጧት በቃል ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ክርስቶስ በሞቱ ለህዝበ አዳም ትንሳኤን አመጣ፡፡ እኔ ቴዎድሮስን ከክርስቶስ የማነፃፅር ጅላጅል ባልሆንም የቴዎድሮስ ራስን መግደል ኢትዮጵያውያን ለእምነታቸውና ሀገራቸው ክብር እስከምን ድረስ መሄድ እንዳለባቸው የሚያስተምር ወደር የሌለው ተምሳሌትነት ነው፤ የአድዋ ጀግኖቻችን ገድል የነቴዎድሮስ እምቢ ለሃገሬ ባይነት መንፈስ የለበትም አይባልም፡፡

ምን ሰራ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ በአጠቃላይ ሃሳቡ እጅግ አከራካሪ ይሆናል፡፡ ከአጼዎቻችን መካከል የሰሩት ስራ እርክት አድርጓቸው ያለፉት ምኒልክ ብቻ ናቸው ብዬ አምናለሁ፤ እርሳቸውም ቢሆኑ ትክክለኛ ተቀባይ ስላልነበራቸው መንፈሳቸው የሚያርፍ አይመስለኝም፡፡ አብዛኛዎቹን የምናከብራቸው ለማንነታችን መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ጠብቀው አስተላልፈውልን ስላለፉ ነው፡፡

ስለ ዘመነ መሳፍንት!

የዘመነ መሳፍንት ወቅት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ያልነበረችበት ሁሉም የራሱን አምባ ይዞ አምባገነን የሆነበት ዘመን ነው፡፡ የአምባ መኳንንትና ሹማምንት ቆይታ ለጥቂት አመታት ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ላስታ፤ በጌምድር፤ ሸዋ፤ ትግሬ፤ ጎጃም…ወዘተ የሚባሉ አገራት እንጂ ሁሉንም አቅፋ የያዘች አንዲት ኢትዮጵያ ባልኖረች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመሃመድ ግራኝ ዘመን የእሳት ዘመን ነው፤ የዘመነ መሳፍንት ዘመን ደግሞ የበረዶ ዘመን ነው፡፡ በረዶውን ፕሮፌሰር አንድ ሽፍታ ሲሉ ያጣጣሉት ቋረኛው ካሳ አቀለጠው፡፡ በረዶው መቅለጡ ብቻ አልነበረም ቁምነገሩ፤ ገደል አፋፍ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ ወደ ደልዳላው ተመለሰች፡፡ ይህ እንግዲህ እንደሚዛናችን ትልቅ ወይም ትንሽ አሊያም ምንም ነጥብ ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ለእኔ ግን ለኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንት ክፍፍል ውጭ ከባሰ አደጋ ውስጥ የገባችበት ዘመን አለ ብዬ አላስብም፤ የግራኝ ጥፋትና የጣሊያን ወረራ ከዚህ ጋር ሊተካከሉ ይችላሉ፡፡ ቴዎድሮስ ከዚህ አኳያ ትልቅ ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ስለሃገር ዕድገት ከማውራታችን በፊት መጀመሪያ አገር የምትባለው ነገር መኖር መቻል አለባት፡፡ እኔ ፕሮፌሰርን ብሆን ኖሮ በአዕምሮዬ ፈጥኖ መምጣት የነበረበት ጉዳይ የቴዎድሮስ ሎሌነትና ሽፍታነት አይደለም፤ ይልቅስ አንድ ተራ የነበረ ሰው ያንን ከሰለሞንና ሳባ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እጅግ ግዙፍ የተራራ ጎምት ድንጋይ እንዴት ደፍሮ ሊጋተረው ቻለ? የሚለው በሆነ ነበር፡፡ ከሆነ ነገር ተነስቶ ታላቅ መሆን ቀላል ነው፤ እንደ ቴዎድሮስ ከምንም ተነስቶ አጼ መሆን ግን እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ለነገሩ ፕሮፌሰር ሰው ናቸውና ሚዛናቸውም ሰውኛ ነው፡፡ አንድ ተራ ሽፍታ በርግጥም ዘሎ የማይታሰበውን ዘውድ ሲጭን ያኔ እነ እቴጌ ምንትዋብ እንደሆኑት ሁሉ ፕሮፌሰርም ደንግጠው ይሆናል፡፡ ወደ ታላቁ መፅሃፍ ስንመጣ ፈጣሪ በሰው መንገድ አይሄድምና መሾም ያለበትን ይሾማል፤ እግዚብሄር ባይሆን ኖሮ አፈቀላጤው አሮን እያለ ዱዳውን ሙሴን ማን ለመሲህነት ይመርጠው ነበር?

የቴዎድሮስ ጭካኔ ማለት ምን ማለት ነው ?

የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች ባልተፈጠሩበት ዘመን የአለም አገዛዝ ሁኔታ አንድ አይነት ነበር፤ በጉልበት፡፡ መጀመሪያ አንድ ሰው አገር የመምራት ራዕይ ይኖረዋል፤ እንደ አድያም ሰገድ እያሱ ዕድለኛ የሆነ ከዙፋን ቤተሰብ ይወለዳል፤ እንድ ቴዎድሮስ ያለው ዕድለቢስ ደግሞ እነ ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት ኮሶ ከምትሸጥ ድሃ እናት ይወለድና ሌሎች ቢሰሙ የሚያስቃቸውን አገር የመምራትን ራዕይ ይሰንቃል፡፡

ቀጥሎ ከራዕይ በኋላ ተከታይ ማፍራት ነው፤ ከዚያ ሰራዊት ማደራጀት፤ አገር ለመምራት የሚቀናቀኑትን ባላጋራዎች ሁሉ መምታት፤ ድል ከቀናም እያስገበሩ መግዛት ነው፡፡ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት ነበረ እንዴ ያኔ? ቢኖርስ በጊዜው ከነበረው ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ አኳያ ያዋጣ ነበር ወይ?

በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ነገስታትና መሪዎች ታሪክ ሳይገድል ስልጣን ላይ የወጣ፤ ስልጣን ይዞም ያልገደለ የለም፡፡ ከዚህም በባሰ ለዙፋን ሲሉ አባቶቻቸውን የገደሉም አሉ፤ ቀዳማዊ እያሱ የተገደለው ዙፋን በጠማው ልጁ ተክለሃይማኖት ነበር፡፡ እጅ እዬቆረጡ ገደል በመጨመር መግደል የጥንት የኢትዮጵያ ነገስታት የአገዳደል ዘይቤ ነው፤ ሃይለስላሴ አቀለልኩት ብለው ወደ አደባባይ ሰቀላ ለውጠውታል መሰለኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የኢትዮጵያን ታሪክ በሚገባ ለመረመረ ጭካኔ የተሞላበትን አገዳደል ሁሉም ይተገብሩት ነበር፤ በአስከፊ ሁኔታ፡፡ ከዚህ አንፃር ቴዎድሮስ ከሌሎች ነገስታት ተለይቶ የጭካኔ ተምሳሌት የሆነበት ምስጢር ምንም ሊገለጥልኝ አልቻልም፡፡ ሁለት ነገሮችን ግን እጠራጠራለሁ፤ አንደኛ ቴዎድሮስ እጅግ የማይገፉት ጦረኛ እየሆነ ሲመጣ ተቀናቃኞቹ ግጥም ማስገጠምን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፤ ወይ ደግሞ ቴዎድሮስ ሲገድል ተደብቆ አልበረም፤…

ሌላው ፕሮፌስር መስፍን ሊያውቁት የሚገባ ነገር የጥንት ነገስታት አባቶቻችን በእምነታቸውና በአላማቸው ወይም በሃገራቸው ጉዳይ ምንም ድርድር የማያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ልበ ብርሃኑ አጼ ዘራ ያዕቆብ ልጆቹ ባዕድ አምላኪ በመሆናቸው ምክንያት በህዝብ ፊት አደባባይ አውጥቶ እስኪሞቱ ገርፏቸዋል፡፡ ‹‹….የእግዚአብሄር ክብር ከሚጎድፍ ልጆቼ ይጥፉ!›› ማለቱ ነው ዘራ ያዕቆብ፡፡ ሁላችንም እግዚአብሄርን ከልጆቻችን እንደምናስበልጥ ጥርጥር የለውም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ይሄንንም ጭካኔ ካሉት ከፍልስጤማውያን ምርኮ የተመለሰውን ፅላተ ሙሴ በደስታ ብዛት በእጁ የነካው ኦዛ በአምላክ ተቀስፎ ስለሞተ ይህንም የእግዜር ጭካኔ እንበለው?

አፄ ዘራ ያዕቆብ ልጆቹን ሲያጠፋ ያስተላለፈው መልዕክት አንድ ነው፤ ሃገርና እግዚአብሄር ከራስ ልጆች ይበልጣሉ፡፡ ቴዎድሮስ ከጨከነ የጨከነባቸው ጠቃሚ ራዕዩን ሊያከሽፉበት ፊቱ ላይ በተደነቀሩት ሰዎች ላይ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ለድሃ የቆመ ሰው ነበር፤ ድሃን አልገደለም፤ ሊገድሉት የመጡትን ግን ምን ያድርጋቸው? እጅ ወደ ላይ ብሎ ይጠብቃቸው? ወይስ ስለ መቻቻል ፖለቲካ ሰብኮ ያሳምናቸው? ፕሮፌስር መስፍን ቢመልሱት ይሻላል፡፡

መቼም የፕሮፌሰርን አስተሳሰብ አምኖ ቴዎድሮስን ከፕሬዚደንት መንግስቱ ሃይለማሪያምና ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የማነፃፀሩን ነገር እውነት ነው ብሎ የሚቀበል ችኩል ተከታይ አይጠፋም፡፡ ለእንዲህ አይነቶቹ እኔ አንድ መልዕክት አለኝ፡፡ መቼም ከፕሮፌሰር መስፍን ይልቅ እኔን አምነው የለም! ቴዎድሮስማ እርስዎ እንዳሉት አይደለም ብለው ይሞግታሉ ብዬ አላምንም፡፡ በትምህርት፤ በእድሜና በልምድ ትልቅ የተባለ ሰው ያጣመመውን በትምህርት፤ በእድሜና በልምድ ትንሽ የሆነ ሰው አመታትን ቢጥር አያቃናውም፡፡ ቢያንስ ግን ቴዎድሮስ ከመንግስቱና መለስ እጅግ የተራራቀ አስተሳሰብ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስ ንግስት ቪክቶሪያ የጦር መሳሪያ እንዲልኩለት የጠዬቀው በኦቶማን ቱርኮች የተያዘችውን ምፅዋን በሃይል ለማስለቀቅ ነበር፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ደግሞ ሰሞኑን ኤርትራ ላይ ጦርነት እንደሚደረግ ፍንጭ የሰጡት ምፅዋን ለማስመለስ አይደለም፤ መድረኮችና አረናዎች እንዳሉት ምፅዋም ሆነ አሰብ የኢትዮጵያ አለመሆናቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለአለምአቀፍ ማህበረሰብ አረጋግጦ የኢትዮጵያን ህዝብ እንቁልልጭ በማለት የእናት አገራቸውን ለማስደሰት ነው፡፡ እስቲ በሞቴ ቴዎድሮስና መለስን ምን አመሳሰላቸው? ያኛው ሃሳቡ እስከ እዬሩሳሌም ይሄኛው ሃሳቡ እስከ አዲስ አለም፡፡ ቴዎድሮስ በዘመኑ ስለ ኢንዱስትሪ አብዮት የሚያስብ ልዩና አስገራሚ ሰው ነው፡፡ ዛሬ በእኛ ዘመን በእኛ አገር የኢንዱስትሪ አብዮት ማለት እንደ ቴዎድሮስ ሃሳብ አይደለም፤ ስልጣን ማቆያ ጥበብ ነው፤ አራት ነጥብ!

መንግስቱ ሃይለማሪያም ደግሞ አጥናፉ አባተን ገድሎ ስልጣን ላይ ከመውጣት፤ አማን አብዶን ገድሎ የኤርትራን ፖለቲካ ከማበላሸት ያላለፈ ተራ ወመኔ ነው፡፡ መንግስቱ ሃይለማሪያም ከተወለደበት ዘመን ብዙ ዓመታት ወደ ኋላ ቆጥሮ መወለድ የነበረበት የስልጣኔ ፋራ ነው፤ ቴዎድሮስ ደግሞ ሰራተኛ እጆችን እያጣጣሉ የኢትዮጵያን ስልጣኔ ማምጣት አይቻልም ብሎ የነገስታት የህልውና ሞተር የሆኑትን የሃይማኖት ሰዎች የተገዳደረ በመሆኑ ወደፊት መወለድ የነበረበት ሰው ነው፡፡ እሱና መንግስቱ ዘመን መቀያዬር ነበረባቸው፡፡ ለነገሩ ቴዎድሮስ ዛሬ ቢወለድስ ምን ያመጣል? እንደነ ዋግሹም ጎበዜ ሁሉ እን ፕሮፌሰር መስፍን ግጥም ያስገጥሙበት ነበር፡፡

በመጨረሻም የምለው ነገር፤ ፕሮፌሰር መስፍን ዙሪያችን ገደልና ጨለማ በሆነብን በዚህ ዘመን በጠባብ ሽንቁር ብልጭ የሚሉልን የግዙፉ ጨለማ ብርሃናችን ነዎትና ይፃፉ ነው፤ ልክ በክህደት ቁልቁለት ላይ እንዳስቀመጡት ከሃዲውንና እውነተኛውን እንለይ ዘንድ ይልፉልን፡፡ ሲፅፉ ካልተጠነቀቁ ግን መቼስ ምን ይደረግ ከእውነት አይበልጡምና ዝም ማለት የማንችል ዝም አንልም፡፡

አሜሪካውያን ታሪክ አልባ በመሆናቸው ምክንያት ታሪክን ሆሊውድ ላቦራቶሪ ውስጥ ፈጥረው በሌለ ታሪክ ኤቨረስት ተራራን የሚያክል አሜሪካዊነትን በትውልዳቸው ልብ ውስጥ ሊፈጥሩ ይጥራሉ፡፡ የኛ ታሪክ ፀሃፊወች ደግሞ {ነጋድራስ ገብረህይዎት ባይከዳኝ ይመስሉኛል እንዳሉት} አንዱን ለማጉላት አንዱን እንጦርጦስ ከማውረድም ባለፈ ጥሩ የሰሩትንም ገልብጠው በተቃራኒው እንዲሳሉ ያስቀምጧቸውና ፈጣሪም ይቅር የማይለውን ሃጢያት ይሰራሉ፡፡ ብልጦቹ የውሸት ታሪክ ፈጥረው ጠንካራ ትውልድ ለመፍጠር ይሞክራሉ፤ እኛ ጠንካራ ታሪክ ሰሪዎቻችን አንኳሰን ትውልዱን በድቡሽት ላይ የቆመ መሰረት አልባ ልናደርገው እንታትራለን፤ እኔ በበኩሌ ፕሮፈሰር ከእንዲህ አይነቱ ጎራ ውስጥ ከማያቸው እንደ መይሳው ይሄንን አላይም ብዬ ሽጉጥ ብጠጣ እምርጣለሁ፡፡ ጨርሻለሁ!
Melkamsew Abate

Advertisements

3 Responses to “የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ታላቅ ስህተት”

 1. dave July 7, 2011 at 5:48 am #

  Dear alexander the great*

  wonderful comment…please don’t hesitate to give such a strong critics on any bad literature
  that would destroy our tradition, history and culture,,,,whoever that person is ,,,the professor is not God….and yet he is ,,,for me he is an opportunist,,,,,that has been ,,,

  Thank you so much for sharing

  Please if u have contribution on any other space

  dave

 2. ፈለገብርሃን July 7, 2011 at 9:06 am #

  ላለፉት 30 ወይም 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የሚታየው የትውልድ ጅግር፡ በእነ ፕሮፌሰር መስፍን ትውልድ የተፈጸመው የነጭ ብሬይንወሺንግ ሜካኒዝም ነው ያገር ታሪክ፡ ያገር ባህል ያገር ሰው እንዳይከበር እንዲናቅ የተደረገው። የነፕሮፌሰር መስፍን ትውልድ የተረገመ ጸረ ኢትዮጵያ፡ ጸረ ጥቁር ትውልድ ነው ብል አላጋነንኩም። ያገሩን ሰው የሚያንቋሽሽ ሰው የሚናቅ ነው!

 3. DADE July 8, 2011 at 8:16 pm #

  antem kebatari nahe lerass siqorsu ayasanesu enda mibalewo hulu antem haqegna baye nahe lemangnawom enasu yamatulen hatyat new eskahun aberon yalewe leje kenatu teqeresxleche enda mibalewe hulu enasum yawo honawe new andu kandu yalteshale lelawo baatswo geze sentu mota sentu tesedede endesuma katebale daregem yaserawo teru serawoch alu eko gen yatefawo D.S. WAYEM FETEHE

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: