‹‹አሸባሪው›› ባልደረባዬ – በዳዊት ከበደ

2 Jul

ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም በቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ቢሮ የጋዜጣዋ ባልደረቦች ሰብሰብ ብለን ኢ-መደበኛ የሚባል አይነት ስብሰባ እያካሄድን ነው። አዲስ ዘመን የሚባለው ‹‹ዕድሜ ጠገብ›› ጋዜጣ በእኔና በባልደረቦቼ ላይ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ስድቦችን በማዝነብ ዕረፍት ያጣበት ሰሞን ነበር። በዚሁ ዕለት የወጣው አዲስ ዘመንም እንደተለመደው በገፅ 3 ላይ ‹‹የውጭ ኃይሎች ወኪል፣ ኒዎ ሊበራል ምንትስ…›› የሚሉ ሐሜቶች ሰፍረውበታል። እናም በዚሁ ኢ-መደበኛ ውይይታችን ‹‹እስኪ እንነጋገርበት እየሆነ ያለው ምንድነው? ምንስ ማድረግ ይጠበቅብናል? በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ ሀሳብ ተለዋወጥን።
በዕለቱ የወጡ ሌሎች ጋዜጦችን እየገለጠ ሲያነብ የቆየው ውብሸት ማንበቡን በድንገት ገታ አድርጎ ቀና አለና ‹‹ወንድሞቼ ከሰማችሁኝ አንድ ነገር እናድርግ፣ እኛ በሕገ-መንግስቱ ጥላ ከለላነት፣ በየደረጃው ያሉ የአገሪቱ ሕጎችን አክብረን የምንሰራ ሰዎች ነን፤ ስለዚህ ለምን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አንወስደውምና በህግ የበላይነት የማይነጥፍ አቋም አንዳለን በተግባር አናሳያቸውም?›› አለ። ሰከን ባለ ሁኔታ ሲካሄድ የነበረው ውይይት በአንዴ ድባቡ ተቀይሮ ወደ ለየለት የክርክር መድረክ ተለወጠ። ‹‹የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ያለበት ደረጃ አናውቅምና ነው መንግስታዊውን አዲስ ዘመን እንክሰስ የምትሉት? አንዱ ባልደረባችን የሰነዘረው አስተያየት ነው፡፡ ሌላው ባልደረባችን ደግሞ ‹‹አዎን እንክሰሰው ከዛ ገለልተኛው ፍርድቤት የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ በሞት ወይም በስቅላት እንዲቀጣ ይፈርድበታል›› ሲል ተሳለቀ።
እንዲህ አይነት ነገሮች ሲከሰቱ ውብሸት ሁሌም ረጋ ባለ መንፈስ ለነገሮች ምላሽ በመስጠት ይታወቃል። ‹‹እኔ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በዚህ መንገድ ከመታገል ውጪ ምርጫ የለንም፤ውጤቱ ለምን ያሳስበናል? እነሱ እንደፈረጁን አይነት አለመሆናችንን በዚህ መንገድ እናሳያቸውና ውጤቱን እንየው፡፡ ከውጤቱ በኋላ ደግሞ ስለ ውጤቱ የምንለውን እንላለን›› አለ፡፡ የኋላ ኋላ ግን ሁላችንም በውብሸት ሀሳብ ተስማማንና ክስ ተመሰረተ። (በነገራችን ላይ የእኛና የአዲስ ዘመንን ጉዳይ የያዘው ፍርድ ቤት እስካሁን ውሳኔ አልሰጠም፡፡ ‹‹ለውሳኔ ተቀጥሯል›› ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ሦስት ቀጠሮዎች አለፉ፤ አሁንም እየጠበቅን ነው)
እኔና ውብሸት የተዋወቅነው ከ11 ዓመት በፊት በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ጆርናሊዝም ስኩል ነው። ትምህርት ቤት የተጀመረው ጓደኝነታችን በሦስት የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የስራ ባልደረባ እንድንሆን አስችሎናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለሙያው ያለው አክብሮት ልዩ ነው። የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት ‹‹እኔ እኮ ኤዲተር ለመሆን ብዙ ይቀረኛል፤ እንደ ሪፖርተር አድርጌ ነው ራሴን የምመለከተው›› ሲል በተደጋጋሚ ያወራል። ኃላፊነት መውሰድ ይወዳል፣ ሰራተኞች በማስተበበርና ሀሳብ በማፍለቅም ይታወቃል። የቤተሰብ ኃላፊ እንደመሆኑ እንደሌሎች ባልደረቦቻችን ቢሮ ማምሸትና ማደር አያዘወትርም። ነገር ግን ደግሞ ከማንም በፊት ንጋት ላይ ቀደሞ ቢሮ በመድረስ ይታወቃል። ከአውራምባ ታይምስ ባልደረቦች መካከል በቁመት ረጅም የሆነው ውብሸት እጅግ ሲበዛ ተጫዋች ነው። በምርጫ 2002 ዋዜማ ከብሮድካስት ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር ከተፈጠረው አለመግባባት ጋር በተያያዘ ከዋና አዘጋጅነት ለመልቀቅ ሲገደድ ‹‹በርካታ የሚያስጠይቁኝ ዘገባዎች እንዳሉ፤ ምርጫውን ለማወክ እንደምፈልግ ኃላፊዎቹ ሰነድ እያሳዩ ነግረውኛል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ላለው እንግዲህ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ከዚህ በኋላ ግን ክስ እንዲጨመርብጭ አልፈልግም፡፡ ደግሞ እውነትም ምርጫው በእኔ ምክንያት ከሚታወክ መልቀቁ ሳይሻል አይቀርም›› አለ፡፡ ውብሸት የጥላቻ ፖለቲካ አራማጅም አይደለም። ‹‹እኛ ጋዜጠኞች ነን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ለመንግስት ማሳየት ነው የሚጠበቅብን። ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ቢኖር ኖሮ እኛ እኮ ሽልማት ነበር የሚባን፣ የሌላ አገር መንግስት ስህተቱን ለማወቅ ብዙ ወጪና ምርምር ያደርጋል፡፡ ስህተቱን በአቋራጭ የሚነግረው ሚዲያ በመሆኑ ተገቢውን እንክብካቤና ከለላ ይሰጠዋል›› ሲል በቀልድ እያዋዛ ለነገሮች ምላሽ ይሰጣል፡፡
‹‹ልጄ ብርቱካን ሚደቅሳ ሆነብኝ››
ውብሸት የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው። የልጁ ስም ፍትህ ውብሸት ይባላል፡፡ ማንም አባት ልጁን እንደሚወድ እሙን ቢሆንም የውብሸት ግን ከዛም ያልፋል። በአንድ ወቅት ለም ሆቴል አካባቢ ከባለቤቱ ጋር የተከራዩት ቤት ደጃፉ ላይ ለልጁ የማይስማማ አቀማመጥ ስለነበረው እሱና ባለቤቱ ወደ ስራ በሚሄዱበት ሰዓት የቤት ሰራተኛዋ ሳታየው ህጻኑ ልጅ ለመውጣት ሲል ወድቆ አደጋ እንዳይደርስበት በማሰብ ሁሌም በር ይቆልፉበታል። በዚህ ምቾት ያልተሰማው ውብሸት ቤት መቀየር አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርስና ለኪራይ እና ተያያዥ ወጪዎች ድርጅቱ እንዲያበድረው አንድ ማመልከቻ ፅፎ ይሰጠኛል። ማመልከቻው በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩትን ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን መነሻ አድርጎ የተጻፈ ነው፡፡ ‹‹ልጄ በጐረቤት ካሉ እኩዮቹ ጋር የመጫወት መብቱን ነፍገነዋል፡፡ ከቤት ድክ ድክ እያለ ለመውጣት ሲሞክር አደጋ እንዳይደርስበት በመስጋት ቤት ላዩ ላይ እየቆለፍንበት መሰረታዊ ነፃነቱ አደጋ ላይ ጥለነዋል፡፡ …በአጠቃላይ ልጄ በአሁኑ ሰዓት ብርቱካን ሚዴቅሳ ሆኖብኛል፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ ደመወዜን አስቀድሞ ይስጠኝና ሌላ ቤት ልከራይ›› ይላል ማመልከቻው በከፊል። ይህ ብቻም አይደለም በየአመቱ የልጁን የልደት ማስታወቂያ በጋዜጣ ላይ ሲያሰራ መንግስትን ሸንቆጥ የሚያደርግ አረፍተ ነገር ማስፈር ይወዳል ‹‹አንተና የአንተ ትውልድ አባላት ሳይሸማቀቁ በነፃነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ…›› የሚል ሀረግ በመልካም ምኞት መግለጫው ላይ ያሰፍራል።
ውብሸት ለሙያው ያለው አክብሮት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ የምንመሰክርለት እኛ ባለደረቦቹ ብቻ አይደደለንም። ባለፈው ረቡዕ በመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረግ በኤርትራ መንግስት የፋይናንስ ድጋፍ የሽብር ቡድን ለማቋቋም ሲያሴር እንደተደረሰበት ስላቃዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ሽመልስ ከማል ከአንድ አመት በፊት ለውብሸት አዎንታዊ ምልከታ እንዳላቸው የገለፁበት አጋጣሚ ማስታወሱ ተገቢ ነው።
በጋና፣ አክራ ከተማ በመረጃ ነፃነት ዙሪያ ተዘጋጅቶ በነበረው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በስፍራው የተገኙት አቶ ሽመልስ በወቅቱ የጋዜጣችን ዋና አዘጋጅ ስለነበረው ውብሸት ታዬ የሰጡኝ አስተያየት አዎንታዊ ነበር። ‹‹መንግስት ለምን ተተቸሁ አይልም ውብሸትም ሆነ ሌሎቻችሁ የምትፅፏቸው ጽሁፎች መንግስት ራሱን እንዲፈትሽ የሚረዱ አጋዥ ግብአቶች ናቸው›› ነበር ያሉት። ጋዜጠኛው ለእስር በተዳረገ ማግስትም ለሲፒጄ በሰጡት አስተያየት መታሰሩን እንደማያውቁና የሚታሰርበት ምክንያትም እንደሌለ ነበር አቶ ሽመልስ የገለፁት። ከሳምንት በኋላ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ግን ፊታቸውን ቅጭም አድርገው የሽብር ቡደን ለማደራጀት እንደተደረሰበት በይፋ ገለፁልን። በጋዜጠኞች ላይ ጥርስ ሲነክሱና ዕድሜና ሞት የሚያስፈርድ ዶሴ ሲጎነጉኑ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ የሚያውቃቸው ያውቸዋል፡፡
ውብሸት ለእስር ከተዳረገ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ባለፈው ረቡዕ ነበር ተደውሎ እንድደርስ በተነገረኝ መሰረት ወደ ደወሉልኝ ኃላፊ ለመድረስ በፍጥነት ስራመድ ውብሸት ደግሞ ከመርማሪው ቢሮ ሲወጣ ድንገት ኮሪደር ላይ ተገናኘን ደብዘዝ ባለ ፈገግታ ‹‹እንግዲህ አሸባሪ ነህ ተብያለሁና ልጄን አደራ›› አለኝ…፡፡ በተደጋጋሚ እንደገለፅኩት የውብሸት መታሰር በአውራምባ ታይምስ ባልደረቦች ስነ-ልቦና ላይ የፈጠረው ጠባሳ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ድረስ አስጠርተው ያነጋገሩኝ የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊ ይህንን በማስመልከት በተለይ ለቪኦኤ በሰጠሁት መግለጫ አለመደሰታቸውን ገልፀውልኛል። ‹‹አንድ ባልደረባችሁ ፖሊስ ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ስላዋለው ስነልቦናችሁ የሚረበሽበት ምክንያት አይገባኝም›› ካሉ በኋላ ትንሽ አየር ወሰድ አድርገው ‹‹የሰራተኞችህን ስነ ልቦና የማረጋጋት ኃላፊነት ያንተ ነው ይህንን ማድረግ ካልቻልክ እንደ አለቃ ብቃትህ ጥያቄ ውስጥ ነው›› አሉኝ፡፡ ጓደኛችንና የስራ ባልደረባችን ታስሮ ይቅርና በሆነ አጋጣሚ የምናውቀው ሰው እንኳን ሲታሰር መደንገጣችንና ማዘናችን እኮ የሰዎች ተፈጥሮአዊ ባህሪ ነው፡፡ ኃላፊው ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ አለፉ…፡፡
ሽብርተኝነት የአለምን ህዝብ ዕለታዊ እንቅስቃሴ እያወከ ያለ አደጋ መሆኑ አያጠያይቅም። ሽብርተኝነት ሊወገዝ ይገባል። በሽብር የሚሳተፉም ሆነ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ሊጠየቁ ይገባል። የእኛ አገር ሽብርተኝነት ግን ትንሽ ሰምና ወርቅ ያዘለ ይመስላል፡፡ 80 ሚሊዮን ህዝብ በሽብርተኝነት ፈርጀን የት እንደምንደርስ አላውቅም፡፡ ውብሸት ቦምብ ታጥቆ የቴሌኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት ሊያፈነዳ ሲል ተይዞ ከሆነ ጓደኛዬና ባልደረባዬ ስለሆነ ከተጠያቂነት መዳን አለበት አልልም። በ11 ዓመት የጓደኝነት ዘመናችን ግን እጁ ላይ እስክሪብቶ እና አጀንዳ እንደማይጠፋ አውቃለሁ። በእርግጥ የውብሸት ብዕር የሚተፋቸው ቃላት የህግ የበላይነትን ለሚጥሱ፣ ሰብአዊ መብት ለማያከብሩ፣ በ‹‹ብተና ፖለቲካ›› ለተካኑ ከቦምብ በላይ ሆነው ሊሆን ይችላል፡፡ እስኪ ቸር ያሰማን፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: